Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  አንዳንድ ትውስታዎች ያለንበትን ከባድ ጊዜ እያዋዙ የሚያስታውሱን ይመስለኛል፡፡ የውጭ ባለሀብቶችን ማማለልና መዋዕለ ንዋይ መሳብ የሚገባት አገር፣ የስግብግቦችና የአገር ፍቅር በውስጣቸው ያልሰረፀባቸው ሰዎች መጫወቻ ስትሆን እያየን ነው፡፡ ለገዛ ወገናቸው ደንታ የማይሰጣቸው ዘረኞች ሁኔታም ያሳስባል፡፡ ከግል ጥቅማቸው በላይ የማያስቡ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ሳስብ አንድ የአሜሪካኖች ቀልድ ትውስ ይለኛል፡፡ እጅግ በጣም ባለፀጋ የነበረ አሜሪካዊ ሞቱ መቃረቡን ሲረዳ ካከማቸው ገንዘብ ላይ ለሕፃናት ማሳደጊያ፣ ለአረጋውያን መጦሪያ፣ ለወጣቶች ንባብ ቤትና ለሴቶች ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በሚገባ ይሰጥና 90 ሚሊዮን ዶላር ይተርፈዋል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከለፋበት ገንዘቡ ላይ ለራሱ የሚሆን ማስቀረት ፈለገ፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሐኪሙን፣ የንስሐ አባቱንና ጠበቃውን የምሳ ግብዣ አዘጋጅቶ ጠራቸው፡፡

  በቀነ ቀጠሮው ሦስቱ የባለፀጋው የቅርብ ሰዎች በቅደም ተከተል ደረሱ፡፡ የምሳ ግብዣው ከተጠናቀቀ በኋላ ባለፀጋውና እንግዶቹ ቡና እየጠጡ ወደ ቁም ነገር ተሸጋገሩ፡፡ ባለፀጋው ስለፈለጋቸው ጉዳይ እንዲህ በማለት ጀመረ፡፡ ‹‹ከነበረኝ ገንዘብ አብዛኛውን ለተለያዩ ወገኖቼ አገልግሎት ይውል ዘንድ አበርክቻለሁ፡፡ የተቀረው 90 ሚሊዮን ዶላር ግን አብሮኝ እንዲቀበር እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ምድር የማምነው እናንተን ስለሆነ፣ ለእያንዳንዳችሁ 30 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ፡፡ ስሞት ግን ሦስታችሁም መቃብሬ ውስጥ ይህንን የለፋሁበትን ገንዘብ አስገቡልኝ አደራ! አደራ!›› በማለት ኑዛዜውን አሰማቸው፡፡ ሦስቱ ሰዎች በድርጊቱ ቢደነግጡም የተነገራቸውን ግን መፈጸም ነበረባቸው፡፡ ጊዜው ደርሶ ሰውዬው ሞተ፡፡ የቀብር ሥርዓቱም ተፈጸመ፡፡

  ይህ ከሆነ ከዓመት በኋላ ቄሱ ሐኪሙና ጠበቃው ዘንድ ይደውላሉ፡፡ የሟችን ሙት ዓመት ለማሰብ የምሣ ግብዣ ማዘጋጀታቸውን ተናግረው በሰንበት ለመገናኘት ይጠይቋቸዋል፡፡ ሦስቱ የሟች ባለፀጋ ወዳጆች በቀጠሯቸው መሠረት ይገናኛሉ፡፡ ባለፀጋውን በህሊና ፀሎት ካሰቡ በኋላ ምሳቸውን እየበሉ ወግ ይጀምራሉ፡፡ ቄሱ፣ ‹‹ወዳጃችን መቃብሬ ውስጥ አስገቡልኝ ካለው 30 ሚሊዮን ዶላር ላይ 15 ሚሊዮን ዶላሩን ቀንሼ ለራሴ በመውሰዴ በጣም ተፀፅቻለሁ፤›› ይላሉ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹እናንተስ እንደኔ ናችሁ ወይስ በታማኝነት ፀንታችኋል?›› በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ሐኪሙ በፍጥነት፣ ‹‹አባ እኔ እንደርስዎ ባልሆንም አሥር ሚሊዮን ለራሴ አስቀርቼ 20 ሚሊዮኑን መቃብሩ ውስጥ ጨምሬያለሁ፤›› ይላል፡፡ ጠበቃው ግን ዝም ብሏል፡፡ ቄሱ በመገረም እያዩት፣ ‹‹አንተስ?›› አሉት፡፡ ጠበቃው በመገረም እያያቸው፣ ‹‹የማትታመኑ ከንቱ ሰዎች ናችሁ፣ እንዴት የሙት ገንዘብ ትበላላችሁ?›› ይላቸዋል፡፡ ሐኪሙ፣ ‹‹ገንዘቡን በሙሉ መቃብር ውስጥ ከተትከው?›› ይለዋል፡፡ ጠበቃውም፣ ‹‹አዎን!›› ይላል፡፡ ቄሱ በመደነቅ፣ ‹‹30 ሚሊዮን ዶላሩን በሙሉ?›› ሲሉት፣ ጠበቃው ኮራ ብሎ፣ ‹‹ያውም በቼክ ነዋ!›› ሲላቸው ቄሱና ሐኪሙ በመደነቅ አፋቸውን ከፍተው ቀሩ ይባላል፡፡ ቄሱና ሐኪሙ በሻርኩ ጠበቃ በመበለጣቸው መናደዳቸው ያስታውቅ ነበር፡፡

  ይህንን ምፀታዊ ቀልድ ከሰማሁ ሰንበትበት ብልም እንዲህ ዓይነቱን ነገር የሚያስታውስ አንድ ገጠመኝ ሰሞኑን ደርሶኛል፡፡ ጓደኛዬ በአንድ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ይሠራል፡፡ እሱ በኤክስፐርት ደረጃ በሚሠራበት የሥራ መደብ ላይ አንድ የውጭ አገር ባለሙያም አብሮት አለ፡፡ ልብ በሉ ይህ የውጭ ባለሙያ በትምህርት ደረጃው ከጓደኛዬ ጋር እኩል ቢሆንም በልምድ ግን ጓደኛዬ በጣም ይበልጠዋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ደመወዛቸውና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞቻቸው የሰማይና የምድር ያህል የተራራቁ ናቸው፡፡ ወደ ውጭ ሲሄዱ በአበልና በመስተንግዶ እኩል ቢሆኑም በክፍያ ግን አይገናኙም፡፡ ይህ ሁኔታ ጓደኛዬን በጣም ስለሚያበሳጨው ከዚህ ፈረንጅ ጓደኛው ጋር መወያየት ይጀምራል፡፡

  ግድ የለሹ ፈረንጅ ፊት ለፊት መናገር ስለሚወድ፣ ‹‹አውሮፓና አፍሪካ እኩል አይደሉም፡፡ እኔና አንተም እንዲሁ፡፡ እንዲያውም አንተ ዕድለኛ ነህ፡፡ እዚህ ድርጅት ውስጥ ባትሠራ ኖሮ አገርህ እዚህ የምታገኘውን አንድ አሥረኛ የማይሞላ ነበር የምትከፍልህ፡፡ ስለዚህ ተመስገን በል፤›› የሚል ዓይነት ማፅናኛ ይወረውርለታል፡፡ አላርፍ ያለው ጓደኛዬ፣ ‹‹ሰው እኩል ስለሆነ እንዲህ ዓይነት መድልኦ መደረግ የለበትም፤›› በማለት ይከራከራል፡፡ ፈረንጁ አልተበገረም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን ኢንቨስተሮች አዲስ አበባና ሌሎች ቦታዎች ላይ መሬት በሚሊዮን በሚቆጠሩ ብሮች በሊዝ መያዛቸውን ሳታውቅ አትቀርም፤›› ይለዋል፡፡ ጓደኛዬ ገርሞት፣ ‹‹ይኼን ከዚህ ጋር ምን አገናኘው?›› ይለዋል፡፡ ፈረንጁ ጀነን እያለ፣ ‹‹ይገናኛል እንጂ! አገርህ አንድ የውጭ ኢንቨስተር ሲመጣ አንድ አውራጃ የሚያህል መሬት በጥቂት መቶ ዶላሮች ለረዥም ዓመታት እንደሚሰጠው አታውቅም ነበር?›› ሲለው፣ ጓደኛዬ የፈረንጁ ብልጠት አናዶት ምነው ባልተናገርኩ ብሎ በራሱ ተማረረ፡፡ አሁን ደግሞ ክልልን አገር ያደረጉ ስግብግቦች የገዛ ወገናቸውን ከማፈናቀል አልፈው፣ ሁሉንም ነገር የራሳቸው ሲያደርጉ እያየና እየሰማ ምሬቱ የት እንደሚደርስ ለማወቅ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ራስ ወዳድነትና ክፋት የዘመኑ መለያ ሆነዋልና፡፡

  (አይዳ ደምሴ፣ ከሣር ቤት)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...