በሩዋንዳ የተፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት ለመዘከር ለሳምንት ያህል በመዲናዋ ኪጋሊ በተካሄደው የወጣቶች ኦሊምፒክ በአትሌቲክስ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን በወርቅ ሜዳሊያዎች የታጀበ ውጤት አስመዝግቦ ተመልሷል፡፡
በአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) አማካይነት በዞን አምስት አገሮች በተከናወነው ጨዋታ በአትሌቲክስ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን በአራት የወርቅ፣ በሁለት የብርና በአንድ የነሐስ በድምሩ ሰባት ሜዳሊያዎችን አስመዝግቧል፡፡ ቡድኑ ከትናንት በስቲያ ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ አገሩ ሲመለስ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ለባለድል አትሌቶች፣ አሠልጣኝና ቡድን መሪ 210 ሺሕ ብር ተሸልመዋል፡፡
ኢትዮጵያን በመወከል ከቀረቡት ሰባት አትሌቶች ሁሉም የሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ተሳታፏቸውን ያጠናቀቁ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በዚሁ መሠረት በ800 ሜትር ሴቶች ፍሬዘር ተስፋዬ፣ በ1500 ሜትር ሴቶች መልካም ዓለማየሁ፣ በተመሳሳይ ርቀት ወንዶች መልካሙ ዘገየና በ3000 ሜትር ወንዶች መንግሥቱ በቀለ አማካይነት የወርቅ ሜዳሊያ ተመዝግቧል፡፡
የብር ሜዳሊያ ያስመዘገቡት ደግሞ በ800 ሜትር ወንዶች ጣሰው ያዳና፣ በ3000 ሜትር ሴቶች መስታወት አማረ ሲሆኑ፣ በ5000 ሜትር ወንዶች በቦኪ ድሪባ አማካይነት የነሐስ ሜዳሊያ መመዝገቡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለልዑካን ቡድኑ ካደረገው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ባሻገር የወርቅ ሜዳሊያ ላስመዘገቡ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 25 ሺሕ ብር፣ ለብር ሜዳሊያ 20 ሺሕ ብር፣ ለነሐስ ሜዳሊያ ደግሞ 15 ሺሕ ብር፣ ለቡድኑ አሠልጣኝ 25 ሺሕ ብርና ለልዑካኑ የቡድን መሪ ደግሞ 30 ሺሕ ብር ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ማበርከቱ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
አኖካ በምሥራቅ አፍሪካ በዞን አምስት አገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው የኦሊምፒክ ጨዋታ ዓላማው በዋናነት ሩዋንዳውያን ያሳለፉትን አስከፊ የእርስ በርስ ፍጅት መታሰቢያ በማድረግ፣ ‹‹ዳግም እንዳይደገም›› በሚል መርህ ወንድማማችነትንና መቻቻልን እንዲያሰርፁ ለማድረግ ነው፡፡
በአኖካ አዘጋጅነት የዞን አምስት አገሮች የተሳተፉበት የወጣቶች ኦሊምፒክ የተከናወነው በአምስት ስፖርቶች በአትሌቲክስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በመረብ ኳስ፣ በብስክሌትና በቴኳንዶ መሆኑ ታውቋል፡፡ በወጣቶች ኦሊምፒክ የተሳተፉት አገሮች ኢትዮጵያ፣ አስተናጋጇ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ብሩንዲ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እንዲሁም በተጋባዥነት ግብፅና ፈረንሣይ ናቸው፡፡