ክፍል ፪
በፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
የኃይል ሚና በኅብረ ብሔርና በኅብረተሰብ ግንባታ ሒደት ውስጥ!
በአውሮፓ ምድር ውስጥ ፍልስፍና፣ ሳይንስ፣ ሥነ ጽሑፍና ድራማ፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ሳይንስ ዳብረው፣ አገሮችም በአዲስ መልክ ቢቀረፁምና የሰው ልጅም እንዲኖርባቸው ለማድረግ ውብ ውብ የአርክቴክቸር ሥራዎች ቢሠሩም ኅብረ ብሔር (Nation State) ካለደም መፋሰስ የተመሠረተበት አንድም የአውሮፓ አገር የለም ማለት ይቻላል። ዕድገትንና ሥልጣኔን የሚፈልጉ ኃይሎች የመኖራቸውን ኃይል፣ ሥልጣኔን አጥብቀው የሚጠሉና የነበራቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሁኔታ ላለማጣት የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉና አጥብቀውም እንደሚታገሉ የአውሮፓው የኅብረተሰብ ታሪክ ያረጋግጣል። በዓለም ታሪክ ውስጥ ጦርነት የተስፋፋበትና ጭቆና ሥር የሰደደበት እንደ አውሮፓው ማኅበረሰብ አልነበረም ማለት ይቻላል። አብዛኛዎቹ ትላልቅ ጦርነቶች፣ ከመቶ ዓመት እስከ ሰላሳ ዓመቱ ጦርነትና፣ በጀርመን ምድር ሰባት ዓመት ድረስ የፈጀው ጦርነት፣ በእንግሊዝ በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል የተካሄደው 20 ዓመት ያህል የፈጀ ጦርነት ሁሉ የሚያረጋግጡት ኅብረ ብሔርን መመሥረትና ሳይንስንና ቴክኖሎጂን ዕውን ለማድረግ የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር ነው። በኋላም የተለኮሱትና ለብዙ ሚሊዮን ሕዝቦች ዕልቂት ተጠያቂ የሆኑት የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች የሚያረጋግጡት የሰውን ልጅ ሙሉ በሙሉ አርቆ እንዲያስብና ከአመፅ እንዲቆጠብ ለማድረግ የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ነው። በተለይም ኢኮኖሚያዊ ኃይል ከፖለቲካና ከወታደራዊ ኃይል ጋር በሚቆላለፉበት ጊዜ አገዛዞች ከአገራቸው አልፈው በሌሎች አገሮች ላይ ጦርነት በማወጅ የአንድን አገር ዕድገት ለብዙ ዓመታት ወደ ኋላ ለመጎተት እንደሚችሉም ማየት ይቻላል። በተለይም ካፒታሊዝም ወደ ኢምፔሪያሊዝምነት ከተሸጋገረና በክስተታዊ ዕውቀት (Empricism) ላይ የተመሠረተው የእንግሊዙ አስተሳሰብ በአሸናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ለኢምፔሪያሊዝም ያደሩና በጥቅም የተገዙ ምሁራን በተለይም የነፃ ንግድንና የሥራ ክፍፍል የሚለውን ዶክትሪን በማስፋፋት ነው፤ የአፍሪካን የጥሬ ሀብት ለመቆጣጠር የቻሉትና ጦርነትም ያወጁቡን። ከሰላሳ ዓመት ጀምሮ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ በየአገሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ሁሉ የሚያረጋግጡት የሦስተኛው ዓለም አገሮች ለዝንተ ዓለም በድህነት ዓለም እየማቀቁ እንዲኖሩ የታቀደ አንደኛው ስትራቴጂ ነው። ይህ ዓይነቱ ፖሊሲ ተቀባይነት ካላገኘ ደግሞ የካፒታሊስት አገሮች የተለያዩ ምክንያቶችን በመፈለግና ጦርነት በመክፈት የሦስት ሺሕ ዓመትና ከዚያም በላይ ታሪክ ያላቸውን አገሮች ድምጥማጣቸውን እንደሚያጠፉ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። የኢራቅንና የሶሪያን ሁኔታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል።
ለማንኛውም ሁሉም የአውሮፓ አገሮች ተመሳሳይ የሆነ የዕድገት መሠረት አልነበራቸውም። በየአገሩ ሰፍኖ የነበረው ሥርዓትና ኅብረተሰብዓዊ አወቃቀር የዕድገታቸውንም አቅጣጫ ሊወስነው ችሏል። የወግ አጥባቂነት፣ በተለይም ደግሞ የካቶሊክ ሃይማኖት ከባላባታዊ ሥርዓት ጋር በተቆላለፈባቸው አገሮች ውስጥ የምርት ኃይሎች እንዳያድጉና፣ እንዲያም ሲል ኅብረ ብሔርን ለመገንባት አስቸጋሪ እንደነበር የኅብረተሰብ ታሪካቸው ያረጋግጣል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አምራች ኃይሎች ታፍነው በመቅረታቸውና ከባህላዊ የአመራረት ሥልት ለመላቀቅ ባልቻሉባቸው እንደ ስፔንና ፖርቱጋል የመሳሰሉት አገሮች ውስጥ የውስጥ ገበያና በማኑፋክቸር ላይ የተመሠረተ ካፒታሊስታዊ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥልት ሊዳበር አልቻለም። በከተማና በገጠርም መካከል የነበረው የሥራ ክፍፍል ግልጽ ስላልነበር ካፒታልና የሥራ ኃይል በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ ስላልቻሉ በማኑፋክቸር ላይ የተመሠረተ የውስጥ ገበያ መገንባት በፍጹም አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ረሃብና በሽታ የተለመዱ እንደነበር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
በሌላ ወገን ደግሞ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በተስፋፋባቸው አገሮች ውስጥ ዕውቀት መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን የካፒታሊዝም ዕድገት ፈጣን ነበር። ሰው ማሰብ ሲጀምርና ከሥራውና ከንግድ ትርፍ ማግኘት ሲጀምር አትኩሮውን ወደ ሥራ ላይ አደረገ። ይህ ዓይነቱ ግለሰብዓዊ ሩጫና ቀስ በቀስም ማርክስ ቬበር እንዳለው ካፒታሊስታዊ መንፈስና (The Spirit of Capitalism) የሥራ ሥነ ምግባር እየተለመዱ በመምጣት የጠቅላላው ሕዝብ መንፈስ በካፒታሊዝም ሎጂክ ዙሪያ እንዲሽከረከር ሊያደርገው በቅቷል። በዚህ መልክና ቀስ በቀስ ደግሞ ከተማዎች በሥርዓት ሲገነቡ የሕዝቡ አስተሳሰብ ሰብሰብ ሲል የአገራዊና የብሔራዊ ስሜቱ መዳበር ቻለ። ይህ ማለት ግን እነዚህ ሁሉ በቀላሉ የተገኙ ዕድገቶችና ድሎች ናቸው ማለት አይደለም። ካፒታሊዝም ሥር እየሰደደና እየተስፋፋ ሲመጣ ግልጽ የሥራ ክፍፍል መዳበሩ ብቻ ሳይሆን፣ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራው ሠራተኛ በከፍተኛ ደረጃ ይበዘበዝ ነበር። ከዚህም ባሻገር በጊዜው እንደ ዛሬው ንቃተ ህሊና የዳበረ ስላልነበር የአካባቢ ውድመት ከፍተኛና በአንዳንድ ከተማዎችም ውስጥ ደግሞ በተለይም የሠራተኛው አኗኗር እጅግ አሰቃቂ ነበር። የሰፊው ሕዝብና፣ በተለይም ደግሞ የሥራ መስክ ለመፈለግ ከገጠር ወደ ከተማዎች የተሰደደው ተጠባባቂ ሠራተኛ (Reserve Armey) አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይኖር እንደነበር በሰፊው ተመዝግቧል፣ በሥዕል መልክም ሊገለጽ ችሏል። የካርል ማርክስ ጓደኛና ደጓሚው ፍሪድሪሽ ኤንግልስም ይኼንን አሰቃቂ የወዝ አደሩን አኗኗር በሚገባ ገልጾታል። ይህም የሚያመለክተው የዛሬው የእኛ የተንደላቀቀ ኑሮና እዚህና እዚያ ካለምንም ችግር በአውሮፕላን መጓዝ የብዙ ዓመታት የሥራና የፈጠራ ውጤትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በደማቸው የከፈሉት ነው ማለት ይቻላል። የገበያ ኢኮኖሚ ሊያድግና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሊወስድ የቻለው ትምህርት ቤት እንደተማርነውና በሸመደድነው ዓይነት ሳይሆን በብዙ ውጣ ውረድና ትግል የተነሳ ነው ካፒታሊዝም ሊያድግና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሊወስድ የቻለው።
እስቲ ደግሞ የጀርመንን የኅብረ ብሔር አገነባብ ታሪክ ባጭሩም ቢሆን እንመልከት። ይኸኛውን መጥቀሱ ዛሬ ላለንበት አስቸጋሪ ሁኔታ ምናልባት እንደትምህርት ሊሆነን ይችላል ብዬ አምናለሁ። የጀርመንን ታሪክ ብቻ ስንወስድ፣ ጀርመን በሰላሳኛው ዓመት ከጦርነት ከተላቀቀች በግምት ከመቶ ሃምሳ ዓመት በኋላ በአንድ ባንዲራ ሥር የተጠቃለለች አገር ለመመሥረት በታላቁ ፍሪድሪሽ የፐርሽያ ንጉሥና በሳክሶን ገዢዎች መካከል ሰባት ዓመት ያህል የፈጀ እልክ አስጨራሽ ጦርነት ተካሂዷል። ጀርመን በተለያዩ መሳፍንታት የምትገዛና በዚህም ምክንያት ለውጭ ወራሪዎች የተጋለጠች አገር ስለነበረች፣ ዴንማርክና ስዊድን፣ ፈረንሣይና ኦስትሪያ ከአንዴም ከሁለቴም በላይ በመውረር ኃይሏን አዳክመው ነበር። ይኼንን የተረዱት ታላቁ ፍሪድሪሽ የሳክሶንን መሳፍንት በሚገባ ከቀጧቸው በኋላ በፈረንሣይ ላይ የመጨረሻውን ጦርነት በማካሄድ ጀርመን በ1871 ዓ.ም. ወደ ኅብረ ብሔር ለመሸጋገር በቃች። ይኼንን መሠረት ለማስያዝ የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድና ኅብረተሰቡ እንዲሰባሰብና ብሔራዊ ባህርይ እንዲኖረው የማይታለፍ ጉዳይ ነበር። ለዚህ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያዳርስና ጭንቅላትን ክፍትና ብሩህ የሚያደርግ ትምህርት በቪሊሄልም ሁምቦልዶት በመንደፍ ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህ መሠረትና በተቀነባበረ ምሁራዊና መንግሥታዊ ኃይል ጀርመን በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ እንግሊዝን በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ ቀድማ መሄድ ቻለች። ቀደም ብለው እንግሊዝና ፈረንሣይ ኢንዱስትሪ አብዮትን ለማካሄድና ወደ አጠቃላይ ዕድገትና ወደ ኅብረ ብሔር ለመሸጋገርና ጠንካራ አገር ለመመሥረት የቻሉት አንዱ ሌላኛውን በመለማመጥ ሳይሆን ኋላ ቀር የሆኑ የውስጥ ኃይሎችን በዕውቀትና በሚሊታሪ ኃይል በመቅጣት ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ ወደ ኅብረ ብሔር ለመሸጋገር ያለው ጉዞ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥበብን የሚጠይቅና አልፎ አልፎም ኃይል ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ታሪክ ያረጋግጣል። በተለይም ዕውቀትንና ዕውነተኛ ሥልጣኔ የማይፈልጉ፣ በዚህም በዚያም አሳበው ጦርነትን የሚጭሩና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር አንድን አገር ለመበጣጠስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በመለማመጥና በአማላጅ ከእልህ አስጨራሽ ባህርያቸውና ተግባራቸው እንዲቆጠቡ በማድረግ አይደለም ወደ ሁለ ገብ ዕድገት መሸጋገር የሚቻለው። እነዚህ ኃይሎች የሚፈልጉትን ስለማይረዱና ሰው መሆናቸውንም ስለማይገነዘቡ የመጨረሻ መጨረሻ ከእኩይ ተግባራቸው ሊያስቆማቸው የሚችለው የተቀነባበረ ኃይል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በፖለቲካ ሥልጣን ላይ የተገለጸለትና በራሱ የሚተማመን፣ እንዲሁም አገር ወዳድ ኃይል ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ሲታይ ለአውሮፓው የኅብረ ብሔር ምሥረታና ዕድገት አመቺው ሁኔታ በአንድ በኩል ዕውቀት በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንሸራሽሩ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መካከል የሚደረገው የሰው ዝውውርና በጋብቻ መተሳሰር ለፈጠራ ሥራና ለውስጣዊ ኃይል ማደግ አመቺ በመሆን ዕድገትን ማፋጠን ችሏል ማለት ይቻላል። በተለይም ግለሰብ ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች፣ እንዲሁም የልዩ ልዩ ዕውቀት ፈጣሪዎች በራሳቸው ተነሳሺነትና ውስጣዊ ፍላጎት በመመራት ለአውሮፓው የማኅበረሰብ ዕድገት ከፍተኛውን አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ ችለዋል። ጠለቅና ሰፋ ያለ ዕውቀት ባላቸውና ዕውቀታቸውን ባጣመሩ ኃይሎች አማካይነት ነው የአውሮፓው ካፒታሊዝም ሊያድግ የቻለው። በዚህም መሠረት የዕውቀት መዳበርና መንሸራሽር፣ እንዲሁም ደግሞ ልዩ ዓይነት የፖለቲካ ሁኔታ መፈጠር ለአንዳንድ አገሮች ፈጣን ዕድገት ሊሰጣቸው ችሏል። እንግሊዝ የኢንዱስትሪ አብዮትን ልታካሄድ የቻለችው ከሆላንድ ተባረውና ከጣሊያን ፈልሰው በመጡ የይሁዲ ምሁሮች አማካይነት ነው። በተጨማሪም ከህንድ የዘረፈችው ቴክኖሎጂ ለዕድገቷ አስተዋጽኦ ሲያበረክት፣ በተለይም በኢኮኖሚ ላይ የተደረገው ጥልቅ ጥናትና ክርክር፣ እንዲሁም ለማኑፋክቸር ማዕከላዊ ቦታ መስጠትና፣ የልብስ አሠራርን ከፍሎሬንስ መኮረጅ የኢንዱስትሪ አብዮትንና የቴክኖሎጅ ምጥቀትን አዳብሯል ማለት ይቻላል። በዚህ ላይ በፍጹም ሞናርኪዎች የተወሰደው ወደ ውስጥ ያተኮረ የአገር ግንባታ ለተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ኅብረ ብሔሮቻቸውን በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት አስችሏቸዋል። እንደዚሁም የጀርመን ሕዝብ ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ከመጡ ስላቮች፣ ከማዕከለኛው ምሥራቅና ከይሁዲዎች ጋር የተቀላቀለ ነው። በተለይም ይሁዲዎች ለጀርመን ፍልስፍና፣ ሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም በታላቁ ፍሪድሪሽ የግዛት ዘመን ከሆላንድና ከፈረንሣይ የዕደ ጥበብ ባለሙያተኞችን አምጥቶ ማስፈርና ሕዝቡን እንዲያሠለጥኑ ማድረግ የተለመደ ነበር። በተለይም በሃይማኖት ምክንያት ክትትል ይደረግባቸው የነበሩ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች፣ ሁገኖትስ የሚባሉት ጀርመን አገር ጥገኝነትን በማግኘት ለጀርመን ዕድገት የማይናቅ አስተዋጽኦ ለማበርከት ችለዋል። በአጭሩ የተለያዩ ነገሮች አንድ ላይ በመጣመርና በመዋሃድ፣ በተለይም ደግሞ ዕውቀትን ማዕከላዊ ቦታ በመስጠት ነው በየአገሩ ጠንካራ ማኅበረሰብ ሊፈጠር የቻለው። አንድም አገር ቢሆን በአንድ ብሔረሰብና ራሱን ከሌላው በማግለልና፣ እኔ ከሌላው የተለየሁ ነኝ በማለት ያደገ አገር የለም። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የተፈጥሮንና የኅብረተሰብን ሕግ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ አፈ ታሪክ የሆነ ወይም ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው አባባልና አስተሳሰብ ነው። ተፈጥሮም ሆነ ማንኛውም ማኅበረሰብ የልዩ ልዩ ነገሮች ቅንብሮች ናቸው። ማንኛውም ነገር በአንድ ነገር ላይ ብቻ በመመሥረት ሊያድግ በፍጹም አይችልም። እንደዚሁም የሰው ልጅ ለማደግ ከሌላው ጋር መገናኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሰው ልጅና እንደ ማኅበረሰብ ለመኖር ከምግብ ባሻገር ቴክኖሎጂና ሳይንስ እንዲሁም ለመንፈስ እደሳ የሚያስፈልጉ ሥዕል፣ ሙዚቃና ልዩ ልዩ ባህላዊ ነገሮች ያስፈልጉታል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከአንድ ብሔረሰብ በተውጣጣ ኃይል የሚዳብሩ ሳይሆኑ፣ ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሔረሰብ የተውጣጡና የተሻለ ተሰጥዕዎ ባላቸው ግለሰቦች አማካይነት ነው። ለዚህ ዓይነት ልዩ ችሎታ ደግሞ የተወሰነ ማኅበረሰባዊ አወቃቀር ወይም አመቺ ሁኔታ መፈጠር አለበት። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ለባህል ዕድገትና ለፈጠራ ሥራ እንደ አመቺ ጉዳዮች ሆነው ሊወሰዱ ይችላሉ።
ያም ሆነ ይህ ሰፋ ባለና በተወሳሰበ የኢኮኖሚ ግንባታ አማካይነት፣ በከተማዎች ዕድገትና በመገናኛና በመመላለሻ መንገዶች አማካይነት ብቻ ነው አንድ ሰውም ሆነ ሕዝብ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወርና እዚያ አዲስ ኑሮን ሲጀምር በተሻለ መልክ የመፍጠር ችሎታውን በማዳበር የአንድ ክልል ሰው ብቻ ሳይሆን የአንድ አገር ዜጋም መሆኑን ይሰማዋል። በዚህም መሠረት በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽና ሰፋ ያለ መሠረት ያለው ኢኮኖሚ ሁሉንም በማስተሳሰር እያንዳንዱም ማንነቱን ሊገልጽ የሚችለው በሥራው፣ በዕውቀቱና በሚፈጥረው ነገር ብቻ ይሆናል ማለት ነው። የሰውም ማንነት የሚገለጸው ባልፈጠረው መሬትና፣ ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ የመጣሁ ነኝ በማለትና ወይም ዘር በመቁጠር ሳይሆን፣ በዕውቀት አማካይነትና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠርና ለአንድ ኅብረተሰብ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ብቻ ነው። በአጭሩ የሰው ልጅ ማንነት መግለጫው ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ መፈጠሩና ያልፈጠረውን መሬትና ውኃ፣ እንዲሁም አየር የእኔ ነው በማለት ሳይሆን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጅ፣ እንዲሁም በሌሎች የፈጠራ ሥራዎች አማካይነት ብቻ እንደሆነ የአውሮፓው የኅብረተሰብ ታሪክ ያረጋግጥልናል።
ከዚህ ሁኔታ በመነሳት በአገራችን ምድር በብሔረሰብና በማንነት ዙሪያ የሚካሄደውን ኢሳይንሳዊ ጩኸት ጠጋ ብለን እንመልከት። በመጀመሪያ ግን ከተወሰነ አካባቢ በመነሳት በአገራችን ምድር ትልቅ አገር የመመሥቱን ጉዳይ እንመልከት። ይህ ዓይነቱ ሒደት ተፈጥሮአዊ ቢሆንም፣ ያልተጠናቀቀው የኅብረ ብሔር ግንባታ ወይም የተጨናገፈው ዕድገታችን ለተለያዩ አገር አፍራሽ ለሆኑ የውስጥ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ መመልከት ይቻላል። በተለይም በዘመነ ግሎባላይዜሽን ፈተናው ከባድና አገራችንም የመፈረካከስ ዕድሏ በቀላሉ መመልከት እንደማያስፈልግ ለማሳየት እወዳለሁ። ዋናው ፈተናችንና በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው የውስጥ ኃይሎች መልካቸውን አሳምረው በተለይም ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር በሚቆላለፉበትና የእነሱን ትዕዛዝ ተግባራዊ በሚያደርጉበት አገር ውስጥ ኅብረተሰብዓዊ ውዝግቡና እዚህና እዚያ የሚፈነዳው ጦርነት አንድ ጠንካራና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሊገለጽ የሚችል አገር ለመገንባት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።
መጠናቀቅ ያልቻለው የኅብረ ብሔር ግንባታና ያስከተለው መዘዝ!
በሁላችንም ዘንድ ያለው ስምምነት ከአክሱም በፊት የነበረው ሥልጣኔና በኋላም ብቅ ያለው ንጉሣዊ አገዛዝና የፊዩዳሊዝም መሠረት መጣል፣ እንዲሁም የክርስትና ሃይማኖት ወደ አገራችን መግባትና መስፋፋት ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ ነው። በተለይም በአክሱም አገዛዝ ዘመን መልክ እየያዘ የመጣው የግዕዝ ፊደል ቀደም ብሎ የተገኘ ወይም የተቀረፀ ቢሆንም በአራተኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና ሃይማኖት ወደ አገራችን ከገባ በኋላ ነው አናባቢዎች በመጨመር ዕምርታን ሊሰጡት የቻሉት። የኋላ ኋላም በቅዱስ ያሬድ መቃኘት የተጀመረው የቤተ ክርስቲያን መዝሙርና የኖታ አጻጻፍ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች መፈጠርና መዳበር የሚያረጋግጡት የሥልጣኔ ወይም የዕድገትን ደረጃን ነው። ይህም የሚያመለክተው ማንኛውም ነገር ከትንሽ በመነሳት እየተስፋፋ እንደሚሄድና ሌሎች አካባቢዎችን እንደሚያዳርስ ነው። ይሁንና የአክሱም ሥልጣኔ በአማካዩ በእርሻና በሩቅ ንግድ ላይ የተመረኮዘ ስለነበር ሥልጣኔው ውስጣዊ ኃይል በማግኘት የተለያዩ ጎሳዎችን ሊያጠቃልልና ወደ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ሊሸጋገር አልቻለም። የመጨረሻ መጨረሻም በቤጃዎች ጦርነትና በዮዲት ወረራ የተነሳ ሥልጣኔው ይወድማል። በተጨማሪም የሚመካበት የሩቅ ንግድ ይዘጋበታል። የተወሰነው ኃይል ወደ ደቡቡ ክፍል በማፈግፈግ በ12ኛውና የኋላ ኋላ ደግሞ በ13ኛው ክፍለ ዘመን በመንሰራራት የዛግዌና የሰሎሞናዊያን ነገሥታት የክርስትናን ሃይማኖትና የግዕዝን ፊደል እንዲያብብ ሊያደርጉት በቅተዋል። ይሁንና የግዕዝ ፊደል ለአማርኛ እንዲያገለግል በመደረጉ ለቋንቋው የበለጠ ማበብ ዕምርታን ሰጥቶታል ማለት ይቻላል።
በሰሎሞናይት ሥርወ መንግሥት ዘመን ነው ፊዩዳሊዝም የሚባለው ሥርዓት የኅብረተሰብ የአኗኗር ሥልት በመሆን ሊዳብር የቻለው። ይህ ሥርዓት እንደ ባህላዊ ሆኖ በመወሰዱና የገበሬውም ኑሮ ተደጋጋሚ በመሆኑና በከፍተኛ ደረጃ በመበዝበዙ ከውስጥ ቴክኖሎጂያዊ ለውጥ በፍጹም ሊመጣ አልቻለም። በተለይም የነጋዴውና የአንጥረኛው የኅብረተሰብ ክፍል ከገበሬው ጋር የነበራቸው ግንኙነት በጣም የላላ ስለነበርና፣ በዚህም አማካይነት በጋብቻና በተለያዩ ዓይነቶች የሚገለጽ ኅብረተሰብዓዊ መተሳሰር ስላልነበር በገንዘብ አማካይነት ሊገለጽ የሚችል ኢኮኖሚ መዳበር አልቻለም። አንጥረኛው በየጊዜው የምርት መሣሪያዎችን እየፈጠረና እያሻሻለ ማቅረብ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የአገር ውስጥ ንግድ ሊያድግና ገበያም የልዩ ልዩ ዕቃዎች መገበያያ በመሆን ሕዝቡን ሊያስተሳስረው አልቻለም። ከአገር ውስጥ ይልቅ የሩቅ ንግድ የሚባለው ነበር የቤተ ክርስቲያንና የባላባቱን የፍጆታ ፍላጎት ያሟላ የነበረው። ከውጭ የሚመጣውም ዕቃ ደግሞ በንጹህ መልኩ ለፍጆታ ብቻ የሚያገለግል ስለነበር ለቴክኖሎጂ ምጥቀት ያለው አስተዋጽኦ አልቦ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም የተነሳ የፊውዳሉ መደብ የሚመካው በመሬቱና ከገበሬው በሚያገኘው ግብር ብቻ ስለነበር የፍጆታ አጠቃቀሙን ሊያሻሽልና ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ ሊያበረክት አልቻለም። ስለሆነም የውስጥ ኃይላቸው (Dynamic Social Forces) ከፍ ያለ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቅ ሊሉና ከተማዎችንና መንደሮችን ሊመሠረቱና ኅብረተሰቡን ሊያያይዙ አልቻሉም። በማኅበረሰቡ ውስጥም ምንም ዓይነት ምሁራዊ እንቅስቃሴ የሚታይ ስላልነበርና፣ አገራችንም ከውጭው ሥልጣኔ የተቋረጠች በመሆኗ ዕውቀት ከውጭ በመግባት አስተሳሰብን በማደስ ቴክኖሎጂያዊ ለውጥ እንዲያመጣ አላስቻለውም። በዚህ ላይ በየቦታው የሚያስተዳድሩት ፊውዳሎች ዋናው ተግባራቸው ጦርነት ማካሄድ ብቻ ስለነበር በራሳቸው ተነሳሽነት ከተማዎችንና መንደሮችን በመመሥረት የዕደ ጥበብ እንቅስቃሴ እንዲዳብር የሚያደርጉት ጥረት አልነበረም። ይህ ማለት ግን አንዳንድ ሙከራዎች ወይም ፈጠራዎች አልነበሩም ማለት አይቻልም። ዛሬ የምንመገባቸው እንጀራና የተለያዩ የወጥ ዓይነቶች፣ እንዲሁም የምንጠጣው ጠላና ካቲካላ በፊውዳሉ ሥርዓት ውስጥ መጠመቅ እንደተጀመረና ከዚያ በመስፋፋት ቀስ በቀስ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ግዛት ማዳረስ እንደቻሉ መገንዘብ ይቻላል። የጠጅን አመጣጥ ታሪክ ስንከታተልና አፈ ታሪኩም እንደሚነግረን ንግሥት ሳባ ኢየሩሳሌም ተምራ እንደመጣችና በግዛቷ ውስጥም እንዲስፋፋ እንደገፋፋች ይነገራል። ይኼንን የተረት ተረት ነው ብለን እንኳ ብንተው በፊውዳሏ ኢትዮጵያ እንደዳበረና እንደተሰፋፋ ይታወቃል። ፈትልና የልብስ ሥራዎችን ስንመለከት የተለመደ እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና ባለው የቴክኖሎጂ ገደብና የመፍጠር ችሎታ አለመዳበር እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ጅማሮች ማደግና በፋብሪካ መልክ እየተጠመቁና እየተሠሩ ሊስፋፉ አልቻሉም። በአንፃሩ ካፒታሊዝም ከማደጉ በፊት እንደነዚህ ዓይነቶች የዕደ ጥበብ ሥራዎችና የካቲካላና የጠላ ጠመቃ በማዕከለኛው ክፍለ ዘመንም በአውሮፓ ምድር ውስጥም የተስፋፋ ነበሩ። ለማንኛውም በአገራችን ምድር የተስፋፋው የምግብ አሥራር፣ የጠላና የካቲካላ አጠማመቅ፣ እንዲሁም አንዳንድ የዕደ ጥበብ ሙያዎች በፊውዳሉ ሥርዓት ውስጥ የፈለቁና የዳበሩ፣ ሥርዓቱ ወደ ሌላ አካባቢዎች ሲስፋፋ እነዚህ ባህላዊ ነገሮች የበለጠ በመሻሻል ዕምርታን በማግኘት አብዛኛው ብሔረሰቦች ሊመገቧቸውና ሊጠቅሙባቸው በቅተዋል። በዚህ መልክ የተለያዩ ባህሎች አንድ ላይ በመዋሃድ በዲያሌክቲካዊ ሒደት ከዝቀተኛ ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ ችለዋል ማለት ይቻላል። ይህም የሚያረጋግጠው ባህል የሚባለው ነገር በአንድ አካባቢ ቢዳብርም የተሻለ ዕምርታን ሊያገኝ የሚችለው ከሌሎች ባህሎች ጋር ሲቀላቀል ወይም ሲዋሃድ ብቻ ነው። አንድም ማኅበረሰብ ውስጣዊ ኃይል ሊያገኝ የሚችለው በዚህ ዓይነት ሒደትና ውህደት ብቻ ነው።
በተለይም ዛሬ አዲስ አበባ በመባል የሚታወቀውና በአፄ ምኒልክ የተቆረቆረው ከተማ ቀደም ብሎ በሸዋ ነገሥታት እንደተመሠረተና በአካባቢው ብዙ ቤተ ክርስቲያናትም እንደነበሩ ይታወቃል። አንዳንድ የሸዋ ነገሥታት የዕደ ጥበብ አዋቂዎችን በመሰብሰብ ሥራቸውን እንዲያሻሽሉ ይገፋፉ እንደነበር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በዚህ ጊዜ ነው “ግራኝ አህመድ” የሚባለው ጦርነት በማወጅ እስከተሸነፈበትና እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ሥልጣኔውን እንዳለ ያወደመውና ብዙ ቤተ ክርስቲያናትን ያቃጠለው። የፊውዳሉ አገዛዝ መደምሰስና የሥልጣኔው መፈራረስ ኦሮሞ ለሚባለው ብሔረሰብ መንገድ በመክፈት የተቀሩት ሥልጣኔዎች ሊወድሙ ችለዋል። ዛሬ ኦሮሞ በመባል የሚታወቀው ጎሳ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ሲስፋፋ ሥልጣኔ ይዞ የመጣ አልነበረም። የዕደ ጥበብ ልምድና ሙያ፣ እንዲሁም ከንግድ ልውውጥና ከከተማ ግንባታ ጋር የሚገናኝ ባህል ያልነበረው ስለነበር በሳይንሱና በፍልስፍና አገላለጽ እንደማኅበረሰብ የሚኖር አልነበረም። የሥራ ክፍፍልም ስለማያውቅ እንደ አገርና እንደ ኅብረ ብሔር የሚቆጠር ባህርይ አልነበረውም። ከዚህ ስነነሳና የዓለም ታሪክም ሆነ በተለይም የአውሮፓው የኅብረተሰብ አገነባብ ታሪክ እንደሚያረጋግጠው አንድ ሕዝብ እንደ ማኅበረሰብና እንደ ኅብረተሰብ ለመጠራት ብዙ ነገሮችን ማሟላት አለበት። እነዚህም የሠለጠነ ቢሮክራሲያዊ ኃይልና ሰፋ ያለ ተቋማትና ሌሎች በቴክኖሎጂ የሚገለጹ የአደረጃጀትና የአመራረት ሥልቶች አንድን ሕዝብ እንደ ማኅበረሰብና እንደ ኅብረተሰብ ሊያስጠሩት ይችላሉ። በተጨማሪም በሥነ ጽሑፍ፣ በሙዚቃና በሙዚቃ መሣሪያዎች አሠራርና አጠቃቀም የዳበረና ተሰባስቦ የሚገኝ ሕዝብ ማኅበራዊና ኅብረተሰብዓዊ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ከዚህች አጭር ሐተታ ስንነሳ ጥቂቱና አክራሪው የኦሮሞ ኤሊት የሚያወራው ያልነበረን ነገርና በኢምፔሪካል ደረጃም ሊረጋገጥ የማይችልን ነገር ነው። በሌላ ወገን ግን እንደዚህ ተብሎ ሲጻፍ አንደኛውን ከፍ፣ ሌላውን ደግሞ ዝቅ አድርጎ ለማየት አይደለም። ያም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ አንዳንድ ጎሳዎች በማደግና የሥራ ክፍፍልን በማዳበር ቀስ በቀስ ወደ ማኅበረሰብ ለመለወጥ ሲችሉ፣ ሌሎች ደግሞ በተለያየ ምክንያት የተነሳ አይባለው ቦታ ረግተው ይቀራሉ፣ ወይም ደግሞ ሻል ያለ የቴክኖሎጂ ዕድገት ባለው ማኅበረሰብ ይዋጣሉ። ያም ተባለ ይህ ሥልጣኔ የኋላ ኋላ ዕምርታን ሊያገኝ የሚችለው የተለያዩ ሕዝቦች ወይም ጎሳዎች ሲቀላቀሉና የየራሳቸውን ልምድ ሲያዋህዱ ወይም ሲያገናኙ ብቻ ነው።
ለማንኛውም ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነትና ከዚያ በኋላ ነው በአፄ ምኒልክ አማካይነት ወደ ኅብረ ብሔር ልትሸጋገር የቻለችው። እንደ ባቡር ሐዲድ የመሳሰሉት፣ የገንዘብ እተማና የማዕከላዊ ባንክ መቋቋም፣ ፖስታ ቤት መክፈትና ቴምብር ማተም፣ ትምህርት ቤት መክፈትና ሌሎችም ለዘመናዊነትና ለኅብረ ብሔር ምሥረታና ግንባታ የሚያገለግሉ ነገሮች በሙሉ በአፄ ምኒልክና በአገዛዛቸው ነው የተቋቋሙት። ውስን በሆነ መልክም የውኃ ቧንቧ የተተከለው በአፄ ምኒልክ አገዛዝ ዘመን ነው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ አፄ ምኒልክ ከአፄ ቴዎድሮስ ቀጥሎ የተገለጸላቸው ንጉሥ (Enlightend Monarchy) ናቸው ማለት ይቻላል። ይህ አጠራር በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ ውስጥ የተለመደ አነጋገር ነበር። ለማለት የተፈለገውም ኋላ ቀር ከሆነ ሥርዓት መላቀቅና ብርሃንን ማየት ማለት ሲሆን፣ በዚህ አማካይነት ነው የኋላ ኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ግለሰብዓዊ ነፃነት ሊገኝና የፈጠራ ሥራም ሊዳብር የቻለው።
ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ በጊዜው የአፄ ምኒልክ ማኅበራዊ መሠረት ወይም የተገለጸለት ኃይል (Social Forces) በጣም ውስን ስለነበር በመጀመሪያው ወቅት የተደረገውን የዘመናዊነት እንቅስቃሴ በአገር ደረጃ ማስፋፋት አልተቻለም። በየክፍለ አገሩም ዘመናዊ ቢሮክራሲ ማቋቋምና ከተማዎችን መገንባት በፍጹም አልተቻለም። ስለሆነም በጊዜው በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ የተፈጠረው ኅብረተሰብዓዊ ቅራኔ፣ ማለትም ውስን ዘመናዊነትና የፊውዳሉ አገዛዝ እዚያው በዚያው ጎን ለጎን መኖር የአፄ ምኒልክ የፈጠሩት ችግር ሳይሆን በጊዜው የነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ የፈጠረው ነገር ማለት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር የኢምፔሪያሊዝም ማደግና መስፋፋት፣ እንዲሁም የሦስተኛው ዓለም አገሮችን የጥሬ ሀብት ለመቀራመት መራወጥ ለጠንካራ ኢኮኖሚ ግንባታና ለኅብረ ብሔር ምሥረታ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በተጨማሪም ዕውቀት የሚባለው ነገር ከውጭ እንዳለ የሚገባ ስለነበር ትክክለኛውን ከተሳሳተው ለመለየት የሚችል ኃይል ስላልነበር ኢምፔሪያሊዝም እንደኛ ያለውን ሕዝብ በቀላሉ ሊያታልል የሚችልበት ሁኔታ ነበር። በሌላ አነጋገር በጊዜው እንደ ጃፓኑ የሜጂ አገዛዝ ዓይነትና የተሻለ ማኅበራዊ መሠረት ያለው በአገራችን ምድር ቢኖር ኖሮ የኢትዮጵያ ዕድገት ምናልባት የተሻለና የተስተካከለ ሊሆን ይችል ነበር። ለማንኛውም አፄ ምኒልክ የነበሩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ስንመለከትና ከሥራቸው የተሰለፈውን ኃይል በምንመረምርበት ጊዜ እሳቸውን እንደ ጭራቅ አድርጎ ማየቱ በጊዜው የነበረውን አስቸጋሪ የኅብረተሰብ አወቃቀር በሚገባ አለማጤን ብቻ ሳይሆን፣ የራስንም ታሪክ በሚገባ መገንዘብ አለመቻል ነው። እንዲያውም የአፄ ምኒልክ አገዛዝ መስፋፋትና አገራችንም በአንድ አገዛዝ ሥር መጠቃለሏ በዝቅተኛ የአኗኗር ሥልት ይኖሩ የነበሩ ጎሳዎችን ከክልላቸው ወጥተው እንዲንቀሳቀሱና ብርሃንን እንዲያዩ አስችሏቸዋል ማለት ይቻላል። ስለዚህም አፄ ምኒልክን መወንጀሉ አላግባብና በታሪክም ዘንድ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። በተለይም የትግራይና የኦሮሞ ኤሊቶች እጅግ ኋላ ቀር በሆነ አመለካከት የሚያስተጋቡት ኢታሪካዊና ኢሳይንሳዊ አነጋገርና አጻጻፍ አንድ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ለሁሉም ሕዝብ የሚጠቅም ማኅበረሰብ እንዳንገነባ እንቅፋት እየሆነን መጥቷል ብል ማጋነን አይሆንም። አንዳንዶች በቅናትና በዝቅተኛ ስሜት እየተነሱ የሚያካሄዱት ዘመቻ ለሳይንሳዊ ክርክር በሩን እየዘጋ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ ላለን ችግር መፍትሄም እንዳንፈላልግ መንገዱን ሁሉ ዘግቷል። ለማንኛውም ይኼንን ትተን ወደ ኋላ ላይ ስንመጣ ለዛሬው መመሰቃቀላችንና ብሔራዊ ባህርይ አለመያዝ አዲስና አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው fekadubekele@gmx.de ማግኘት ይቻላል፡፡