Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  አዲስ አበባ ከአቡጃና ከብራስልስ ልትማር የሚገባት ተሞክሮ

  በይርጋለም ማኅተመ (ዶ/ር)

  በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰተው ለውጥ የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደ አንድ የለውጡ አቀጣጣይ ነዳጅ ቢሆንም ከተማዋ የለውጡን ትግል በመምራትም ሆነ በመሳተፍ የጎላ ሚና አልነበራትም። በዚህ ምክንያት አዲስ አበባ መቼ ነው ከእንቅልፏ የምትነቃው እየተባለች ስትወቀስ ቆይታለች። በእኔ ዕይታ አዲስ አበባ ለለውጡ ጉልህ ሚና ያልተጫወተችው አንቀላፍታ ሳይሆን ለዘመናት መፍትሔ ባላገኘው የማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ችግር የተነሳ በሥጋት ደመና ስለተከበበች ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አሁን አዲስ አበባ ያለችበትን ሁኔታ ከከተማዋ ታሪክ ጋር በማገናዘብ መዳሰስና አዲስ አበባ ከተከበበችበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የመውጫ በሮችን ለመጠቆም ነው።

  ይህ ጽሑፍ የግል ሙያዊ አስተያየት ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ላይ አሁን እየተንፀባረቀ ያለውን የማንንም አጀንዳ በመደገፍ ወይም በመቃወም ላይ የተመሠረተ አይደለም። አዲስ አበባ የማናት? ይህ ጥያቄ የሰሞኑ የአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት፣ የማኅበራዊ መድረክ የንትርክ አጀንዳ፣ የአደባባይ ተቃውሞና የከተማዋ የሥጋት ምንጭ ሆኖ ሰንብቷል። ጥያቄውም ሆነ የሚሰነዘረው መልስ ስሜታዊና ቁጣ አዘል ከመሆኑ የተነሳ ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ነገሩን ወደ ግጭት ሊያመራው ይችላል። ብዙ ሰው አዲስ አበባ የማናት የሚለውን ጥያቄ የጎሳ ፌዴራሊዝም ያመጣው ጣጣ ነው ብሎ ያምናል። በመሠረቱ የጎሳ ፌዴራሊዝም ኖረም፣ አልኖረም ይህ ጥያቄ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ አገሮች የሚነሳ ጥያቄ ነው። በርሊን (ጀርመን) ብራስልስ (ቤልጂየም) ኒው ዴልሂ (ህንድ) እንዲሁም አቡጃ (ናይጄሪያ) ከአዲስ አበባ ጋር የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ስላለ ከእነሱ ልምድ መቅሰም ይቻላል። ይህንን በሚመለከት ወደ ፊት ጊዜ ሳገኝ በሰፊው እመለስበታለሁ።

  ወደ ዋናው ጉዳይ ስመለስ፣ አዲስ አበባ የማናት የሚለው ጥያቄ በእኔ ዕይታ ምንጩ አዲስ አበባን የራስ ከማድረግ ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን ከፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ከሥጋት የመነጨ ጥያቄ ነው። ይህንን የፍትሕና የሥጋት ችግር መፍታት የሚቻለው ለአዲስ አበባ ባለቤት በማፈላለግ ሳይሆን፣ ሥጋትን አስወግዶ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በማስፈን ብቻ ነው። ስለዚህ አዲስ አበባ የማናት የሚለው ክርክር ጉንጭ ከማልፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም።

  አከራካሪውልዩ ጥቅም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 49 ቁጥር 5 እንዲህ ይላል ‹‹የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡›› ይህ አንቀጽ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር ለሚኖራት ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች ጥሩ መነሻ ቢሆንም ዝርዝር ጉዳዮቹ በወቅቱ በሕግ ባለመወሰናቸውናልዩ ጥቅምየሚለው ሐረግ ስላልተብራራ ለአሻሚ ትርጉም በር ከመክፈቱም በላይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ‹‹ልዩ ጥቅም ማለት የባለቤትነት ማረጋገጫ ነው፤›› በሚሉና ‹‹ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር የለም›› በሚሉ ሁለት ጫፍ የረገጡ ቡድኖችን ፈጥሮ የአዲስ አበባን ችግር እያወሳሰበው ይገኛል።

  ​​አዲስ አበባ ከአቡጃና ከብራስልስ ልትማር የሚገባት ተሞክሮ

   

  ልዩ ጥቅም ማለት ምን ማለት ነው?

  በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ልዩ ጥቅም የሚለው ሐረግ ከእንግሊዝኛውእስፔሻል ኢንተረስትበቀጥታ የተወሰደ ሲሆን የአማርኛው ትርጉም ሙሉ በሙሉ የእንግሊዝኛውን ሐሳብ አይገልጸውም። ሕገ መንግሥቱ በተጻፈበት ዓውድ መሠረት እስፔሻል ኢንተረስት ማለት ሁለት ወገኖች ወይም ቡድኖች ተደራድረው አንዱ የሌላውን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ የድርድሩ ውጤት ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር ማለት ነው። ይህ አሠራር ደግሞ በየትኛውም ፌዴራሊዝምን በሚከተሉ አገሮች የሚሠራበት መንገድ ነው።

  አዲስ አበባ ላይ ችግር የፈጠረው ልዩ ጥቅም የሚለው ስላልተብራራና የፌዴራሉ መንግሥት በጊዜው የሕግ ማሰሪያ ሳያዘጋጅ ከተማዋበመመሪያ ቁጥር አንድና ሁለትእንድትመራ ስለፈቀደ ነው። ልዩ ጥቅም ማለት የጉዳት ማካካሻ ነው፡፡ የአዲስ አበባን ከተማ ወደ የትኛውም ክልል ብንወስዳት በዙሪያዋ ለሚገኝ ክልል የምታመጣው ጥቅምና ጉዳት አለ።

  ይህ ደግሞ የማናስቀረው የማንኛውም ከተማ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ከሌሎች አገሮች ልምድ ስንነሳ የልዩ ጥቅም መሠረታዊ ሐሳብ በፌዴራል ከተማ ዙሪያ የሚገኝ ክልል ለከተማዋ ካለው ቅርበት አንፃር የሚፈጠረውን ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም በማጎልበት የፌዴራል ከተማዋ በክልሉ ላይ ለምታሳድረው ተፅዕኖ ተገቢና ፍትሐዊ ማካካሻ ክልሉ እንዲያገኝ የሕግ አሠራር መዘርጋት ማለት ነው። በየትኛውም አገር የፌዴራል ከተማ ከሌሎች ከተሞች የተሻለ የማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሀብታዊ፣ የጤናና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ያገኛል።

  ከፌዴራል ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ የክልል አስተዳደሮችም የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ ናቸው። አዲስ አበባም እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ግልጋሎቶች ስትሰጥ ኖራለች፣ ወደ ፊትም ትሰጣለች። ሌሎች ክልሎች ከአዲስ አበባ ርቀው ስለሚገኙ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ አይሆኑም። ይህ ደግሞ አዲስ አበባ ለጎረቤት ክልል ከምትሰጠው ልዩ ጥቅም አንዱ ነው። ሌሎችንም ብዙ መዘርዘር ይቻላል። አዲስ አበባ በጎረቤት ክልል ላይ የምታሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖር ይችላል፡፡ ማንኛውም ከተማ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ እንዲሁም ይሞታል። በዚህ ሒደት ውስጥ ከተማ ለዕድገቱ የሚሆን ግብዓትን በአብዛኛው የሚያገኘው ከጎረቤት ክልል ነው። በተጨማሪም በከተማው ውስጥ የሚፈጠረው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ የሚወገደው በጎረቤት ክልል በሚገኝ መሬት ላይ ነው።

  አዲስ አበባ ለዕድገቷና መስፋፋቷ የሚያስፈልጋትን የግንባታና ሌሎች ግብዓቷን በብዛት የምታገኘው ከኦሮሚያ ክልል ነው። እንዲሁም ከተማዋ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ የሚያስፈልጋትን መሬት የምታገኘው ከዚሁ ክልል ነው። የአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መንግሥትና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ መስተዳድሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላት የማይካድ ሀቅ ነው። ይህንን አሉታዊ ተፅዕኖ አዲስ አበባ ለጎረቤቷ በምትፈጥረው መልካም አጋጣሚ ማካካስ ሲቻል በአስተዳደራዊ ድክመትና የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ይህ ባለመደረጉ በአዲስ አበባና በጎረቤት ክልል መካከል ያለው ግንኙነት መርህ አልባና አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ውዝግብ አድጎ መንግሥትን ዋጋ እያስከፈለ ሲገኝ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ሥጋት ላይ ሲጥል እንዲሁም በኦሮሚያ ክልልየልዩ ጥቅምጥያቄን አስከትሏል። ይህንን ችግር ለመፍታት ከስሜት የፀዳ የሰከነ ውይይት፣ አገራዊ ኃላፊነት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የሕግ የበላይነትና የሌሎች አገሮችንም ልምድ መቅሰም ግድ ይላል።

  ከአቡጃ ምን እንማራለን?

  አቡጃ የናይጄሪያ የፌዴራል ከተማ ስትሆን ከተመሠረተች ሃምሳ ዓመት አይሞላትም። ከአቡጃ በፊት የናይጄሪያ ዋና ከተማ ሌጎስ ስትሆን አቡጃ አዲሷ የናይጄሪያ ፌዴራል ከተማ ሆና የተመረጠችበትን ምክንያት የወቅቱ የናይጄሪያ መሪ እንዲህ በማለት ነበር ያስረዱት ‹‹አዲሲቷ ከተማ ሁሉንም የናይጄሪያ ጎሳዎች በእኩል የምታገለግል የአንድነት ተምሳሌት ናት፤›› በማለት ነበር። ምንም እንኳን አቡጃ የተመሠረተችበት ቦታ የብዙ ብሔረሰቦች መኖሪያ ቢሆንም፣ ዋና ከተማዋ ከተመሠረተች በኋላ የየትኛውም ብሔር ሳትሆን የናይጄሪያውያን የአንድነት ተምሳሌት ሆና እያገለገለች ትገኛለች።

  አቡጃን ለመመሥረት ናይጄሪያውያን ከዋሽንግተን ዲሲ (ዩናይትድ ስቴትስ) ከብራዚልያ (ብራዚል) ከኢዝላማባድ (ፓኪስታን) ከፒተርስበርግ (ሩሲያ) እና ከፓሪስ (ፈረንሣይ) በቂ ልምድ ቀስመዋል። ከእነዚህ አገሮች በወሰዱት ልምድ መሠረት የአቡጃ ከተማ ምሥረታ ሰነድ ላይ የሚከተሉትን ጠቃሚ ነጥቦችን አካተዋል።

  • የአቡጃ ከተማ ሕጋዊ ድንበርና የወደፊት የመስፋፊያ መሬት ባንክ በግልጽና በዝርዝር ተቀምጧል።
  • አቡጃ ስትመሠረት ከመሬት ይዞታቸው ለሚፈናቀሉ ዜጎች የካሳ ክፍያና መልሶ ማቋቋሚያ ዝርዝር መመሪያ ተካቷል።
  • የመሬት ወረራንና ሌብነትን የሚከላከል ጠንካራ ተቋም ተፈጥሯል።
  • የአቡጃ ምሥረታ ለናይጄሪያውያን አዲስ የፍትሕ፣ የሰላምና የአንድነት ዘመን ብሥራት መሆኑ ታውጇል።
  • አቡጃን የአንድነት ማዕከል ብሎ ሰይሟል።

  ዛሬ እያንዳንዱ ናይጄሪያዊ አቡጃ የማነች ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ስላለው አቡጃ የማነች ብሎ አይወዛገብም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአቡጃ ከተማ የእያንዳንዱ ናይጄሪያዊ እንደሆነች የምሥረታ ሰነዱ ስለሚናገር ነው። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የአቡጃ ተሞክሮዎች ዛሬ አዲስ አበባ ካለችበት አጣብቂኝና ሥጋት ውስጥ ለማውጣት በብዙ ሊጠቅመን ይችላል።

  ከብራስልስ ምን እንማራለን?

  ኢትዮጵያና ቤልጂዬየም በብዙ ነገር ቢለያዩም የፌዴራል አመሠራረታቸው የመመሳሰል ባህሪ አለው። የትኛውም የፌዴራሊዝም አስተዳደር መነሻ ሐሳቡ ሁለት ነው። የተለያዩ ራሳቸውን የቻሉ ግዛቶች ለመተባበርና አንድ ላይ ለማደግ በመስማማት የሚጣመሩበት የፌዴራል አስተዳደር የመጀመሪያው ሲሆን፣ ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት ጀርመንና ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ናችው። ሁለተኛው የፌዴራል መነሻ ሐሳብ በአሐዳዊ አስተዳደር የሚተዳደሩ ግዛቶች ራስን በራስ ለማስተዳደር ከመነጨ ፍላጎት ወደ ፌዴራል አስተዳደር የሚሸጋገሩበት ሒደት ነው።

  ኢትዮጵያና ቤልጅየም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። ኢትዮጵያና ቤልጅየም በፌዴራል አወቃቀርም የመመሳሰል ባህሪ ይታይባቸዋል። የቤልጅየም ፌዴራሊዝም የተዋቀረው ማኅበረሰብን፣ ቋንቋንና ክልልን አንድ ላይ በማጣመር የተዋቀር ሲሆን የኢትዮጵያ ደግሞ ቋንቋንና ብሔርን መሠረት ያደረገ ነው። የቤልጅየም የፌዴራሊዝም አወቃቀር በሦስት ክልል የተከፈለ ሲሆን፣ የፍሌሚሽ ክልል (የፍሌሚሽ ማኅበረሰብ በብዛት የሚኖርበት) የዋሉን ክልል (የፈረንሣይ ማኅበረሰብ በብዛት የሚኖርበት) እና የብራስልስ ክልል (የፌዴራሉ ዋና ከተማ) ተብለው ይጠራሉ። ብራስልስ እንደ አዲስ አበባ ዋና ከተማነቱን ከአሐዳዊ አስተዳደር ወደ ፌዴራሊዝም ይዞ የተሸጋገረ ከተማ ነው። ይሁን እንጂ የፌዴራል ሥርዓቱ ሲዋቀር ብራስልስ በአዲስ መልክ በአሥራ ዘጠኝ የመዘጋጃ አስተዳደር ተዋቅሯል። ከዚህ ውስጥ አንዱ መዘጋጃ ብራስልስ ሲሆን ሌሎቹ አሥራ ስምንቱ የመዘጋጃ አስተዳደሮች የብራስልስ የመስፋፊያ ዞኖች ተብለው የተዋቀሩ ናቸው። ብራሰልስ በፍሌሚሽ ማኅበረሰብ ክልል ተከቦ ያለ ክልል በመሆኑ ፍሌሚሾች በየጊዜው መሬታችን ተወሰደ የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ።

  ይሁን እንጂ ይህ ቅሬታ በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ መንግሥት መካከል በተደረገ ድርድር መሠረት፣ ብራስልስ ከአሥራ ዘጠኙ መዘጋጃ ውጪ እንዳትስፋፋ በመገደብ የመሬት እጥረት ሲፈጠር በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት መካከል በሚደረግ ድርድር ይወሰናል በሚል ሐሳብ በመስማማት ቅሬታውን ማስወገድ ተችሏል። እንደ አለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ከአሐዳዊ አስተዳደር ወደ ፌዴራሊዝም ስትቀየር አዲስ አበባ ላይ መሠራት የነበረበት ሥራ አልተሠራም። አሁንም ዋጋ ቢያስከፍልም ከአቡጃና ብራስልስ ልምድ ወስዶ የተበላሸውን ለማስተካከል ዕድል አለ።

  ከአዲስ አበባ ታሪክ ምን እንማራለን?

  የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አዲስ አበባን በሚመለከት ሰፊ ጥናት አድርጎ ከአራት በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትሟል። በዚህ ሒደት ውስት ጸሐፊው ያስተዋለው ነገር ቢኖር አዲስ አበባ ማንነቷን የተቀማች የመሪ ዕቅድ መሞከሪያ ቤተ ሙከራ እንደሆነች ነው። በእኔ እምነት የአዲስ አበባ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ማንነት በሕግ ካልተረጋገጠ የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ መመለስ አይቻልም። በመጀመሪያ አዲስ አበባ እንዴት የመሪ ዕቅድ ወይም ማስተር ፕላን ቤተ ሙከራ እንደሆነች ላስረዳና ከዛ ወደ ማንነት ጥያቄ እመለሳለሁ። አዲስ አበባ ስትቆረቆር የኢትዮጵያውያንን የቦታ አጠቃቀምና የማኅበረሰብ አሰፋፈር ፍልስፍና የተከተለ ነበር።

  ይህም የመኖሪያ ሠፈርን፣ የእምነት ማዕከልን፣ የገበያንና የፖለቲካ ማዕከልን ለይቶ በማስቀመጥ ነው። አዲስ አበባ ስትመሠረት ሥዕል አንድ ላይ የተቀመጠውን ገጽታ ይዛ ሲሆን፣ ይህንን አገር በቀል መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) ወደ ዘመናዊ የከተማ መሪ ዕቅድ ማሸጋገር ተስኗት የሌላ አገር መሪ ዕቅድ ፍልስፍናና ርዕዮተ ዓለም በግድ ሲጫንባት ቆይቷል። ጣሊያን አዲስ አበባን ከተቆጣጠረችሦስት ወር በኋላ እ.ኤ.አ.  1936 ኮርቤዥር የተባለ ፈረንሣዊና የሲዊዘርላንድ ዜግነት ያለው ታዋቂ የሥነ ሕንፃ ባለሙያ ለሞሶሎኒ የአዲስ አበባን መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት እንደሚረዳው በመግለጽ ደብዳቤ ይጽፍለታል።

  ሞሶሎኒም በሐሳቡ ተደስቶ በምሥራቅ አፍሪካ የታላቋን ጣሊያን የቅኝ ግዛት ከተማ ማየት እንደሚፈልግ ህልሙን ነገረው። ኮርቤዥርም የሞሶሎኒን ህልም ከራሱ ፍልስፍና ጋር በማዋሃድ በአካል ዓይቷት ለማያውቀው ከተማና ለማያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥዕል ሁለት የተቀመጠውን መሪ ዕቅድ አዘጋጀ። ይህ ግዴለሽነትና ቅዠት የተቀላቀለበት መሪ ዕቅድ ከአዲስ አበባ ውጭ በዓለም ላይ የትም አገር ተሞክሮ አያውቅም። አዲስ አበባ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ራሷን ሳትሆን የባዕድ የመሪ ዕቅድ መጫወቻ ሜዳ ሆና ረጅም ዘመን ተጉዛለች።  በሥዕል ሁለት ላይ የተቀመጠው የአዲስ አበባ መሪ ዕቅድ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ የምትባል ከተማ እንደሌለች በመቁጠር በባዶ ሜዳ ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ታቅዶ የተዘጋጀ መሪ ዕቅድ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያን ወቅት አዲስ አበባ ከአየር ላይ ስትታይ ባዶ መሬት ሳትሆን በሥዕል ሦስት ላይ የተቀመጠው ገጽታ ነበራት። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም አዲስ አበባ የመሪ ዕቅድ መሞከሪያ ሜዳ ሆና የእንግሊዝና የፈረንሣይ ታዋቂ የከተማ መሪ ዕቅድ ባለሙያዎች የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ በዋናነት ተሳትፈዋል። ለምሳሌ፣ ታዋቂው የሎንዶን መሪ ዕቅድ አዘጋጅ አቤርክሮምባይ እንዲሁም የፓሪስ ከተማ መሪ ዕቅድ አዘጋጅ ዲማራይን አዲስ አበባ ሎንዶንንና ፓሪስን እንድትመስል መሪ ዕቅድ አዘጋጅተውላት ነበር። በደርግ ዘመን ደግሞ አዲስ አበባ የሶሻሊስት ከተማ እንድትመስል ተፈርዶባት ነበር። በዚህም መሠረት የደርግ መንግሥት ፊቱን ወደ ሶሻሊስት አገር በማዞር ፕሮፌሰር ፖሎኒን ከሃንጋሪ በማስመጣት አዲስ አበባ ቡዳፔስትን እንድትመስል መሪ ዕቅድ አዘጋጅቶላት ነበር።

  ፕሮፌሰር ፖሎኒ በይበልጥ የሚታወቀው የአብዮት አደባባይን በመሥራት ስለነበር የአሁኑን መስቀል አደባባይ በዘመናዊ መልክ ያዘጋጀ ሰው ነው። ፕሮፌሰር ፖሎኒ የአዲስ አበባ ክልል እስከ አዳማ እንዲደርስ ለደርግ ሐሳብ አቅርቦ እንደነበር ይታወቃል። እ.ኤ.አ. እስከ 1986 ድረስ የአዲስ አበባ መሪ ዕቅድ ሲዘጋጅ የነበረው ለአዲስ አበባ ባዕድ በሆኑ ባለሙያዎችና በባዕድ ፍልስፍና ስለነበር አዲስ አበባ መምሰልና መሆን የሚገባትን ከተማ ሳትመስል የመቶ ዓመት ጉዞዋን ጨረሰች። ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሳተፉበት የመጀመሪያው መሪ ዕቅድ የተዘጋጀው እ.ኤ.አ. 1986 ነበር። ይህ አጋጣሚ አዲስ አበባ ታሪካዊ ማንነቷን መልሳ እንድታገኝ መንገድ ቢከፍትም ሕጋዊና ፖለቲካዊ ማንነቷ እስከ ዛሬም ድረስ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል።

  እንግዲህ ከላይ እንደ ተመለከትነው አዲስ አበባ በኢትዮጵያውያን ብትቆረቆርም በታሪኳ ውስጥ የብዙ አገሮችን ከተማ አሻራ ይዛ ነው ያደገችው። በባዕዳን ይዘጋጅላት የነበረው መሪ ዕቅድም ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሯን የሚፈታ ሳይሆን የጊዜውን ፍልስፍናና ርዕዮተ ዓለም እንዲያንፀባርቅ ተደርጎ ነበር። በዚህ ምክንያት አዲስ አበባ ታሪካዊ ማንነቷን ያጣች ሲሆን የከተማዋ ሕጋዊ ወሰንም በትክክል ተከልሎ ስለማያውቅ ሕጋዊ ማንነቷም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ ካላት ክልላዊ፣ አገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚና አንፃር የሚመጥናትን የፖለቲካ አመራር ስላላገኘች እንደ መንደር በመመሪያ ቁጥር አንድና ሁለት ስትመራ ቆይታለች።

  እንግዲህ ከአዲስ አበባ ታሪክ የምንማረው ቁምነገር አዲስ አበባ ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ማንነቷን በማጣቷ ዛሬ ለምናየው ችግር መፈጠር ዋነኛው ምክንያት ነው። የመፍትሔ ሐሳቦች

  • አዲስ አበባ የሌሎችን በፌዴራል የሚተዳደሩ አገሮችን ዋና ከተማ በተለይም ከአቡጃና ከብራስልስ ልምድ በመውሰድ የአዲስ አበባን አስተዳደር በአዲስ መልክ ማዋቀር ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል።
  • ከተማዋ ስትዋቀር የከተማ ክልልና የመስፋፊያ ክልል ተብሎ በሕግ የተወሰነ ግልጽ ወሰን ማበጀት አሁን ያለውን ውዝግብ ሊያስቀር ይችላል።
  • አዲስ አበባ ዛሬ ያለባትን ችግር ብቻ ሳይሆን በሃያና ሠላሳ ዓመት ውስጥ ሊገጥማት የሚችለውን ችግር በማሰብ መሪ ዕቅድ ሊኖራት ይገባል።
  • አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ፣ በዙሪያዋ ላሉ አስተዳደሮችና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሕጋዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሥርዓት እንዲኖራት ፖለቲካዊና ሕጋዊ ሥርዓት መዘርጋት።
  • የከተሞችን መስፋፋት በፖለቲካ ድንበር ማቆም ስለማይቻል ከተሞችን በፌዴራልና በክልል በጋራ የማስተዳደር ሕግና ሥርዓት መዘርጋት። ይህ ወደ ፊት በክልልና በፌዴራል ከተሞች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን አላስፈላጊ ውዝግብ ሊያስቀር ይችላል።
  • የኦሮሚያና ክልል የፌዴራል መንግሥት ከስሜት ነፃ በሆነ፣ በአገራዊ ኃላፊነትና በፖለቲካ ቁርጠኝነት ተቀራርበው ከሠሩ አዲስ አበባን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንድነትና የብዝኃነት መገለጫ ማድረግ ይቻላል። መልካም ንባብ!

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው yirgalemm2001@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  Related Articles