Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገር“የብሔር ጥያቄ” የሥልጣን ህልም ሰበብ

  “የብሔር ጥያቄ” የሥልጣን ህልም ሰበብ

  ቀን:

  በያሬድ በላይ

  “የእገሌ ብሔር ጥያቄ”  ወይም “የእገሌ ሕዝብ ፍላጎት”  የሚለው ቃል የዘር ፖለቲካ በማቀንቀን ሥልጣን ለመያዝ በሚያልሙ የአገራችን ፖለቲከኞች የሚዘወተር ነው፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች ይህን ቃል የሚጠቀሙት አርቆ ሳያስብና ነገሮችን ሳያስተውል፣ በስሜታዊነት የሚገፋፋውን የኅብረተሰብ ክፍል በማነሳሳትና ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት፣ ከተቻላቸውም በማለያየት ሥልጣን እንይዛለን ብልው ከንቱ ህልም በማለማቸው እንጂ፣ በእውነት ለሕዝብና ለአገር በጎ በመመኘት አለመሆኑን ተግባራቸው ይመሰክራል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የማንኛውም ሕዝብ ፍልጎት ግልጽ ነው፡፡ ሁሉም የሚፈልገው ሰላምን፣ ፍትሕን፣ እኩልነትን፣ ብልፅግናንና በተከበረች አገር በአንድነት መኖርን ነው፡፡ ከንቱ የሥልጣን ፍላጎትንና የጥላቻ ልብ ካላቸው ዘረኛ ግለሰቦችና ቡድኖች በስተቀር፣ ማንኛውም ሕዝብ/ኅብረተሰብ አንድነትን እንጂ መበታተንን ወይም መለያየትን አይፈልግም፡፡

  የአምላክ በጎ ፈቃድ ሆኖ እነሆ በአሁኑ ወቅት ለእነዚህ የሕዝብ ፍላጎቶች መሳካት ቀን ከሌት ያለ እረፍት የሚሰሩ የለውጥ መሪዎች አግኝተናል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ለአገርና ለሕዝብ በጎ የሚመኝ ኢትዮጵያዊ ከጎናቸው በመቆም ለለውጡ መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨትና የተለያዩ እኩይ ተግባሮችን በማቀድና በመፈጸም ለውጡን ለማጨናገፍ መሞከር፣ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጸም እንደ አጥፍቶ መጥፋት የሚቆጠር ትልቅ ስህተትና በደል ነው፡፡ እስኪ ቆም ብለን በጥሞና አርቀን እናስብ፡፡ እንበልና ይህ እኩይ ፍላጎታቸው ቢሳካና ለውጡ ቢጨናገፍ ምንድነው በአገራችን ሊከሰት የሚችለው? ከመቶ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት፣ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባትና አንዱ ዘር ከሌላው ተጋብቶና ተዋልዶ፣ በደምና ሥጋ ተዋህዶ በአንድነት የሚኖርባት ትልቅ አገር ብትፈርስ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከሳሪ ወይም ተጎጂ ነው የሚሆነው፡፡ በአንድነትና በእኩልነት መኖር ግን ለሁሉም ይበጃል እንጂ ማንንም አይጎዳም፡፡ ያለን ወቅታዊ ምርጫ ሁለት ብቻ ነው፡፡

  አንደኛው የተጀመረውን ለውጥ በመደገፍ በተከበረችና በበለፀገች ትልቅ አገር ውስጥ በሰላም፣ በእኩልነት፣ በፍቅርና በአንድነት መኖርና ሉዓላዊት አገርን ለትውልድ ማሻገር ነው፡፡

  ሁለተኛው ደግሞ ለውጡን በማጨናገፍ በፈረሰች አገር (Failed State) ውስጥ በጦርነትና በረሃብ መሰቃየት ነው፡፡ በትክክል የሚያስብ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ሁለተኛውን መንገድ ይመርጣል ብዬ አላስብም፡፡ የኢትዮጵያ አምላክና የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር አይፈቅዱም፡፡

  ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተከሰቱት ችግሮች መሠረታዊ መንስዔአቸው ምንድነው? ይህንን ጥያቅ በትክክል ለመመለስና ወደ መፍትሔ ለመሄድ፣ እውነቱ ሳይሸፋፈንና ሳያድበሰበስ እንደሚከተለው በግልጽ መነገር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶችና የሕዝብ መፈናቀሎች መሠረታዊ መንስዔአቸው ምንድ ነው? የሚለው ጥያቄ መልስ ወደዚህ ጽሑፍ አርዕስት ይወስደናል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች መፈጠር ዋነኛው ምክንያት ከ27 ዓመታት ወዲህ በአገራችን ፖለቲከኞች የተዘጋጀውና በጸፉት ሕገ መንግሥት ተደግፎ አገራችን ስትመራበት የቆየችው፣ በዓለም ብቸኛ የሆንበት የጎሳ ፌዴራሊዝም (Ethnic Based Federalism) ሥርዓት ነው፡፡

  ለዚህ የጎሳ ፌዴራሊዝም መጠንሰስ ምክንያት የሆነው ደግሞ፣ በ1966 ዓ.ም. በአገራችን የተከሰተውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ “የእገሌ ሕዝብ ነፃ አውጪ” በሚል ሰበብና ስያሜ የተደራጁ፣ የሥልጣን ፍልጎት ያላቸው ዘረኛ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚከተሉት አስተሳሰብና አካሄድ ነው፡፡ እስኪ ቆም ብልን እናስብ ማንን ከማን ነው ነፃ የሚያወጡት? ተጋብቶና ተዋልዶ በአንድነት የኖረን ሕዝብ ማለያየት ወይም ማጣላት ነፃ ማውጣት አይደለም፡፡ ይልቁንም ማኮሰስና ማክሰር እንጂ፡፡ ለከንቱ ሥልጣን ፍላጎት ብሎ አገርንና ሕዝብን መበደልም ነው፡፡ ማንኛውም ሕዝብ አንድነትን፣ እኩልነትን፣ ሰላምንና ብልፅግናን ይሻል እንጂ መለያየትን ወይም መጣላትን አይፈልግም፡፡

  አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ የአገራችን ፖለቲከኞች “እኔ የእገሌ ሕዝብ ብሔርተኛ ነኝ” ብለው አፋቸውን ሞልተው በይፋ በሚዲያ ሲናገሩ ስሰማ ይዘገንነኛል፡፡ አንድ ሰው እንዲህ ሲያስብና ሲናገር፣ በሌላ አገላለጽ ዘረኛ (Racist) መሆኑንና ራሱ ከመጣበት ዘር በስተቀር ለሌላው ኢትዮጵያዊ ደንታ እንደሌለው፣ ወይም ጥላቻ እንዳለው ነው የሚያሳየው፡፡ እውነቱን ለመናገር ዘረኝነት ለማንም አይበጅም፣ ሁሉንም ነው የሚጎዳው ወይም የሚያጠፋው፡፡ በዘረኝነት ቅስቀሳ አንድን የኅብረተሰብ ክፍል (ዘር) አነሳስቼ ሥልጣን ይዤ በሰላም እኖራለሁ ማለት ከንቱ ህልም ወይም ቅዠት ነው፡፡ እዚህ ላይ ከ25 ዓመታት በፊት የተከሰተውን የሩዋንዳን ሁኔታ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በወቅቱ አገዛዝ ላይ የነበሩት ፖለቲከኞች ባቀነባበሩት ሴራ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማስነሳትና አንዱ ዘር ሌላውን እንዲጨፈጭፍ በማድረግ፣ ዓለምን ያሳዘነና የአገሪቱን ታሪክ ለዘለዓለም የሚያጎድፍ ተግባር ፈጸሙ፡፡ ሆኖም ትንሿ የምሥራቅ አፍሪካ አገር ከሰቆቃው በኋላ ከዘረኝነት የፀዳ መሪና መንግሥት በማግኘቷ ዛሬም እንደ አገር ቆማ ቀጥላለች፡፡ የተጨፍጫፊዎቹ ወገኖች ይቅርታ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚ ወገኖች ግን ለዘለዓለም ከህሊና ቁስል፣ ከኃፍረትና ከፀፀት ሊላቀቁ አይችሉም፡፡

  በአገራችን ዘረኛ ፖለቲከኞች የሚዘወተረውና በዚህ ጽሑፍ ርዕስ የተጠቀሰው “ብሔር” ወይም “Nation” የሚባለው ቃል ትክክለኛ ትርጉሙ “አገር” ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ብሔራዊ መዝሙር (National Anthem)፤ ብሔራዊ ቡድን (National Team) ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ የጎሳ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱን የመሠረቱት የአገራችን ፖለቲከኞች በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለምና በጻፉት ሕገ መንግሥት፣ የአንድ አገር ሕዝብን በጎሳ ለመከፋፈል ካስፈለገም ለማለያየት እንዲያመች ተደርጎ የተለየ ትርጉም ተሰጥቶት ቆይቷል፡፡

  ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፣ በአሁኑ ወቅት ለአገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ራዕይ ያላቸው፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የሚወዱ፣ ከፍተኛ ችሎታና ብቃት ያላቸው፣ ሌብነትንና ግፍን የሚያወግዙ፣ ፍትሕን፣ ፍቅርንና ይቅርታን የሚከተሉና ለአገር አንድነትና ብልፅግና የሚተጉ የለውጥ መሪዎች አሉን፡፡ በወቅታዊው ወጀብና ፈተና ውስጥ ሆነው እንኳን አገርን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት እያየን ነው፡፡ ስለሆነም በምንመኛት ታላቅና ሰላማዊ አገር ለመኖርና የተከበረች ሉዓላዊት አገር ለትውልድ ለማስተላለፍ እንድንችል፣ ዜጎች ሁሉ ከመሪዎቻችን ጎን ሆነን ለዚህ የተቀደሰ ዓላማና ለለውጡ መሳካት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባናል ብዬ አስባለሁ፡፡

  ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው yared.bellay@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...