ክፍል ፩
በፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
መግቢያ
እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች ውስጥ በሃይማኖትና በብሔረሰብ ስም ተሳቦ በየጊዜው የሚነሳው መጋጨትና እንዲያም ሲል መገዳደል ዋናው ምክንያት ሌላ ነገር ሳይሆን በእነዚህ አገሮች ውስጥ መካሄድና መደረግ ያለበት መንፈሳዊ ተሃድሶ ከቁም ነገር ውስጥ ስለማይገባና ስላልተካሄደም ነው። በተለይም የፖለቲካ ሥልጣንን የጨበጡና ሀብትን አካብተው የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩና፣ ወይም ደግሞ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚታገሉና በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ አንዳንድ የነፃ አውጭ ድርጅት ነን ባዮች ጥቃቅን ልዩነቶችን እየፈለጉና ከሌላው በልጠው ለመገኘት ሲሉ የማያስፈልግና ሳይንሳዊ መሠረቶች የሌላቸውን ቃላት በመወርወር አንደኛው የኅብረተሰብ ክፍል በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ በቀላሉ ሊገታ የማይችል ግጭት ወይም የወንድማማቾች መተላለቅ እንዲፈጠር ለማድረግ ይበቃሉ።
በተለይም የኅብረተሰብን ታሪክና ውጣ ውረድነትን በተጣመመ መልክ በመተርጎምና፣ የሚኖሩበትን ኅብረተሰብ ከሌሎች አደጉ ከሚባሉት አገሮች ጋር ሳያነጻጽሩ፣ ጭቆናና በደል ደርሶብናል፣ ወይም የአንድ ጎሳ የበላይነት የሰፈነበት ነው በማለት ከሀቁ የራቀ ነገር በማውራት ልዩነቱ እንዲሰፋ፣ መጠራጠር እንዲኖርና የመጨረሻ መጨረሻ በቀላሉ እልባት የማያገኝ ጦርነት እንዲቀሰቀስ የማይጭሩት እሳት የለም። ጭቆና የሚባለው ነገር በእኛ አገር ብቻ ያለ ነገር አድርገው በማቅረብና በማናፈስ መሠረታዊ ከሆኑ ጥያቄዎች በመሸሸ አንድ ምስኪን ሕዝብ በቀላሉ ሊወጣ የማይችለው ማጥ ውስጥ እንዲገባ ሁኔታውን ያመቻቻሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሰው አስተሳሰብ፣ በተለይም ደግሞ የወጣቱ ጭንቅላት በማያስፈልግ አስተሳሰብ በመጠመድ ተግባሩ ወደ ፀብ አጫሪነት እንዲያመራ ይደረጋል። ለእውነተኛ ነፃነት መሠረት ከሆነውና በራስ ላይ ዕምነት ከሚያሳድረው ሳይንሳዊ ዕውቀት እንዲሸሽ በማድረግ ደሃና ኋላ ቀርቶ እንዲኖር ያደርጋሉ።
ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ አገዛዞች በደንብ ሳያገናዝቡ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም ካላግባብ ሀብት ማካበት ለድህነትና በራሳቸው ለሃይማኖትና ለብሔረሰብ ግጭት ምክንያት ይሆናሉ። ምክንያቱም ከውጭ የሚመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እውነተኛና የተስተካከለ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዕድገት ስለማያመጡ ሆድ የባሰው ወጣት መሸሸጊያ የሚያደርገው የብሔረሰብንና የሃይማኖትን ጥያቄዎች በማንገብ ነው። የአገራችን ታሪክ እንደሚያረጋግጠው መንግሥቶቻችን በውጭ ኃይሎች እየተመከሩ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የሥራ አጥነትን ወይም ፈትነትን የሚቀንሱ ሳይሆኑ በራሳቸው ለችግሩ ተጨማሪ ምክንያት በመሆንና በአንድ አገር ውስጥ የተዛባ ሁኔታ በመፍጠር ኅብረተሰባዊ ቅራኔ እንዲከሰትና እንዲሰፋ ለማድረግ በቅተዋል። በዚህ መልክ ካለ ብዙ ግንዛቤና ንቃተ ህሊና መዳበር ጉድለት የተነሳ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች አንዱን ብሔረሰብ የሚጠቅሙ፣ ሌላውን ደግሞ የሚጎዱ ተደርገው በመተርጎም የራሳቸውን አጀንዳ ዕውን ለማድረግ ለሚፈልጉ ጥቂት ኃይሎች ወይም ኤሊት ነን ለሚሉት አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።
ዛሬ በአገራችን ምድር በብሔረሰብና አልፎ አልፎ በሃይማኖት ስም ተሳቦ በወንድማማቾች መካከል የሚከሰተው አለመግባባትና ደም መፋሰስ በውጭ ኃይሎችና፣ የዚህም ሆነ የዚያኛው ብሔረሰብ ኤሊቶችና እኛ ነን መሪህ በሚሉ የተጠነሰሰና የተስፋፋ ነው። የጭቆናና የመበደል ጉዳዮች የሚነሱትና እንደ ልዩነት የሚራገቡት በእርግጥም በድህነት ዓለም ውስጥ ከሚኖረው ምስኪን ሕዝባችን ሳይሆን፣ ጥያቄዎች የሚነሱት የተንደላቀቀ ኑሮ ከሚኖረውና ራሱ ሳይገባው ከውጭ የሚመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ የራሱን ሕዝብ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ ከሚገፈትረው ይኼኛውን ወይም ያኛውን ብሔረሰብ እወክላለሁ ከሚለው ኤሊት ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ኤሊት በእርግጥም የሚታገለው እወክለዋለሁ ለሚለው ብሔረሰብ ሳይሆን የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። የውጭ ኃይሎች ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱን ግራ የተጋባና ያልተገለጸለትን ኤሊት በጥቅም በመግዛት ልዩነቱ እንዲሰፋና የድህነቱም ዘመን እንዲራዘም ያደርጋሉ። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለች የረዥም ጊዜ ታሪክ፣ የተሟላ ቋንቋና ልዩ ልዩ የሚያማምሩ ባህሎችና እጅግ የሚያምር መልክዓ ምድር ያላት አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ማደጓን ስለማይፈልጉ አለ የሚባለውን የብሔረሰብ ልዩነት ተገን በማድረግ ሕዝባችን ተንሳፎና ግራ ተጋብቶ እንዲኖር የማይፈጥሩት ተንኮል የለም። መሣሪያ የሚሆናቸውም ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ የተውጣጣና ግራ የገባው ኤሊት ነኝ የሚለው ኃይል ነው። ከጥቅሙ በስተቀር አርቆ ማሰብ የማይችልና በውጭ ኃይሎች ቡራኬ የሚኖረውና የሚጠመዘዘው ዋናው ተግባሩም ሳይንስን፣ ፍልስፍናና ልዩ ልዩ የዕውቀት ዘርፎችን በማዳበር የዕድገት ኃይል ከመሆን ይልቅ ጥቁር ወንድሙንና እህቱን ሰላም መንሳት ነው። ኃይላቸውን ሰብሰብ አድርገው በአንድነት አገራቸውን እንዳይገነቡና በዓለም ሕዝብ ፊት ተከብረው እንዳይኖሩ ማድረግ ነው።
ከዚህ አደገኛና አገራችንን ወደ ድንጋይ ዘመን ሊለውጣት ከሚችለው ሁኔታ በመነሳት፣ ለምን በእንደዚህ ዓይነቱ ኤሊት በተለይ በአጠቃላይ ደግሞ በጠቅላላው ኤሊት ነኝ በሚለው ዘንድ የሐሳብ መዘበራረቅ በመፈጠር አንድን አገር የጦርነት ዓውድማ አድርጎ የታሪክ ቅርስን ለማጥፋት የሚደረገውን አደገኛ አካሄድ ለማሳየት እሞክራለሁ። ከዚህ በመነሳት ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ባልሆነ አስተሳሰብ ያልታነፀ ጭንቅላት ለምን ለጦርነትና ለአገር ውድመት ምክንያት እንደሆነ በንፅፅራዊ አገላለጽ ለማረጋገጥ እሞክራለሁ። ለዚህ ዓይነቱ ንፅፅር ሊጠቅመን የሚችለው የአውሮፓው የኅብረ ብሔር አወቃቀርና የካፒታሊዝም በአሸናፊነት መውጣትና ዛሬ የዓለምን ሕዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል መወሰንን እንደመነሻ በመውሰድ ነው። ስለሆነም ከአገራችን ይልቅ በአውሮፓ ምድር የበለጠ ደም መፋሰስና ጭቆና እንደነበርና የአውሮፖው ሕዝብ ከብዙ መቶ ዓመታት ጦርነትና መፈናቀል በኋላ ራሱን በራሱ በማግኘት አነሰም በዛም ውስጠ ኃይሉ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚና ማኅበረሰብ እንደገነባ መገንዘብ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ኃይልና የማያቋርጥ ጦርነት ሳይሆን የመጨረሻ መጨረሻ ዋናው የዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል፣ የሐሳብ ጥራትና በሐሳብ ዙሪያ የተደረገ ምርምርና ክርክር ለኅብረተሰብ ዕድገት ወሳኝ ሚናን እንደተጫወቱ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ እንዴት የአውሮፓው ኅብረተሰብ የፍልስፍና፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የማቲማቲክስ፣ የሊትሬቸርና የድራማ፣ እንዲሁም ከጭንቅላት ውስጥ የሚፈልቁ የልዩ ልዩ ዕውቀቶች ባለቤት በመሆን የበላይነትን ሊቀዳጅ እንደቻለ በተቻለ መጠን ማየት ይቻላል። በዚህም መሠረት ተንኮል፣ አጉል ጥላቻ፣ መናናቅ፣ ሥራን አለማክበር፣ በዲሲፕሊን አለመሥራትና ኃላፊነት አለመሰማት እንዳሉ ተወግደው የአውሮፓው ማኅበረሰብ በካፒታሊዝም የሚገለጽ ዕድገት ባለቤት ለመሆን እንደበቃና ዓለምን እንደሚያሽከረክራት መረዳት ይቻላል።
ከጭንቅላት መዘበራረቅ ወደ ከፍተኛ ንቃተ ህሊና የመሽጋገር ሒደት ጉዳይ!
የመጀመሪያዎቹ የተፈጥሮ ፈላስፋዎች የሚባሉት የግሪክ ጠቢባን ከሦስት ሺሕ ዓመታት በፊት ምርምራቸውን ሲጀምሩ አትኩሮአቸው የተፈጥሮን ምስጢርና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ተፈጥሮ ከምን ከምን ነገሮች እንደተሠራችና፣ ምንስ ነገር እንደያዛት ማወቅ ነበር። ስለሆነም እያንዳንዱ ፈላስፋ በመሰለውና ባመነበት መንገድ ተፈጥሮ የተሠራው ከውኃና ከእሳት ነው ሲል፣ ሌላው ደግሞ ውኃ፣ እሳት፣ አፈርና አየር ናቸው በማለት የተፈጥሮን ምንነትና አሠራሩን ለማወቅ ጥረት ያደርጉ ነበር። ለዚህ መነሻቸው የሆነው ቀደም ብሎ ከነበረው ከአፈ ታሪክ (ሚቶሎጂ) በመላቀቅ ሎጂካዊ አስተሳሰብን ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ነው የተፈጥሮን ምስጢርና ቀስ በቀስም የሰውን ልጅ አስተሳሰብ ለመረዳት የቻሉት።፡
በተለይም አራቱ ንጥረ ነገሮች ተቀባይነትን ካገኙ በኋላ፣ የኋላ ኋላ ብቅ ያሉት እንደ ሶቅራተስ፣ ፕላቶና አሪስቶትል የመሳሰሉት ፈላስፋዎች ደግሞ ከጊዜው አወዛጋቢና የጦርነት ሁኔታ በመነሳት ምርምር ማድረግ የጀመሩት ለምን ሰላምን የሚነሱ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ? ስግብግብነትና ሥልጣን ማካበት (Greed and Power) እና በሌላው ላይ የራስን ፍላጎት መጫን ምክንያቶቻቸው ምንድንናቸው? በማለት የሞራል፣ የሥነ ምግባርን፣ የእኩልነትንና (የፍትሕ) የዕውቀትንም ጉዳዮች በማንሳት ነበር ለእነዚህ አስቸጋሪ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሙከራ ያደርጉ የነበረው። በጊዜው ስግብግብነትና ሥልጣን፣ እንዲሁም ደግሞ ከሌላው በልጦ ለመገኘት ሲባል፣ ወይም ደግሞ ሌላን አካባቢ በኃይል ለመያዝ አሰቃቂና ተከታታይ ጦርነት ይካሄድ ስለነበር የዚህ ዓይነቱን የሥልጣኔና የሰላም ጠንቅ የሆነውን ዋና ምክንያት መጠየቅና መፍትሄ መፈለግ የግሪክ ፈላስፋዎች ዋናው ተግባርና ታሪካዊ ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህም በመነሳት የምርምራቸው አትኩሮ ጭንቅላትንና የንቃተ ህሊናን ጉዳይና፣ ከዚህ ጋር የተያያዘውን አርቆ የማሰብና ያለማሰብ ጉዳይ፣ የሎጂክንና የኢንተሌክትን ጉዳይ፣ በረቀቀ መልክ ማሰብን፣ ወደ ውስጥ መመልከትንና በነገሮች መካከል ያለውን መተሳሰርና፣ ዕውቀት የሚባለው ነገር ከጭንቅላት ብቻ የሚፈልቅ መሆኑን ማሳየት ነበር። በመሆኑም ከዚህ ጋር የተያያዙትን መሠረተ ሐሳቦች እንደ መንግሥት ጉዳይ፣ የዴሞክራሲና የእኩልነትን ጥያቄ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የሰውን ልጅ የኑሮ ትርጉም በመረዳት እንዴት የተረጋጋና እኩልነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ መመሥረት ይቻላል? በማለት ጥያቄዎችን በመጠየቅ መልስ ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። ስለሆነም በምድር ላይ እንደሚታዩት የማቴርያላዊና የባህላዊ ዕድገት ደረጃዎች የሰው ልጅ ጭንቅላት በረቀቀና ሎጂካዊ በሆነ መልክ ያስባል፣ አዳዲስ ነገሮችን ይፈጥራል፣ በዚያው መጠንም የኑሮውን ሁኔታ በማሻሻል ከእንስሳ የተሻለ መሆኑን ያሳያል፣ ወይም ደግሞ አስተሳሰቡ ውስንና በነገሮች መካከል መተሳሰር እንዳለ የማይገነዘብ ይሆናል። ስለሆነም ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር፣ ለጦርነትም ሆነ ለሰላም መኖር ዋናው ወሳኝ ነገር የአዕምሮአችን መዳበርና አለመዳበር ነው። ፕላቶ ሪፑብሊክ በሚለው በተለይም ስለፍትሐዊ አገዛዝ አስፈላጊነት በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ መነሻው የሰውን ጭንቅላት ማዕከላዊ ቦታ በመስጠት ነው። በፕላቶን ምርምር መሠረት የሰው ልጅ ጭንቅላት በሦስት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን፣ እነሱም አርቆ ማሰብ (Reason)፣ መንፈስና (Spirit) ፍላጎት (Apetit) ሲሆኑ፣ የሁለቱ አዛዥ ወይም ተቆጣጣሪ አርቆ ማሰብ ነው። በመሆኑም እንደ አርቆ የማሰብ ወይም ንቃተ ህሊና ደረጃ የመንፈስና የፍላጎትም ሁኔታ ይወሰናል ማለት ነው። ይህም ማለት የአንድ ሰው የማሰብ ኃይል ካደገ ወይም በሁሉም አቅጣጫ የሚመለከት ከሆነ መንፈስንና ፍላጎቱን ሊቆጣጠር ይችላል። ይሁንና የማሰብ ኃይል በራሱ ደግሞ በትክክለኛ ወይም በማያሳስት ዕውቀት የሚወሰን ነው። አንድ ፍልስፍናዊ መሠረት የሌለውና የሰውን አዕምሮ ለመቆጣጠር (Manipulate) በተዘጋጀ ትምህርት የሠለጠነ ሰው እውነትን ከውሽት የመለየት ኃይሉ ደካማ ስለሚሆን የማሰብ ኃይሉም ውስን ይሆናል። ስለሆነም እንደዚህ ዓይነቱ ሰው የፍላጎቱ ተገዢ ስለሚሆን በስግብግብ መንፈስ በመመራት ለሰላምና ለዕድገት ጠንቅ በመሆን አንድ ሕዝብ እፎይ ብሎ እንዳይኖር ያደርጋል።
ከዚህ በመነሳትና የመንፈስን ወይም የአዕምሮን ጉዳይ ማዕከላዊ ቦታ በመስጠት በሰው ልጅና በኮስሞስ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ መካከል ያለውን ግንኙነት በመመርመር፣ የሰው ልጅም ካለምክንያት እንዳልተፈጠረና ተልዕኮውን በመረዳት የግዴታ የተፈጥሮን ምስጢር ማወቅ እንዳለበት፣ ዕውቀት የሚባለው ነገር ከሰው ጭንቅላት ውስጥ ብቻ መፍለቅ እንደሚችል አመለከቱ። በዚህም መሠረት እንደተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሒሳብ፣ አርክቴክቸርና መዚቃ… ወዘተ. የመሳሰሉትን በማዳበር የሰው ልጅ ካሰበበት ሰላማዊ ኑሮ መኖር እንደሚችል አመለከቱ። በዚህ መሠረት በመጥፎ ነገር ያልተወጠረው የመጀመሪያዎቹና የተከታታዩ ፈላስፋዎች ጭንቅላት ተፈጥሮን በመቃኘት ለሰው ልጅ መመሪያ የሚሆነውን ሁለንተናዊ ዕውቀት ማፍለቅ ቻለ። የሰው ልጅም ከጨለማ ኑሮ በመውጣትና ራሱን በማግኘት በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን በማውጣትና ቅርፅ በመስጠት ከእንስሳ ባህርዩ ሊላቀቅ እንደሚችል አመለከቱ፡፡ ይህ ዓይነቱ የሰውን ጭንቅላት ማዕከላዊ ቦታ ሰጥቶ ምርምር ማድረግና በጊዜው ይካሄድ የነበረው ፈጠራ የመጀመሪያው የዕድገት ወይም የዘመናዊነት ደረጃ በመባል ይታወቃል። በዚህ መልክ ማቀድ (Planning) ማደራጀትና (Organization) ያለሙትን ተግባራዊ ማድረግ (Action) የጭንቅላትን የንቃተ ህሊና መዳበር የሚያሳዩ ሲሆኑ፣ ማንኛውም ነገር በስሜትና በግብታዊነት የሚሠራ ሳይሆን፣ አንድ ሰው አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ ከፈለገ የግዴታ የተወሰነ የአሠራር ሥልትን ማዳበርና ጥልቅ ምርምር ማድረግ እንዳለበት የሳይንስ መመሪያ ሊሆን በቃ። ይሁንና ግን ይህ የግሪኮቹ የመጀመሪያው የሥልጣኔ መነሻ በሮማውያን ወረራ ምክንያት የተነሳ በዚያው መልክ እንዳይቀጥልና ወደ ሌሎች አገሮች እንዳይስፋፋ ይታገዳል። ስለሆነም ከግሪክ ሥልጣኔ መጥፋት በኋላ የአውሮፓው ሕዝብ እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲወድቅ ይደረጋል።
የአውሮፓ ሕዝብ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በጭፍን የካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎችና የፊውዳል አገዛዞች በጦርነት፣ በረሃብና በበሽታ በሚሰቃይበት ዘመን እነ ዳንቴ መነሻቸው የነበረው ጭንቅላትን ማዕከላዊ ቦታ በመስጠትና ጭንቅላት በትክክለኛ ዕውቀት ከተቀረፀ ተዓምር መሥራት እንደሚችል በመገንዘብ ነው። ዳንቴም የአምላኮች ኮሜዲ በሚለው ግሩም መጽሐፉ ውስጥ ለማሳየት እንደሞከረው የሰው ልጅ ጭንቅላት በተሳሳተ ርዕዮተ ዓለምና በተዘበራረቀ ሁኔታዎች እንደሚታወርና የሚያደርገውን ሁሉ ማገናዘብ እንደማይችልና፣ ከጨለማው ወደ ብርሃኑ ዓለም ለመውጣትና ራሱን ለማግኘት ትክክለኛውን መንገድ መከተል እንዳለበት ያስተምረናል። በዚህም መሠረት ዳንቴ የመጀመሪያውን ተሃድሶ (Renaissance) መሠረት ሲጥል፣ ተከታታዩ ትውልድ እሱ በጣለው መሠረት ላይ በመመርኮዝ በሥዕል፣ በአርክቴክቸር፣ በኦፔራ፣ በዕደ ጥብበና ሰብዓዊነትን ያላበሰ ትምህርት በማስፋፋት ለእነ ጋሊሌዮ፣ ቡርኖ ጋርዲያኖ፣ ፔትራርካና አያሌ ሳይንቲስቶችና ሠዓሊዎች የሥልጣኔውን በር ለመከፈት ችሏል። ይህ ተከታታይነት ያለው በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በመዳበር፣ በመስፋፋትና በጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽ የማሰብ ኃይል በዚህ ዙሪያ ብቻ የሚሽከረከርና ችግርም ሲፈጠር ለመፍታት የሚቻለው በማሰብ ኃይልና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር ብቻ እንደሆነ ተቀባይነትን ያገኝ በጭንቅላት ውስጥ የተቀረፀ (Progrtammed) ዘዴ ሆነ። በኢጣሊያን አገር በተለይም የፕላቶንን ፍልስፋናና ዕውቀት በሚያራምዱ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ከተጀመረ በኋላ ብርሃኑን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በማንፀባረቅ በየአገሩ ብቅ ያለው አዳዲስ ምሁራዊ ትውልድ የየአገሩን ኋላ ቀርነትና የሰውን የአስተሳሰብ መወላገድ ወይንም የራሱን ምንነት አለመገንዘብ በሬናሳንስ መነፅርና በግሪኮች የፍልስፍና ዕውቀት እንዲመለከት ተገደደ። በዚህም መሠረት ለጦርነትና በጨለማ ኑሮ ለመኖር ዋናው ምክንያት መንፈስ በማያስፈልጉ ነገሮች በመወጠሩና የተፈጥሮን ምንነት ለመረዳት የሚያስቸለው ዕውቀት በጭንቅላቱ ውስጥ መቀረፅ ባለመቻሉ ነው። በመሆኑም የአውሮፓ ሕዝብ የድንቁርናው መስዋዕት ለመሆን የበቃውና የገዢዎችን ጦርነትና ድህነትን ፈልፋይ አገዛዝ አሜን ብሎ የተቀበለው ከእግዚአብሔር የመጣ ትዕዛዝ አድርጎ በማመን ነበር።
ከዚህ በመነሳት አዳዲስ ብቅ ያሉና የተገለጸላቸው ሊቃውንት ጥያቄዎችን በመጠይቅና ካለው ባህላዊ አኗኗርና የአገዛዝ ሥልት ጋር በመጋፈጥ በሰው ጭንቅላት ውስጥ ብርሃን እንዲታይ ለማድረግ ቻሉ። ስለሆነም የአውሮፓው ሕዝብ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ከሬናሳንስ በኋላ የግዴታ በሪፍሮሜሽንና በኢንላይተንሜንት የመንፈስ ተሃድሶና ጭንቅላትን የማጽዳት ሒደት ውስጥ ማለፍ ነበረበት። ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ አዕምሮ ባህላዊ ከሚባሉና አዕምሮን ከሚቆልፉና ለድህነትና ለጦርነት ዋና ምክንያት ከሆኑ ነገሮች በመላቀቅና ራሱን በማግኘት በተፈጥሮ ላይ የበላይነትን የሚቀዳጅበት መንገድ ተከፈተለት።
በተለይም በ16ኛው ክፍለ ዘመን በማርቲን ሉተር አማካይነት በሃይማኖት ላይ የጥገና ለውጥ እንቅስቃሴ ሲካሄድ ዋናው ዓላማው መጽሐፍ ቅዱስንና ጳጳሶች የሚሉትን ዝም ብሎ መቀበል ሳይሆን፣ ህሊናን ወይም አዕምሮን ዋናው የመመራመሪያና የመመዘኛ መሣሪያ በማድረግ ነው። የማርቲን ሉተር የሪፎርሜሽን እንቅስቃሴ ለአዲስ አስተሳሰብ በሩን ሲከፍት፣ መከራከርና መጠየቅ፣ እንዲሁም በአንድ ነገር ላይ ተወስኖ አለመቆየትና፣ ጥቂቶች የሚናገሩትን ዝም ብሎ አለመቀበል የዕውቀት መመራመሪያ ዘዴ በመሆን ምሁራዊ ዕምርታን አመጣ። ከማርቲን ሉተር ንጹህ በንጹህ የሃይማኖት አስተሳሰብ ራሳቸውን ያላቀቁ ኃይሎች ደግሞ የማኅበራዊ ጥያቄን በማንሳት ለካፒታሊዝም ዕድገትና ብሎም ሠርቶ መበልጸግን መመሪያ በማድረግ የኢኮኖሚ ጥያቄም መልክ መያዝ ቻለ።
ይህ በተለይም በካቶሊክ ሃይማኖት ጥብቅ የሆነ እምነት ላይ የተጀመረው ዘመቻና መዳበር የቻለው አዲስ አስተሳሰብ ለጀርመኑ አይዲያሊስቶች ተብለው በመጠራት በሚታወቁት የጀርመን ፈላስፎች መንገዱን ከፈተ። ፍልስፍና ይበልጥ በመስፋፋት ዕውቀት ብቻ ሳይሆን፣ ሥነ ምግባርና ግብረ ገብነት፣ እንዲሁም ከዕውቀት ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ነገሮች በመፈጠርና በመዳበር የሰው ልጅ በተሻለ መንገድ ማሰብ እንደሚችልና፣ በተለይም ሄግል ሁለንታዊ በሚለው አስተሳሰቡ በጠቅላላው ዕውቀት የሚባለውን ነገር፣ ከፖለቲካ እስክ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ተፈጥሮን እስከመረዳትና በተፈጥሮና በሰው ልጅ መካከል ስለሚኖረው ግንኙነትና፣ ሌሎች የዕውቀት ዘርፎችን ሁሉ በማጠቃለል የሰው ልጅ ሁለንታዊ ዕውቀትን ሊቀስም እንደሚችልና መጣርም እንዳለበት ማሳየት ቻለ። ይሁንና ግን በካንት ዕምነት የሰው ልጅ ከተወሰነ ነገር በላይ እርቆ ሊሄድ እንደማይችልና ሁሉንም ነገር አጠቃሎ የማየትና የመገንዘብ ኃይል ሊኖረው እንደማይችል አመለከተ። በዚህም መሠረት በተለይም የእግዚአብሔር መኖር ከሰው የማሰብ ኃይል ውጭ ስለሆነ ስለሱ መኖርና አለመኖር በፍጹም ማረጋገጥ እንደማይቻል በማሳየት በዕምነትና በሳይንስ መካከል ሊኖር የሚገባውን ወሰን አሳየ። ይህ ማለት ግን ካንት እግዚአብሔር የለም ብሎ አላስተማረም፣ ያለመኖሩንም አልተቀበለም። ለማለት የፈለገው በቀጥታ ለማረጋገጥና ለማየት በማንችለው ነገር ላይ መነታረክ የለብንም ማለቱ ነው።
ይህ ዓይነቱ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መዳበር የቻለውና እየተፍታታ የመጣው ዕውቀት የግዴታ ለሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ብቻ ሳይሆን ለግለሰብዓዊ ነፃነትም በር ከፈተ። ፖለቲካዊ ነፃነትም ለአንድ አገር ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት የተገነዘቡ በተለይም የእንግሊዝ ሊቃውንት ጊዜው የብርሃን ዘመን ነው በማለት በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን መተሳሰብንና መፈላለግን በማመልከት፣ ዲስፖታዊ አገዛዞች በሰፈኑበት ቦታ በሁሉም መልክ ሊገለጽ የሚችል ኅብረተሰብዓዊ ዕድገት ሊመጣ እንደማይችል አመለከቱ። በዚህም መሠረት ዘ ሩል ኦፍ ሎው (The Rule of Law) የሚለውን የማኅበረሰብ መመሪያ በማዳበር ራሱም መንግሥት የሕግ ተገዢም መሆን እንዳለበት አመኑ። በዚህም መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ ከሕግ በፊት እኩል ሲሆን፣ መብቱንና ግዴታውን ማወቅ እንዳለበት አሳሰቡ። በዚህ ዓይነቱ ኅብረተሰብዓዊ ስምምነት (Social Contract) ብቻ አንድ ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ መኖር የሚችል ሲሆን፣ በዚያው መሠረትም በፈጠራ ሥራና በሙያው ማንነቱን ሊገልጽ ይችላል። ይሁንና ግን በእንግሊዝ አገር የፈለቀው የሊበራሊዝም ቲዎሪ በሚታዩ ነገሮች ላይ (Phenomenal) የሚያተኩር ሲሆን፣ ፕላቶ እንደሚለው ከዚያ ባሻገር የሚኖረውን ነገር እንድናይ የሚያግዘን ዕውቀት አይደለም። በዚህም መሠረት በተለያዩ ነገሮች መካከል ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት፣ መተሳሰርና ተለዋዋጭ መሆንን አያመለከትም። ይኼንን በምሳሌ ማየት ይቻላል። በዛሬው ዓለም በብዙ የካፒታሊስት አገሮች ሊበራሊዝምና የገበያ ኢኮኖሚ ሰፍነዋል ብለው አንዳንዶች ለማሳመን ቢሞክሩና የሕዝብ ተጠሪዎችም በሕዝብ ቢመረጡም፣ በሌላ ወገን ግን መንግሥታትና የሕዝብ ተወካዮች ነን የሚሉት በሎቢይስቶች ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሊበራሊዝም በ18ኛው ክፍለ ዘመን የፈለቀና የዳበረ አስተሳሰብ ሲሆን፣ በተለይም የግል ሀብት በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ሥር በመምጣት በተለይም በሕዝብ የተመረጥን ነን የሚሉ የካፒታሊስት አገሮች አገዛዞች በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የተወሰነውን የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚጠቅሙበትና ሌላውን የሚጎዱበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በተለይም በንጹህ መልክ የገበያ ኢኮኖሚ ይካሄድ ይመስል በመተርጎምና ሁሉም ነገር ለገበያው ኃይሎች መለቀቅ አለበት በማለት የገበያን ኢኮኖሚ ወደ ርዕዮተ ዓለምነት (Ideology) ለውጠውታል። በሦስተኛ ደረጃ፣ የዛሬው ካፒታሊዝም በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ ዘመን እንዳለው ዓይነት ሳይሆን የተወሳሰበ የመጣና ጥቂት ኦሊጎሎፖሊስቶች ከአገራቸው በማለፍ የብዙ አገሮችን ሕዝቦች ሕይወት የሚቆጣጠሩበትና፣ በተለይም የአፍሪካን መንግሥታት ሽባ ያደረጉበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ስለሆነም አብዛኛዎቹ የዘመኑ ፈላስፋዎችና የተገለጸላቸው ምሁራን የዓለም ሕዝብ አዲስና ተጨማሪ የኢንላይተንሜንት ወይም የመንፈስ ተሃድሶ እንደሚያስፈልገው ያሳስባሉ። ከዚህ ስንነሳ በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ ሊበራሎች የፈለቀው አስተሳሰብ ውስንነት ሲኖረው፣ የእነሶክራተስ፣ ፕላቶ፣ ላይብኒዝ፣ ካንትና ሄግል እንዲሁም ኋላ የተነሱት የጀርመን ፈላስፋዎች አሁንም ቢሆን እጅግ ጠቃሚነትና ዘለዓለማዊነትም ያለው መመሪያ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ጉዳይ በተለይም ኳንተም ፍዚክስ (Quantum Physics) ከሚባለው ቲዎሪ ጋር በመገናኘት አንድ ማኅበረሰብ ሁለንታዊ በሆነ መልክ መታየት እንዳለበትና፣ ችግሮችም ሁለገብ በሆነ የችግር መፍቻ መሣሪያ መንገድ ነው ሊፈቱት የሚችለው። እንደነ ፕላቶን ፍልስፍናም ኳንተም ፊዚክስ ዋናው መነሻው ጭንቅላት ሲሆን፣ በሰው ልጅና በጠቅላላው በተፈጥሮ መካከል የግዴታ መደጋገፍና ግንኙነት መኖር እንዳለበት ያሳስባል። በሌላ አነጋገር ተፈጥሮ ወደተራ ተበዝባዥነት መለወጥ ያለበት ጉዳይ ሳይሆን የግዴታ እንክባክቤ የሚያስፈልገውና ለተከታታዩ ትውልድም ሊተላለፍ እንዲችል ሆኖ መዘጋጀት እንዳለበት በጥብቅ ያሳስባል።
ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ዓይነቱ በተወሰኑ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የዳበረው ምሁራዊ እንቅስቃሴ የተከታታዩንም ደቀ መዝሙር ጭንቅላት በማነፅና የማሰብ አድማሱን በማስፋት ለኅብረተሰብ ግንባታ የሚያገለግል ልዩ ልዩ ዕውቀቶችን እንዲያፈልቅ አግዞታል ማለት ይቻላል። አንደኛው ምሁር ያዳበረውን ዕውቀት ሌላው ዝም ብሎ በጭፍን የሚከተል ሳይሆን ትክክል መሆኑና አለመሆኑን ከፍልስፍናና ከተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር በመመርመርና የጎደለውን በሟሟላት ለተስተካከለ የኅብረተሰብ ዕድገት አቅጣጫዎችን ማሳየት የአውሮፓ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ዋና ተግባርና ባህል ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉት ዕውቀቶች የርዕዮተ ዓለም ባህርይ በመውሰድ እንደየ ሁኔታው በሀብትና በፖለቲካ አይሎ የወጣውን የኅብረተሰብ ክፍል ጥቅም እንዲያንፀባርቁ ሆነው ሊዘጋጁ የቻለበት ሁኔታም መፈጠር ችሏል። በተለይም ካፒታሊዝም እንደ ሥርዓተ ማኅበር በአሸናፊነት ሲወጣ ካለሱ ሌላ አማራጭ መንገድ የለም ወይም አለ በሚሉ ምሁራን ዘንድ ክርክር በመፍጠር ይህ ዓይነቱ ምሁራዊ ውዝግብ ዓለም አቀፋዊ ባህርይም ሊወስድ ችሏል። ያም ሆነ ይህ ካፒታሊዝም ውስጥ ባለው ውስጣዊ ኃይል መሠረት ሌሎች የማኅበረሰብ ቲዎሪዎች፣ ማለትም እንደ ሶስዮሎጂ፣ የሥነ ልቦና ሳይንስ፣ የከተማ ግንባታና የአርክቴክቸር ሳይንስና ሌሎችም በመዳበርና በመስፋፋት በአጠቃላይ ሲታይ የምሁራን አስተሳሰብ ወይም ጭንቅላት ጥያቄን በመጠየቅና ኅብረተሰብዓዊና ማኅበራዊ ችግሮችን በመፍታት ብቻ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ በቃ። በሌላ አነጋገር ማንኛውም በምሁሮች ዘንድ የሚደረግ ክርክር በአፈ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን የግዴታ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ ባህርይ በመውሰድ ንትርክ አልባ ባህል ሊዳብር ቻለ። በዚህ መልክ በጥቂት የአውሮፓ አገሮች የዳበረው ዕውቀት ውስን በሆነ መልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋት ለትምህርት ቤቶችና ለዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት መመሪያ ለመሆን በቅቷል። እንደዚህ ዓይነቱ በብዙ መልኮች የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ፈጠራ በሌሎች አህጉሮችና አገሮች በፍጹም አይታወቅም። ከሁለት ሺሕና ከሦስት ሺሕ ዓመታት በፊት፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በስምንተኛው ክፍለ ዘመን በባግዳድ ሳይንስና ማቲማቲክስ እስከተወሰነ ደረጃ ቢስፋፉም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብቻ ነው በከፍተኛ ደረጃ ዕውቀት ሊስፋፋና የካፒታሊዝምም ዕድገት ሊፋጠን የቻለው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ ጭቆናን አስመልክቶ ጦርነቶች ቢካሄዱም የመጨረሻ መጨረሻ ኅብረተሰብዓዊ ችግሮች ሊፈቱ የቻሉት በተፈጥሮ ሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ዕውቀቶች አማካይነት ብቻ ነው። ባጭሩ የመጨረሻ መጨረሻ ካፒታሊዝም በአሽናፊነት ሊወጣ የቻለው በመጮህና ጥቂት መፈክሮችን በማስተጋባትና ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት ሳይሆን ተከታታይነት ባለው ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው።
ይህ የሚያስገነዝበን ምንድነው? ይህ ዓይነቱ የመንፈስ ተሃድሶ ሒደትና ውጣ ውረድነት የሚያስተምረን ማንኛውም ኅብረተሰብዓዊ ችግር ሊፈታ የሚችለው በዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው። ኅብረተሰብዓዊ ፕሮጀክቶችን ማቀድ፣ ማደራጀትና ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው። በሌላ ወገን ደግሞ ትክክለኛ ዕውቀት በደንብ ሥር ባልሰደደበትና ምሁራዊ ክርክር እንደ ባህል ባልዳበረበት አገር ተምሬያለሁ የሚለው ጥቂቱ ምሁር ሁልጊዜ የሚያደላው በአቋራጭ ሥልጣን ላይ ቁጢጥ ማለትንና የአንድን አገር ሕዝብ ህልም ማጨለምና ሰቆቃውን ማብዛት ነው። በዚህ መልክ በአንዳንድ ምሁራን ጭንቅላት ውስጥ እንደ መጥፎ ሶፍትዌር የተተከለው የተዛባ አስተሳሰብ ወደ ውስጥና ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት ስለማይችል በዓለም አቀፍ ደረጃ ኅብረተሰብዓዊ ውዝግቦችና ድህነት እንዲስፋፉና የየአገሩ ሕዝቦችም ዘለዓለማቸውን የተዝረከረከ ኑሮ እንዲኖሩ ለማድረግ የሚጥሩ ኃይሎች ጉያ ሥር በመውደቅና ትዕዛዝ በመቀበል ሳይንሳዊ ይዘት የሌላቸውን ፖሊሲዎች ተግባራዊ በማድረግ አንድ አገርና ኅብረተሰብ ታሪክ መሥሪያ መድረኮች መሆናቸው ቀርቶ ብልግናና አመጽ የሚስፋፉባቸው ለመሆን እንደበቁ የምናየው ሀቅ ነው።
ከዚህ ስንነሳ ሰፋ ያለ ዕውቀት በዳበረባቸው አገሮች ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ሲፈጠሩና በዚያው መሠረትም ኅብረተሰብዓዊ መተሳሰር በካፒታሊዝም ሎጂክ ሲገለጽ፣ እንደኛ ባለው አገር ደግሞ ኅብረተሰቡን ሊያያይዙ የሚችሉ አሠራሮችና ኢኮኖሚያዊ አደረጃጀቶች ከጥንታዊ ባህርያቸው ባለመላቀቅ ሕዝቡ ወደባሰ ድህነት የሚገፈተርበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በተለይም ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የማይችል ኅብረተሰብ የውጭ ኃይሎች መስዋዕት በመሆን ለዝንተ ዓለም ፍዳውን እንዲያይ ይደረጋል። በአጠቃላይ ሲታይ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ችግሮችን መፍቻ ዕውቀቶች በተወሰነና ቀስ በቀስ የማሰብ ኃይሉ መዳበር በቻለ ማኅበረሰብ ሊፈጠሩና ምጥቀትን የሚያገኙ ቢሆንም፣ የምዕራቡ ዓለም ወይም የነጭ ዘር የቴክኖሎጂን ዕድገት ከማኅበራዊ ይዘቱ (Social Context) በማውጣት ሳይንስንና ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅና በተወሳሰበ መልክ ማዳበር የሚችለው የነጭ ዘር ብቻ ነው በማለት እንደኛ ባለው ወደ ኋላ በቀረው ምሁር ላይ የዝቅተኝነት ስሜት እንዲያድርበት ለማድረግ በቅቷል። በሌላ ወገን ግን ማንኛውም ኅብረተሰብ የተወሰነ የኅብረተሰብ ዕድገትን በመጓዝ ነው እዚህ ዓይነቱ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው። በሌላ አነጋገር ማንኛውም ኅብረተሰብ ከቴክኖሎጂዎች ጋር አልተፈጠረም ወይንም ለተወሰነ የሰው ልጅ ብቻ ቴክኖሎጂዎች ተዘጋጅተው አልጠበቁትም። በተጨማሪም በጣም ጥቂት የሆነው የሰው ልጅ ከማሰብና ከመፍጠር ጋር ሲወለድ፣ ሌላው ደግሞ እንዳያስብና እንዳይፈጥር ሆኖ ጭንቅላቱ ተጣሞ አልተወለደም። የብዙ አገሮችን የኅብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ገረፍ ገረፍ አድርጎ ለተመለከተ ሁሉም አገሮችና ሕዝቦች በአነሳሳቸው ተመሳሳይ ባህርይዎች አላቸው። በማዕከለኛው ክፍለ ዘመንም በብዙ አገሮች የአሠራር ሥልቶች ተመሳሳይ ባህርይ ነበራቸው። ይህ ማለት ዛሬ የምናየው ዕድገት ብዙ ውጣ ወረድንና ኅብረተሰብዓዊ ውዝግብ ከተፈጠረ በኋላ የተገኘ ነው።
ያም ተባለ ይህ ዛሬ የምናያቸውና የምንጠቀምባቸው ተክኖሎጂዎች በሙሉ፣ የሰው ልጅም ወደ ህዋ የሚጓዝበት መሣሪያ፣ ለጥፋት የሚሠራውም የጦር መሣሪያዎች… ወዘተ. እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከሰማይ ዱብ ያሉ ሳይሆኑ ጭንቅላትን በከፍተኛ ደረጃ በማስጨነቅ የተገኙ ውጤቶችና እየተሻሻሉ የመጡ ናቸው። ከተማዎችና መንደሮች፣ ድልድዮችና ካናሎች፣ እንዲሁም፣ ልዩ ልዩ ነገሮች የሚሠሩት በሰው የማሰብ ኃይልና በዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው። በአንፃሩ ደግሞ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ጠባብ ከሆነ የሌሎች ኃይሎች መጫወቻ እንደሚሆንና፣ የተፈጥሮ ሀብት እንኳ ቢኖረውም የዝንተ ዓለሙን በድህነት እየማቀቀ እንደሚኖር የራሳችን አገር ተጨባጩ ሁኔታ ያረጋግጥልናል። በተለይም በሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ አንድ መጥፎ ነገር ከተተከለ ከዚህ ዓይነቱ ኅብረተሰብን ከሚያናጋ ባህርይ ለማላቀቅ በጣም እንደሚያስቸግር የአገራችን ሁኔታ ያረጋግጣል። የአንድ ልጅ ጭንቅላት ከጨቅላነቱ ጀምሮ ልክ እንደ አበባ ወይም ፍሬ እንደሚሰጥ አትክልት በየጊዜው ልዩ እንክብካቤ ካልተደረገለትና ሳይታወቅ ጭንቅላቱ በመጥፎ አስተሳሰብ ከተቀረፀ ተግባሩ ሁሉ ሌላውን የሚጎዳና ማኅበራዊ ሰላምን የሚያናጋ ይሆናል። እንደዚህ ዓይነቱ ባህርይም በተራ የአካዴሚክስ ዕውቀት በማስትሬትና በዶክትሬት ዲግሪ በፍጹም ሊለውጥ ወይም ሊወገድ አይችልም። በተለይም በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለውን የተወሳሰበ ችግር ስንመለከት የችግሮቹና የመዘበራረቁ ዋና ምክንያት ያልተማረው ምስኪን ሕዝብ ሳይሆን ራሱ ተምሬያለሁ የሚለውና ዶክትሬት ዲግሪን የጨበጠው ነው ለድህነትና ለጦርነት፣ እንዲሁም ለተዘበራረቀ ኑሮ ዋናው ምክንያት።
ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ነው አርባ ዓመት ያህል እልህ ውስጥ አስገብቶን የሚያጫርሰንን አስቸጋሪና የተጣመመ ጭንቅላት መረዳት የምንችለው። የአገራችን ዋናው ችግር ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ መጣሁ የሚለው ጥቂቱ ኤሊት ንቃተ ህሊናውን ለማዳበር በሚያስችሉት የንቃተ ህሊና ሒደቶች ውስጥ ማለፍ ባለመቻሉ ብቻ ነው። ይኼንን ጉዳይ ካንትም ሆነ ሄግል በጽሑፎቻቸው ውስጥ ማረጋገጥ ችለዋል። የግሪክ ፈላስፎችም ይኼንን ነው የሚያሳስቡን። ማለትም የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ሊዳብር የሚችለው፣ በአንድ በኩል በራሱ ጥረት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የማቴሪያል ሁኔታዎችና የአኗኗር ሥልቶች ሲሻሻሉ ወይም ሲለወጡ የሰው ልጅም የሠለጠነ ባህርይ ማዳበር ይችላል። በመሆኑም በሚያስፈልገው ጊዜ ከትክክለኛ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ጋር መተዋወቅ የማሰብ አድማስን ያሰፋል። ከጠብ ጫሪነትና ከአገር አፍራሽነት ያድናል። በሌላ ወገን ደግሞ የተበላሸ ወይም ለዕድገት የማያመችና የማደግና የመስፋፋት ባህርይ የሌለው ቴክኖሎጂዎችን አገራቸው ውስጥ የሚያስገቡና እነሱን የሚጠቀሙ አገሮች የሠለጠነ ማኅበረሰብ የመገንባትና ከአንደኛው የዕድገት ደረጃ ወደ ተሻለው የመሸጋገር አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ ይሆናል። ይኼንን ወደ አገራችን ሁኔታ ስንተረጉመው ዛሬ የሚያፋልጠን ጉዳይና እንዳንግባባ ምክንያት የሆነን የገዢ መደቦቻቸን በአስፈላጊውና በትክክለኛው ወቅት ከትክክለኛ ዕውቀት፣ እንዲያም ሲል ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር እንድንተዋወቅና ጠንካራ ኅብረተሰብ እንድነገነባ ጥረት ስላላደረጉ፣ ወይም ደግሞ ስላልተገለጸላቸው ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን የማንወጣው ማጥ ውስጥ በመግባት የተከታታዩንም ትውልድ በቀላሉ ሊፈታው የማይችለው ችግር ውስጥ እንዲወድቅ እናደርገዋለን ማለት ነው።
ይቀጥላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው fekadubekele@gmx.de ማግኘት ይቻላል፡፡