Friday, August 19, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ችግር አውቀውት ይሆን?

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ችግር አውቀውት ይሆን?

  ቀን:

  በጌታቸው አስፋው

  ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር መቀየር እንዳለበት አውቀናል፣ በሚገባም ተዘጋጅተንበታል፤›› ማለታቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እየደጋገሙ እያስደመጡ ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ችግር ሥር መሠረት በሚገባ ገብቷቸው ለዚህም ዝግጁ ሆነው ይሆንን?

  እንደ ቀዳሚዎቻቸው ሁለት የኢሕአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የክፍላተ ኢኮኖሚዎች ፕሮጀክቶች ዕቅድ ክንውን ዲስኩር ሲናገሩት ቀላል ሲሠሩት ከባድ እንዳይሆንባቸው፣ አራት ጥያቄዎችን አንስቼ እንዴት ሊፈቷቸው እንደሆነ መጠየቅ እሻለሁ፡፡

  የመጀመርያው ጥያቄዬ ቀዳሚዎቻቸው ሁለቱ የኢሕአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሥራ አጥ ሁኔታን ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ጥሪት (Revolving Fund) ከመመመደብ የማይክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ እሳቸው በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዴት ሊፈቱት እንዳሰቡ እርግጠኛ ሆነዋል ወይ የሚል ነው፡፡

  ‹አልማዝን ዓይቼ አልማዝን ባያት

  ሦስተኛዋ አልማዝ ብትመጣ ድንገት

  ሁለቱን አልማዞች ስላስረሳችኝ . . . › የክቡር  አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ (ዶ/ር) ደርግ ንጉሡን ከሥልጣን ባወረደበት ወቅት ለሦስቱ የደርግ ሊቃነ መናብርት ዘፈነ ተብሎ ይነገራል፡፡ ቀዳሚዎቹንም ሆኑ የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትሮቻችንን በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምርጫ ያደናገሩ ሦስቱ አልማዞች ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ናቸው፡፡

  አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገሪቱ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ  ክምችት መሟጠጥን አስመልክቶ አንዴ ዳያስፖራው ዘንድ፣ ሌላ ጊዜ ዓለም ቀፍ ድርጅቶች ዘንድ፣ ሦስተኛ ጊዜ የአገሮች መንግሥታት ዘንድ ከመሯሯጥ ጋር ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ምሶሶ የሆኑት አራት አምስት ድርጅቶችን ለሽያጭ አቅርበዋል፡፡

  ይህ ሁሉ ታዲያ የሦስቱን አልማዞች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አስተሳስሮ በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመፍታት የሚያስችል ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የመነጨ የኢኮኖሚ ምርምር ባለመደረጉ፣ ከምርምሩም ተነስቶ ትክክለኛ ፖሊሲ ለመቅረፅ ባለመቻሉ ነው፡፡ እኛ ለኢትዮጵያ አዲስ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ለመንደፍ የሚያስችል ዕውቀት ላይኖረን ይችላል፡፡ ሌሎች ሰዎች የተነተኑትን ጽንሰ ሐሳብ ከእኛው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አገናዝበን ፖሊሲ ለመቅረፅ መጠቀም እንዴት አቃተን?

  ወጣቱን በሕይወቱ እስኪቆርጥ ድረስ ለስደት ዳርጎ የቆየው ኋላም ወደ አመፅ ያስገባው ሥራ ማጣትና ኑሮን ለመምራት አለመቻል ነው፡፡ እንደ ሌሎች አገር ሰዎች የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ሰው ሠራሽ ሀብትና አዳዲስ ቴክኖሎጂ ቀይሮ መጠቀም ባለመቻል፣ ተፈጥሮ ባደለችው መሬት የእኛ ብቻ ነው ተባብሎ ሽሚያ ውስጥ ገባ፡፡

  በዓለም ደረጃ የታወቁ ኢኮኖሚስቶች ከጻፏቸው ኢኮኖሚ ነክ ጽሑፎች ዋነኞቹ የሥራ አጥነትና የሥራ ቅጥርን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ዴቪድ ሪካርዶ ስለደመወዝ መጣኝና የሥራ ቅጥር ተዛምዶ ጽፏል፡፡ ካርል ማርክስም የሪካርዶን የሸቀጦች ዋጋ በፈሰሰ ጉልበት መጠን መለካት ጽንሰ ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ የካፒታሊዝምን ብዝበዛ አጋልጧል፡፡ አልፍሬድ ማርሻልን የመሳሰሉ የኒኦ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች የሠራተኛ ቅጥር የሚፈለገው በቀጣይ የሠራተኛ ምርታማነት (Marginal Labour Productivity) ልክ እንደሆነ ተንትነዋል፡፡

  ከእነዚህ የሊበራል ማይክሮ ኢኮኖሚና የሶሻሊዝም የሥራ ቅጥር ጽንሰ ሐሳቦች በተለየ ሁኔታ፣ ዓለም ከታላቁ ዝቅጠት የወጣችበትን የሥራ ቅጥር የማክሮ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ የነደፈው ኬንስ ነው፡፡ ኬንስ በዋጋ ላይ የተመሠረተውን የሊበራል ማይክሮ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ በጥቅል አገራዊ ገቢ ላይ በተመሠረተ የፖሊሲ ማክሮ ኢኮኖሚ ትንታኔ ቀልብሷል፡፡

  የሥራ ቅጥር፣ ወለድና የጥሬ ገንዘብ አጠቃላይ ጽንሰ ሐሳብ (The General Theory of Employment, Interest, Money) በተባለው ዝነኛ መጽሐፉ ኬንስ የሥራ ቅጥርን ከጥቅል የምርት ፍላጎት፣ የወለድ መጣኝ፣ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትና ከመሳሰሉ የብሔራዊ ኢኮኖሚ መለኪያዎች ጋር ያገናኛል፡፡ የሥራ ቅጥርንና የኢኮኖሚ ዕድገትን ከአምራቹ ወይም ከምርት አቅርቦት ጎን (Supply Side) ሳይሆን፣ ከሸማቹ ወይም ከምርት ፍላጎት (Demand Side) ጋር አገናኝቶ ተንትኗል፡፡ ስለዚህም አስተምህሮው የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚክስ (Demand Side Economics) ተብሏል፡፡

  ይህ የቀድሞ የኢሕአዴግ መሪዎች ለአምራቹ ብቻ ከሰጡት ትኩረት ለየት ያለ አካሄድ ነው፡፡ ‹በአንድ እጅ አይጨበጨብም› እንደሚባለው ፍላጎትን ወደ ጎን ትቶ አቅርቦት ላይ ብቻ ማትኮር ወንዝ አላሻገረንም፡፡ ስለአምራቹ ሲታሰብ የሚያመርትበት የማምረቻ መሣሪያ አለው ወይ ተብሎ እንደሚታሰበው ሁሉ፣ ስለሸማቹ ሲታሰብም የሚሸምትበት ገቢ አለው ወይ ተብሎ መታሰብ አለበት፡፡ አለበለዚያ ምርትና ገቢ ወይም አቅርቦትና ፍላጎት አይጣጣሙም፡፡ ሁለቱ እንዲጣጣሙ አቅርቦትንም ሆነ ፍላጎትን በማክሮ ወይም ጥቅል ኢኮኖሚ ደረጃም ሆነ በማይክሮ ወይም ዝርዝር ኢኮኖሚ ደረጃ መመልከት ይቻላል፡፡

  ኬንስ የጥቅል ምርት ፈላጊዎች የሆኑት ቤተሰቦች፣ ድርጅቶች፣ መንግሥትና ኤክስፖርት ከየራሳቸው የግል ምክንያቶች ጋር በወለድ መጣኝ መተለቅና ማነስ ምክንያትም ሸመታዎቻቸውን እንደሚቀንሱና እንደሚጨምሩ፣ ይህም የሥራ ቅጥር ሁኔታን እንደሚለዋውጥ ተንትኗል፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ ዕይታ የሥራ አጥ ቅነሳ ፖሊሲን ከወለድ መጣኝ ፖሊሲ ነጥሎ ማየት አይቻልም፡፡

  ታዲያ ባለፉት በርካታ የኢሕአዴግ ዘመናት ባንኮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደለበው የወለድ መጣኝ የቤተሰቦችን የፍጆታ ወጪ፣ የአምራች ድርጅቶችን ኢንቬስትመንት ወጪ፣ የመንግሥትን የመሠረተ ልማት ወጪ፣ የኤክስፖርት እንቅስቃሴን ወጪ፣ በአጠቃላይ የጥቅል ፍላጎትን ወጪ ብሎም የሥራ ቅጥርን ማቀጨጩን በሳይንሳዊ ትንተና ማረጋገጥ እንዴት አይቻልም? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቆጣቢው ከዋጋ ንረት በግማሽ ያነሰ ሰባት በመቶ አክሳሪ የወለድ መጣኝ እየከፈሉ፣ እስከ ሃያ በመቶ ወለድ የሚያገኙትን ንግድ ባንኮች በአዲሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አስተዳደራቸው ሊደፍሩ ይሆን?

  ከአገሬ ድርሻዬን ላንሳ እየተባለ የሚቀለድበትና ግማሾቹ በተደራጁ በጥቂት ወራት ውስጥ የሚፈርሱት የቀድሞው መንግሥት የሥራ ዕድል ፈጠራ ተዘዋዋሪ ጥሪት (Revolving Fund) የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚ ፖሊሲ ብቻውን ረዥም መንገድ እንዳላስኬደ ታይቷል፡፡ ምክንያቱም በአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚ ፖሊሲ የተመረተው እንዲሸጥ ገቢን በማሳደግ የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚ ፖሊሲ አልታገዘምና ነው፡፡ በአንድ እጅ ብቻ ለማጨብጨብ ነው የተሞከረው፡፡

  የአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ካቢኔም ባሳለፍነው አንድ ዓመት ውስጥ ዓይኑ ምርትን በማበረታታት የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ላይ ብቻ እንጂ፣ የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚው ላይ ሊያማትር ባለመቻሉ ችግሮች ተባብሰው ቀጠሉ እንጂ አልተቀረፉም፡፡ ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊቀይሩት ያሰቡት የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ለውጥ በወለድ መጣኝና በኢንቨስትመንት ግንኙነት የአቅርቦት ጎን ማክሮ ኢኮኖሚና በገቢ መጠንና የወጭ ግንኙነት የፍላጎት ጎን ማክሮ ኢኮኖሚ ትንታኔ መሠረት፣ የሥራ ቅጥርና የወለድ መጣኝ የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያስገነዝበውን የታላላቅ ምሁራን ጽንሰ ሐሳብ ከግምት ለመውሰድ ዝግጁ ነውን?

  ሁለተኛው ጥያቄዬ የዘመናችን ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች የሚያስገነዝቡት ለማክሮ ኢኮኖሚ ጤናማነትና ስኬት የሸማቹና የአምራቹ ተገበያዮች አዋቂ መሆን፣ ለማክሮ ኢኮኖሚው የማይክሮ ኢኮኖሚው መሠረታውያን (Microeconomic Foundations of the Macro Economy) በጣም አስፈላጊነት ነው፡፡ በውድድራዊ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ምንጊዜም ሸማቾች በሚሸምቱት ሸቀጥ ዋጋ ልክ ከሸቀጡ የሚያገኙትን ጠቀሜታ ከፍተኛ (የላቀ) ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አምራቾችም በሚያመርቱት ምርት ወጪ ልክ ከምርቱ የሚያገኙትን ትርፍ ከፍተኛ (የላቀ) ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ ይህ ጥረትም ሰውን አዋቂ ኢኮኖሚያዊ ሰው ያደርገዋል የሚለው አጠቃላይ የማይክሮ ኢኮኖሚ መርህ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ያህል እውነትነት አለው?

  ዝርዝሩ ለጥቅሉ የሚሰጠው አለው፣ ጥቅሉም ለዝርዝሩ የሚሰጠው አለው፡፡ የሚቀባበሉት የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መረጃዎች ዝርዝሩ ወይም ግላዊው በማይክሮ ደረጃ የራሱን ፖሊሲ ለመቅረፅና ጥቅሉ ወይም ብሔራዊው በማክሮ ደረጃ የራሱን ፖሊሲ ለመቅረፅ በጣም አስፈላጊያቸው ነው፡፡ ‹‹ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን›› በሚል ርዕስ በመስከረም 2007 ዓ.ም. ባሳተምኩት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መጽሐፍ የዝርዝሩንና የጥቅሉን ተዛምዶ አመልክቼአለሁ፡፡

  የግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚው ተዛምዶ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ምን ይመስላል? የግለሰቦች የሸማችነትንና የአምራችነት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አዋቂነት ለብሔራዊ ኢኮኖሚው በጎ ተፅዕኖ እያደረገ ነው? ወይስ እየጎዳው ነው? በግልና በጋራ በገበያ ውስጥ ተወዳድረን እያደግን ነው? ወይስ እየተሻማን ነው? ከሽሚያ ሰውነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ሰውነት እየተቀየርን ነው? ወይስ ከኢኮኖሚያዊ ሰውነት ወደ ሽሚያ ሰውነት እየተቀየርን ነው?

  ባለፉት በርካታ ዓመታት ‹ደንበኛ ንጉሥ ነው› የሚባለው ሸማች ከሸመታው የሚያገኘውን ጠቀሜታ የላቀ ለማድረግም ሆነ፣ አምራቹ ከሽያጩ የሚያገኘውን ትርፍ የላቀ ለማድረግ እንዳይሞክር ሸመታው በውጭ ሸቀጦች የተጥለቀለቀ ሆኗል፡፡ ግብይቱ ኢትዮጵያዊ ሸማችንና ኢትዮጵያዊ አምራችን ያገናኘ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዊ ሸማችንና ቻይናዊ አምራችን ያገናኘ ነበር፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ አምራቹን ከማበረታታት የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚክስ ጎን ለጎን ሸማቹን ለማበረታታት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ምን ዓይነት አጠቃላይ የገቢ መጠንና የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመንደፍ ያስባሉ የሚለው ሁለተኛው ጥያቄዬ ነው፡፡

  ሦስተኛው ጥያቄዬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢኮኖሚ ጉዳይ ከሰጡት ጊዜያቸው ውስጥ ከሞላ ጎደል ጠቅላላውን የያዘው፣ በአገሪቱ ባለሙያዎችና በመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን የተሰጠውን የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭና የውጭ ምንዛሪ መጣኝ የተመለከተ ጉዳይ ነው፡፡ 

  የውጭ ምንዛሪ ግኝት በኤክስፖርት ተወዳዳሪነት ላይና የኤክስፖርት ተወዳዳሪነትም፣ በእርግጠኛ አማካይ የምንዛሪ መጣኝ (Real Effective Exchange Rate) ላይ ጥገኞች ናቸው፡፡ እርግጠኛ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ በዋጋ ንረት ላይና የዋጋ ንረትም በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ ጥገኛ ናቸው፡፡

  በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ባለፉት በርካታ ዓመታት በየዓመቱ በ28 በመቶ ሲያድግ እንደነበረም፣ ብሔራዊ ባንክ በየዓመቱ የሚያወጣው ሪፖርት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ለወደፊት የዋጋ ንረትንና በውጭ ምንዛሪ መጣኝ የብርን ዋጋ መውደቅ ለመከላከል አኮማታሪ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲን መከተል እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዘብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግን የምርት ፍላጎትን ለማበረታታት የኅብረተሰቡን ገቢ ለማሳደግ አስፋፊ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ መከተል እንደሚያስፈልግ ይታመናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተዘጋጅተንበታል በሚሉት አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር እነዚህን ቅራኔዎች እንዴት ለመፍታት አስበው ይሆን? 

  አራተኛው ጥያቄዬ በይዘት ከሁለተኛው ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም በአካሄድ ስለሚለይና የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት አሥርት ዓመታት በቀድሞው የኢሕአዴግ አስተዳደር ሲታለል የኖረበት ስለሆነ፣ ራሱን የቻለ ጥያቄ ላደርገው የፈለግሁት ትራንስፎርሜሽን ስለሚለው ቃል ነው፡፡

  ካርል ፖላኒ የተባሉ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው የሃንጋሪ ተወላጅ የፖለቲካ ኢኮኖሚስት እ... 1944 ‹‹ታላቁ ትራንስፎርሜሽን›› በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ፣ በእንግሊዝ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በጀመረበት ወቅት የተካሄደውን ለውጥ ያትታል፡፡ እንደ ጸሐፊው አመለካት የገበያ ኢኮኖሚና የአውሮፓ ብሔራዊ መንግሥታት ከከተማ አስተዳደርነት (City States) ወደ አሁኑ የአገሮች ቅር የተቀየሩበት (Nation Building) ተለያይተው የሚታዩ ነገሮች ሳይሆኑ፣ በገበያ ማኅበረሰብ (Market Society) አፈጣጠር ውስጥ የፈለቁ የተያያዙ ክስተቶች ናቸው፡፡

  በገበያ ማኅበረሰብ (Market Society) መፈጠር ምክንያት የሰው ልጆች የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ተለውጧል፡፡ ቀድሞ የነበረው ቡድናዊና ማኅበረሰባዊ አመለካከትና አደረጃጀት ተደምስሶ በምትኩ አዲስ በዜግነት ላይ ብቻ የተመሠረተ አመለካከትና የገበያ ማኅበረሰባዊ አደረጃጀት ተተክቷል፡፡ ከገበያ ማኅበረሰብ በፊት መሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች፣ እንዲሁም ምርት የማምረትና የመከፋፈል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በጎሳ መሪዎች ወይም በባላባቶች የተያዙ ሲሆን፣ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ወይም የገበያ ማኅበረሰብ መፈጠር፣ኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት፣ብሔራዊ አገሮች መንግሥታት መመሥረት፣ በአጠቃላይ አነጋገር የትራንስፎርሜሽኑ ለውጥ በፊት የነበረውን የሕዝቦች ቡድናዊ ኮንትራታዊ ውል የኑሮ ሥርዓት ቀይሮታል፡፡ ‹ወገኔ ያስተዳድረኝ› ከሚል ጠባብ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወደ ‹ኑሮዬን የሚያሻሽልልኝ ችሎታ ያለው ሰው ያስተዳድረኝ› የሚል ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ ተለውጧል፡፡

  ኢኮኖሚ ማለት ሀብት መፍጠርና የተፈጠረውን ሀብት መጠቀም ማለት ሲሆን፣ በመፍጠሩ ሒደት የተፈጥሮ ሀብት በምርታማነት ላይ ተመርኩዞ በክፍላተ ኢኮኖሚዎች ይደለደላል፡፡ በመጠቀሙ ሒደት ሰው ሠራሹ ሀብት በፍትሐዊነት ላይ ተመርኩዞ ለሰዎች ይከፋፈላል፡፡

  ከቀረበው ሀተታ እንደምንረዳው ምንም እንኳ ገበያም ሆነ መንግሥት የተፈጥሮ ሀብትን በክፍለ ኢኮኖሚዎች በመደልደልና ለሰዎች በማከፋፈል የየራሳቸው የሆነ ጉድለት ቢኖርባቸውም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በፊት የነበሩት መሪዎቻችን የተፈጥሮ ሀብትን በምርታማነት ላይ ተመርኩዞ በክፍላተ ኢኮኖሚዎች በመደልደሉ የሀብት አፈጣጠር ላይ ግብርናውን በእጃቸው ጎትተው ወደ ኢንዱስትሪ ለማምጣት ያደረጉት የትራንስፎርሜሽን ሙከራ እንዳልተሳካላቸው ዓይተናል፡፡ በሀብት አጠቃቀሙም በውድድር ምትክ ሽሚያ ነግሦ እንደነበር ታዝበናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የገበያ ማኅበረሰብ በመፍጠርና ገበያው በክፍለ ኢኮኖሚዎች የሀብት ድልድል በማድረግ፣ የሀብት አጠቃቀሙም በውድድር ላይ እንዲመሠረት ከቀዳሚዎቻቸው በተለየ መንገድ ለማስተግበር በባለሙያና በመዋቅራዊ አደረጃጀት ምን ዝግጅት አላቸው?

  የገበያ ማኅበረሰብ መፈጠር ለትራንስፎርሜሽን ቅድመ ሁኔታ ሲሆን፣ የግለሰቦች የመሬትና ሌሎች የምርት ግብረ ኃይሎች (Factors of Production) ባለቤት መሆንም ለገበያ ማኅበረሰብ መፈጠር ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ የመሬት ባለቤትነትን ለክልል መንግሥታትና ብሔረሰብ አባላት ብቻ ሰጥቶ፣ ሌሎች ዜጎችን በአገራቸው ባይተዋር ያደረገውን ቡድናዊ ኮንትራታዊ ውል ‹የጎሳ ፌዴራሊዝም› ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀይሩታልን?

  ከዚህ በላይ የቀረቡት ጥያቄዎች መመለስ እንደሚገባቸው እንዳለ ሆኖ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የረዥም ጊዜና የአጭር ጊዜ ግቦች ሲኖሩት የረዥም ጊዜው ግብ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ የአጭር ጊዜ ግብ ግን ገበያዎችን በማረጋጋት ላይ ያተኩራል፡፡ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ውጣ ውረድ ዙር (Business Cycle) የገበያ መዋዠቅን ለማረጋጋት የሚነደፉ የአጭር ጊዜ ፖሊሲዎች ሲሆኑ፣ ለረዥም ጊዜ ግብም መሠረት ናቸው፡፡

  የብሔራዊ ባንክ ገዥ በቅርቡ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዝ ላይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በግንባታ ሥራ መቀዛቀዝም ተረጋግጧል፡፡ የመንግሥት ግብር እየከፈሉ በመደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ የግንባታ ድርጅቶችና ሰዎች ወደ ኢመደበኛና ሕገወጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት እየተገደዱ ነው፡፡

  ኢኮኖሚውን አረጋግቶና በረዥም ጊዜ ስትራቴጂ አሳድጎ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፈጠር አስፋፊ የጥሬ ገንዘብና የበጀት ጉድለት ፖሊሲን መከተል የግድ ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፍጆታና የመዋዕለ ንዋይ ሸማቾችን ከዋጋ ንረት ለመከላከል አኮማታሪ የጥሬ ገንዘብና የበጀት ጉድለት ፖሊሲን መከተል የግድ ይላል:: ሁለቱ  የሥራ አጥነትና የዋጋ ንረት አልማዞች መካከል አንደኛውን ለመምረጥ የሚያስቸግርበት ሁኔታ አለ፡፡ በታዳጊ አገሮች ደግሞ ከጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲው ጋር የሚቆራኘው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሦስተኛዋ አልማዝ ጉዳይ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ የዋጋ ንረትና ሥራ አጥነት በጥምረት ስለተከሰቱ አስፋፊም ሆነ አኮማታሪ የንግድ ሥራ ውጣ ውረድ ዙር አለዛቢ፣ ተቃራኒ የጥሬ ገንዘብና የበጀት ጉድለት ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ውጤት አልባ አደረጓቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም ነው ፈረንጆቹ በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ልጓም ሚዛን ከመጠበቅ ይልቅ፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በቅልጥፍና ከመንግሥት ክፍለ ኢኮኖሚ ይሻላል ብለው የጥንቱን ሊበራል ኢኮኖሚ በአዲስ ስያሜ ኒዮ ሊበራሊዝም ብለው ያደሱት፡፡

  እድሳቱ ብዙ ዓይነት ዕርምጃዎችን የያዘ ነው፡፡ ከዋና ዋናዎቹም አንዱ መንግሥት ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ግብር ባይሰበስብ፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በሚያገኘው ትርፍ የምርምርና ሥርዓት ተግባሮችን አከናውኖ ኢኮኖሚውን በፍጥነት ያሳድጋል ነው፡፡ በዚህ የዕድገት ሞዴል ከ1980ዎቹ ጀምሮ ዓለም በኮምፒዩተርና በሞባይል ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን አድጎ ለእኛም ትሩፋቱ ደርሶናል፡፡

  በ2008 ዓ.ም. የገንዘብ ቀውስ የኢኮኖሚ ሚዛን መጓደልና የገበያ አለመስተካከል ስለገጠሟቸው፣ ምዕራባውያንም እንደገና የገበያ ኢኮኖሚውን በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ልጓም መግራት አዘንብለዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በፊት በአውሮፓ ወደ ነበረውና የሊበራሊዝም ተቃራኒ ወደ ሆነው በመንግሥት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የውጭ ንግድ ቁጥጥር ማድረግ (Mercantalism) የኢኮኖሚ ፍልስፍና ተመልሰው አሜሪካና ቻይና የንግድ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡

  እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ከሥራ አጥነትና ከዋጋ ንረት በተጨማሪ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሦስተኛ አልማዝም እንደ ተጣማሪ ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በአሁኑ ጊዜ ሁለቱን አልማዞች ረስቶ በሦስተኛዋ አልማዝ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ላይ ያተኮረ ይመስላል፡፡

  ከዚህም በላይ ታዳጊ አገሮች ገበያውን በፖሊሲ ከመግራት ጎን ለጎን ስለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ቅልጥፍናና መሠረተ ልማትና ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ሰማንያ በመቶ ለሚሆነው ለገጠሩ ሕዝብ ለማዳረስም ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡

  የብሔራዊ ባንክ ገዥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ መቀዛቀዝ ላይ እንደሚገኝ ባመኑ ከሳምንት በኋላ፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽነሯ ሦስተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚገዛ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ እየተዘጋጀ እንደሆነ አበሰሩ፡፡

  እኔ እንደ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያነቴ የማውቀው በቀውስ ውስጥ ሆኖ የረዥም ጊዜ መሪ ዕቅድ ማዘጋጀት ጠቃሚ እንዳልሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ዕቅድ ከነበሩ መረጃዎች ተነስቶ የወደፊቱን ግብና ዓለማ በመተንበይ ካሰቡት ለመድረስ አስፈላጊ ሀብትን መደልደል ማለት ነው፡፡

  የነበሩት መረጃዎች የወደፊቱን የሚያስተነብዩ እንዳልሆኑ በመረጃው ትክክለኛነት ባላምንበትም፣ የመንግሥት ግብር መጣኝ ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረበት 13.7 በመቶ ወደ 10.7 በመቶ መውረዱን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የወደፊቱን ለመተንበይ የትኛውን መረጃ ልንጠቀም ነው? ከአሥር ዓመት በፊት የነበረውን ወይስ የዘንድሮውን? ግራ አጋቢ ነው፡፡ ዕቅድ ደግሞ ግራ በሚያጋባ መረጃ ላይ አይመሠረትም፡፡

  አውሮፓውያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ በኋላ ከቀውስ ለመውጣት ማርሻል ፕላን የተሰኘውን ዕቅድ ያዘጋጁ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የሚዘጋጀው ዕቅድ ከቀውስ ለመውጣት እንደሆነ ኮሚሽነሯ አልገለጹም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ከአሮጌው ኢሕአዴግ ዕዳና ባዶ ካዝና እንደተረከቡ ቢነገርም፣ አገሪቱ በኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንዳለች አልተነገረም፡፡

  ከዚህ እልፍ ሲል ደግሞ በፖለቲካው አገሪቱ ምን ዓይነት ፌዴራላዊ ቅርፅ እንደሚኖራት ገና አልተወሰነም፡፡ ሕገ መንግሥቱም ሊቀየር ይችላል፡፡ በፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ረገድም የመሬት ይዞታ ሥሪቱ ሊቀየር ይችላል፡፡ መንግሥት ከሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት ጀምሮ የገንዘብ ገበያ እንዲመሠረት እንደሚፈቅድ ተናግሯል፡፡ ሌሎች ሥር ነቀል ለውጦችም ይጠበቃሉ፡፡

  ዕቅድ በኢኮኖሚ አስተዳደር ዕርከኖች ውስጥ አራተኛ ደረጃ ነው፡፡ በቅድሚያ የአገሪቱ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ይተነተናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በተተነተነው ነባራዊ ሁኔታ መሠረት አገሪቱ የምትከተለው ኢኮኖሚያዊ ጽንሰ ሐሳብ ይመረጣል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ጽንሰ ሐሳቡን ተከትሎ ፖሊሲዎች ይቀረፃሉ፡፡ አራተኛው ዕቅድ ፖሊሲዎቹን ለመተግበር የሚወጣ ዝርዝር የተግባር መግለጫ ሲሆን፣ የታቀደውን መተግበርም አምስተኛው ዕርከን ነው፡፡ ይህ የሚያመለክተው አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ የማዘጋጀት ደረጃ ላይ እንዳልሆነች ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በግንቦት 2010 .ም. ያሳተምኩት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት›› መጽሐፍ፣ በአምስቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዕርከኖች ተዋቅሮ በስፋት ተብራርቷል፡፡

  ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነደፉትን የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ለመምራት የሚያስችል መዋቅራዊ አደረጃጀትና ባለሙያ አላቸው ይሆን? የጠቅላይ ሚኒስትሩን አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ከእነዚህና ከሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አንፃር እየተከታተሉ የሚገመግሙ ገለልተኛ ተመራማሪና ጸሐፊ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በአገር ውስጥም በውጭ አገርም ስላሉ፣ እንደ ቀድሞው በዋዛ ፈዛዛ እንደማይታለፉ ተረድተውታል ወይ?

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.com.  ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ አቀረበ

  መንግስት ስኳር ኢንተርፕራይዞችን ወደግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ባለሐብቶች እንዲሳተፉ...

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...