Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትለደደቢት በ‹‹እንቅርት ላይ…›› የሆነው የፌዴሬሽኑ ውሳኔ

  ለደደቢት በ‹‹እንቅርት ላይ…›› የሆነው የፌዴሬሽኑ ውሳኔ

  ቀን:

  እግር ኳስ የሚወጣበትን ያህል ውጤታማ ባይሆንም ተጫዋቾችን ጨምሮ በዙሪያው ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በጥናት ላይ ያልተመሠረተው ይህ የክለቦች አደረጃጀትና ተጫዋቾች ክፍያ መናር፣ አሁን ላይ አቅም አላቸው ተብለው የሚታመኑ ክለቦችን ሳይቀር ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመዳረግ የአንዳንዶቹን ሕልውና እንዲያከትም ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡ መፍረሱን በይፋ አውጆ በማግስቱ መኖሩን ያረጋገጠው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

   

  የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አገሪቱን ማስተዳደር በጀመረ ማግስት፣ ለገሃር አካባቢ የተፀነሰው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከታላላቆቹ ተርታ ለመመደብ የፈጀበት ዕድሜ ከአሥር ዓመት ብዙም የዘለለ አልነበረም፡፡ በአጭር የምስረታ ዕድሜ ከዲቪዚዮን ወደ ብሔራዊ ሊግ ከዚያም ወደ ፕሪሚየር ሊግ አድጎ በ2005 የውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ አይዘነጋም፡፡

  ደረጃው ቢለያይም እንደ አውሮፓውያኑ ክለቦች ስያሜ ከፋይናንስ አቅማቸው ጨምሮ በጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱ የኢትዮጵያ ክለቦች ተርታ ተመድቦ የዘለቀው ደደቢት፣ ለተጨዋቾች የዝውውርና ወርኃዊ ክፍያ መናር በፈር ቀዳጅነቱ ይጠቀሳል፡፡ በደደቢት የተጀመረው የተጨዋቾች ከፍተኛ ክፍያ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና እያለ ወደ ሌሎችም የክልል ክለቦችና ተዛምቶ ወደ ኢትዮጵያ ለሚፈልሱ አፍሪካውያን ተጨዋቾች መበራከት የጎላ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

  የዕድገቱን ያህል ውድቀቱም ፈጣን የሆነው ደደቢት በአሁኑ ወቅት ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት የፕሪሚየር ሊጉን መርሐ ግብር ለማከናወን እንደማይችል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካስታወቀ በኋላ፣ በማግስቱ ደግሞ ‹‹እቀጥላለሁ›› ማለቱ ተሰምቷል፡፡

  በፋይናንስ ቀውስ እየታመሰ የሚገኘው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የፋሲል ከተማ አቻውን በመቐለ ስታድየም ባስተናገደበት ጨዋታ ‹‹ደጋፊዎቼ›› ያላቸው ተመልካቾች በእንግዳው ቡድን ተጫዋቾች ላይ ባሳዩት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በፌዴሬሽኑ በገንዘብ 150,000 ብር ቅጣትና በሜዳው ሁለት ጨዋታ በዝግ ስታዲየም እንዲጫወት ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡

  ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ 23ኛ ሳምንት ጨዋታ ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ የነበረ ቢሆንም፣ ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውሱ ምክንያት መጫወት ባለመቻሉ፣ ሦስት ነጥብና ሦስት ንፁህ ጎል በፎርፌ እንዲያጣ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ደደቢት ይህን ቅጣት ‹‹ይከፍላል፣ አይከፍልም›› በሚል በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ ሌላ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ በክለቡ ኃላፊዎች በኩል ያለውን አስተያየት ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

  በፌዴሬሽኑ የውድድር ደንብ መሠረት ክለቡ ለአወዳዳሪው አካል ውድድር ለማቋረጥ ያቀረበው ምክንያት አጥጋቢ ካልሆነ፣ ፎርፌው እንደተጠበቀ ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል የፌዴሬሽን ምንጮች ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...