Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ‹‹ሞክሼ›› ኆኄያትና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት

  በይኩኖአምላክ መዝገቡ ዘርአብሩክ

  ለምሳሌ ‹‹አማርኛ››ን ለማጥናት ፈለግን እንበል፡፡ መቼስ መነሻችን ‹አማርኛ› የሚለውን ስም ትርጒም ማወቅ ነው፡፡ ስለዚኽ የቃሉን ትርጒም ፍለጋ በመጀመሪያ መዝገበ ቃላትን እንጠይቃለን፡፡ ለምሳሌ በአለቃ ደስታ ተክለወልድ የተዘጋጀውን ታላቁን ‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት› እንፈትሽ፡፡ በፊደል ተራ ኼደን ‹አማርኛ›ን ስናገኝ መልስ የለም፡፡ ይልቁንም መዝገበ ቃላቱ ‹ዐማርኛ› ብለን በዓይኑ መነሻነት እንድንፈልግ ይመራናል፡፡ በዚኽ ዓይነት የ‹አማርኛ› ጥናታችን ከመነሻው ጀምሮ በፊደል ጥያቄ የተበረዘ፥ የታመቀ ይኾናል፡፡ ከቶም የቋንቋውን ባሕሪ በጥልቀት ለመረዳት ስንፈልግ የሞክሼ ኆኄያትን ዋና ቦታ ማወቅ የምርምራችን ዓይነተኛ አካል ይኾናል፡፡ በተለይ ንጽጽራዊ ጥናት ለማካኼድ ከ‹ሞክሼ› ኆኄያት እውቀት ውጭ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ያውና ‹ዐዲስ› የሚለው ያማርኛ መዝገበ ቃላት በዓይኑ መጻፉ ከግዕዙ እና ከዐረብኛው ‹ዲስ፥ ከትግርኛው ‹ዱሽ› ጋር ያለውን ተፈጥሯዊ ዝምድና በማስታወስ ነው፡፡ በዚኽ አምሳል በተለምዶ ‹ሞክሼ› የሚባሉት ኆኄያት ዐማርኛን ከግዕዝ፥ ከትግርኛ፥ ከዐረቢ፥ ከዕብራይስጥ እና ከሌሎችም ቋንቋዎች ጋር ማገናኛ ሥሮች ናቸው፡፡ ናቸውናም ዐማርኛን አበጥሮ ለማወቅ ምናልባት ብቸኛ ርስተ ልሳን ናቸው፡፡ ይኽ ጽሑፍ በቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር የ‹ሞክሼ› ኆኄያቱን ሚና በጥቂቱ ለማሳየት ነው ዕቅዱ፡፡ ይልቁንም ቅዱስ ቍርዐንን ባነበቡ እና የ‹ሞክሼ› ኆኄያቱን ድምጾች በጥራት በሚጠሩ የዐማርኛ ተናጋሪዎች እና በትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ የእኒኽ ድምጾች ‹ሞክሼ›ነት ምን ያክል አጠራጣሪ እንደኾነ ለማስረዳት ይጥራል፡፡ የጥናቱ ትኩረት እጅግ በርካታ የዐማርኛ ቋንቋ ብቻ ተናጋሪ ‹አልሐምዱ ሊላ› ሲል የሚያወጣቸው፥ በትግርኛው ቋሚነት ያላቸው እና ልዩነት ማስረዳት፥ የእነ ‹ሎት› እና ‹ላት›፥ ‹ንጉ› እና ‹ነጃ› ወዘተ ድምጻዊ እና ታሪካዊ ትሥሥር ማሳየት፥ የ‹ሞክሼ› ፊደላቱም በቋንቋ ጥናት ትውፊት እና መጪ ዕድል ላይ ያላቸውን ወሳኝ ሚና ማመላከት ነው፡፡

  መግቢያ፡ ሞክሼነት

  ሞክሼነት የተለያዩን ነገሮችን ባንድ ስም መጥራት፥ የተለያዩን ኹነቶች ባንድ ቅጽል ማጉላት፥ የተለያዩን ተግባሮችን ባንድ ግስ መግሰስ ነው፡፡ ሰውን እና እኽልን ‹ዘር› ብሎ ስም፥ እውቀትን እና ቅላትን ‹ብስል› ብሎ ቅጽል፥ ዐጥርን እና ሰውን ‹ካበ› ብሎ ግስ መስጠት የሞክሼነት መነሻ ሳይኾን አይቀርም፡፡ ለተመሳሰለ ኹነት አንድ ቃል መጠቀም ነው ሞክሼነት፡፡ ብዛትን – መዋለድን አይቶ ዘር ይላል፤- ዝርው፥ ዝርግ፥ ብትን ለማለት፡፡ ይኽም ለሰው፥ ለእንስሳ፥ ለአዝርእትም ስም ሊኾን ይችላል፡፡ ቅጽልም እንዲኹ ስል፥ ብስል፥ ምስል፥ ዐጭር፥ ዝርዝር፥ ምንዝር፥ ስንዝር ሲል ይገኛል፡፡ የግስ አብነት ሠራ፥ ጠራ፥ መራ ሲኾን – ሠራ፥ አረሠ፥ ጐለጐለ፥ ዐረመ፥ ዐጨደ፥ ከመረ፥ ወቃ፡፡ ሠራ፥ አበጀ፥ አዘጋጀ፥ (ስሙን፥ የሰማይ ቤቱን ወዘተ)፡፡ ጠራ – ተጣራ፥  ጠራ – ዋስ ጠራ፥ ጠራ – ጠዳ ወዘተ፡፡ ‹መራ›ም እንዲኹ ብዙ አገባብ ሊኖረው ይችላል፡፡ እንግዲኽ ክሼነት የሰያሚያን አተያይ መመሳሰል፥  የሰያሚያን ካንድ የቃልና የሐሳብ ወንዝ መቀዳት – መቅዳት የሚፈጥረው የቋንቋ መልክ ነው፡፡ አንድም ለእያንዳንዱ በጥቂት ለተለያየ ነገር በጥቂትም ቢኾን የተለያየ ስም ለመስጠት ካለመቻል የመጣ፥  ሐሳብ ከቃል የመብዛቱ ውጤት ነው ሞክሼነት፡፡ ለዚኽ ነው በስለት የተገኘን ልጅ ‹ጠኝ፥  ሰማኸኝ›፥  የብቸኞች ልጅ ‹እታፈራኹ፥  ወንድማገኘኹ›፥  ከመከራ በኋላ የተገኘን ‹ደበሸ፥  ተካልኝ፥  ማስረሻ…› ወዘተ መባላቸው፡፡ የተገኙበት ኹናቴ ሲመሳሰል ስማቸው ይመሳሰላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በአንድ ስም የተጠራ ሰው ሲወደድ የኋላን ልጆች በርሱ በመሰየም ሞክሼነት ይበረክታል፡- አዳም፥  ሐዋ፥  ቴዎድሮስ፥  ዐብደላህ፥  ለተማርያም… ገብረየስ፥  መሐመድ አወል እንዲሉ፡፡

  ቋንቋ፥  ፊደል

  ቋንቋ (ስም) በዐይነ ሥጋ፥ በዐይነ ኅሊና የታየን፥  በልብ የታሰበን ግዙፍና ረቂቅ ነገር ማርቀቅና ማግዘፍ ነው ተግባሩ፡፡ ደንጊያን ለመጥቀስ በተፈለገ ቍጥር ግዙፉን ደንጊያ ተሸክሞ እርሱን እየነኩ፥  እያመለከቱ መጥቀስ ስለማይቻል በውስን የድምጽ ቅንብር ረቂቅ ስም ሰጥቶ ያ ስም በተጠራ ቍጥር ደንጊያ በኅሊና መንኰራኵር ተሳፍሮ እተጠራበት ዘንድ እንዲመጣ ማድረግ ማስደረግ ሰው በቋንቋ መሣሪያ የሚከውነው ድንቅ ሥራ ነው፡፡ ግዙፉ፥ ከቶም ግዑዙ ህላዌ ረቂቅ መልክ ነሥቶ በኅሊና ወንዝ ሲንሸራሸር እንዲገኝ ማስቻል መቼስ ትልቅ ታምር ነው፡፡  ትልቁን አድቅቆ፥ ደቃቁን አርቅቆ ማምጣት፡፡ ይኽ ነው ማርቀቅ፡፡ በዚኽ አንጻር ደግሞ ረቂቁን ማጒላት አለ፡፡ የማይታይ መልክ ያላቸውን እነ ሕልም፥ ምኞት፥ ስስት፥ ደስታ፥ ጭንቀት በየሰዉ ልብ ውስጥ የየራሳቸውን መልክ ይዘው (እየያዙ) እንዲታዩ፥  እንዲጨበጡ ያደርጋቸዋል፡፡

  ቋንቋ ይኽን የማርቀቅና የማግዘፍ ሥራ ሲሠራ ራሱ ግን በግዝፈት እና በርቀት መካከል ይገኛል፡፡ ምናልባትም ከግዝፈት ይልቅ ለርቀት ይቀርባል፡፡ ዋና መሣርያው ድምጽ ሲኾን ለቅጽበት ብቻ ተሰምቶ (ተጨብጦ) መልሶ እልም ይላል፡፡ መሰማቱ ግዝፈቱ፥  ፈጥኖ መጥፋቱና አለመታየቱ ደግሞ ርቀቱ ነው፡፡ ይኸም የቋንቋ ጠባይ ሰው ደጋግሞ ሊሰማ የሚሻውን ቃል/ድምጽ የሚያቈይበትን መላ እንዲፈጥር ግድ አለው፡፡ ያ መላ እየተራቀቀ ደሕና ቦታ ላይ ደርሷል፡፡ የዚኽ መላ ቀዳሚው ፍሬ ግን ምናልባት ማስተዋል ወይም ጥሞና ሳይኾን አይቀርም፡፡ የተባለው ቃል እንዳይሰወርበት የሚሻ ኹሉ ኹለመናውን ለዚያ ቃል ትዝታ አስገዝቶ፥ ቃሉን በልቡ ቋጥሮ፥ በሌላ የቃል ጐርፍ እንዳይወሰድበት ሰውሮ (ለመሰወር ሲልም ተሰውሮ) መኖር መጣ፡፡ ጥሞና፡፡ ይኸ ብቻ አልበቃም – የተወደደን ቃል ዜማ አልብሶ፥  ከልሶ፥  ሠልሶ ማኖር ማቈየትም ቻለ፡ ሰው፡፡ የዜማ ጣዕም ቃል በብዙ ሰው ልብ እንዲኖር ማባበያ ነው፡፡ እርግጥ ነው ቃል በዜማ መለወሱ ውዱን ቃል ለማኖር፥  ለማቈየት ብቻ ሳይኾን በቃል ከሰው ጋ መኖር የተነሳ ሰው ‹ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ› የፍሬ ባለቤት ይኾን ዘንድ ነውም ይላሉ፡፡ ከውሃ ዳር ያለች ዛፍ በየጊዜው እንድታፈራ ቃል ያለውም ሰው፥  ነገድ፥  ሕዝብ ወኵሎ ዘገብረ ይፌጽም› ተብሎለታልና ‹ኹን› ያለው ይኾንለታል፡፡ እንዳቅሙ ፈጣሪውን ይመስላል፡፡ ለሰው ከሥራ፥  ከማከናወን ሌላ ዕድር የት አለውና? (በመፍጠር፥ በሥራ ፈጣሪውን ካልመሰለ ሊቀጣም አይደል? በሌላ ቢቀር በራብና ቍር?)

  ሌላኛው ቃልን ከጥፋት መዳኛው፥  ከችኮላ ማዝገሚያው ሥጋዌ ነው- አካል መንሣት፡፡ አካል ቅርጽ ነው – ቅርጸት – ቅርጠት፡፡ በዝርዉ ህላዌ ውስጥ ቍርጥ ያለ መልክ፥  ልክ መያዝ፡፡ ልክ የሚኖር መነሻና መድረሻ ሲታወቅ፥  ሲወሰን፥  ሲቈጠር ነው፡፡ መቍጠር መለየትን ይከተላል – ያልተለየ አይቈጠርም፡፡ ደግሞ እኒኽ ኹሉ፡ መለካት፥  መወሰን፥  መለየት፥  መቍጠር አንድ ስም አላቸው – መጻፍ፡፡ ቈፍሮ፥ ፈልፍሎ፥ ቀብቶ መልክ ማውጣት ነው – መጻፍ፡፡ ልዩነት – ቅርጽነት – ቅርጥነት – ቍርጥነት ለጽሑፍ ከመሰጠቱ በፊት ግን ይለብሰው ዘንድ ጽሑፍ ለተቈረጠለት (እንደ ሸማ) ለቃል ይስማማዋል፡፡ ጫፍና ሥሩ ላልተለየ የድምጽ ፍሰት አይደለም ጽሑፍ መፈጠሩ – ቅጥ ላለው ቃል እንጂ፡፡ ቃል ግን መልሶ መነሻና መድረሻው እስተማይታወቅ ድረስ ይበዛ ይዋለድ ያዘ፡፡ እናም ቍጥሩ /ልኩ/ ላልታወቀ ቃል ልክ – መልክ- ጽሑፍ ማበጀት ቸገረ፡፡ ስለዚኽ ቃልን (ምርቱን) ለመጻፍ (ለመለየት፥ ለመወሰን፥ ለመቍጠር) መማሰን ይልቅ የቃልን ዘር (ድምጽን) መጻፍ (መለየት፥ መወሰን፥ መቍጠር) የሚሻል መሰለ፡፡ ኧረ እንዲያውም ተሻለ!

  እዚኽ ውስጥ ያለው ስሌት ሥራን – ድካምን ማቅለል ነው፡፡ ወይም በጥቂት ድካም ብዙ ተግባር ማከናወን፡፡ ቃል በየጊዜው እንዳሸን ሲፈላ ቢገኝ የድምጾቹን ምንጮች ብቻ ይዞ መንፈላሰስ፡፡ እንዲያው ከዘመናት አንዴ ዓዳዲስ ድምጾች ቢወለዱ እንኳ ሃገረ ሙላዳቸው ርቆ ቢርቅ ያው ከጉሮሮና ከከንፈር ድንበር ስለማይወጣ መልካቸውን በደምሳሳው ተልሞ መቈየት ነው፡፡ ይኽን ሥራ ነው ቀረጻ የሚሉት – ፊደል ቀረጻ – ቀረጣ – ቈረጣ፡፡

  ፊደል መቅረጥ – መቅረጽ የጥንቱ ሰው ቃልን የማኖር እሾት ኹለተኛ ውጤት፥  በቃል ከመያዝ ቀጥሎ ያጐነቆለ ፍሬ ነው፡፡ የጥንቱ ሰው ጀምሮ ልጁ፥  የልጅ ልጁ የፈጸመው፥  ጥቂት የቀረው ሥራ ነው፡፡ የፊደል ዋና ተግባሩ ቃልን ማኖር፥  ማቈየት፥  ቃል ላይጠፋ ድኖ፥  ላይረቅ – ላይርቅ ተተክሎ፥  ከሃውልት በላይ ደንድኖ ጊዜን ይሻገር ዘንድ፥  ካባት ለልጅ፥  ከልጅ ለልጅ ልጅ ብቻ ሳይኾን የትውልድ ትሥሥር ኖረም አልኖረ ቃል ከሰው ለሰው ቅጽበትንም ቢሉ አእላፍ ዓመታትን፥  ጣገብንም ቢሉ ውቂያኖሶችን አልፎ ይደርስ ዘንድ የሚያስችለው መንኰራኵር ነው፡፡

  እንግዲያው ፊደል ለቃል (አንድም ለሰው) ይኸን ሥራ እንዲሠራ ቢያንስ አንድ ዋና ግዴታ ማሟላት አለበት፡፡ ይኽም ዋና ግዴታ ታማኝነት ነው – ያስያዙትን አለመልቀቅ፥  መልኩን እንደሻ አለመለወጥ፡፡ መልእክቱን አንድ ቦታ ወይም አንድ ጊዜ ላይ አድርሶ ከዐደራው የሚፈታ፥  የሚለቀቅ አይደለምና፥  እልፍ ባለ ቍጥር ሌላ ጠያቂ፥  ሌላ ተቀባይ አለውና፡ ስላለው፥  ስላለበት ከያዘው ላይ አንዳች እራፊ – ቅራፊ መጣል አይችልም፡፡ ይኸም ተብሏል፡- ‹የውጣ፥  እንተ አሐቲ ቅርፀታ ኢተኀልፍ እምኦሪት ወእምነቢያት›፡፡ ኦሪትን፥  ነቢያትን በየፈርጁ ልበስ – ታሪክኸ ኦሪትኽ፥  አባቶችኽ ነቢያትኽ ማደሉ!?

  ፊደል በያዘው ላይ ግን ሊጨምር ይችላል – የቀደመን ቃል ለኋለኛ ማድረስ ነውና ሥራው – ማገናኘት፡፡ ቋንቋ ማገናኛ ነው፡፡ ፊደልም ያውና ማገናኛ ኾነ – የረቂቁ ቋንቋ ግዙፍ ወኪል፡፡ በርቀትና በግዘፍ መኻል ተመላላሹ ቋንቋ የረቂቁ ሐሳብ ማግዘፊያ ነው፡፡ ድምጾችን ቀዶ፥  ቀርጾና ፈልፍሎ ሐሳብን በነዚያ ውስጥ ይቀዳል፡፡ ኾኖም ፈሳሹ ሐሳብ የተቀዳባቸው የድምጽ ቅዶች ራሳቸው ከጥቂቱ የሰው ዕድሜ ውስጥ እንኳ ኢምንት ኾነ የሕይወት ዘመናቸው፡፡ ቅጽበት፡፡ ከቅጽበቷም ብሶ ደግሞ ለመታየት አይሹም፥  በጆሮ በኩል ኽው ብለው ኾነ ሚያልፉ፡፡ ስለዚኽ እነሱኑ መጨበጥ፥  ማቈየት ይቻል ዘንድ ሌላ ቅድ፥  ሌላ ቅርጽ አስፈለገ፡፡ ፊደል – የሚሰማ ብቻ ሳይኾን የሚታይም ጭምር፡፡ ሲጠራ ይሰማል፡ ሳይጠራ ደግሞ ይታያል፡፡ ባያዩትም የትም አይኼድ – ይቀመጣል፡፡ ስለዚ ፊደል ረቂቁን ሐሳብ በከፊል፥  ለቅጽበት የሚያገዝፈው ቃል ራሱ ደግሞ ተመልሶ ሙሉ ግዘፍ የሚያገኝበት፥ አግኝቶም የሚኖርበ ቦታ፥  በቃል ውስጥ ያለንም ሐሳብ ሰው የሚቈርስበት ገበታ ነው፡፡ ይኽም የተባለ ነው – ጥንት፡፡  [ባጋጣሚ ጥሩ ቃል ነች፡፡ ምን ጊዜም የተመጋቢ ጥሪ በገበታው ላይ ከቀረበው ምግብ ለመቍረስ እንጂ ገበታውን ራሱን ለመቍረስ አይደለም]

  [‹‹በዘመናችን ግን ስንኳን ሌላ ዓይነት ሊጨመር ያው ከጥንት የቈየው ፊደልና ንባብ የጥፈቱ ሥርዓት፥  የፊደሉ አገባብ እንደ ጥቱ አልተጠበቀም አልተጠነቀቀም፡፡ ጥፈቱም አለመምርና አለትምርት በመላ፥  በግምት፥  በልማድ፥  በድፍረት ስለኾነ ሥርዓቱ ኹሉ ፊደሉም ሳይቀር መጕደልና ማነስ፥ መናደድና መፍረስ፥  መጥፋት፥  መበላሸት ዠምሯል፡፡ ፊደሎች [. . .] ፭ እንዲወጡ በብዙ ሰዎች ልብ ሐሳብና ምኞት ተነሥቶ እንደ ደጀ ጠኒ ይጕላላል፤ አንዳንድ ጊዜም እየፈላና እየገነፈለ በግልጥ ይነገራል፤ ሥራውንም እንኳ የጀመሩት ሰዎች ይኖራሉ፤ ወሰው ያለላቸው የለም እንጂ፡፡›› (ኪወክ፡ መዝገበ ፊደል ሴማውያት፡ ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. ገጽ ፳፮)]

  እስካኹን ያልነውን እንሰር፡- ሰው ያለ ሐሳብ ሊኖር አይችልም፡፡ ሐሳብም ያለ ቃል፥ ካለ ቋንቋ አይታሰብም – ቢያንስ በዚኽ በምናውቀው ዐጸደ ህላዌ፡፡ በሌላ መልክ፥ በሌላ ህላዊ እንጃ፡፡ ቃልም ያለ መያዣ፥ እንበለ መጨበጫ አይኖርም፡፡ ለዚኽም ምስክሩ ከፊደል መፈጠርና ከሕትመት ሥራ መራቀቅ በኋላ የሰው ልጅ (መፍጠር የቻለው ዘውግ – ይኽ ለጊዜው እኛን አይጨምርም) የፈጠረው ድምጽን፥  ቅስቃሴን፥  ባጠቃላይ ሕይወታዊ ተሐውሶን ማቆያ ጥበብ፡ የጥበቡም አበዛዝ ነው፡፡ ይኽ ጥበብ ከፊደል ጋር ተባብሮ የሰውን የማስታወስ እሾት፥  የሰው ቃልን ካለፈው ትውፊቱ የመውሰድ፥  ካለው ከዘመነኛው ጋርም የመለዋወጥ ሡሥ ምን ያኽል ከፍተኛ እንደኾነ ያስረዳል፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ ‹ያለፈው ምኔ ነው!? በድሮ በሬ ያረሠ የለም!› የሚሉ ሰላላ ድምጾች የሚሰሙበት ወቅት ነው፡፡ ኾኖም ይኽ አባባል ሰው ጥንተ ታሪኩን ለመረዳት፥  መጻኢ ዕድሉንም ለመተንበይ ሲል ከፈጠራቸው የቃል ማኖሪያ ጥበባት፥  ለነዚኽም ጥበባት መፈጠር ሲል ካዘራው ወዝና ላብ አንጻር ሲታይ መናኛ አባባል ኾኖ ይታያል፡፡ ባጭሩ ሐሳብ ለሰው የእስትንፋስ ያኽል ያሻዋል፡፡ ለሐሳብም ቋንቋ እስትንፋሱ ነው፡፡ ለቋንቋም ደግሞ ፊደል ገላው ነው፡፡ ሰው ገል ነውና ረቂቃኑ አይጨበጡለትም፡፡ ረቂቁን ልሳን ለገልነቱ በቀረበ፣ በተቀረጸ ፊደል ይጨብጠዋል፡፡ ያኖረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በፊደሉ ከታችነት ያኖረውን ሐሳብ ሲፈልገው እየመዘዘ ሊሰማው፥ ሊያነሳ – ሊጥለው፥ ዕድሜውን ሊያጓድንበት ይችላል፡፡ ይገባል፡፡ ይኸንም ነው የቋንቋ ጥናት የሚሉት፡፡ መነሻው ለዘመናት የካበተ፥ በፊደል ጎተራነት የተከተተ የቃል ሃብት ነው፡፡ መድረሻው ራስን ማወቅ ይሉታል፡፡ ሰው የረቂቁን ቋንቋ ነገረ ፍጥረት፥ ከቅርጸ ድምጽ እስከ ቅርጸ ሐሳብ ያለውን ኺደት፥ የግዙፋኑ መርቀቅ፥ የረቂቃኑ መግዘፍ ምሥጢሩን ከተረዳ ብዙ በረባ ነበር፡፡ ሊረባም ነው ምኞቱ – ያድርግለት፥ ይኹንለትና፡፡

  እኛም እንደሰውነታችን ምኞታችን ለመርባት ነው፡፡ ከሰው የፍለጋ ማሳ ላይ የራሳችንን ዕመም ይዘናል፡፡ የዚኸ ዕመምም አንዱ – ምናልባትም ቀዳሚው መስክ ነገረ ልሳን ነው፡፡ በሰፊውም ተተልሟል፡፡ በትልሙ ላይ ከብዙ ምእት ዓመታት በፊት ፊደል ተዘርቶበት፥ ፊደሉም ጣዕመ ልሳንን አገዳ ኾነው የተሸከሙ – የሚሸከሙ አገባቦች፥ አዋጆች፥ ሐተታዎችን አብቅሏል፡፡ ቡቃያው እንዳይጫጭም በርከት ብለን እጅ በ‘ጅ ለመረባረብ ይኸውና እየተነሳሳን ያለን ይመስላል፡፡ ከነገረ ልሳን ቀደምት ገባሮች አንዱ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፡

  ‹‹ማእረሩሰ ለግዕዝ ብዙሕ ወፍድፉድ

  ወገባሩ ኅዳጥ ወውሑድ

  ሰአልዎ እንከ ኦ አርዳእ

  ለበዐለ ማእረር እግዚኦ

  ከመ ይወስከ ካዕበ እምድሩ

  ገባረ ለማእረሩ››

  ብለውናል፡፡ ‹‹ነገረ ልሳነ ብዙ ምርት የሚሰጥ ግብርና ነው፡ ሠራተኛ አንሶ ሥራው ሳይሠራ እንዳይቀር ግን በጸሎትና በሥራ ትጉ – ብዙም ኹነ›› ነው ያሉን፡፡ ስንበዛ አንዳንድ ደንጊያ ጥለን ግንቡን፥ አንዳንድ ወራጅ አዋጥተንም ጣራውን እንሠራለን፡፡ በዚኽ የሥራ መስክ ለመሳተፍ ስል ስለ አማርኛ ቋንቋ ጥናትና ለጥናቱም በተለምዶ ‹ሞክሼ› የሚባሉት – በመባላቸውም የተነሳ ህልውናቸው በገዳይና ገላጋይ ብርታት ላይ የተንጠለጠለባቸው ፊደላት ስለሚያበረክቱት የዳበረ እርዳታ ጥቂት ዐሳብ ለመስጠት እወዳለኹ፡፡ ፊደላቱ ዐማርኛን ከዐማርኛ ጋር ቅርብ ዝምድና ካላቸው ቋንቋዎች ከነ ትግርኛና ከነ ዐረቢ አንጻር ለማጥናት ስንሻ እንዴት እንደሚረዱን ቈንጠር አድርጌ ለማየት ነው እንግዲኸ፡፡ ‹‹ለምንሳ ንጽጽሩ ያስፈልጋል? ዐማርኛን ራሱን ችሎ ማጥናት ይቻል የለም ወይ?›› ቢሉ ዐማርኛን ጠንቅቆ ለማወቅ ከእኅት ልሳናቱ ጋር ማናበብ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪ – መርማሪ ነኸ እንበል፡፡ ይኸን የጠራ የዐማርኛ ግጥም ታገኛለኸ፡-

  ያላህን ነገር ምኑን አውቀሽው

  ወይ እኔ እበላው አንቺ ዐርመሽው፡፡

  ከግጥሙ ምን ትረዳለኸ? ‹‹የተዘራውን አንቺ ደክመሽ ዐርመሽ (ዐረሙን ነቅለሽ) ስታበቂ እኔ እበላው ይኾናል›› ነው ቀረብ ብሎ የሚታየው ትርጉም፡፡ በዚኽ ትርጒም ለመቍረጥ እንዳትችል ግን ብዙ ጥያቄዎች ብቅ ይሉብኻል፡-

  1. እርሷ ያረመችውን ለምን እርሱ ብቻ ይብላ? ያረመ ከመብላት ምን ያግደዋል?
  2. በማረም እና በመብላት መካከል ብዙ ርቀት አለና ያስ ርቀት ለምን ተፈጠረ? ለምሳሌ ‹‹ወይ እኔ እበላው አንቺ ዐርመሽው›› ከማለት ይልቅ ‹‹ወይ እኔ እበላው አንቺ ጋግረሽው›› ቢል ይሻለው አልነበር ወይ? ለመብላት ከማረም ይልቅ መጋገር ይቀርባል፡፡ በመብላትና በማረም መካከል ቢያንስ ማጨድ፥ ማኸድ፥ መፍጨት፥ ማቡካት ወዘተርፈ አሉ፡፡
  3. በዚኽስ ውስጥስ ያላህ እጅ ከቶ ለምን ተጠራ?

  ‹‹አንቺ ዐርመሽው›› የሚለው ሐረግ ፈጥኖ የሚሰጠው ትርጉም ‹‹ዐረሙን አንቺ ነቅለሽው፥ ደክመሽበት›› የሚለው ሐሳብ ነው፡፡ ይኸም ስለ ኾነ ነው ከላይ ያነሳናቸው ጥያቄዎች ብቅ የሚሉ፡፡ ጥያቄዎቹም ወደ መንታ መንገድ ይመሩናል፡፡ አንደኛው መንገድ ‹‹ግጥሙ እምብዛም የተዋጣለት አይደለም፥ አረ እንዲያውም ቤት ከመምታት ያለፈ ትርጉም የለውም›› ብሎ መዝጋት ነው፡፡ ይኸ አንድ ከባድ አደጋ አለው –  አለማወቅ፡፡ ግጥሙ ከሰው ወደ ሰው ሲተላለፍ ኖሮ፥ በመዝገበ ቃላት አዘጋጁም ተመርጦ መመዝገቡ አንዳች ቍም ነገር እንዳለው ምስክር ነውና ደርሶ ግጥሙን ከጥቅም ውጭ ማድረግ አያዋጣም – ያን ማድረግ የእውቀት አምላክ የሚጠይቀውን መባ ማስቀረት፥ ከቶም በመባው መቅረብ ከሚገኘው የእውቀት እዣት መጠማትን ያመጣል፡፡ ስለዚኸ መንገዱ አያስኬድም፡፡ አያስኬድምናም ሌላ መንገድ ይውጣ፡፡ እነሆ!

  ይኸኛው መንገድ ‹‹አንቺ ዐርመሽው›› ለሚለው ሐረግ ከላይ ከቀረበው የተለየ ትርጒም መሻት ነው፡፡ የፍለጋችንንም አቅጣጫ ለማጥበብ ‹‹አንቺ›› ከሚለው ቃል ይልቅ ‹‹ዐርመሽው›› በሚለው ቃል ላይ ትኩረት ማድረግ ሳይበጅ አይቀርም፤ ምክንያቱ ‹‹አንቺ›› የታወቀ ተውላጠ ስም ነውና፡፡ ቀጣዩ ሥራ የ‹‹ዐርመሽው››ን ሥረ መሠረት መፈለግ ይኾናል፡፡ ይኸም ወደ ‹‹ዐረመ›› ያደርሰናል፡፡ ‹‹ዐረመ›› ማለት ‹‹ኰተኰተ፥ ነቀለ›› ነው – ዐረምን ፥ ዳዋን፡፡ ኾኖም ይኸ ትርጒም መልሶ እቀደመው ችግር ላይ ጣለን፡፡ ኹለተኛና ሦስተኛ ምርጫ ስንፈልግ ግን እነሆ፡- ‹‹ዐረመ፣ (ሐረመ) ተወ፥ ከለከለ፥ ለየ፥ ቀደሰ›› መኾኑን እንገነዘባለን፡፡ ይኸም ግጥማችንን ለመፍታት የገጠመንን ችግር ከላልን፡፡ ያውና፡-

  ‹‹ያላህን ነገር ምኑን አውቀሽው

  ወይ እኔ እበላው አንቺ ዐርመሽው››

  የሚለው ግጥም የሰውን ዐቅመ ቢስነት፥ ሰው ይኸን ረስቶ ለዱኒያ ሲሮጥ ደግሞ ‹‹እበላው›› ካለው ሊከለከል፥ አለውዴታው ሊተሐረም መቻሉን ያስታውሳል፡፡ እንዲኽ ያሉት ቃላት ዘላቂን እውነት ሊያስታውሱን የተፈጠሩ ስለኾነ ሊታወሱ ይገባል ሲልም ባለቤቱ (ሰው) ሲቀባበል ያኖራቸዋል፡፡ የመቀባበሉ ኺደት ወደላቀ ደረጃ ደርሶም ተጻፈ፡፡ እዚኽ ላይ ዋና ነጥባችን የዚችን ግጥም ውበት እናጣጥም፥ ዋጋዋም ዋጋ ይኾነን ዘንድ የሐመሩ ሐ እና የዐይኑ ዐ ኹነኛ ቦታ መታወቅ አለበት፡፡ ገጣሚው ከቅዱሱ ቍርዐን የአላህን ስም ተምሮ፥ በርሱም ብርሃንነት ኑሮውን አይቶ ነው ይችን ግጥም የተቀኘ፡፡ ይኸም ‹‹ሐራም››ን ከዐረቢም ቢሉ ከትግርኛ ሸምቶ፥ ወርሶ፥ ‹‹ሐ››ን ወደ ዐማርኛ አለሳልሶ በማቅረቡ ይታወቃል፡፡ ከዚኽችም ቍንጽል የ‹‹ሐ›› እና የ‹‹ዐ›› እርዳታ የምንማረው ቍምነገር አኹን ተከናውኖ የሚታየን ዐማርኛ የብዙ ልሳናት ሽምን፥ ቅምም ሊኾን እንደሚችል መገንዘብ ነው፡፡ ስለዚኽም ዐማርኛን አጥርቶ ለማወቅ ቃላቱ የቆሙበትን የሐሳብ መሠረት ማወቅ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡

  ቃል ስም ኾኖ ነገሮችን የሚጠራ፥ የሚያስታውስ፥ የሚወክል ስለመኾኑ ብዙ ተነግሯል፡፡ እውነትም ነው፡፡ እየተረሳ ያለ የሚመስል ከዚኽ ያላነሰ የቃል ሥራ ግን አለ፡፡ ይኸም የቃል ተግባር አንድ ስም አንድን ነገር የሚወክልበት ፥ ስሙ ነገሩን ጠቅሶ የተጠቀሰውን ነገር ከማሳሰብ ይልቅ ስሙ ነገሩን እንደ ሥዕል አጒልቶ የማሳየት ተግባር ነው፡፡ አንድ ምሳሌ እንጥቀስ፡ ‹‹ከተማ››፡፡ ይኸ ስም ሰዎች በሕብረት፥ ቅርብ ለቅርብ ኾነው፥ ቤቶች ሠርተው የሚኖሩበትን ቦታ ኹሉ ይጠራል፡፡ የቃሉን አመጣጥ ለተመለከተ ግን ‹‹ከተማ›› የሚለው ቃል ‹‹ከተማ››ን ከሚጠቅሰው፥ ከሚጠራው ይልቅ ይሥለዋል ቢባል ያመቻል፡፡ ሥርወ ቃሉ የግዕዙ ‹‹ኀተመ›› ነው – ዘጋ፡፡ ይኸም ‹‹ኀተመ›› ‹‹ዘጋ›› ተብሎ መተርጐሙ በግዕዝ ብቻ ሳይኾን በዐረቢውም ትርጒሙ እሱው ነው፡ ዘጋ፡፡ ‹‹ታዲያ ‹ከተማ›ን ከ‹መዘጋት› ጋር ምን አገናኘው?›› ብለን ብንጠይቅ ‹‹ከተማ›› (ቃሉ) እንደ ሥዕል፣ ተበታትነው የነበሩ መንደሮች ተቀራርበው፥ በመካከላቸው ያለን ክፍተት ዘግተው፥ ገጥመው ሲገኙ በዐይነ ኅሊና ያስቃኘናል፡፡ ስለዚኸ ‹‹ከተመ›› ማለት ‹‹ገጠመ፥ ዘጋ›› ማለት ነው፡፡ ይኸም ብዙ ዘሮች አሉት፡- ማኅተም – ኻቲም – የነገር፥ የመልእክት፥ የሐተታ መዝጊያ፡፡ አንድ ስም እዚኽ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ከተሰያሚው ጋር ያለው ዝምድና ተፈጥሯዊ እንጂ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ለጊዜው በ‹‹ኀተመ፥›› እና በ‹‹ዘጋ›› መካከል ሥጋዊ – ነፍሳዊ ዝምድና እንዳለ መናገር ባንችልም በ‹‹ኀተመ፥›› እና በ‹‹ከተመ›› መካከል ግን ሊፋቅ የማይችል ዝምድና አለ፡፡ ‹‹ከተመ››ን ያስገኘው ‹‹ኀተመ›› ነው፡፡ ሰዎች ከወገናቸው ጋር ተከተው፥ ቃፊር ማቆሚያ ማማ ሠርተው፥ ባንድ ግቢ ታጥረው የሚኖሩ ስለኾነ ነው ‹‹ከተሙ›› መባሉ – ገደሙ፥ ገጠሙ፥ አበሩ፥ መጤ እንዳይገባባቸው ዘጉ ስለማለት፡፡ ይኸን በቁሙ ዐማርኛ የኾነ ቃል ለማወቅ ዘንድሮ ‹‹ትርፍ ነው›› እየተባለ መከራውን ባየው በብዙኃን ‹‹ኀ›› እና በዐረቢው  መካከል ያለውን ዝምድና መረዳት ይገባል፡፡ ይኸም በአንድ ቃል ብቻ የሚደረስበት ውሳኔ አይደለም – ብዙ ምስክር ሊጠራ ይቻላል – ይገባል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ እነሆ፡-‹‹አኀዘ›› ብሎ ‹‹ያዘ›› ‹‹እኁ›› ብሎ ‹‹ወንድም›› ይላል፡፡

  ይኸ ውይይት አንድ ቍም ነገር ብቻ ለማስታወስ ቢችል በቂ ነው፡፡ የግዕዝ/የዐማርኛ ፊደል በጥሩ ስም ‹‹ገበታ›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በገበታው ከቀረበው ላይ እንዲመገቡ የተጠሩ አንዳንድ ሰዎች ግን ‹‹ገበታው ተንዛዛብን – ይቀነስልን›› የሚሉ የስንፍና ድምጾችን እያሰሙ ነው – ረዘም ላሉ ጊዜያት፡፡ ከፊደሉ ጥቂቱን ከመጠቀም አንስቶ በፊደሉ ጨርሶ እስካለመጠቀም ድረስ ለራሳቸው መብት አላቸው (ያንን መብት እየተጠቀሙበት እንዳሉም የንግግራቸው ቈዳነት እየመሰከረ ነው)፡፡ ኾኖም ያን ቀንሶ የመጠቀም እና ጨርሶ ያለመጠቀም መብት ለራሳቸው ከመውሰድ አልፈው በፊደሉ አለመጠቀምን እንደ ብቸኛ አማራጭ ወስደው ኹሉንም ትውልድ የሚያሰንፍ ሐሳብ ሲሰጡ ይሰማል፡፡ ይኽችን ዐጭር ሐተታ እኒኽን ሰዎች ‹‹ሃይ›› ለማለት እንድንጠቀምባት ሳቀርብ ፊደላችን አብሪ ኮከብ መኾኑን እያሳሰብኩ ነው፡- የተሸመንበት ባህል ጫፍ ሥሩ የት እንደሚደርስ የሚጠቁም ኮከብ፡፡ ከዋክብትን ያጠፋ ትውልድ በጨለማ መዋጡ እንደማይቀር እናስብ፡፡ ‹‹ፊደል ይቀነስ›› የሚሉንንም ‹‹አረ ለእኔስ ብርሃን ነው እሚበጀኝ›› እንበላቸው፡፡   

  ሰላም!                                                                                                                                                                                                                                                                                                       

  ከአዘጋጁ፡- አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ባሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነ  ጽሑፍ መምህርነት በተለየ ትኩረት በግዕዝ፣ ትግርኛና አማርኛ ሥነ ጽሑፍ ታሪክና ቅርስ ላይ ጥናቶች አድርገዋል፡፡  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  Related Articles