Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክቅጥአምባሩ የጠፋበትን የመታወቂያ አሠራርና ሕግ ወደ ዲጂታል የማዞር አስፈላጊነት

  ቅጥአምባሩ የጠፋበትን የመታወቂያ አሠራርና ሕግ ወደ ዲጂታል የማዞር አስፈላጊነት

  ቀን:

  በውብሸት ሙላት

  ከወራት በፊት የአንድ ብሔር ተወላጅ ብቻ ለሆኑ ሰዎች አንዳንድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ያሉ ክፍለ ከተሞች መታወቂያ እየሰጡ በሚል ሕዝባዊ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ ለአጀንዳነቱ መነሻ የሆኑት መታወቂያ ማውጣት ሊያስገኝ የሚችለውን ወይም ሊስከትል የሚችለውን ለውጥ ከግምት በማስገባት ነው፡፡ ይኼ የመታወቂያ አስተዳደር ሥርዓቱ ወጥ ቢሆን (ለምሳሌ ብሔራዊ መታወቂያ)፣ አንድ ሰው በተደራራቢነት ሊያገኛቸው የሚችሉ ዕድሎችን ማስቀረት የሚችል ቢሆን ከላይ እንደተገለጸው ዓይነት አጀንዳ የመነሳት አጋጣሚው ዝቅ ይላል፡፡ የመታወቂያ ሥርዓታችን የአንድ የመታወቂያ ካርድ (Identity Card) መኖር ሊያስገኘው የሚታሰበውን አገልግሎት ማበርከት የሚችል አይደለም፡፡

  በዚህ ችግር ውስጥ እያለን፣ ዓይናችን እያየ የዲጂታሉ ዓለም ለውጥ ጥሎን እየከነፈ ነው፡፡ እንደ አገር ማግኘት ያለብንን ጥቅም ወይም ድርሻ እያገኘን አይደለም፡፡ የዲጂታሉ ዓለም በተለይም በመሠረታዊነት ድንበር አልባ፣ አንድ ከተማ ዓይነት ቢሆንም፣ በዚያ ውስጥ ያለን ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ ሌሎች አገልግሎቶችም በአግባቡ እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡ ለምርጫ አልተጠቀምንበትም፡፡ ለመንግሥታዊ አገልግሎት እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡

  በቂ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ የለንም፡፡ የኢንተርኔት ፍጥነትና ጥራቱም ዝቅተኛ ነው፡፡ ባለው መጠን ለመጠቀም እንኳን የሚያስችሉ እንደ ዲጂታል ገንዘብ፣ መታወቂያ፣ ፊርማ ወዘተ የሉንም፡፡

  የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በኢትዮጵያ ያለውን የመታወቂያ ሁኔታ መዳሰስና በተለይም የዲጂታል መታወቂያን አስፈላጊነት ማጠየቅ ነው፡፡

  ቅጥአማባሩ የጠፋበት የመታወቂያ ሁኔታ

  በፍትሐ ብሔር ሕጉ መሠረት ሰው በስምና በአካባቢው ተለይቶ እንዲታወቅ የተቀመጡ አንቀጾች አሉ፡፡ የተጸውኦ (First Name)፣ የአባት (Patronymic) እና የቤተሰብ ስም (Family Name) በሕግ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ የቤተሰብ ስም የሚለው ለኢትዮጵያ እንግዳ ነገር ስለሆነም ይመስላል ለተግባራዊነቱ የተጀመረ ሙከራ አልነበረም፡፡ በ1952 .. በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ተጽፎ በ2004 .. በአዋጅ ቁጥር 760/2004 አማካይነት ከሃምሳ ሁለት ዓመታት ከንቱ ቆይታ በኋላ ተሽሯል፡፡ ስለሆነም ስም ሲባል የግል፣ የአባት  እና የአባት አባት (አያት) በዚሁ ቅደም ተከተል እንደያዘ ቀጥሏል፡፡

  በሕግ ልማድን ማስገበር ሳይቻል ቀርቶ ልማዱ ሕጉን አስገድዶታል፡፡ አንድ ሰው ከሌላው ከሚለይባቸው መገለጫዎች አንደኛው በስሙ አማካይነት መሆኑ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡

  ሁለተኛው የሰው መለያ፣ በፍትሐ ብሔር ሕጉም ላይ የተገለጸው፣ መኖሪያ ቦታ (Residence) እና በመደበኛ ቦታ (Domicile) ናቸው፡፡ የመኖሪያ ቦታም ይሁን መደበኛ ቦታ፣ አገሪቱን የአስተዳደር አወቃቀር ተከትሎ በዚያው አንፃር የሚገለጽ ነው፡፡ ጎጥ፣ ቀበሌ (ገንዳ)፣ ወረዳ፣  አውራጃ፣ ክፍለ አገር፣ ጠቅላይ ግዛት፣ ክልል ወዘተ የመሳሰሉትን እንደ ዘመኑ ሁኔታ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በጥቅሉም በተለምዶ አድራሻ ተብለው ይተወቃሉ፡፡

  በመሆኑም፣ አንድን ሰው ከሌላ ሰው ለመለየት ጥቅም ላይ የሚውሉ መግለጫዎች ስለሆኑ የማንነት መለያ ወይም መታወቂያ ላይ እንደሚሰፍሩ ይተወቃል፡፡ በኢትዮጵያ፣ ዝርዝርና ባለማወላዳት ግልጽ የሆነ የመታወቂያ ሕግ ሳይኖር በተግባር ግን በቀበሌ ደረጃ መሰጠቱ እንደቀጠለ ነው፡፡

  በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ16 ሺሕ በላይ ቀበሌዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ቀበሌዎች ደረጃ ነው አንድን ሰው ማን እንደሆነ የሚለይበት መታወቂያ የሚሰጡት፡፡ በቀበሌ ደረጃ የሚሰጡት መታወቂያዎችን በሚመለከት መረጃዎቹ ተጠቃለው በአንድ ቋት አይገኙም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ መታወቂያዎቹ ፀንተው የሚቆዩበት የአገልግሎት ዘመናቸው ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በመታወቂያው ላይ የሚካተቱት መግለጫዎችም እንዲሁ የተወሰነ ልዩነት አላቸው፡፡ የመታወቂያ ወረቀት መልኩም ሆነ መጠኑ ልዩነት ይስተዋልበታል፡፡ በአጭሩ ወጥነት ይጎድላቸዋል፡፡

   የቀበሌ መታወቂያዎቹ እንዳሉ ሆነው፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲባል የሚሰጡ ሌሎች የመታወቂያ ዓይነቶችም አሉ፡፡ የመንጃ ፈቃድ፣ የማኅበራዊ ዋስትና (የጡረታ)፣ የመሥሪያ ቤት፣ የግብር መክፈያ መለያ ቁጥርና ሌሎችም መታወቂያዎች አሉ፡፡ ይዘታቸውን የሚወስኑት አገልግሎቱን የሚሰጡት ድርጅቶች ናቸው፡፡

  የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ (ሰኔ፣ 2009 ..) ይፋ የሆነው ‹‹መታወቂያ ለልማት›› (Identification for Development) በሚለው መርሃ ግብሩ በሚል የዓለም ባንክ ስለኢትዮጵያ የመታወቂያ ሁኔታ ያሠራው ጥናትም (Country Diagnostic: Ethiopia) የሚያረጋግጥው ይኼንኑ ቅጥአምባሩ የጠፋበትን የመታወቂያ አሠራር ሁኔታ ነው፡፡ አንድ ሰው ከተለያዩ ቀበሌዎች ከአንድ በላይ የቀበሌ መታወቂያ ሊኖረው ይችላል፡፡ አሁን ያለው የመታወቂያ አስተዳደር ለፎርጂድ አሠራር የተጋለጠም የተመቸም ነው፡፡

  በትክክል የአንድ ሰው ማንነት (መለያ) በማረጋገጥ ረገድም አስተማማኝ ሊባል የሚችል ሰነድም ነው ማለት ይቸግራል፡፡ አንድን ሰው ስሙን፣ አድራሻውን፣ የወላጆቹ ስም፣ ብሔሩን፣ የተወለደበትን ጊዜና ቦታ መግለጽን እንጂ ከሌላ ሰው የሚለይበትን ሥርዓት ለመዘርጋት የታሰበ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ አለ ብንል መቶ ሚሊዮኑም የሚለዩበትን የራሳቸው መታወቂያ የሚሰጥ ሥርዓት አይደለም አሁን አገልግሎት ላይ ያለው የመታወቂያ ሥርዓት፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ነበር አዋጅ ቁጥር 760/2004 ‹‹የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ›› ሁኔታ የሚወስን አዋጅ የወጣው፡፡

  ብሔራዊ መታወቂያ

  የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው በቀበሌ የሚሰጠውን መታወቂያ የመቀየር ዕቅድ ከተወጠነ አሥር ዓመት ሆነው፡፡ ከ16 ሺሕ ቀበሌዎች በላይ የሚተዳደረውን የመታወቂያ አሰጣጥ፣ ወጥና በተማከለ አሠራር በመተካት ብሔራዊ መታወቂያ እንዲኖር በቀድሞው የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በመረጃ ግንኙነት ደኅንነት ኤጀንሲ (INSA) አማካይነት የተለያዩ ተግባራት መከናወን ጀምረው ነበር፡፡ ለጣት አሻራ መውሰጃ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ለመግዛትም ጭምር ጨረታ ወጥቶ በዓለም ባንክ ድረ ገጽ ላይ ታትሞ ነበር፡፡

   እንደውም፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ እስከ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ያለውን ኗሪ በሁለት ዓመት፣ ቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ከአራት እስከ አምስት ዓመት ውስጥ ብሔራዊ መታወቂያ እንዲኖረው የማደረግ ዕቅድም ወጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ዕቅድ መሠረት እስከ 2009 .. ድረስ የብሔራዊ መታወቂያ መስጠት ዕቅዱ ይከናወን ነበር፡፡ ከዚያ፣ ዕድሜያቸው ለመታወቂያ ለደረሱ ሰዎች መስጠት፣ ያለውን መታወቂያ ማስተዳደርና የመሳሰሉትን ተግባራት ማከናወን ነበር በቋሚነት የሚቀጥለው ሥራ፡፡ ያው ይኼም ታቅዶ የቀረ ፕሮጀክት ነው፡፡ 

  የብሔራዊ መታወቂያን ለማስተዳደር የወጣው አዋጅ ግን ከላይ ስማቸው እንደተገለጹት ተቋማት ዕቅድ በፈጠነ ሁኔታ እንዲከናወን የሚፈቅድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለማከናወንም ብሔራዊ መታወቂያ ለመስጠትም የሚቋቋሙት ሁለት መሥሪያ ቤቶች ሥራ እንዲጀመር በአዋጁ ላይ የተገለጸው ሐምሌ 1 ቀን  2008 .. ነው፡፡  እስከዚያው ድረስ ግን እንደቀድሞው የቀበሌ አስተዳደርና ሌሎች መሥሪያ ቤቶች መታወቂያ እየሰጡ፣ ወሳኝ ኩነቶችን እየመዘገቡ እንዲቀጥሉ በአዋጅ ቁጥር 760/2004፣ አንቀጽ 67 ላይ ተገልጿል፡፡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ፣ አንድ ዓመት ዘግይቶ በ2009 .. ሥራ ጀምሯል፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ የሚሰጥ ድርጅትን የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲያቋቁም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 55 ላይ ኃላፊነት ጥሎበታል፣ የተጣለበትን ባይወጣም ቅሉ፡፡

  ሁለቱም ተቋማት ጎን ለጎን እንዲቋቋሙ ሕግ አውጭው ቢፈልግም አስፈጻሚው አካል አንዱን ለብቻው አስቀድሞታል፡፡ እንደውም፣ መቅደም የነበረበት የሚመስለው ብሔራዊ መታወቂያ የሚሰጠው ተቋም ነበር፡፡ ምክንያቱም፣ ብሔራዊ መለያ ቁጥርን የወሳኝ ኩነት ሰነዶች ላይ ማካተት በሌሎች አገሮችም የተለመደ አሠራር በመሆኑ፣ እንዲሁም የአንድ ሰው የዕድሜ ልክ መለያ ቁጥር በመሆን ስለሚያገለግል በርካታ ፋይዳዎች ይኖሩታል፡፡

  ብሔራዊ መታወቂያ ማውጣት የማንኛውም ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው ግዴታ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ለአካለ መጠን ላልደረሰ ሰው በቤተሰቡ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ብቻ ይሆናል፡፡ መታወቂያ ለማውጣት ከመዝገብ የሚገቡ መረጃዎች አሉ፡፡ ከመዝገብ ቢገቡም መታወቂያ ላይ ግን የማይሠፍሩ ደግሞ አሉ፡፡ በአስገዳጅነት ከመዝገብ የሚገቡት፣ ትክክለኝነታቸውም መረጋገጥ ያለባቸው፣ ትክክል ሳይሆኑ ቢቀሩ በወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡ እነዚህም ስም ከእነ አያት፣ ልዩ ምልክት ካለ ይኼንኑ፣ ወላጆች ስምና ዜግነት፣ የትውልድ ቀንና ቦታ፣ ጾታና የጋብቻ ሁኔታ፣ መደበኛ ቦታና ሥራ፣ብሔርና ሃይማኖት፣ ፎቶግራፍና የጣት አሻራ እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ተቋማት የሚወስኗቸው መረጃዎችም ሊጨመሩ ይችላሉ፡፡

  መታወቂያ ላይ የሚወጣው ሙሉ ስም ከእነ አያት፣ ጾታ፣ የትውልድ ቀንና ቦታ፣ መደበኛ የመኖሪያ ቦታ፣ የጣት አሻራ፣ ፊርማ፣ ብሔራዊ የመለያ ቁጥርና የመታወቂያ ካርድ ቁጥር እንዲሁም መታወቂያው የተሰጠበት ቀንና አገልግሎቱ የሚያበቃበት ቀን ናቸው፡፡

  ለአንድ ሰው የሚሰጠው ብሔራዊ መለያ ቁጥር አንድ ብቻ ሆኖ ከሌላ ሰው ቁጥር የተለየ መሆን አለበት፡፡ ባለመታወቂያው ሁልጊዜ የመያዝ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ለብሔራዊ መታወቂያ ሰዎችን መመዝገብ፣ መረጃዎቹን ማጣራትና ማረጋገጥ፣ መታወቂያ መስጠት፣ መታወቂያ ማደስ፣ ሲጠፋ ወይም ሲበላሽ የሚተካበት ሁኔታ፣ መታወቂ የሚሰረዝበት ምክንያቶች ወዘተ በአዋጁ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የአንድ መታወቂያ ‹‹የሕይወት ዑደት››  መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ወሳኝ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ይኼውም ብሔራዊ መታወቂያ የሚል ስያሜ የተሰጠው የዲጂታል መታወቂያን ይጨምራል ወይ? የሚል ነው፡፡

  ዲጂታል መታወቂያ

  መታወቂያ አንድን ሰው ማነህ ሲባል እኔ ነኝ በማለት የሚናገረውን ማረጋገጫ ሥርዓት ነው፡፡ አንድ ሰው በገሃዱ ዓለም የራሱን ማንነት የሚያስረዳበት፣ ሌላውም የሚተማመንበት አሠራር እንደሚያስፈለገው ሁሉ በዲጂታሉ ዓለምም አንድ ሰው ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወይም ከማሽን ጋር በሚኖረው ግንኙነት ለማንነቱ ማሳወቂያም መተማመኛም ማስፈለግ ከጀመረው ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ እየሆነው ነው፡፡ በዲጂታሉ ዓለም መንግሥት ለዜጎቹ አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡

  በዚህም፣ የተቀላጠፈ፣ እንግልትን የቀነሰ፣ ጊዜና ወጪን የቆጠበ አገልግሎት ለማዳረስ ዓይነተኛ መድረክ መሆኑን ቀጥሎበታል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የንግድ ተቋማትም አገልግሎታቸውንና ግብይታቸውን ዲጂታል ማድረጋቸውን ወይም በአማራጭ ማቅረባቸውን አጧጡፈውታል፡፡ የሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም በአካል ከሚደረገው ወደ ዲጂታሉ በመፍለስ ላይ ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይገደብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም የገቢ ምንጭነቱም ከሌላው ዘርፍ ይበልጥ እያስከነዳ ይገኛል፡፡

  በዚህ ዘርፍ በሚደረገው የግብይት ሥርዓት ብሎም ኢኮኖሚያዊ ድርሻ በተሻለ ሁኔታ ተቋዳሽ ለመሆን በዲጂታል ዓለም ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች አስተማማኝነት ያለው ሥርዓት አንዱ ሌላውን የሚያምንበት፣ እንደ ቃሉ ባይገኝ የሚጠየቅበት አሠራር እንዲኖር ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አልፎም በፖለቲካው መስክም ምርጫ ለማከናወን በብዙ አገሮች ዜጎች በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ድምፅ መስጠት ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡

  እነዚህንና ሌሎች ትካሮችን ለመከወን ወሳኝ ሚና ካላቸው አሠራር አንዱ ዲጂታል መታወቂያ ነው፡፡ በዲጂታል ዓለም ውስጥ ግንኙነት የሚያደርገው ሮቦት ይሁን ሰው፣ ውሻ ይሁን ድርጅት፣ ወዘተ መለየት የሚያስችል አሠራር ያስፈልጋል፡፡ ዋነኛው ደግሞ ኤሌክትሮኒክ ወይም ዲጂታል መታወቂያ ነው፡፡

  ዲጂታል መታወቂያን በሚመለከት ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሕብረት ጨምሮ በርካታ ተቋማት ለአብነት የሚሆኑ መመርያዎችን አዘጋጅተዋል፡፡ በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ አገሮችም ፋይዳውን በመረዳት የዲጂታል መታወቂያን በሚመለከት ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፈው፣ ሕግ አውጥተው ወደ ተግባር ከተሸጋገሩ ሃያ ዓመት የሞላቸው አሉ፡፡ እንደ ኢስቶኒያ ያሉት አገሮች ደግሞ በአስደማሚ ብቃትና ውጤታማነት ተግባራዊ በማድረግ ለበርካታ አገሮች አርዓያ ሆነዋል፡፡ ህንድ ከአጠቃላይ ሕዝቧ 1.2 ቢሊዮን የሚሆነው ዲጂታል መታወቂያ አለው፡፡ የቀራት 100 ሚሊዮን የሚሆን ብቻ ነው፡፡ ዲጂታል መታወቂያ ከሌላው (ለምሳሌ ብሔራዊ መታወቂያ) በምን ይለያል? አገሮችስ ይኼን ያህል ለምን ትኩረት ሰጡት?

  የዲጂታል መታወቂያ ጽንሰ ሐሳብ ከሌሎች ዓይነት መታወቂያዎች የተለየ አይደለም፡፡ ሊለይ የሚችለው ከሚሰጠው አገልግሎት፣ አስተማማኝነት፣ የማረጋገጫ ሒደቱ ወዘተ አኳያ ነው፡፡ ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት ጥቅም ላይ የሚውለው ቴክኖሎጂም እንዲሁ የተለየ መሆኑ አይቀርም፡፡ ዞሮ ዞሮ፣ አንድን ሰው አንድና ከዚያ በላይ የሆኑ መለያዎችን በመጠቀም ከሌላ ሰው ነጥሎ የሚወክል ብሎም መለየት እንዲቻል ለማድረግ ሲባል ጥቅም ላይ የሚውል አሠራር ነው፡፡

  ዲጂታል’ የሚያሰኘው እንደማንኛውም የኮምፒውተር ፕሮግራም ወይም መግቢያ መረጃዎችን ወደ ቁጥር በመቀየር የሚከናወን በመሆኑ ነው፡፡ በዲጂታል መታወቂያ ሰው የሚወከለው በአኃዝ (በዲጂት) ነው፡፡ በዚያው በዲጂታል ዓለም ውስጥና ዲጂታል መረጃዎችን በመጠቀም አገልግሎት በሚሰጡ ቁሳቁሶች አማካይነት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

  ለዲጂታል መታወቂያ በግብዓትነት ጥቅም ላይ በመዋል የተዘወተሩት ከልደት ጋር የተያያዙ መረጃዎች (የትውልድ ቀንና ቦታ)፣ ቁመት፣ ክብደት፣ የዓይንና የፊት ቀለምና ቅርጽ፣ ግለሰባዊ መለያዎች (ለምሳሌ የማኅበራዊ ዋስትና ቁጥር)፣ የባዮሜትሪክ መረጃዎች (ለምሳሌ አሻራ፣ ዲኤንኤ፣ የዓይን ብሌን…) ይገኙበታል፡፡

  ለመታወቂያው በግብዓትነት ከሚውሉት መረጃዎች አንፃር፣ በአገራችን ተግባራዊ እንዲሆን በሕግ ከተወሰነው ብሔራዊ መታወቂያ ጋር ቀረቤታ አለው፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ ላይ አሻራ ማስገባት አስገዳጅ መስፈርት ነው፡፡ በአካል ጉዳት ምክንያት የጣት አሻራ መስጠት የማይችል ሰውን በሚመለከት አግባብ ባለው አካል ፊት ቀርቦ ሌላ መለያ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህ መለያዎች የዓይን ብሌን (Iris)፣ የፊት ቅርጽና መልክ፣ ዲኤንኤ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዲጂታል መታወቂያ ሲሰጥ ባዮሜትሪክ መረጃን ለመጠቀም ከተወሰነ ያው ተመሳሳይ ግብዓትን (መለያን) ጥቅም ላይ አውለዋል ማለት ነው፡፡

  አንድ ሰው ለተለያዩ ዓላማዎች የሚውሉ በርካታ ዲጂታል መታወቂያዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለባንክ አገልግሎት፣ ለምርጫ፣ ለጤና፣ ለግብር አከፋፈል ወዘተ. እንዲህ ዓይነቶቹ መታወቂያዎች ደንበኞችን ብቻ ለመለየትና አገልግሎት ለመስጠት እንጂ የአንድ አገር ሕዝብን በመለያነት የሚያገለግሉ ናቸው ሊባል አይችልም፡፡ ስለሆነም፣ በዚህ ጽሑፍም ምንም እንኳን እነዚህ መታወቂያዎች በሥሪታቸው ዲጅታል ቢሆኑም አገር አቀፋዊ መታወቂያ ስላልሆኑ ዲጂታል መታወቂያ የሚባል በኢትዮጵያ የለምና እነዚህን ለማለት አይደለም፡፡ ልክ እንደ ብሔራዊ መታወቂያ ለሁሉም ሰው የሚሰጠውን ነው የሚመለከተው፡፡

  በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑትና በግሉ ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በሚመለከት የተገልጋዮችን ምቾት ያሻሽላል፡፡ በየትኛውም ጊዜ አገልግሎት መስጠትና ማግኘት ያስችላል፡፡ የተደራሽነት ወጪን ይቀንሳል፡፡ አካታችነትን ይጨምራል፡፡ የአገልግሎት መስጫ ዋጋን ያሻሽላል፡፡ ወንጀልን ለመከላከል፣ ማጭበርበርን ለመቀነስና ባለው ፋይዳ የአገር ደኅንነት ሥጋትን ለመቀነስ ይጠቅማል፡፡በግሉ ዘርፍ ውስጥ ደግሞ አዳዲስ ገቢዎችን በማስገኘት ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦው ከፍ እንዲል ያግዛል፡፡

  ዲጂታል መታወቂያን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስከትላቸው ሥጋቶችም አሉ፡፡በመጀመርያው ረድፍ ላይ የሚያርፈው የግለሰቦችን መረጃዎች ተክትሎ የሚመጣው የግላዊነትና የደኅንነት ሥጋት ነው፡፡ የዜጎች ግላዊነት እየጠበበ እንዲሁም የግል መረጃዎች በብዙዎች እጅ ሊገባ የሚችልበት አጋጣሚ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ዲጂታል መታወቂያው ዘለቄታ እንዲኖረው ከፍ ያለ ገንዘብና ሀብት መመደብ ያስፈልጋል፡፡ ቴክኖሎጂዎች ቶሎ ቶሎ ማርጀትም ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ሥጋቶችና ተግዳሮቶችን ከግምት ያስገባ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ  ነው፡፡

  በመሆኑም ዲጂታል መታወቂያን ተግባራዊ የሚደርጉ አገሮች ትኩረት ሰጥተው አጥብቀው ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆች አሉ፡፡ ከእነዚህ መርሆች መካከል ጠቅለል ጠቅለል በማድረግ በአጭር በአጭሩ ብቻ እንቃኝ፡፡ እነዚህን መርሆች በመከተል ዕውን ለማድረግ ጥረት ለማድረግ አስቀድሞ ግልጽ የሆነ የዲጂታል መታወቂያ ራዕይና ግብ መቅረጽ አስፈላጊ ነው፡፡ ጥናት በማድረግ የመታወቂያው አስፈላጊነት፣ ለምን ለምን ጉዳይ እንደሚጠቅም፣ ምን ምን አገልግሎቶችን ሊያቅፍ እንደሚችል መወሰን አስፈላጊ ነው፡፡ አስፈላጊነቱ ቁርጥ ከሆነ መርሆቹን ዕውን ለማድረግ ሕግና አሠራር መዘርጋት ግድ ይላል፡፡ ወደ መርሆቹ እንለፍ፡፡

  የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ ከኢኮኖሚያዊና ከማኅበራዊ ፋይዳው አንፃር ሁሉንም የኅብረተሰብ አካልም ሆኑ የአገልግሎት ዘርፎች በሚሸፍን መልኩ ጥቅልና አካታች (Comprehensiveness) መሆን አለበት፡፡

  ሁለተኛው መርህ ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር ወይም አለመጣሱ ነው፡፡ በተለይም የግላዊነትን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ ከሌሎች ሰዎች የሚደረግ ግንኙነት ምሥጢራዊነቱ የተጠበቀ መሆን፣ የመረጃ ደኅንነት መጠበቅ በቀላሉ ለአደጋ የሚጋለጡ፣ መንግሥትና መረጃ ዘራፊዎች እንዳሻቸው ሊጠቀሙባቸውም ይችላሉ፡፡ ስለሆነም፣ የሕዝብ ጥቅምና የግለሰብ መብትን አንዱ ሌላውን ሳይጎዳ ተግባራዊ የሚሆንበትን አሠራር ማስፈን አስቀድሞ ማቀድ ብሎም ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል፡፡

  ሥጋቶችን መቀነስና መቋቋም በሚያስችል መልኩ ለማስተዳደር የተመቸ ሥርዓት መዘርጋት ሌላው መርህ ነው፡፡ ዲጂታል መታወቂያ ጥቅም ላይ ሲውል በተጠቃሚዎችም በባለድርሻ አካላትም ሆነ በሌሎች አካላት አመኔታ የሚጣልበት መሆን አለበት፡፡ ቀጣይነት ወይም ዘለቄታዊነትም እንዲሁ ሌላው መርህ ነው፡፡ ከአገልግሎት መበራከትም ሆነ ከሕዝብ መጨመር አንፃርም እንደ ሁኔታው በመለዋወጥ መስፋትና ማደግ እንዲችል ተደርጎ ነው ተግባራዊ መደረግ ያለበት፡፡

  ሌላውና ቁልፍ የሆነው መርህ ደግሞ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችል፣ የቴክኖሎጂዎችን እርስ በርሳዊ መስማማትና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በማድረግ (Interoperability) የተጠቃሚዎችን ምቾትም አላስፈላጊ ወጭም የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል አሠራር ተፈጻሚ የሚሆንበትን ሥርዓት ማበጀት ነው፡፡

  የአንድ ሰው መታወቂያ ከሌላ ሰው የተለየ፣ ከሌላ ሰው ጋር ሳያምታታ የሚለይ መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም ጠንካራና አስተማማኝ መጻኢ ቴክኖሎጂዎችንም በማሰብ የተዘጋጀ መሆን አለበት፡፡ ሌላው፣ የመረጃ መጥራት ጋር የተገናኘ ነው፡፡

  ከላይ የተዘረዘሩት መርሆች እንዳሉ ሆነው፣ ዲጂታል መታወቂያ የሚሰጠውን ማን ይሁን በሚለውን በሚመለከት አገሮች ከሦስቱ አካሄዶች አንዱን ይመርጣሉ፡፡ አንደኛው፣ ፖሊሲና ሕግ ከማውጣት ጀምሮ መታወቂያ ማዘጋጀትና መረጃዎችን ማጣራትም ማረጋገጥንም ራሱ መንግሥት የሚሠራበት አካሄድ ነው፡፡ ህንድ፣ ታንዛኒያና ኢስቶኒያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

  ሁለተኛው፣ መንግሥት ሥርዓትና ሕግ በማውጣት ደንብ አስከባሪነት ብቻ ተወስኖ የግሉ ዘርፍ እንዲሠራው ማድረግን መምረጥ ነው፡፡ ለዚህ ካናዳ ጥሩ ምሳሌ ናት፡፡ 

  ሦስተኛው መንግሥት እንደ ደንብ አስከባሪም እንደ አገናኝ ተቋምም ሆኖ የሚሠራበት አካሄድ ነው፡፡ መንግሥት ዜጎችንና ዲጂታል መታወቂያ የሚሰጡ ድርጅቶችን ያገናኛል፣ ይወስናል፡፡

  ከሦስቱ አካሄዶች መካከል የትኛውንም መከተል ይቻላል፡፡ የሦስቱም ጠንካራና ደካማ ጎን አላቸው፡፡ ዜጎችም ሆኑ ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ የሚያወጡበትን ሁኔታ በሚመለከት በርካታ አገሮች ፈቃደኝነትን መሠረት ሲያደርጉ የተወሰኑት ደግሞ አስገዳጅ አድርገውታል፡፡ በእርግጥ በፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው በማለት አንዳንድ አገልግሎቶችን ግን ያለ ዲጂታል መታወቂያ ማግኘት እንዳይችሉ በዕቅድ ሁኔታነት በማስቀመጥ የእጅ አዙር ግዳጅን ጥቅም ላይ ያውላሉ፡፡

  ኢትዮጵያም ዲጂታል መታወቂያ ጥቅም ላይ ማዋል አማራጭ የለውም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከዚያ በፊትም እንዲሁም ጎን ለጎን መከናወን ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ የተወሰኑትን ብቻ እናንሳ፡፡ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ወደ ሥራ ለመግባት የኤሌክትሮኒክ/የዲጂታል ፊርማ አዋጅ ከወጣ ዓመት ያለፈው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሥራ ላይ አልዋለም፡፡ ለማዋልም የሚቀሩ የቤት ሥራዎች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ይህንን ሥራ ማስጀመር አንዱ ነው፡፡

  ሁለተኛው፣ ለመታወቂያ ሲባል የሚሰበሰቡ መረጃዎችን ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ዝርዝር ሕግ ካልወጣ አሁን ያለው የኮምፒውተር ወንጀል ሕግም ይሁን የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጁ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች በቂ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የመረዛ ጥበቃ አዋጅ ማውጣት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ዲጂታል ፊርማን ለመጠቀም የሚያስችል መሠረተ ልማትም ተቋማዊ መዋቅርና ሕግ ማውጣትም ሌላው ነው፡፡ በተለይ የኤሌክትሮኒክ መረጃ ልውውጥና ግንኙነት ሕግ ማውጣት ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡

  ዲጂታል መታወቂያ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ከሆነ፣ አኳኋኑ ልክ እንደ ብሔራዊ መታወቂያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ወይም/እና የሌላ አገር ዜጋ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖርን ሁሉ ስለሚመለከት ተጨማሪ ሕግ ከወጣም ማውጣት ያለበት የፌዴራሉ መንግሥት እንጂ የክልሎች ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዲጂታል መታወቂያ መስጠት እንደ ጀመረ ቢሰማም ይህም ቢሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው አካል ነው ማለት አይቻልም፡፡

  መታወቂያ የሚሰጠውን ወይም የሚቆጣጠረውን መንግሥታዊ ተቋም በሚመለከት ብሔራዊ መታወቂያ እንዲሰጥ በሕግ ቀድሞ ስለተወሰነ ሥራውም ቢሆን አንድ ዓይነት ነው ለማለት በሚቀርብ ደረጃ ተመሳሳይ ስለሆነ ያለቀ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ስንቃኝ በርካታ አገሮች ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ወይም ለፖሊስ የሚሰጡት ይበረክታሉ፡፡ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ሌላ ተቋም በማደራጀት ወይም ከላይ ከተገለጹት ውጭ ላሉ መሥሪያ ቤቶችም ይሰጣሉ፡፡

  ለማጠቃለል ያህል በኢትዮጵያ ያለው የመታወቂያ አስተዳደር ማንነትን ለማመሳከሪያነት ሊውል እንደሚችለው ሁሉ ለማሳከሪያነትም ይውላል፡፡ ከተለያዩ ተቋማትና ቀበሌዎች መታወቂያ በመውሰድ አንድ ሰው ብዙ መለያዎች እንዲኖረው የተመቸ ነው፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ እንዲኖር አዋጅ ቢወጣም አስፈጻሚው አካል ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል፡፡ ፓርላማውም ይህንን ጉዳይ የረሳው ይመስላል፡፡ እንኳን መታወቂያው መሥሪያ ቤቱም የለምና፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ፣ መረጃዎቹ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ እንዲያዙ ሕጉ ቢያዝም መታወቂያው ግን ታትሞ የሚሰጥ፣ በእጅ የሚያዝ ነው፡፡ ዲጂታል መታወቂያ ሲሰጥ ልክ እንደ ብሔራዊ መታወቂያው ታትሞ ሊሰጥ ቢችልም ተደራቢ አገልግሎት ቢኖረውም፣ በኢንተርኔትም ይሁን በሌላ ዓይነት ተመሳሳይ የግንኙነት ዘዴን በመጠቀም ማንነትን ለማረጋገጫ እንዲውል ታስቦ አይደለም ሕጉ ላይ የተቀመጠው፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ አዋጅ በማውጣት ወይም ደንብ በማዘጋጀት ብሔራዊ መታወቂያውንም ዲጂታል መታወቂያውን በአንድነት እንዲሰጥ ማደረግ ይጠበቃል፡፡ የዲጂታል መታወቂያ መኖር ጥቅሙ የትየለሌ ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...