Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትየኢትዮጵያ ሐኪሞችም የአገራቸውን ሕመም ገና አላወቁትም

  የኢትዮጵያ ሐኪሞችም የአገራቸውን ሕመም ገና አላወቁትም

  ቀን:

  በገነት ዓለሙ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከጤና ባለሙያዎች (ወኪሎች) ጋር ያደረጉትን የሚያዝያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ስብሰባ የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ባቀረቡት ልክ ተከታትዬዋለሁ፡፡ የተለያዩ እኔ የተከታተልኳቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጉዳዩን ያቀረቡት ደስ እንዳላቸውና እነሱን እንዳሰኛቸው በዜና ፕሮግራማቸው ብቻ ሳይሆን፣ በልዩ ‹‹ፕሮግራም›› እንዳለ እንደወረደ ጭምር ነው፡፡ እንዳለና እንደወረደ አቀራረባቸው ግን ሲበዛ ይለያያል፡፡ የመለያየቱ ብዛትና ክፋት ደግሞ፣ የተለመደውን መሃላችንን እንድናጠናክር ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሚዲያ ‹‹ማመን ቀብሮ ነው›› ማለትን፡፡

  ኢትዮጵያ ውስጥ ቴሌቪዥን ማለት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) መሆኑ ከቀረ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በዚህ ረገድ ዋልታ ቴሌቪዥንን የሚስተካከል አላገኘሁም፡፡ ዋልታ አሁንም ደግሞ ለማስረገጥ፣ በዚህ ረገድ (ከብዙ ማስተካከያ ጋር) የኢትዮጵያ ‘C-Span’ ማለትም ፐብሊክ አፌርስ ኔትወርክን መንገድ እየያዘና ተለይቶ የወጣ ላይ አገልግሎት ለመስጠት የቆረጠ ይመስላል፡፡ ብዙዎቹን የዕለቱን ወይም የሳምንቱን ዋና ዋና የአገር ጉዳይ የስብሰባ ውሎዎች እንዳለ ዘርግፎ የሚያቀርብልን ዋልታ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎችን ጉዳይ ግን ከዋልታ ይልቅ እንደ አጋጣሚ ይሁን በሌላ ምክንያት ‹‹እንዳለ›› ዘርግፎ ያቀረበልን ፋና ነው፡፡

  ፋና ቴሌቪዥን ያስቀረው ወይም የቆራረጠው ኖረም አልኖረም ባለሙያዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የዋሉበትን ውሎ እስኪሰለቸኝ ድረስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ትዕግሥት ማድነቅ እስከገደድ ድረስ፣ ምናልባትም እነዚህን የሕክምና ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የመድኃኒት ባለሙያዎች ምን ልዩ አደረጋቸው ብዬ እስኪደንቀኝ ድረስ የተባለውንና የሚበቃኝን ያህል ሰምቻለሁ፡፡

  ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር የተሰበሰቡት (ከጥቂት ማጋነን ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰበሰቡት ወይም ለስብሰባ የጠሩት) ሐኪሞች፣ (የጤና ባለሙያዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎች) የተሰማሩበት ዘርፍ ፖለቲካውም ጭምር ያለበት እያደር እየተባባሰ፣ እየጨመረ የመጣው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን የሚጨፍሩበት መስክ መሆኑ እውነት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከሌሎች መካከል የሕክምናው አገልግሎትና ‹‹ኢንዱስትሪ››ው ሌላው ገንዘብ የሚሠራበት፣ የሚታተምበት፣ ብር የሚፈተልበት መስክ ሆኗል፡፡ በመንግሥታዊ የሕክምና መስጫዎች ውስጥ ግዴለሽነት፣ መሰላቸት፣ የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች መጓደልና የበሽተኛ/ታካሚ መድኃኒትም በሥልት የሚፈጸም ስርቆት በታካሚዎች ላይ ጥቃት ያደርሳል፡፡ በግል ሕክምና መስጫዎች ዘንድ ደግሞ ጥቃት የሚመጣው እያቀማጠሉ ከመጋጥ ከባለሙያ ተብዬዎች ፍላጎትና ስግብግብነት ነው፡፡ በጨዋነት ሽፋን የመበላለጥ ካልሆነ በስተቀር ከትንሿ የግል ክሊኒክ አንስቶ እስከ ትልልቁ ሆስፒታል ድረስ፣ የሚሰጠውን አገልግሎት የሚመራው ወፍራምና ፈጣን ትርፍ የማግኘት ፍላጎት ነው፡፡

  የታካሚውን የጤና ችግር ለማወቅ ከሚያስፈልገው በላይ ወፍራም ብር የሚያስገኝ የምርመራ ዓይነት ይታዘዛል፡፡ ‹‹ቆይ እስቲ ይህንን ሞክረን ካልሆነ ሌላ…›› እያሉ ከምርመራ ምርመራ፣ ከአንድ የሕክምና ዓይነት ወደ ሌላ እያሸጋገሩ የታካሚውን ፈውስ ማጓተት፣ የሚበጅና የማይበጀውን መድኃኒት በውድ ዋጋ ከዚያው ማስገዛት፣ በትውከትና በተቅማጥ ተደናግጦ የመጣውን ወይም ደካክሞ የታየውን ድንገተኛ የማታ ታካሚ ሁሉ አስተኝቶና ግሉኮስ ሰክቶ መርፌ ምንትስ እያሉ መጋጥ፣ ተስፋ የሌለውን በሽተኛ (ነባርም ይሁን አዲስ ገቢ) ለአሳካሚ ቤተሰቦች የሚገኝበትን ሁኔታ ሳያሳውቁ የሚድን አስመስሎ ልዩ ልዩ ‹‹ሕክምና›› እየሰጡና ያልተሰጠም ‹‹እየሰጡ›› አሳካሚ በቃኝ እስኪል ወይም የታካሚው ሬሳ እስኪወጣ ድረስ፣ በሺሕና በአሥር ሺሕ ቤት መቆንደድ የመሳሰለው ሁሉ የሚፈጸምበት ሌላው የውንብድና ማዕድ ነው፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ መንገዶች ጥሩ ማጅራት መቺ ያልሆነ የሕክምና ባለሙያ ፈላጊ የለውም፡፡ ይህን ዓይነት ምርመራ ለምን ሳታዝዝ ቀረህ የሚል ጥያቄ ይመጣበታል፡፡ አልገባ ካለው ይሰናበታል፡፡ እንዲያውም የሐኪሙ ከፊል ደመወዝ በምርመራ ከሚያስገኘው ገቢ ጋር ላይ ታች የሚልበት ሥልት አለ፡፡

  የመንግሥት ሕክምና ቤቶችም የባለሙያ ምንጭ ሆነው ከማገልገላቸው ሌላ የመድኃኒት ምንጭ፣ የገበያ ማስታወቂያ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ በትርፍ ጊዜ ተቀጣሪነትም ሆነ በሌላ የጥቅም ግንኙነት እንዲህ ያለ ቦታ ይህን ምርመራ አድርጋችሁ ኑ፣ እዚህ ቦታ ይህን መድኃኒት ታገኛላችሁ፣ እዚህ የተሟላ ሕክምና የለም፣ ፅዳቱም አያስተማምንም… እየተባለ የድለላ ሥራ የሚሠራባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

  በአጠቃላይ በአገሪቱ ከሠለጠኑት በሽታዎች በላይ፣ በበሽታ ላይ እንዲዘምት የተፈጠረውና የተሰማራው ሠራዊት ራሱ ጥሩ ስም የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ሐዘን ቤቶች የሐኪምና የሕክምና ቤቶች መቀርጠፊያ፣ የክስ ዝርዝር መስሚያ የሆኑትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

  በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የአገራችን የሕክምና አገልግሎት እንዲሁም የተጠቀሱት የጤና፣ የሕክምና፣ የመድኃኒት ባለሙያዎች ችግርና የሥራ ሁኔታ ጭምር ለውይይት ቢቀርብና ጥያቄ ቢነሳበት ክፋት የለውም፡፡ እንዲያውም ተገቢና የአገር ጉዳይም ነው፡፡

  ጉዳዩን የሚያስተዛዝብና የሚያሳዝን ያደረገው ግን የሐኪሞች ጉዳይ፣ በተለይም በዚህ ቀውጢ የለውጥ ወቅት የ‹‹ማስጠንቀቂያ›› የሥራ ማቆም አድማ ዓይነት ማስፈራሪያ ‹‹መቅደም›› ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡

  በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሠራተኞች ሁሉ የሚደንቅ፣ ግን እንኳንስ ተግባር ላይ ሊውል በቅጡም ተሰምቶ የማያውቅ መብት አላቸው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42 የሚደነግገው ይህንን ‹‹ሰምተነው›› የማናውቀውን መብት ነው፡፡ የፋብሪካና የአገልግሎት ሠራተኞች፣ ሌሎች የገጠር ሠራተኞች፣ ከተወሰነ የኃላፊነት ደረጃ በታች ያሉና የሥራ ጠባያቸው የሚፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የሥራና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ለማሻሻል በማኅበር የመደራጀት መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት የሠራተኛ ማኅበራትንና ሌሎች ማኅበራትን የማደራጀት፣ ከአሠሪዎችና ጥቅማቸውን ከሚነኩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር የመደራደር መብትን ያካትታል፡፡ እነዚህ ሠራተኞችና የሠራተኛ ክፍሎች ሥራ ማቆምን ጨምሮ ቅሬታቸውን የማሰማት መብት አላቸው፡፡ በእነዚህ ዕውቅና ባገኙት የመደራጀት፣ ሥራ በማቆም ጨምሮ ቅሬታ የማሰማት መብቶች ለመጠቀም የሚችሉት የመንግሥት ሠራተኞችም በሕግ ይወሰናሉ የሚለው የተጠቀሰው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ነው፡፡

  ከዚህ ሕገ መንግሥት በላይ የሆኑ ገዥዎቻችን ግን ንባቡንና ጽሑፉን ዘወትር ተገትሮ የምናየውን ድንጋጌ ረግጠው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42(1)(ሐ) መሠረት የመደራጀትና ሥራ ማቆምን ጨምሮ ቅሬታ የማሰማት መብት ያላቸውን የመንግሥት የሠራተኛ ክፍሎች ሕግ እንኳን ማውጣት ሳይፈቅዱ እነሆ 24 ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡ ለውጡ የመጣው በዚህ ሁሉ ጫና ጭምር ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ሐኪሞችም (የጤና ባለሙያዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የመድኃኒት ባለሙያዎች) የሚባሉት ሁሉ በግልም ሆነ በመንግሥት ዘርፍ የተሰማሩት ጭምር የዚህ አፈናና ጭቆና ሰለባዎች ነበሩ፡፡ ሙያው የሐኪሞች ማኅበር፣ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማኅበር፣ የፋርማሲስቶች ማኅበር፣ የነርሶች ማኅበር፣ የጤና ረዳቶች ማኅበር፣ የላቦራቶሪ ቴክኒሺያኖች ማኅበር፣ የራዲዮግራፊ ቴክኒሺያኖች ማኅበር ከተባሉ የተለያዩ ባለሙያዎች ማኅበራት የተውጣጡ ተወካዮች ጭምር ያሉበት የጤና ባለሙያዎች መማክርት ጉባዔ የሚባል የጤና ሚኒስትርን የሚያማክር ሚና ጭምር ያለው እስከ መሆን የደረሰ አቅምና አቋም የነበረው ቢሆንም፣ ይህንን እንኳን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ነባር አማካሪነቱን የሚያሳጣ ችግር ለመጋፈጥ ያልቻለ ሙያ ሆኖ ቆይቷል፡፡

  በተለያየ ስም የሚጠሩ ከላይ የተገለጹት ስምና ስያሜ ያላቸው የሙያው ማኅበራት ህልውና በራሱ በሙያውና በማኅበሩ ቅጥር ውስጥ ከተገደበ የተወሰነ ውር ውር በስተቀር ሕዝብ ውስጥ የገባ፣ የሕዝብን ንቃትና ግንዛቤ ያነሳ፣ የሕዝብ ድጋፍ ያገኘ፣ እዚህ ግባ የሚባል አንዳች ፋይዳ ያለው በስሙ የሚጠራ ‹‹ሙያ›› ሠርቶ የማያውቅ ሙያ፣ በተለይም በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ሕዝቦችና ወጣቶች ትግልና በገዥው መንግሥት የድቆሳ መስተጋብር መካከል ተፈልቅቆ የወጣው የእነ ዓብይ አህመድ መንግሥታዊ አመራር ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ባለበት ወቅት፣ ‹‹የሥራ ሁኔታዎችን›› ጉዳይ እንደራደር ብሎ ‹‹ማስፈራራቱ›› በጣም የሚደንቅና ለአገር የማይበጅ አሳሳች ሚና ነበር፡፡ ይህንን ዓብይ በጣም የሚያውቁት አለዚያም በእኔ ግምት ቢያንስ ቢያንስ የሚጠረጥሩት ይመስለኛል፡፡ በዕለቱ ውሎ፣ በተለይም በመልሳቸው መግቢያና አልፎ አልፎም ደጋግመው ጣልቃ እያስገቡ የተናገሩትን ያስተውሷል፡፡ ‘የጥፋት መልዕክተኛ አትሁኑ፡፡ ታሪክ ዘለዓለም የሚያስታውሰው አደናቃፊውን አይደለም’ እያሉ ያስተላለፉት መልዕክት ይህን ከቁም ነገር ያስገባ ይመስለኛል፡፡

  ይህ በሩብ ምዕት ዓመት እሮሮና መስዋዕትነት ላይ የበቀለ፣ አሁን ደግሞ ‹‹ዕድሜ›› ለአደናቃፊዎቹ እንጂ በመንከርፈፍና በመቁነጥነጥ መሀል ተገሻሮ አቤት አቤት እያለ ያለ ለውጥ የመምህራንንም ሆነ የሲቪል አቪዬሽን ሠራተኞችን (በተለይም የአየር ተቆጣጣሪዎችን)፣ የጤና ባለሙያዎችንም ሆነ የሌላ ሙያ ሠራተኞችን የሠራተኛና አሠሪ ግንኙነት የኢትዮጵያ አጀንዳ አድርጎ ማቅረብ ያለበት በጭራሽ አይመስለኝም፡፡

  ይህን የምለው የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን የሚመለከትና የሚያሳስብ ጥያቄ የለም ብዬ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጤና ክብካቤ ጉዳይ እንዲያውም የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን አንገብጋቢ ጥያቄ ለመፍታት ግን መጀመርያ በለውጡ ላይ፣ በለውጡ መጠናከርና አሸንፎ መውጣት ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የጤና፣ የሕክምና ባለሙያዎች በምሬት ያነሱት ‹‹የወጪ መጋራት›› ጣጣ አካል የሆነው የሥራ መብት ችግር ጉዳይ፣ ጤና ጥበቃ ውስጥ ብቻ ድል ተመቶ የሚገላገሉት አይደለም፡፡ እዚሁ ምሳሌ ውስጥ ትንሽ ቆይተን ጉዳዩን በአጭሩ ብንመለከተው፣ የተማርክበትን ወጪ በአገልግሎት ሳትከፍል ወይም በምትኩ ገንዘቡን በመቶ ሺዎች በጥሬ ገንዘብ ሳትመልስ ስንብት አይሰጥህም፣ ዲግሪ አይሰጥም ማለት የጤናው ዘርፍ፣ ወይም የትምህርቱ ዘርፍ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከወጪ መጋራት አዋጅና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ሌላ በሰርኩለር መብትና ግዴታ የሚያቋቁሙ አሠራሮች ጉዳይ የአንድ የጤና ዘርፍ ወይም የትምህርት ዘርፍ ጉዳይ ሳይሆን፣ ከሕግ በላይ ሆኖ ይጠቅመኛል ያሉትን ‹‹ሕግ›› የማውጣት የአድራጊ ፈጣሪነት የመንግሥት ሥልጣን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬም፣ አሁን በዚህ ሳምንት ውስጥ በራሱ እንደሚታየው በገቢዎች ሚኒስቴር ውስጥ፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ‹‹የትብብር›› ክንውን ውስጥ የሚታይ ከሕግ በላይ የመሆን አባዜ ነው፡፡ ይህንን እስከ መጨረሻው ድል ለመምታት ለየብቻ በእንጭፍጫፊ ጉዳዮች ላይ ከመንደፋደፍ መውጣት፣ ይልቁንም ዋነኛውን የለውጥ አቅጣጫ ከሚያስቱ ድንግዝግዞች ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡

  ሌላ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ ይህ ምሳሌ የሐኪሞቻችን ጥያቄና የጠቅላይ ሚኒስትር ምላሽ በየፊናቸው ያስከተለውን ስሜትና የስሜት መጐሽ የሚመለከት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የተከበሩ የጤና (የሕክምና) የመድኃኒት ባለሙያዎች ዓብይ በአንድ የ‹‹ይሁን!›› ትዕዛዝ ተስማምቻለሁ ፈቃድ የጤናውን ችግር ከ50/60 ዓመት ችግሩ አላወጣውም ብለው ድጋፋቸውን ነፍገውታል፣ ፍቅራቸውን ነስተውታል፣ ያንንም በአደባባይና በመብታቸው ውስጥ ሆነው በሚገልጹበት ሁኔታ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ በፌስቡክ፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር በስለትም፣ በጥረትም፣ በኩሸትም የሚጠባበቁ የለውጥ ተጠናዋቾች ቢያንስ ቢያንስ ስሜታቸውን አርክተውበታል፡፡ አላልናችሁም ነበር ወይ? ብለው አቅራርተውበታል፡፡ ለአንዳንዶቹ ዓብይ ፀረ ፌሚኒዝም መሆናቸውን ያረጋገጡበት መድረክ ሆኖ ከዓብይ ጋር ተጣላን፣ ግፋ ሲልም ተቆራረጥን ያሉት ያልተባለውን ተባለ ብለው ነው፡፡

  ለውጡ ጨርሶና አካቶ መለወጥ ካለባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ እንደሚታየውና እንደሚነዘነዘው የተሻለ የሥራና የገቢ ዕድል ወዳለበት አገር ሄዶ መሥራትን ነውር፣ ከዚያም አልፎ ሕገ መንግሥቱንም ረግጦና የዜጋ የመውጫ ቪዛ ሕግ መቅረቱን ‹‹ዘንግቶ›› ክልክል የሚያደርገውን አሠራር ነው፡፡ በዚህ መስክ ከማናቸውም በላይ በጣም ጎልቶ የሚነገረው (ከምስኪኖቹ የዓረብ አገር ፈላሲዎች) በላይ የጤና ባለሙያዎች ‹‹እስራት››፣ በውልና በከበደ ግዴታ እግር ከወርች መታሰር ነው፡፡ ዛሬ ለውጡ አዲስ መፍትሔ እያበሰረ ነው፡፡ ብዙ ባለሙያ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ መፍለሱ እኮ ማስፈራት የለበትም እያለ ነው፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሙያተኛ (የጤና፣ የሕክምና፣ የመድኃኒት ባለሙያ ጭምር) በውጭ በመፈለጉ ተደስተን፣ በተሻለ የችሎታና የሥነ ምግባር ብቃት ገበያውን ለማስፋትና ለመሙላት፣ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ፍላጎትም ለመሸፈን የሚችል የሰው ኃይል በየጊዜው ለማፍራት መረባረብ አንዱ የልማታችን ዕቅድ ይሁን እየተባለ ነው፡፡ ሁለት ነገሮች እዚህ ላይ ይነሳሉ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰው ኃይል የውስጥ ፍላጎት ማለት የዜጋው ብቻ አይደለም፡፡ ጥራትና ደረጃቸው ከለሙት አገሮች ጋር የተመጣጠነ የሕክምና፣ የመዝናኛ አገልግሎቶችን በቀለለ ዋጋ ማቅረብ መቻል የውጭ ምንዛሪ የሚስብ የውስጥ ፍላጎት ነው፡፡ ሁለተኛው መሰመር ያለበት ጉዳይ የተሻለ የችሎታና የሥነ ምግባር ብቃት ያለው (ለምሳሌ) የጤና ባለሙያ የማፍራት፣ የአገር ውስጥም የውጭ አገርም ገበያውን ለመሙላትና ለማስፋት የሚያስፈልገው ቁልፍ ጉዳይ አንዱ የትምህርቱን ሥርዓት ከሥር ከመሠረቱ መለወጥ ጭምር ነው፡፡

  ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ጊዜ ተናግረውታል፡፡ መደማመጥ ስለሌለ የምንሰማው ሌላ፣ ውስጣችን የሚተናነቀንን መልስ እያሰብን ስለሆነ አይሰማም እንጂ፡፡

  እናም የኢትዮጵያ የጤና፣ የሕክምና፣ የመድኃኒት ባለሙያዎች ጤና የላቸውም እንዴ? እነዚህ ሰዎች ያማቸዋል ወይ? እነዚህ ሰዎች የአገራቸውን ሕመም ገና አላወቁትም እንዴ? እያልኩ ደጋግሜ የምጠይቀው፣ የሁሉም የለውጥ ኃይሎች (የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ) የመጀመርያው ደረጃ አብሮ የመሥራት ተልዕኮ ዴሞክራሲው የሚፈልጋቸውን ሁኔታዎች የማመቻቸት ነው፡፡ መሆንም ያለበት ይኸው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው የዴሞክራሲ ጅምሩን በጥያቄና በጫጫታ ጋጋታ እንዲቀጭ ዕድል መስጠት ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...