Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትበባሮ ቱምሳ መንገድ ከክፍልፋይነት አዘቅት ውስጥ መውጣት

  በባሮ ቱምሳ መንገድ ከክፍልፋይነት አዘቅት ውስጥ መውጣት

  ቀን:

  በታደሰ ሻንቆ

  መቋሰልን ሊያፈልቁ የሚችሉ ትልልቅ የብሔርተኛ ቀዳዳዎችን እስካልዘጋን ድረስ ስሜታችንን ብናስታርቅም፣ ተመልሰን የመናቆር ወጥመዶች ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡ እንዲያውም እነሆ ዛሬ የትርምስና የሰዎችን በገፍ የመፈናቀል ጣጣዎችን ማስቆም ባለመቻላችን፣ ዕርዳታ ፈላጊነትና ረሃብተኝነት ‹‹በአዲስ መልክ›› ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ጀምሮ የጌዴኦን ፈተና ይዞልን መጥቷል፡፡ እናም በክፍልፋይነት በተሟሸ አዕምሮ ማሰብ፣ በብሔር በተሰባሰባ ፓርቲ መግዛትና በብሔረሰብ/ብሔረሰቦች ባለቤትነት ላይ የተመሠረተ የአገር አከፋፈል እስከ ቀጠለ ድረስ፣ የሕገ መንግሥቱም ካስማ ይኼው አስተሳሰብና አደረጃጀት እስከ ሆነ ድረስ፣ በብሔረሰብ፣ በቋንቋና በሌሎች ፈርጆች ከሚደረግ አድልኦ ዜጎች የሚጠበቁበትን እኩል የሕግ ዋስትና የደነገገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25፣ እንዲሁም በየትም የአገሪቱ ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራትና ቤት ንብረት የማፍራት መብት (አንቀጽ 32) ከይስመላ ያለፈ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡

  ምክንያቱም ብሔርተኛው ፖለቲካዊና አስተዳዳራዊ አደረጃጀትም ሆነ ለሕገ መንግሥቱ ካስማ የሆነው ብሔርተኛ አስተሳሰብ፣ የእነዚህን አንቀጾች መደፈር በውስጠ ታዋቂ የሚፈቅድ ስለሚሆን (አንቀጹ መጣስ የሚጀምረው ሕዝብን የክልል ባለቤትና ባይተዋር አድርጎ ከመከፋፈል ነውና)፡፡ እስካሁን ባለ ልምድ ክልሎች በየይዞታቸው ውስጥ፣ ባለቤትነት የማይመለከታቸውን ማኅበረሰቦች ወደ ፖለቲካ ሥልጣን የመውጣት ዕድልንም ሆነ የሥራ ዕድልን መገደባቸው፣ አንዳንዶቹ እንዲያውም በክልላዊ ሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ይህንኑ አንጓላይነት ማስፈራቸው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ከመጣስ ይልቅ፣ ለአገሪቱ ሕገ መንግሥትና ለአገሪቱ ፖለቲካዊ አወቃቀር ካስማ ለሆነው አስተሳሰብ ያለኃፍረት ታማኝ የመሆን ጉዳይ ነው፡፡

  የቁጥር ብልጫ ኖረም አልኖረ ዋናው ገዥ ወይም አውራ መመዘኛ ብሔረሰባዊ ባለቤትነት እስከሆነ ድረስ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲም ከይስሙላ ያለፈ መሠረት ሊቆናጠጡ አይችሉም፡፡ ሥርዓታዊ ማህፀን ያለው መንጓላል ቅሬታ ማፍለቁም አይቋረጥም፡፡ አመለካካት በብሔርተኛነት እስከተዋጠ ድረስ፣ የአስተዳደሮችና የአውታራት አደራጀጀት በብሔረሰባዊ ባለቤትነት ዕይታ እስከ ተመራ ድረስ፣ ፍትሕና ሕግ አስከባሪነት ሁሉ ለአድልኦ መጋለጡ አይቀርም፡፡ ብሔርተኛነት ግለሰቦችን የሚያያቸው በየብሔረሰብ ኮሮጃቸው ውስጥ መድቦ ነውና ግለሰብነታቸውን ሲያይ የብሔረሰብ ኮሮጇቸውን አይዘነጋም፡፡

  ስለሆነም ብሔረሰባቸው የተለያየ ግለሰቦች አፍ እላፊ ሲነጋገሩና አምባጓሮ ሲፈጥሩ ፀባቸውን በግለሰባዊነት ብቻ ዓይቶ ለማለፍ አይሆንለትም፡፡ ጠባቸውን ብሔረሰባዊ አድርጎ ለመተርጎም ይፈጥናል፡፡ የብሔርተኛነት የአስተሳብ ምሰሶ ብሔሬ በሌላ ብሔር ተበደለ/ተጠቃ ከሚል የሚጀምር እንደ መሆኑም፣ የበደል ግንኙነቱ ቢቋረጥም ብሔርተኝነቱ ከቀጠለ የድሮን እያነሳ ከማፍተልተል ወይም የብሔር ክብር/ጥቅም የነካ አዲስ በደል መሰል ነገር በመብራት ከመፈለግ አይቦዝንም፡፡

  የተለያየ ብሔረሰባዊ አመጣጥ ባላቸው ግለሰቦች መሀል የሚደረጉ ጠቦችና አፍ እላፊ ንግግሮች መላ ብሔረሰብን የመዳፈር ትርጉም በቀላሉ የሚሰጣቸውም ብሔርተኛነት ለሚሻው ተጠቃን፣ ተነካን ባይነት ማገዶ መሆን ስለሚችሉ ነው፡፡ ይህ ማለት የአመለካከትና የአደረጃጀት ሥርዓቱ ራሱ በአንድ አፍ እላፊ ምላስ ብሔረሰባዊ ፀብ ለማቀጣጠል የሚያስችል ባልቦላ ለእያንዳንዱ ብሔርተኛ ግለሰብ ያስታጥቀዋል፡፡ የኅብረተሰብ ሰላም ያንን ያህል መጫወቻ ለመሆን ይጋለጣል ማለት ነው፡፡

  የግለሰቦች ፀብና የቃላት ምልልስ የብሔረሰቦች መነካካት ተደርጎ ለመተርጎም ዕድል እስካገኘ ድረስም መሸካከር መመረቱ የማይቀር ነው፡፡ ብሔርተኛ ቡድን ሕዝቤ ከሚለው ብሔረሰብ ጋር ዝምድናውን የሚቋጥረው በድፍኑ ብሔረሰቡን ከሌላው ለይቶ ማትኮሪያው በማድረግ፣ በማሞጋገስና ‹‹ጥቃትህን እየታገልኩ ነው/ለጥቅምህ የቆምኩልህ ጠበቃህ ነኝ›› በማለት ላይ እንደመሆኑ፣ በብሔርተኛው ቡድን የተማረኩ የብሔረሰቡ አባላት የቡድኑን ገመና በክፍት አዕምሮ ለማየትና ለማጋለጥ ይቸገራሉ፡፡ ብሔርተኛ ቡድኑም ባለው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ መርሐ ግብርና ተግባሩ ተቀባይነቱ የሚሰፈርበት ግፊት ስለሌለ፣ ገመናውን እያፀዳ ወደፊት የሚራመድበት ዕድል ደካማ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ገመናን ከማየትና ከማሳየት ይልቅ ራስን በመሸንገል (የቡድኑን ጥፋት በሌላ ላይ በማላከክ/በብሔረሰቡ ላይ ለደረሰ ችግር ማሳበቢያ በመፈለግ፣ ቡድኑ ላይ የሚደርግ ነቀፋንና ውንጀላን ሁሉ በብሔረሰቡ ላይ የተሰነዘረ አድርጎ በመውሰድ) ይጠመዳሉ፡፡ ወጥመዱ የሚጀምረው ገና በብሔርተኛነት ራስን ከሌለው ለይቶ መንቀሳቀስ ሲጀመር ነው፡፡

   ብሔርተኛነት የብሔረሰቡን መገፋትና መበደል ቢያይም፣ ከሌላው ጋር ትግል አዛምዶ በመታገል ፈንታ ለብቻ ራስን የለየ ትግል ውስጥ መግባት፣ ተነጥሎ የመጠቃት ጥፋት መሆኑን ማስተዋል ትልቅ ችግሩ ነው፡፡ ለብቻ በመጮኼ፣ ለብቻ ትጥቅ ትግል ውስጥ በመግባቴ ሕዝቤ ተለይቶ እንዲጠቃ አጋልጫለሁ፣ ስቃዩም እንዲራዘም አድርጌያለሁ ብሎ ጥፋትን ማመንና ወደ ኅብረ ብሔራዊ መንገድ መግባት በኢትዮጵያ የብሔርተኛ ትግል ውስጥ ጉልህ ሆኖ የኖረ ገመና ነው፡፡ ብሔርተኛነት በ1983 ዓ.ም. ድል ከተቀዳጀ ወዲህ በተቋቋመ አንጓላይ የብሔርተኛ አገዛዝ ራሴንም ብሔረሰቤንም በጥላቻ/በቅያሜ አስጠመድኩ በማለት፣ ጥፋትን የመቀበልና የመታረም ጉዳይ ዛሬም የሞት ያህል የሚሸሽ ነው፡፡ ለትግራይ ወገኖቻችን መጠመድ መዘዝ የሆነው ሕወሓታዊ የበላይ ገዥነትና ሀብት አግበስባሽነት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሳለ፣ ከሕወሓት ውስጥ ይቅርና ያለ ኃጢያቱ ጥላቻ ከተረፈው ትግራዊ በኩልም ይኼንን የድርጅቱን መዘዘኛነት ፊት ለፊት አውጥቶ  የመኮነን ደፋር እንቅስቃሴ ገና ነው፡፡

  በየትኛውም ብሔረሰብ ውስጥ ሕግ ጣሾችና የመብት ጥቃት አድራሾች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ የዳውድ ኦነግ በሰላም በር አገር ውስጥ ከገባ በኋላ በኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች ውስጥ በጠብመንጃ አማካይነት ሲያካሂድ የነበረው አማሽነት፣ ፈጣን መንግሥታዊ ዕርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኦነግ በኦሮሞ ብሔርተኛነት ዕይታ ለኦሮሞ ብሔር የቆመና የታገለ ተደርጎ ሲቆጠር እንደመኖሩ፣ የዳውድ ቡድን በዚህ ዝና ውስጥ ተሸጉጦ በአተራማሽነት ያደረሰው በደል ካስከተለው ፖለቲካዊ ጫና ይልቅ፣ በኦነግ ላይ ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ በኦሮሞ ታጋዮች ላይ ‹‹ዛሬም እንደ ትናንቱ የመንግሥት ጥይትና ካቴና ቀጠለ›› የሚል ጫጫታ ፈጣሪነቱ የበለጠ ይሆን ነበር፡፡

  የቡድኑ ብጥበጣ ክፉኛ እያስመረረና ይዞታ እያሰፋ መጥቶ የኦሮሚያና የፌዴራል መንግሥት የበረታ ዕርምጃ መውሰድ ውስጥ ሲገቡ፣ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ዘንድ ከሁሉ ቀድሞ የታየው ነገር፣ ሰላማዊ ትድድርን አናግተው በዜጎች ላይ ወንጀሎች የፈጸሙ ለፍርድ የመቅረባቸው ጥያቄ አልነበረም፡፡ ብሔርተኝነትን ከፍትሕ ይበልጥ ያብከነከነው ኦሮሚያን የሚያስተዳድረው ኦዴፓ ለኦሮሞ የቆመ ድርጅት ሆኖ፣ ኦነግም ለኦሮሞ ሲታገል የኖረ የኦሮሞ ድርጅት ሆኖ እንዴት ለኦሮሞ የቆሙ የብሔሩ ልጆች እርስ በርስ ይዋጋሉ የሚል ጉዳይ ነበር፡፡ የአንድ ብሔር ልጆችን በማስታረቅ ዳስ ውስጥ ተጠያቂነት ጉስቁልና ደርሶበታል፡፡ ብሔርተኛነት ይህን ያህል የበደል ተጠያቂነትን በብሔር ታጋይነት ውለታና ዝና እስከ ማድበስበስ ሊሄድ ይችላል፡፡ ለብሔርህ ጥቅም የተሰዋሁ/የደማሁ ባይነት፣ በደልና ዘረፋ ከሌላ ብሔር ብቻ የሚፈልቅና የብሔር ልጅ በገዛ ብሔሩ ላይ የማያደርገው የሚያስመስል ብዥታም ለመፍጠርና በዚህ ዓይንን ለመጋረድ የተመቸም መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ለዚህ ዓይነት ብዥታ የኦሮሞ ሕዝብ ከኦነግ ጋር ባለው ታሪካዊ ቁርኝት የተጋለጠ መሆኑን ያስተዋለ ሰው፣ የትግራይም ሕዝብ ከሕወሓት ጋር ባለው የታሪክ ትስስር ያለበትን ፈተና ማጤን አይከብደውም፡፡

  ለትግራይ ሰዎች በጨፈገገ ስሜት መታየት ዳፋ የሆነው የሕወሓት መጠመድ የፈለቀው ከትግሬነት ሳይሆን፣ በብሔር መሰባሰብን ምርኩዝ አድርጎ ሥልጣን ላይ የወጣ ሕወሓታዊ ቡድን ሥልጣንን የስነጋና የሀብት መመጥመጫ መሣሪያ ከማድረጉ መመንጨቱን አገር ያውቃል፡፡ ዛሬ የዴሞክራሲ ለውጡን በዋናነት እየመራ ያለው የኦሮሞ ቡድንም በአክራሪ ብሔረተኞችና በሥልጣን ጥመኞች ተንሸራትቶ ሕወሓት የገባበት ወጥመድ ውስጥ እንዳይከቱት፣ ዋስትናው ከመላ ሕዝብ ድጋፍ ጋር የዴሞክራሲ ለውጡን ማንደርደርና በቶሎ የብሔርተኛ አደራጃጀት ቆዳውን ገፍፎ ኅብረ ብሔራዊ ቅልቅል ውስጥ መግባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ጥርጣሬና ቅዋሜ አዋክቦት፣ አፈናን የሥልጣን ማስቀጠያ ዋና መሣሪያ ወደ ማድረግ ከዞረ፣ ታሪክ ራሱን የመድገሙ ነገር ወይም በሥርዓተ አልባ ቀውስ የመተላለቃችን አደጋ ሲያስጨንቅ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጭንቀት አኳያ ኦዴፓ ብዙ ቡድኖችን ይዞ ወደ ውህድ ፓርቲ ለመሸጋገር መቁረጡ (ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን የማበልፀግ ሥራ ከመቀጠሉ ጋር ተደምሮ) ትልቅ ዕፎይታ ነው፡፡

   የሌላ ብሔር ባለሀብትን በዘራፊነት የሚያይ ብሔረሰቡን ምን ያህል የኢንቨስትመንትን ዕድገት እያወለካከፈና እያስደነበረ እንዳለ፣ በመሬት ቅርጫ መልክ የሚገለጸውም ብሔርተኛ ግብግብም በሰላምና በዴሞክራሲ ተቻችሎ ለመኖር ምን ያህል መሰናክል እንደሆነ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ኅብረተሰብ አይነግሩም፡፡ ወልቃይት ጠገዴና ራያ ዛሬ ለትግራይና ለአማራ ክልል ደም የሚያስጠሙና ቀረርቶ የሚያመርቱ ሌላ ‹‹ባድመ›› (ሌላ የመሬት ጉዳይ) ሆነዋል፡፡ መሬቱ ላይ ያለው ሕዝብ መብት ከተረሳማ የመቼውን፡፡

  ብሔርተኛነት/ክልልተኛነት ይህን ያህል ጉድጓድና ፉካ የበዛበት ሆኖ ሳለ ፉካዎችን የሚደፍን ማሻሻያ በማድረግ ፈንታ በፉካዎቹ ማን እየገባ ነው የሚያጋጨን ወይም ማን እየገፈተረ ነው ጉድጓድ ውስጥ የሚጥለን ብሎ መብከንከን ቅልጥ ያለ ሰበበኛነት ነው፡፡ ከሁሉ በፊት መደረግ ያለበት ሰበበኝነትን ትቶ ለተንኮለኛ/ለሴራኛ መግቢያ የሚሆኑ ለራሳችንም መውደቂያ የሚሆኑ ጉድጓዶችንና ፉካዎችን መዝጋት ነው፡፡ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ አማራንና ቅማንትን በብዙ ነገር የጎዳውን ወደ ውጊያ የተቀየረ ግጭትን በተመለከተ የውክልና ጦርነት እየተካሄደብን ነው ሲባል በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡ እንዲህ ያለ አተረጓጎም ከፖለቲካ አኳያ ጅል አተረጓጎም ነው፣ ትርፍ አያስገኝምና፡፡ ችግሩ የጥቂቶች በጥቅም መገዛት ከሆነ ከቅማንት ጋር እነዚያን ለጥቅም ያደሩ ይዞና በማስረጃ ለሕዝብ አጋልጦ ችግሩን መቅጨት ነው፡፡

  ችግሩ የጥቂቶች ካልሆነ (በእውነትም አይደለም)፣ የቅማንት ሕዝብ መድኃኒት ተደርጎበት የሌሎች መሣሪያ ሆኗል ከማለት የማይሻል ፋይዳ ቢስ አሳባቢነትን ትቶ፣ ላለመግባባትና የብቻ አስተዳዳራዊ ይዞታ ለመጠየቅ ያደረሰውን ቀዳዳ ለይቶ በማወቅ መድፈን ነው፡፡ ይኼውም በቅማንትነት ላይ ሲሰነዘር የኖረው የንቀት አመለካከት ቀዳዳ፣ ከክፍልፋይ ብሔርተኛ ቀዳዳ ጋርና ከክፍልፋይ ልሂቃን የሥልጣን ጥቅም ጋር ተገናኝቶ ጥያቄውን እንደ ወለደ፣ የክልሉ አስተዳደር ጥያቄውን ያስተናገደበት የአፈና በትርም ችግር እንዳባባሰ፣ (ይህ ሁሉ የገዛ ብልሽት፣ መሰሪዎች ተቆርቋሪ በመምሰል ሥራቸውን እንዲሠሩ እንደሚጠቅም) ማስተዋል ተቀዳሚ ነው፡፡ እውነቱን ተቀብሎ ቀዳዳዎቹን ለመድፈን ቁርጠኝነቱ ካለ፣ ከመማረር ወጥቶ ከቅማንት ልሂቃን/የፖለቲካ ቡድን ጋር ለዕርቅ የቆረጠና ደም ፍላት የሌለበት የአንጀት ውይይት (ለሕዝብ የሚደርስ) መክፈት፣ ለተሠራው ጥፋት ሁሉ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ፣ ከቅማንቴነት ጀርባ ያለውን የተለየ የቋንቋ የባህልና የእምነት ታሪክ፣ የጊዜያት መዋሀድ ከፈጠረው ከመጠሪያና ከውስን ሥነ ልቦና ልዩነት በቀር አምሳያነት የገዘፈበትን የዛሬ ማኅረሰባዊ ገጽታ መቀበል፣ ታሪክን ወደ ኋላ ተመልሶ ለማረምም ሆነ በተወራረሰ ሕዝብ መሀል አጥር ለማበጀት ሳይሞከር በቅማንቴነት ላይ የኖረውን የተዛባ አመለካከት ከመላው ሕዝብ ጋር ለማስወገድ መግባባትና ዓላማው የምር መሆኑን የሚያረጋግጥ ግብረ ኃይል ማቋቋም፣ ሥራውን በቅርብ የሚከታተሉ ቅማንቴዎች በጎንደር አስተዳደር አመራር ውስጥ ማካተት፣ የቅማንት ‹‹ዞን››ን ለማስተዳደር የሚቋቋም/የተቋቋሙ ፓርቲዎች ቢኖሩ ለቅማንቴነት ብቻ የቆምን የሚል አንጓላይ ምልመላ የማያደርጉ፣ የዛሬውን የቅማንቴነትና የአማራነት አንድም ሁለትም የመሆን እውነታ የተቀበሉ እንዲሆኑ (ከተቻለም በሶሲዮ ኢኮኖሚያዊ መርሐ ግብር ላይ ያተኮረና ከአንድ ዞን ያለፈ ዕይታና ድርጅታዊ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው) መግባባት፣ በዚሁ መንፈስ ላይ ተመሥርቶ መነታረኪያና መሣሪያ የመማዘዣ ሰበብ የሆኑት ቀበሌዎች ያለ ሸፍጥ ነዋሪያቸው በወደደበት በኩል እንዲካተቱ መስማማትና በንግግር ሊፈታ የሚችል ጉዳይ ወደ ግብግብና ወደ እሳት ሄዶ ለደረሰው መከራ ከሁለት በኩል በሚፈስ ፀፀት በሕዝብ  ፊት መንበርከክ፡፡

  እዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት የአንድ ክልል ውስጣዊ ችግርን ከመፍታት ያለፈ ውጤት አለው፡፡ አገራዊ ችግርንም በመፍታት ረገድ መንገድ ጠራጊ ልምድ ይሰጣል፡፡ በየአካባቢው ያሉ ዓይነተኛ ችግሮች ዓይነተኛ መፍትሔዎቻቸውን እንዲሹ ያነቃል፣ ዓይነተኛ መፍትሔዎችም አገር አቀፋዊ ችግሮችን ከማቃለል ጋር ተያይዘው ሊገመዱ የሚችሉ ናቸው፡፡

   ግትር ብሔርተኞች ብሔርተኛ አስተሳሰብ ከእነ ገዥነትና አወቃቀሩ በ27 ዓመታት ልምድ ውስጥ በአመለካከት ላይ ያደረሰውን ክፍልፋይነትና ከክፍልፋይነት የሚነሳውን ቁርቁስ እያስተዋሉ፣ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በአወቃቀርና በብሔርተኛ ፓርቲ አደረጃጀታችን ምክንያት ሳይሆን ዴሞክራሲና እውነተኛ ፌዴራላዊነት ስላልነበረ ነው ብሎ በማለትና ሁሉም ጣጣ ከሕወሓት አምባገነንት የመጣ በማስመሰል፣ ክርክር ያሸነፉ/ብሔርተኛነታቸውን ከተጠያቂነት ያዳኑ ይመስላቸዋል፡፡ የሕወሓት ቁንጮ ገዥነት ከአናት ነበር ቢባልስ፣ ዕውን ክልሎች በውስጥ ጉዳያቸው አንፃራዊ ነፃነት ጨርሶ አልነበራቸውም? ይገዙ የነበሩት ቡድኖች ይዘርፉና ይደቁሱ የነበሩት፣ እያንጓለሉ ሲገፉና ሲያፈናቅሉ የነበሩት ሕወሓቶች እጃቸውን ጠምዝዘው ስላስገደዷቸው ነበር? በብሔረሰብ መሰባሰብን እንደ ሃይማኖት እንዲይዙት ያደረጓቸውና ጠንቆቹን እንዳያዩ የከለሏቸው ሕወሓቶች ናቸው?

  ከ1983 ዓ.ም. በፊት እንኖር የነበረው በአምባገነንት ሥር (በዴሞክራሲ አልባነት ሥር) ነበር፡፡ ግን ክፍልፋይነትና አገርህ አይደለም እያሉ ማፈናቀልና ወሰን ወይም ሞት የሚል ዓይነት መዋጋት አልነበረም፡፡ የችግሩ ምክንያት ላይ ለመድረስ ከተፈለገ፣ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የተቀፈቀፉትን ችግሮች ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ከተደረጉ የአስተሳሰብ፣ የአገዛዝና የአወቃቀር ለውጦች ጋር አገናዝቦ ማየት የግድ ነው፡፡

  በአንድ አስተዳደራዊ አካባቢ ውስጥ ካለ ኅብረተሰብ ውስጥ የተወሰነ ማኅበረሰብን/ማኅበረሰቦችን የአካባቢው ባለቤት፣ ሌላውን ባይተዋር ባደረገ አወቃቀርና ገዥነት ውስጥ እንዴት ሆኖ ነው የእኩል ዜግነትና የሰብዓዊ መብት መረጋገጥ ሊኖር የሚችለው? ሁለቱ የሚጣሉ መሆናቸውን (አንዱ ባለበት ሌላው ሊገኝ አለመቻሉን) የ27 ዓመታት ልምዳችን ምስክርነት ሲሰጥ እንደኖረ አለመቀበል፣ እውነቱን ለማየትና መፍትሔ ለመፈለግ ካለመፈቀድ እኩል ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ከልምድ ያለ መማር ግትርነት በብሔር ፓርቲና ክልልተኛነት አንጓሎ መግዛት ጥሞናል ከማለት ሊመጣ ይችላል፣ ወይም ፊት የነበሩት ገዥዎች ሌሎች ቡድኖች ነበሩና እኛ እነሱ ባለፉበት አልፈን ችግሩን እስካላረጋገጥን ድረስ ችግሩን ከወዲሁ አንቀበልም ከማለት ሊመጣ ይችላል፡፡

  እንዲያው ለመሆኑ በየብሔር ፓርቲ የመግዛት ዘይቤን መቀጠል ተገቢና ልክ የምናደርበት መከራከሪያችን ምንድነው? አገሪቱ ብሔረሰበ ብዙ ስለሆነች እንዳንል፣ ብሔረሰበ ብዙ መሆን በእኛ አገር ብቻ ያለ አይደለም፡፡ አግላይ ብሔርተኛ አገዛዝ የሌለባቸው ብሔረ ብዙ ኅብረተሰቦች በዓለማችን ሞልተዋል፡፡

  በየብሔር ፓርቲ መደራጀትና በየብሔር ፓርቲ መግዛት መቀጠል ያለበት የብሔር ጭቆናን ለመከላከል ነው እንዳንል፣ የዚህ ዘይቤ የ27 ዓመታት ልምድ ያሳየን የብሔር ጭቆና በማንጓለልና በማፈናቀል እንዴት እንደተባዛ፣ ማለትም የብሔር ተጨቋኝ ነበርን ይሉ የነበሩ ቡድኖች የበዳይነት ብድር ሲመልሱ እንደነበር ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሲቋቋም በዳይነቱ ይወገዳል አንል ነገር፣ በቋንቋ ላይ በተመሠረተ የአስተዳደር አከፋፈል ምድር ውስጥ እንኳ ቢሆን፣ ዴሞክራሲ ጤናማ ሕይወት ሊያገኝ የሚችለው አግላይ በሆነው የብሔረሰብ ፓርቲነት ላይ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ የሐሳብ አማራጮች ላይ ነው፡፡ እና ቢያንስ ከአንጓላይ የፓርቲ አደረጃጀት ወጥተን የሶሲዮ ኢኮኖሚ አማራጮችን የድጋፍና የፓርቲ አባላት መሰባሰቢያ ስለምን አናደርግም? በብሔረሰብ እትብት ከመነገድ በቀር ለዚያ የሚሆን ሶሲዮ ኢኮኖሚያዊ የሐሳብ ዝግጅት ስለሌለን? በሐሳብ ተወዳድሮ አሸንፎ ሥልጣን ላይ መውጣት ስለሚከብድ? በብሔርተኝነት እትብት ስሜትን እየነዘሩ የፖለቲካ ድጋፍን መሸመት ስለሚቀል? እስካሁን ለተደረደሩት ‹‹ጥያቄዎች›› መልስ ለመስጠት የሚሞክር ብሔርተኛ ካለ የጉድ ነው! ጥያቄዎቹ መልስ የሚሹ ሳይሆኑ፣ ብሔርተኛ የፓርቲ አደራጃጀትና ወገናዊ ገዥነቱ በተቋቋመበት ሥርዓተ ኑሮ ውስጥ የዜጎች ከመድልኦ የመጠበቅ ዋስትና የይስሙላ እንደሚሆን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡

  በፌዴራላዊነት ውስጥ ባለን ራስን በራስ የማስተደር መዋቅር ላይ የሚመለከታቸው ሕዝቦች ሁሉ መክረው ዘክረው፣ እንዳለ የምናቆየውም የሚስተካከለውም ነገር ለይቶለት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በቋንቋ የመሥራት (የመማር፣ የመዳኘት)፣ ባህልን የመንከባከብና የማጎልበት መብቶች ሁሉ እንደተከበሩ ከየትኛውም ብሔረሰብ የበቀለ የአገር ልጅ በየትም ቦታ አገሬ ብሎ፣ የትኛውንም የአገር ልጅ ወገኔ ብሎ፣ በእኩልነት መንፈስ የሚኖርበት ሁኔታ እንዲፈጠር የፖለቲካ አስተሳሰባችንና አደረጃጀታችን ከከፋፋይነትና ከአግላይነት መውጣቱ የግድ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ለውጥ ሽግግራችን በዚህ አቅጣጫ ህሊናችንን አንቅቶ፣ ቢያንስ ቢያንስ የትኛውም ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ እኩልነት የቆመ ነው ወይስ አይደለም? ለዴሞክራሲ የቆመ መሆኑን በራሱ በድርጅቱ ውስጥ ዴሞክራሲን በመኖር አሳይቷል? ለእኩልነት መቆሙንስ ሁሉን አሳታፊ በሆነ አባልነትና የሶሲዮ ኢኮኖሚ መርሐ ግብሩ አሳይቷል? ወይስ በአግላይነት የተሰባሰበና ድፍን የብሔር በደልን እያሰሰ ስሜት በመንዘር የሚነግድ ነው? በሚሉ መመዘኛዎች ለመገምገም ካላበቃን (የፓርቲ ምርጫችን አግላይነትና ሕዝበኛ የስሜት ጨዋታን አልፎ ካልሄደ) የልፋታችን ውጤት ውኃ ወቀጣ ይሆናል፡፡ ብዙ የጓጓንለትን ዴሞክራሲንና ዕርቀ ሰላም ከንቱ የሚያደርግ ቁርቁስ ተመልሶ ይጠልፈናል፡፡ ሁሉም ሕዝብ  የደገፈውና ተስፋውን የጣለበት የዴሞክራሲ ለውጥ፣ ዋናውን ጥማት (የፖለቲካ ሰላምንና እኩል ዜግነትን) ባላስገኘ ጊዜ የሚከተለው የቁርቁስ ቀውስ ደግሞ ከበፊቱ የከፋና በተስፋ መቁረጥ የጠለሸ ሊሆን ይችላል፡፡

   በዚህ እየተብሰለሰልኩ ሳለሁ አንድ ወዳጄ አንድ የቆየ ጽሑፍ ኮፒ ይሰጠኛል፡፡ ጽሑፉ ‹‹Decentralization and Nation Building in Ethiopia›› የተሰኘ ባሮ ቱምሳ፣ ዛሬ ‹‹አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ›› ተብሎ በሚጠራው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለነበረው የሕግ ፋኩልቲ ሚያዝያ ግድም በ1965 ዓ.ም. (April 15, 1973) ያቀረበው መንደርዳሪያ ጥናት (ቴሲስ) ነው፡፡ የጥናቱን ቀዳሚ ክፍሎች ነካክቼ ምዕራፍ ሦስት ውስጥ ስገባ፣ ያገኘሁት ነገር ጮቤ እርገጥ ከሚያሰኝ ስሜት ጋር ዕይታዬን በዕንባ እንክብሎች ያጥበረበረ ነበር፡፡

  ባሮ ቱምሳ የዛሬ 46 ዓመት ኢትዮጵያን በጥሞና አስተውሎ፣ በኢትዮጵያ ከአካባቢ አካባቢ የገዘፈ ክምችት ያላቸው ብሔረሰቦች ቢኖሩም አንዳቸውም ለየብቻቸው አካባቢን ሞልተው የያዙበት ሁኔታ አለመኖሩንና ሌሎች ማኅበረሰቦች ተጎዳኝተው/ተሰባጥረው መገኘታቸውን ተቀብሎ፣ ይህም የአብሮ መገኘትና የመደባለቅ አዝማሚያ በጎ ውጤት ያለውና መቀልበስ የማይኖርበት አይቀሬ ታሪካዊ ሒደት መሆኑን ተረድቶ (ገጽ 108)፣ ብሔረሰቦች በማኅበራዊ ፍትሕ፣ በእኩልነት፣ በመከባበርና በወንድማማችነት ተዘማምደው በፈጣን ልማት የሚጎለምሱበትን ውጤት አልሞ፣ ውስጣዊ የአስተዳዳር ክፍፍሎችን ባዘሉ አምስት ትልልቅ ራስ ገዝ ምድሮች ኢትዮጵያን የደለደለ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡

  ባሮ ቱምሳ እኛ የተዘፈቅንበትን የዛሬን የግጭትና የንቁሪያ ጣጣ ሳያይ የተገለጠለት መለኛነት፣ እኛ ይህን ሁሉ ቀውስ ካየንና እናስብለታለን የምንለው ሕዝብ ሁሉ ከታመሰ በኋላ አልገለጥልን እንደምን ይለናል!? የእሱን መንደርደሪያ አሻሽሎና አበልፅጎ በስድስት ያህል ትልልቅ (ሰሜን ምድር፣ ምሥራቅ ምድር፣ ምዕራብ ምድር፣ መሀል ምድር፣ ደቡብ ምሥራቅና ደቡባዊ በሚሉ ዓይነት ኅብረ ብሔራዊ ምድሮች) ውስጥ የብሔረሰብ መብቶችንና የዜግነት መብቶችን አስማምቶ ማስተናገድ ይቻለናል፡፡ ውስጣዊ አስተዳደሮች ከብሔረሰብ ማንነት ጋር የተያያዙ መብቶች ሳይጎድሉ መሟላት ይችላሉ፡፡ የፌዴራል አባላቱ ምድሮች በቅንብራቸው ኅብረ ብሔራዊ እንደመሆናቸው፣ ኅብረ ብሔራዊ ዕይታና ፖለቲካ ይጎለብትባቸዋል፡፡ የፖሊስና የዳኝነት አውታራትም በየትኛውም ሥፍራ ለዓድሏዊነት በማይመቹና ለሙያቸው መታመንን መሠረት አድርገው የራስ ገዙን ግቢ በኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር የሚያገለግሉ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ፈርጆች ከአንድ የበለጡ ቋንቋዎችን የጋራ መሥሪያ ከማድረግ ጋርና ከኢኮኖሚ ልማት መላላስ ጋር ተጋግዘው በአካባቢዎች ደረጃም ሆነ በአገር ደረጃ የጋራ ማንነትን ስለሚያዳብሩም፣ ጠባብ ወገንተኛነት የመበጥበጥ ዕድሉ እየከሳ እንጂ እየወፈረ አይሄድም፡፡ አሁን ያሉብንን ጣጣዎች በተመለከተም የባሮ ቱምሳ ሐሳብ ተቃንቶ በተግባር ላይ ቢውል፣ ከራያ ወልቃይት አንስቶ እስከ ሞያሌ ድረስ በአራቱም አቅጣጫዎች ያሉ ውዝግቦችን ወዲያውኑ ከሥራ ውጪ ማድረግ ያስችላል፡፡

  ይህንን ሁሉ ማድረግ እየቻልን ከዚህ ቀደም በሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ውስጥ ያደረግነው የልማት ጥረት ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ ሳለ፣ በዴሞክራሲ ለውጥ ሰላምን ተቀዳጅተው የበለጠ ይመዘዛሉ (ለውጣቸው፣ ሰላማቸውና ግስጋሴያቸው ለአፍሪካ ቀንድ ይተርፋል) ብሎ አፍሪካና ዓለም ተስፋ ጥሎብን ሳለ፣ በጣጣዎች መንገላታትና ወደ አደጋ ማምራት ከበለጠብን በማን ልናዝን!? የእኛ የመበላላት እሳት አንድ ጊዜ ከተቀጣጠለ ደግሞ አሁን በዓለማችን ካየናቸው ሲኦሎች ሁሉ ሊከፋና እዚህ ደረጃ ላይ ላቆመው እችላለሁ የማይባል (ከአናት ሊያጠፉ ከሚሞክሩት የበለጠ ሥር ሥሩን እየሄዱ የሚያራግቡትና የሚቆሰቁሱት የሚያይሉበት) ሊሆን ይችላል፡፡ አርቆ አሳቢዎች ከአገሮች አልፈው፣ ምድሪቱና የሰው ልጅ እንዳይጠፉ ሰው ሥልጣኔውን እንዲያርም ከመወትወት አልፈው፣ ምድር ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ የህዋ ውስጥ ለውጦችን እስከ መከታተል በሚለፉበት ዘመን፣ በዓለም አንድ ነጥብ ላይ የምንኖር ሰዎች ምርምር የማይሹና በጉያችን ሆነው ሊበሉን የሚያዛጉ መዘዞቻችን ማምከን አቅቶን እሳት ቢበላን ምን ሊባል? የሰማይ ፍርጃ!?

  ህልውናችንን ለማትረፍ ከእኛ ለእኛ በላይ የሚያስብና የሚደርስ ፍጡር አይኖርም፡፡ እሳት ማስቀረት አቅቶን ፍርስራሽና አመድ ቢውጠን ለራሳችን ይጎድልብናል እንጂ፣ በሶሪያና በየመን ሲሆን እንዳየነው ለምድሪቱ እጅግም አናጎድልም፡፡ የሰው ልጅ ራሱ ሥልጣኔውን ማረም አቅቶት ቢጠፋ እንኳ፣ ለራሱ ይጎድልበታል እንጂ እግዜሩ በምልዓተ ህዋው ውስጥ የህያው ፍጡር ሥልጣኔ የሚጎድልበት አይመስልም፡፡ የእኛ ምድር ባለችበት ጋላክሲ ውስጥ እንኳ ቢሊዮኖች ፀሐያዊ ሥርዓቶች መኖራቸው፣ ሕይወትና ሥልጣኔን የእኛ የሰዎች ብቻ አድርጎ ማሰብን ፉርሽ ያደርገዋልና፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...