Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርየአገር አመራር መንገዶቻችን እንዴት ነበሩ?

  የአገር አመራር መንገዶቻችን እንዴት ነበሩ?

  ቀን:

  በግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹መንገዶቻችን ምን ይመስላሉ?›› በሚል ርዕስ ስለምንጓዝባቸው የመኪና መንገዶቻችን ላይ በሚታዩት ችግሮች ዙሪያ ሐሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ በአሁኑ ጽሑፍ ደግሞ የአመራር መንገዶቻችንን እንዴት ነበሩ በሚል ርዕስ  ጥቂት ነጥቦች ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

  ለአንድ ዓመት ኢትዮጵያን የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከታዋቂዎቹ ከአብርሃም ሊንከን፣ ከማኅተመ ጋንዲና ከደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላ ጋር ያልተናነሰ ታዋቂነት ያገኙ ምሁር ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ ለአገራችንና ለሕዝባችን ያላቸው ሐሳብና ዓላማ በጣም የሚደነቅ ነው፡፡ ባለፉት አራት የኢትዮጵያ መንግሥታት ሥርዓት ሥር ለመኖር ዕድል የነበረኝ ሰው ነኝ፡፡

  እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሁሉንም ሕዝብ በአንድ ዓይንና ልብ እንዲሁም በእኩልነት የሚመለከት መሪ አላየሁም፡፡ እንደውም ስለመጪው ምርጫ ሲወራም፣ በአገር ደረጃ ከዓብይ (ዶ/ር) ጋር የሚወዳደር ሰብዕና ያለው ሰው ያልታየ በመሆኑ ያለምንም ጥርጣሬ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እሳቸውን መምረጡ ስለማይቀር፣ ቢያንስ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሌሎች ዕጩዎችንና ፖለቲከኞችን ለምርጫ ማቅረቡ ኪሳራ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡

  ባለፈው አንድ ዓመት ከመቼውም ይበልጥ ሰላማዊ የመንግሥት አስተዳደራዊ ሽግግር ተደርጓል፡፡ ይህን ለውጥ ለመቀልበስ ግን ብዙ ሲሞከር ቆይቷል፡፡ ያለፈው ዓመት ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለአዋቂም ሆነ ለጨቅላ ሕፃናት ሳይቀር የጭንቀት፣ የስደትና የግድያ ወቅት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካላቸው ወታደራዊ ማንነት በተጨማሪ በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው ዕምነትም ጭምር ከግድያ መትረፋቸው ይታወቃል፡፡ በመስቀል አደባባይ የሰኔ 16ቱ ሕዝባዊ ሠልፍ ወቅት በእሳቸውና በባለሥልጣኖቻቸው ላይ ቦንብ ተወርውሮባቸዋል፡፡ በርካታ ወታደሮችም ከነትጥቃቸው በድፍረት ቤተ መንግሥት ገብተው ግልበጣ ለማድረግ አደገኛ ሙከራ ማድረጋቸውም ከአንድ ዓመት ያነሰ ታሪክ ነው፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግልበጣ ቤተ መንግሥት የገባውን ጦር ሐሳብና አቅጣጫውን በማስቀየር ፑሽ አፕ አሠርተው ሸኝተውታል፡፡ ከኤርትራ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ለዘመናት ተለያይተን ኖረናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ግን በሁለቱም አገሮች መካከል ዕርቅ ተፈጥሯል፡፡ ለዘመናት ሰላምም ጦርነትም ባለየለት ድንበር ላይ ሰላም ሰፍኖ፣ ድንበር ላይ የተገተገተው ጦር ቤቱ እንዲገባ በማድረግ ያላበቃው የሁለቱ አገሮች አዲስ ስምምነት፣ በዚህ ሳያበቃ ከብዙዎች ጎረቤት አገሮች ጋርም የእርስ በርስ ግንኙነታችን ከመቼውም ይበልጥ እንዲጠናከር ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባካሄዱት የዲፕሎማሲ ሥራ ለአገሪቱ ከፍተኛ ዕርዳታ አስገኝተዋል፡፡

  እነዚህ ከላይ ከሚጠቀሱት አስተዋጽኦዎች ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣ በዓመቱ ከሞላ ጎደል በአገሪቱ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው የህዳሴ እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ ብሎ በአንፃሩ በብሔር ጦርነትና በሰላም ጥማት ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡ በዓመቱ ውስጥ ከመቼውም ይበልጥ በአብዛኞቹ ክልሎች ሰላም አልነበረም፡፡ ለዚህም ዋነኞቹ ምክንያቶች ከዚህ በታች የቀረቡት ናቸው፡፡

   ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንደያዙ ሰሞን በቅን አስተሳሰብ ለዓመታት ታስረው የነበሩትን አስፈትተዋል፡፡ ከአገር ውጭ በተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶችና አመለካከቶች ሳቢያ የተሰደዱትን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ወደ አገር ከተመለሱት አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ሲሆኑ፣ ለነበረን አለመግባባት ግን ከእነዚህ መካከል ያሉ ቆስቋሾቹ ይገኙበታል፡፡ ለችግራችን ሌሎቹ ዋነኛ ምክንያቶች፣ በሥልጣን ላይ የነበሩትና የእነርሱ አጫፋሪዎች ናቸው፡፡

  ከውጭ የገቡትም፣ የተፈቱትም ሆኑ ከሥልጣን የተንሸራቱት ከመቼውም ይልቅ ሕዝቡን በብሔር ፖለቲካና በጎጥ ከፋፍለው ሕዝቡና መንግሥትን እርስ በርስ በማጋጨት አራውጠዋል፡፡ ጥቂቶቹ አሁንም ሩጫቸውን ስላልጨረሱ፣ የቀሯቸውን ቀዳዳዎችን እያሰሱ እንደሆኑ ይገመታል፡፡ በዚህ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ተፈናቅለዋል፡፡ ለልመና አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ይህን እኔ ከምገልጸው በላይ ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ እርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመፈናቀል ፈተና ዛሬ ባይጀመርም፣ ቀደም ሲል በነበረው መፈናቀል ግን ለዘመናት በድርቅና በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ነበር፡፡ የአሁኑን ልዩ የሚያደርገው ግን የብሔርን ፖለቲካ መሠረት ያደረገ መፈናቀል፣ ስደትና ግድያ መሆኑ ነው፡፡

  ለዓብነት በተለያዩ ሚዲያዎች እንደተገለጸው ከአማራ ክልል 900,000 ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ሰሞኑን እንደተሰማው የሕዝብ ጭፍጨፋ ተካሂዷል፡፡ በአማራና በትግራይ አዋሳኝ ክልሎች የሚኖሩ የቅማንት ተወላጆች ላነሱት የማንነት ጥያቄ መንግሥት ወቅቱን ጠብቆ ምላሽ ባለመስጠቱ ሳቢያ የታየው ውጥረትና ግጭቱን መስማት ይዘገንናል፡፡ በደቡብ ክልል በጌዲኦ ዞን ከ300,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በባስኬቶና በመለኮነት ወረዳ ነዋሪዎች መካከል በተነሳው ግጭት ስድስት ሰዎች ሞተው 37,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በአላባ ጠንባሮ ከአሥር በላይ ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለው ምዕመናንም ተሰደዋል፡፡

  በኦሮሚያ ክልል ከ600,000 በላይ ዜጎች ከሞቀ ዓውዳቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በምዕራብ ወለጋ በሆሮ ጉድሩ በተደራጁ ታጣቂዎች ወደ 80 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የሕዝብ ገንዘብ ከባንክ ተዘርፏል፡፡ በቄለም ወለጋ ሰባት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ በባሌ ጎባ ኦርቶዶክሳውያን ተደብድበዋል፡፡ በምዕራብ አርሲ ዞን በቅርቡ በሻሸመኔ ከተማ ቄሮዎች ወጥተው የከተማውን ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አሽገዋል፡፡

  የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ ከወንጌል ባሻገር፣ በትምህርት፣ በጤናና በልማት መስኮች የሰው ልጅን ሁሉ ለማገልገል የተቋቋመ የሃይማኖት ድርጅት ነው፡፡ በእነዚህ ዘርፎች ዙሪያ ቤተ ክርስቲያኒቱ በዓለም ዙሪያ ትንቀሳቀሳለች፡፡ በአገራችንም በሁሉም ክልሎች ለብዙ ዘመናት ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ካቋቋመቻቸው ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ኮሌጅ ነው፡፡ ይህ ተቋም በምዕራብ አርሲ ዞን የሚገኝ ሲሆን፣ በርካታ ምሁራንንም አፍርቷል፡፡ ሕዝባችን ተገቢውን የትምህርት ጣዕም እንደ ልብ ባልቀመሰበት ዘመን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የመሠረት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም የብዙዎችን የዕውቀት ዓይን አብርቷል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ እጅግ የሚያሳዝነው ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተቋሙ ድጎማ ይሆን ዘንድ ከመንግሥት ተሰጥቶት ለዘመናት በቆየው የመሬት ይዞታው ላይ ጥቂት የአካባቢው ቄሮዎች መሬቱን ለመቀማት ባደረጉት ሙከራ በንብረትና ሠራተኞች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ይህ ተግባር አሁንም አልተቋረጠም፡፡ በወረዳውና በዞኑ አስተዳደር በኩል እነዚህን ወጣቶች ለመምከር ሙከራ ቢደረግም የተቀበሏቸው ግን አይመስሉም፡፡

  በእንዲህ ያሉ አገር አቀፍ የሥርዓት አልበኝነት ድርጊቶች የተጨነቀ አንድ ጨቅላ ተማሪ፣ ይህንኑ በሚዲያ በኩል በትክክል አስቀምጦታል፡፡ ሕፃኑ ትምህርቱን ለምን እንዳቋረጠ ሲጠየቅ ‹ትምህርት ቤት ሄጄ ስመለስ ወላጆቼን ዳግም የማግኘት ዋስትና ስለሌለኝ ነው ያቋረጥኩት› ሲል የሰጠው መልስ በጨቅላ ሕፃናት አዕምሮ እንኳ የተፈጠረውን ተፅዕኖ በትክክል ይገልጸዋል፡፡

  በዓመቱ እነዚህን መሰል ብዙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ነበር፡፡ የሕዝቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ የመንግሥት ብቃትና ዝግጁነት ነበር ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ የእኛ መከላከያና ፖሊስ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀር ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንደሚወጣ እንሰማለን፡፡ ታዲያ የአገራችንን ሕዝብ ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዴት እንዳልቻሉ መገመት ይቸግረኛል፡፡ እግዚአብሔር አያርገውና በዚህ ከቀጠሉ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሚዲያ እንደተናገሩት እንደ ሩዋንዳ ጎሳዎች የአገራችን ሕዝቦችም በብሔር ፖለቲካ እርስ በርስ ይጨፋጨፋሉ የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለኝ፡፡

  በመንግሥት በኩል የሚታየው ዋነኛ ችግር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጡ መመርያዎች በተግባር ሲፈጸሙ አይታይም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከተረከቡበት ዕለት ጀምሮ መሠረታዊ መመርያዎችን እየሰጡ ሲሆን፣ የታዩት ክፍተቶችም መመርያዎችን ማስፈጸም ከሚገባቸው አብዛኛዎቹ የክልል አስተዳዳሪዎችና ሚኒስትሮች ዙሪያ የታየ ነው፡፡ ይህ በአብዛኛዎቹ ክልሎች እስከ ቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ድረስ በአብዛኞቹ ዘርፎች ጉልህ ችግሮች ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ እነዚህም ከባለሙያ አመዳደብ ወይም አመራረጥ ላይ ከፍተኛ ችግሮች እንዳሉ አመላካች ናቸው፡፡ የአንድ ሥራ መሪ ብቃት ማነስ ምልክቶች አንዱ ሁሉንም ሥራ በራሱ ለመጨረስ መሞከር ነው፡፡ አንድ ብቃት ያለው መሪ ተቀዳሚ ተግባር ሥራን ለሌሎች አባላት  ማከፋፈልና እያንዳንዱ ሠራተኛ ኃላፊነቱን በትክክል መወጣቱን መቆጣጠር ነው፡፡

  ከእነዚህም ሌላ በአገራችን ችግር ከተከሰተ በኋላ ብቻ ለዕርዳታ እጅ መዘርጋቱ የተለመደ ሙዚቃ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አፀያፊና የአገሪቱን ስም ከሚያጎድፉ ዋነኛው ነው፡፡ ይህን ለመከላከል የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በጣም አናሳ ናቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም መፈናቅሉም ግድያውም ሆነ ስደት ከተፈጸመ በኋላ ድርጊቱን በፈጸሙ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ አስተማሪ አይደለም፡፡ በሌላ አባባል በወንጀለኞችና ቆስቋሾች ላይ የሚያስተምር ዕርምጃ አይወሰድም፡፡

  በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በንጉሣዊ አስተዳደር የነበሩትን ችግሮች እንዳሉ ሆነው የሕዝብ መሰደድና መገደል ቀርቶ አንድ ሰው እንኳን በአካባቢው ሲገደል አደጋ አድራሹ ሰው ወይም ቡድን ተይዞ ለሕግ እስኪቀርብ ድረስ ‹‹በአውጫጭኝ›› ሕዝቡ ወጥቶ ጥፋተኛው ተለይቶ በሕዝብ ቁጥጥር ሥር እስኪሆን ተመልሶ ማንም ሰው ቤቱ አይገባም፡፡ ሕዝብ ወንጀለኛውን ሲያጋልጥ መንግሥትም የሚወስደው ዕርምጃ ሌላ ወንጀል እንዳይደገምና ፈፅሞ እንዳይታሰብ የሚያስተምር ዕርምጃ ይወሰድ ነበር፡፡ አሁን ግን ተራው ሕዝብ ቀርቶ በአካባቢው አመራር ክትትል የሚደረገው እጅግ አናሳ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በየሠፈሩ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡

  ባለፉት 27 ዓመታት በነበረው መንግሥት ደግሞ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው በየአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች እርስ በርስ ፀብና መፈናቀል ከሞላ ጎደል አልነበረም፡፡ የአገሪቱም ሕግ ይከበር ነበር፡፡ አሁን ግን የተሻልን መሆን ሲገባ ሕዝባችን ለከፋ የብሔርተኝነት ፖለቲካ፣ ለክፉ ስደትና ዕልቂት ተጋልጧል፡፡ በሌላ መልኩ በነበረን አንድ ዓመት በብሔርተኝነት እርስ በርስ ጭፍጨፋ የልማት ትኩረታችን በጣም ዝቅ በማለቱ ከፍተኛ ክፍተት ታይቷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የፍትሕ አሰጣጥ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡ በፍርድ ቤቶች ያለ ገንዘብ ፍትሕ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ግርግር የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ዜጎች ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ የምርት ጥራት ተቆጣጣሪ ኃይል አናሳ በመሆኑ በእንጀራ አቅም እንኳ ሰጋቱራና ጄሶ እየተቀላቀለ ለሕዝብ በመሸጡ ለብዙዎች ጤና ማጣት ምክንያት ሆኗል፡፡

  በአጠቃላይ በተለያዩት ዘርፎች የሕግ ጥለትና የአመራር ዕጦት በቃላት ከሚገልጸው በላይ ነበር፡፡ እነዚህ አብዛኞቹ ከጠንካራ አመራር ዕጦት የተከሰቱ ጉልህ ችግሮች ለዘመናት በድህነትና ፍትሕ ዕጦት ለኖረው ሕዝባችን ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ ሆኗል፡፡ ስለፍትሕ አስፈላጊነት ሲታሰብ ኤልኖር ሮዝቬልት ሲናገሩ ‹‹የዜጎች መብት ካልተከበረ መንግሥት የሕግ የበላይነት ካላስከበረና የዜጎች ሕይወት ሲመሳቀል ማየት አገሪቱ እንደፈረሰች የማየት ምልክቶች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ስለሆነም ያሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ለአገራችን ያላቸው ራዕይ የሚደገፍ ሆኖም ከመቼውም ይበልጥ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለፈበት የጭንቀት ዓመት በአዲሱ ዓመት እንዳይደገም በከፍተኛ ሁኔታ ሊታሰብበት የሚገባና ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ በአጠቃላይ በአገሪቱ እንዲኖረንና በሰላም ወጥተን በሰላም እንድንገባ ያላሰለሰ ጥረት እንዲደረግ የዚህ ርዕስ ፍሬ ነጥብ ነው፡፡

  (ዱቤ ጡሴ (ዶ/ር)፣ ከአዲስ አበባ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...