Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የፖለቲካው ስብራቶች የሚጠገኑት በሐሳብ ነፃነት ብቻ ነው!

  ኢትዮጵያ ውስጥ የሐሳብ ነፃነት ሳይከበር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል ብሎ መጠበቅ፣ ከእባብ እንቁላል እርግብ ይፈለፈላል ብሎ ተስፋ የማድረግ ያህል ነው፡፡ የሐሳብ ነፃነት መከበር ያለበት በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በፖለቲከኞች፣ በሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ በምሁራን፣ በወጣቶች፣ በሴቶችና በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚቀርቡበት ገበያ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡም የፈለገውን ሐሳብ በነፃነት መርጦ መብቱን ያጣጥማል፡፡ ይህ በዓለም ላይ ተቀባይነት ያገኘ ዕድሜ ጠገብ መርህ ነው፡፡ ከዚህ መርህ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ግን፣ የጉልበት አማራጭ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ሠልፍ ስም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ በሚገባ እያመላከቱን ነው፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ዱላና ገጀራ ይዞ መገኘት ጉድ ሲያሰኝ ከርሞ፣ ሰሞኑን ደግሞ ይለይላችሁ ተብሎ ጠመንጃ የታጠቁ ጉዶች ተስተውለዋል፡፡ የሐሳብ ነፃነትን የሚጋፉ እንቅስቃሴዎችን በቶሎ ማስቆም ካልተቻለ፣ መንገዱ ለአምባገነንነት እየተመቻቸ መሆኑን ማመን አለብን፡፡

  ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹አዲስ ወግ›› በተሰኘው የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ዋና ዋና የሚባሉ የአገሪቱን የፖለቲካ ስብራቶች አውስተው ነበር፡፡ በስምንት ነጥቦች የተቀነበቡት ሐሳቦች ከግልና ከራስ ቡድን ጥቅም በዘለለ በአንድነት ስሜት አለመንቀሳቀስ፣ በምንጠይቀው ልክ በተሰማራንበት መስክ አመርቂ ውጤት አለማስመዝገብ፣ ዋልታ ረገጥነት (ጽንፈኝነት)፣ ያለፈውን ከአሁኑና ከወደፊቱ ጋር አስማምቶ አለመጓዝ፣ የተሰማራንበትን ሙያ ገሸሽ በማድረግ በፖለቲካ አቀንቃኝነት ብቻ መጠመድ፣ እስካሁን የተገኙ ድሎችን ማሳነስ፣ መገናኛ ብዙኃን ታሪክ የመጻፍ ሒደት ውስጥ መሆናቸውን ችላ ብለው ጠብ አጫሪና የተዛባ ዘገባ ማሰራጨት፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሥነ ምግባር አለመኖር ናቸው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ስብራቶች ብዛት ከዚህም በዘለለ ሰፊና ጥልቅ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የፖለቲካውን ቅብብሎሽ ወግ አለማወቅ፣ የፖለቲካ ንግግሩንም ሆነ ክርክሩን መቅኖቢስ አድርጎታል፡፡ ይህ ወግ በሠለጠነ መንገድ ቢከናወን ኖሮ የሐሳብ ልዕልና የበላይነቱን ይዞ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስብራቶች ይጠገኑ ነበር፡፡ ነገር ግን ለዚህ መታደል አልተቻለም፡፡

  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል አንዱና ዋነኛው፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ያለ ገደብ ማስከበር ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል ተቋማትን መገንባት ነው፡፡ ዜጎች በፈለጉት መንገድ እየተደራጁ የውይይትና የክርክር ባህል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሲቪክ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲደራጁ መሥራት የግድ ይሆናል፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲህ በዝተውና ተዝረክርከው ሳይሆን፣ ሰብሰብ በማለት የፖለቲካ የጨዋታ ሕጉን በማሳመር የፖሊሲ አጀንዳዎችን ይዘው መቅረብ የሚችሉበት ቁመና ላይ መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመራጩን ሕዝብ ልብ ለማሸነፍ የሚያስችል ብቃትና ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህ መሠረት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ድንጋይ፣ ዱላ፣ ገጀራና ጠመንጃ ድርሽ እንዳይሉ ማድረግ የሚቻል ከሆነ የፖለቲካ ስብራቶች ይጠገናሉ፡፡ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥትም ሆነ፣ ነገ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ወገኖች ለሐሳብ ነፃነት ቅድሚያ ይስጡ፡፡ መንግሥትን የሚመሩም ሆነ ፖለቲከኞች ምሥጋና የሚፈልጉትን ያህል ለወቀሳም ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ ራስ ወዳድነትም ሆነ ጽንፈኝነት፣ ዳተኝነትም ሆነ መሰሪነት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚወገዱት በሐሳብ የበላይነት እንጂ በልመና ወይም በመፈክር አይደለም፡፡

  እዚህ ላይ ሌላው ሊሰመርበት የሚያስፈልገው የሚዲያ ጉዳይ ነው፡፡ ሚዲያ የተለያዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱበት እንጂ፣ ባለቤቶቹ ወይም ጋዜጠኞቹ የግል አስተያየታቸውን የሚያስተጋቡበት መድረክ ሊሆን አይገባም፡፡ ሚዲያ የሚመራው ራሱን በቻለ ሙያና ሥነ ምግባር ሲሆን፣ የነፃ አውጭነት ወይም የፈራጅነት ሚና እንዲኖረው አይፈቀድም፡፡ ሚዲያ በከፍተኛ የሙያ ሥነ ምግባር እየተመራ የተጣሩ መረጃዎችን ለተመልካቾች፣ ለአድማጮችና ለአንባቢያን የማቅረብ የሙያ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዚያ ውጪ የተለያዩ አስተያየቶች ያሉዋቸው ግለሰቦች ወይም ስብስቦች በነፃነት ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ መድረኩን ያመቻቻል፡፡ ሚዲያ ለውጡን የመደገፍ ሚና እንደሌለው ሁሉ ለማደናቀፍም አይሠራም፡፡ ይልቁንም ለውጡ እንዴት እየተከናወነ እንደሆነ በትጋት ይዘግባል፡፡ ተቃራኒ ሐሳብ ያላቸውን ያሟግታል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች አለን የሚሉ ወገኖች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ያደርጋል፡፡ የሚዲያው በሥነ ምግባር የታነፀ ሙያዊ ኃላፊነት በሕዝብ የህሊና ፍርድ ብቻ ነው የሚዳኘው፡፡ ከዚያ በተረፈ ሚዲያው የማንም ተላላኪ እንዳይሆን ነው መንግሥትም ሆነ ይመለከተናል የሚሉ ሁሉ ጠንክረው መሥራት ያለባቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አካል የሆነው የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ እንዲህ ሲታይ፣ ከፖለቲካ ስብራቶች መካከል አንደኛው ተጠገነ ማለት ነው፡፡

  በዚህ ወሳኝ ወቅት ለሐሳብ ነፃነት በፅናት መቆም አለመቻል፣ ኢትዮጵያ የገጠማትን ወርቃማ ዕድል እንደማበላሸት ይቆጠራል፡፡ በአደባባይ ጠመንጃ ታጥቆ ወጥቶ ሕዝባዊ ውይይትን ማደናቀፍ እንደ ቀልድ ከታየ፣ ወይም ይህንን ዓይነቱ ድርጊት በማናቸውም መንገድ ተቀባይነት እንዳለው ለመከራከር ጥረት ከተደረገ፣ ወይም በሽግግር ውስጥ ባለች አገር ሊያጋጥም የሚችል ክስተት ነው ተብሎ በቸልተኝነት ከታለፈ የቁልቁለቱ ጉዞ በፍጥነት ተጀምሯል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ ወጣቶች ከስሜታዊነት ወደ ምክንያታዊነት፣ ከአመፃ ወደ ተሟጋችነት እንዲለወጡ የአዕምሮ ብልፅግናው ላይ መሥራት ይሻላል፡፡ መብቱን የሚጠይቅ ትውልድ መፈጠሩ ደስ የሚያሰኝ ሆኖ ሳለ፣ መብትን ለማስከበር ገጀራ ወይም ጠመንጃ ይዞ መነሳት ግን የማይወጡት አደጋ ውስጥ ይከታል፡፡ ወጣቶችን ውይይትን፣ ክርክርንና የሰጥቶ መቀበልን መርህ የሚያስተምሩ የሲቪክ ማኅበራትን በመገንባት ችግሩን መቅረፍ ተገቢ ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ዕድል መስጠት የሚጠቅመው፣ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ መድረስ የሚችል ትውልድ ለመፍጠር ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በማናቸውም ጉዳዮች ላይ በሰከነ መንገድ መነጋገር ከባድ አይሆንም፡፡ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ሲወጣ ዱላውን እየነቀነቀ የሚወጣውም ሆነ፣ በአካባቢዬ ማንም መጥቶ መወያየት አይችልም ብሎ ጠመንጃ የሚነቀንቀው መታየት የጀመረው ለሐሳብ ነፃነት የተሰጠው ዋጋ አናሳ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቁ የአገራችን የፖለቲካ ስብራት ነው፡፡ ከዚህ ዓይነት ጉድ ውስጥ መውጣት የሚቻለው ግን የሐሳብ ነፃነት ሲከበር ብቻ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...