Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትለኢትዮጵያ እግር ኳስ እመርታ የዩኒቨርሲቲዎች ጅምር

  ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እመርታ የዩኒቨርሲቲዎች ጅምር

  ቀን:

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በሁለቱም ፆታ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 15 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎችን የሚያቅፍ ስፖርታዊ አደረጃጀትን እንዲከተሉ የሚያስችል ስምምነትን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱን በከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚኒስቴር አማካይነት የተፈራረሙት 15 ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡

  የስምምነቱ ዓላማ ታዳጊ ስፖርተኞችን በብቃትና በጥራት ማፍራት የሚችሉ የትምህርት ተቋማት ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገትና ልማት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው፡፡

  እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በስምምነቱ መሠረት ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 15 ዓመት በታች ታዳጊዎች ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሚገኙባቸው አካባቢዎችና ትምህርት ቤቶች በመመልመል እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ እስከ 120 ታዳጊዎችን በሁለቱም ፆታ በማቀፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና እንዲያገኙ የሚደረግበት የአሠራር ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፡፡

  ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የታዳጊዎች እግር ኳስ ልማት በመላ አገሪቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል ይችል ዘንድ፣ የመግባቢያ ሰነድ ከ15 ዪኒቨርሲቲዎች ጋር የተፈራረመው መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ነው፡፡

  የታዳጊዎች የእግር ኳስ ልማት መግባቢያ ሰነድ የተፈጸመው፤ የሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስትር ሒሩት ወልደማርያም (ዶ/ር)፣ የስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና የ15ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ ዲኖችና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ነው፡፡

  ዩኒቨርሲቲዎቹ ከተቋቋሙባቸው ዓላማዎች አንዱ ማኅበራዊ አገልግሎት መስጠት ስለመሆኑ  በሚኒስትሯ ተነግሯል፡፡ ይሁንና ስምምነቱ በመግባቢያ ሰነድ ደረጃ መከናወኑ በቂ እንዳልሆነ፣ የዚህ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደምም መከናወናቸው ግምት ገብቶ ስምምነቱ ወደ ተግባር በቶሎ የሚቀየርበትና ዓላማውንም የሚያሳካ ጉዞ የሚጀምርበት አካሄድ ማመቻቸትና ማሳየት የሁሉም ስሜትና ፍላጎት ነው፡፡

  በመሆኑም ይህ ጅምር ያውም ዩኒቨርሲቲዎችን ማዕከል ያደረገው መነሻ፣ በወረቀትና በወሬ ሳይገደብ እንደታሰበው መሬት ወርዶ ታዳጊዎችን አፍርቶና አግኝቶ፣ አገሪቱን አኩርቶ፣ ፍሬያማ የሚሆንበትን ጊዜ ከወዲሁ በመመኘት ብቻ ሳይሆን፣ ለውጤት በመሥራት ኢትዮጵያ ከእግር ኳሱ የምታተርፍበት እንቅስቃሴ እንዲሆን ማድረግ በተለይ የዩኒቨርሲቲዎቹ ዋና ድርሻ መሆኑም ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል፡፡

  በጀትና መሰል ችግሮችን ምክንያት በማድረግ ምንም እንኳን በዩኒቨርሲቲዎቹ ተነሳሽነት ባይሆንም፣ የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚኒስቴር ለዚህ ሥራ ትኩረት መስጠቱ ከጅምሩ በላይ ተግባራዊ ውጤቱ እንዲያጓጓ ማድረጉ ከወዲሁ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል የሚሉ አስተያየቶች በርክተዋል፡፡ ይሁንና እንዲህ ያሉ ጅምሮች ከዚህ ቀደምም በየፊናቸው መመርያና ሰነዶች ተዘጋጅተውላቸው ካበቁ በኋላ ተደነቃቅፈው በወሬ ቀርተዋልና የዚህ ስምምነት ፍጻሜም ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥመው ግን ሥጋት ያለባቸው አልጠፉም፡፡

  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው፣ እግር ኳስ በኢትዮጵያ የተወዳጅነቱን ያህል ውጤታማ ሆኗል ባይባልም፣ በዚህ ወቅት ግን ዘርፉ ራሱ የግድ የሚልበት አጋጣሚ መሆኑንና በተለይም አገሪቱ ከራሷም አልፎ የአፍሪካ አግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከመሠረቱ በጣት ከሚቆጠሩ አገሮች ግንባር ቀደም እንደመሆኗ ስሟንና ክብሯን የሚመጥን እግር ኳሳዊ ቁመና እንዲኖራት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

  ይህንኑ የአቶ ኢሳያስ ጅራን አስተያየት አስመልክቶ ፌደሬሽኑ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራች ከመሆኗ ባሻገር በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእግር ኳስ ቀዳሚ ከሚባሉት አገሮች አንፃር ሲታይ እጅጉን ወደ ኋላ የቀረ በመሆኑ አንቱ የሚያሰኛት ውጤት የላትም፡፡ ይህም ከትውልድ ወደ ትውልድ መቀጠል ስለሌለበት የግድ አንድ ቦታ እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዓላማም ብቁና ተፎካካሪ ታዳጊ ወጣቶችን ወይም እግር ኳሰኞችን ልክ በሩጫው እንዳኮሩን አትሌቶቻችን ማፍራት መቻል ነው፡፡››

  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሥልጠናው ጀምሮ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ለታለመለት ዓላማ ግብ ይደርስ ዘንድ አቅም በፈቀደ መጠን ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ከመሆኑም በላይ በፌዴሬሽኑ የተዘጋጀውን የመግባቢያ ሰነድ ተቋማቱ በቅድሚያ እንዲወስዱና ወደ ተግባር እንዲገቡ ማሳሰቢያ መሰጠቱ ታውቋል፡፡

  ሚኒስትሯ በበኩላቸው፣ በዕለቱ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከ15ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተከናወነው የመግባቢያ ሰነድ ትርጉሙ ግልጽ ነው፣ ‹‹የነገዎቹን አዳነ ግርማ፣ የነገዎቹን ሳላዲን ሰይድ፣ የነገዎቹን ሽመልስ በቀለ፣ የነገዎቹን ሎዛ አበራን፣ የነገዎቹን ብርቱካን ገብረ ክርስቶስንና የመሳሰሉትን እግር ኳሰኞችን መፍጠር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሥራው በዋናነት ለሚመለከተው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ብቻ የሚተው መሆን የሌለበትና እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለዚህ የሚመጥን አቅም ስላለ የመፍትሔው አካል በመሆን ኢትዮጵያ በእግር ኳስ አንድ ዕርምጃ እንድትራመድ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በዛሬው ዕለት ይህን የመግባቢያ ሰነድ የፈረማችሁ ዩኒቨርሲቲዎች ሥራውን በአግብቡ በመሥራትና በመከታተል ውጤታማ ሥራ እንድትሠሩና የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራች የሆነችው አገራችን ወደ ተሻለ የእግር ኳስ ማማ እንደምናመጣት ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ማለታቸው ጭምር በመግለጫው ተካቷል፡፡

  በመግባቢያ ሰነዱ ፊርማቸውን ያኖሩት ዩኒቨርሲቲዎች ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ሐሮሚያ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና አሶሳ ዪኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡ የቀሩት የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣይ የዚህ ስምምነት አካል እንዲሆኑ በከፍተኛ ትምህርትና ሳይንስ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካይነት የማሳመን ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

  በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የተጨዋቾችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ፣ የኃይል አጠቃቀም፣ አተነፋፈስና መሰል መረጃዎችን ለመቀበል የሚያስችል ካታፑልት የተሰኘ ዘመናዊ መሣሪያ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዕርዳታ መስጠቱ ታውቋል፡፡

  እንደ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክና ልማት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኩሩ ማብራሪያ፣ ካታፑልት የተሰኘው መሣሪያ ተጨዋቾች በደረታው ላይ እንዲያስሩት ይደረግና ሜዳ ውስጥ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በጂፕኤስ አማካይነት ከሳተላይት መረጃን የሚቀበል ነው፡፡ በመረጃው መሠረት ተጨዋቹ በሜዳ ውስጥ የሚሸፍናቸው ርቀቶች፣ ከአካላዊ ብቃት ጀምሮ የአተነፋፈስ ችግር ካለበት፣ የኳስ ቅብብል ክህሎትና ፍጥነት መረጃው ከተወሰደ በኋላ ለተጨዋቹ በሥልጠና አልያም በሥነ ልቦናና መሰል ዕገዛዎች እንዲደረግለት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡

  ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መሣሪያው ከሳተላይት የሚቀበለውን መረጃ ማንበብና በመረጃው መሠረት ለተጨዋቹ የሚያስፈልገውን ዕገዛ ለማድረግ ሁለት ከፍተኛ ባለሙያዎችን ወደ ደቡብ አፍሪካ ልኮ ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረጉን ያብራሩት አቶ መኮንን፣ ሙያተኞቹም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘሩ በቀለ (ዶ/ር) እና በቀድሞ የአየር ኃይል ባልደረባ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ቸርነት አሰፋ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

  ለቶኪዮ የ2020 ኦሊምፒክ የመጀመርያ ማጣሪያውን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የኡጋንዳ አቻውን የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች፣ ካታፑልት የተሰኘውን አዲሱን መሣሪያ በደረታቸው በማድረግ ልምምድ በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

  በተመሳሳይ በወንዶች ከ23 ዓመት በታች የመጀመርያ ማጣሪያውን ከማሊ አቻው ጋር አድርጎ በሜዳው በአቻ ውጤት ተለያይቶ ከሜዳው ውጪ 4 ለ0 በድምሩ 5 ለ1 የተሸነፈው የኢሊምፒክ ቡድን ለሽንፈቱ ምክንያት ያደረገው ባማኮ ላይ የነበረውን የአየር ሁኔታ መረዳት ባለመቻሉ ተጨዋቾች ሙሉን የጨዋታ ጊዜ የተመጣጠነ አቅም መጠቀም የሚያስችላቸውን ኃይል መቆጠብ ባለመቻላቸው የመጣ ሽንፈት መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...