Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርመሪዎቻችን የአገራችንን መሠረታዊ ችግሮች ካወቁ ለምን አይፈቱልንም?

  መሪዎቻችን የአገራችንን መሠረታዊ ችግሮች ካወቁ ለምን አይፈቱልንም?

  ቀን:

  የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች አንድ የሕዝብን ነፃነትና እኩልነት የሚገድብ የአምባገነን ሥርዓት፣ ሁለት ያልተመጠነ የሕዝብ መዋለድና መባዛት እንዲሁም ሦስት ዝቅተኛ ምርታማነት ናቸው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ በእርግጥ ችግሮቹን አያውቁም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አፄ ምኒሊክ ያሰባሰቡትን ግዛቶች በክፍለ አገሮች አካልለው ሲያስተደሳድሩም፣ በእነኝህ ችግሮች ላይ ግን ምንም ዓይነት መፍትሔ የጠነሰሱ አይመስለኝም፡፡ በአንፃሩ ዝና ላይ ሲያቀነቅኑ ቆይተው በ66ቱ ዓብዮት ድንገት ሳያስቡት በሕዝባዊ አመፅ ከነአጋሮቻቸው ተወገዱ፡፡

  ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የአምባገነንነት ችግሮቹ ቢያውቅም፣ ሕዝባዊ አስተዳደር ግን አልመሠረተም፡፡ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ሥልጣኑን በአግባቡ መወጣት አቅቶት ግን በአመፀኛ የኤርትራና የትግራይ ታጋዮች ተፈንግሎ ለስደት ተዳረገ፡፡ አብዛኛው የደርግ አባላትም በረጅም ጊዜ እስራት ዳሽቀዋል፡፡ እነ መለስ ዜናዊም በእውነት ዕውቀት ቢኖራቸው ኖሮ ለረጅም ጊዜ ሥር የሰደደውንና ትግራይንና ኢትዮጵያን ያቆረቆዘውን የጎበዝ አለቃ /መሳፍንታዊ/ ሥርዓት በዴሞክራሲ ይቀይሩት ነበር፡፡ በአንፃሩ ሕዝብ በየክልሉ በፉክክር እንዲባዛ አደርገዋል፡፡ የአሁኑ የቄሮ ብዛት ችግር የወያኔ አጉል አስተዳደር ውጤት ነው፡፡ በወረት .‹‹ልዩነት ውበት ነው›› በሚል ዜማ ብሔር ብሔረሰቦችን ዳንኪራ ቢያስጨፍሩም ዋና ተግባራቸው ግን ድንቁርና ላይ የተመሠረተ ቂም በቀል፣ የሕዝብ ሀብት ዝርፊያና ሕዝቦችን ከፋፍሎ መግዛት ነበር፡፡ መሠረታዊ ችግሮቻችን አሁንም እንደነበሩ አሉ፡፡ መሪዎች ግን ይቀያየራሉ፡፡

  ሕይወት ልዩ የተፈጥሮ ፀጋ ናት ይባላል፡፡ የፈለቀችው በምድር ንጥረ ነገሮችና ውህዶች ተፈጥሮአዊ ፀጋና ከፀሐይ ለረጅም ጊዜ በተከታታይ በፈለቁት ጨረሮች የኃይል /Energy/ ተፅዕኖ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በሕይወት ዘንድ ደግሞ ትልቁና ዋናው ፀጋ የሚባለው ነፃነት ነው፡፡ ነፃነት ሰው የሚፈልገውን ኑሮ ለማሳካት እንደልቡ ለመንቀሳቀስና ዘላቂነቱን ለማስረፅ ስለሚጠቅመው ነው፡፡ ሰው ማኅበረሰባዊ እንደመሆኑም እኩልነትና ነፃነት የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል፡፡ ነጮች ይህን በመረዳት በሕግ የበላይነት የዴሞክራሲ ሥርዓትን መሥርተዋል፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄደው ሌላው ዘዴያቸው የሕዝብ ብዛትን ከተፈጥሮ ሀብት ጋር አጣጥሞ  መኖር ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሰው በዚች ምድር ሲኖር ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ይፈጽማል ይባላል፡፡ ይኸውም አንድ የኑሮ ፍላጎቱን ለማሟላት ያመርታል ሁለት ዘሩን ለመተካት ይዋለዳል፡፡

  የሕዝብ ጥናቶች ውጤቶች እንደሚያሳዩት መዋለድ ፈጣን ሲሆን ማምረት ግን ዘገምተኛ ነው፡፡ ሕዝብ ሲበዛ ደግሞ ድህነት ይሰርፃል፣ የተፈጥሮ ሀብት ይባክናል፣ የእርስ በርስ ግጭትም ይከሰታል፡፡ ነጮች ይህን ችግር በመረዳት የመዋለድንና የምርታማነትን ሚዛን ጠብቆ ለመዝለቅ ‹‹ራስህን ተካ›› የሚል የመዋለድ ሥርዓት እየተከተሉ ይኖራሉ፡፡ እኛ ደግሞ የሕዝብ ብዛትን እያባባስን ዘወትር እርስ በርስ ስንተራመስ እንኖራለን፡፡ በአጉል ባህል ስለተተበተብንም እንኳን ጠቃሚ ዘዴ ለመፍጠር ለመኮረጅም እንቸገራለን፡፡ በተፈጥሮ የሕዝብ ብዛት ችግር የሚፈታው በጦርነት፣ በበሽታና በተፈጥሮአዊ አደጋ (ምሳሌ ጎርፍ) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እኛም ችግራችንን ለመፍታት ይህን ዘዴ የምንጠብቅ ይመስላል፡፡

  እኛ ኢትዮጵያኖች ሌላም ችግር አለብን፡፡ ምርታማነታችን ከዓለም አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ኑሮአችንን ከሞላ ጎደል የምናስተካክለው ከአደጉ አገሮች በምናገኘው ድጎማ ነው፡፡ ስለዕውቀታችንና ገናና ታሪካችን ግን ብዙ እናውራለን፡፡ ለመሆኑ በምርታማነት ዝቅተኛ የሆንበት ምክንያቱ ምንድነው? አንዱ ምክንያት በበሽታና ተውሳክ ስለምንጠቃ ይመስለኛል፡፡ ሥልጣኔ ስለሌለን የእግዜሩ ጥቃትን ፍጡሮች ሁሉ እየተረባረቡብን ያቆረቁዙናል፡፡ ሰው ግን ከእግዜር ያገኘው ዋና ፀጋ ዕውቀት ነው ይባላል፡፡ እኛ ይህን ፀጋ አላዳበርነውም፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ ‹‹ዓለም ከንቱ ነች›› የሚል ፍልስፍና ላይ ስለምናተኩር ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ተፈጥሮ ምስቅልቅልነት ይታይባታል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ግን ሁኔታዎችን ተረድቶ ዘላቂነት ማስረፅ ላይ ማተኮር እንጂ ‹‹ውጪ ነፍስ›› ላይ ማጠንጠን ትክክልም ጠቃሚም አይደለም፡፡

  መግቢያው ላይ በጠቀሷቸው መሠረታዊ ችግሮች ምክንያት የእርስ በርስ ግንኙነታችን ሻካራ ሆኗል፡፡ ዘረኝነት፣ ራስ ወዳድነት፣ አድሎ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ መጋጨት ወዘተ. . . እናንፀባርቃለን፡፡ ታጋይ መለስ ዜናዊ ያለ የሌለውን ጉልበት ያዋለው ቂም በቀል ላይ ነበር፡፡ የሆነ ግላዊ ቁርሾ የነበረው ይመስላል፡፡ እነበቀለ ገርባ ዘረኝነት ያቀነቅናሉ፡፡ እነርሱም የሆነ ቂም ስለሚመዘምዛቸው ይመስለኛል፡፡ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ግዛት ሲያስፋፉ ዜጎችን እየሳሙና እየሸለሙ ብቻ አልነበረም፡፡ አንዳንዴ እየጎዱና እያስገደዱ ጭምር ነበር፡፡ ዓድዋ ጦርነት ላይ ግን ቅኝ ገዥዋን ጣሊያንን እንድንደቁሳትና በኢትዮጵያዊነት ጀግንነታችን እንድንኮራ በቆራጥነት ስለመሩን እኛም በእሳቸው እንኮራለን፡፡ ቪቫ ምኒልክ እንነሳለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት በእኩልነትና በነፃነት ሥርዓት ከሰመረ ደግሞ ለበለጠ ስኬት እንደሚያበቃን እንተማመናለን፡፡

  እኔም በግሌ ቁርሾ አለኝ፡፡ ወቅቱ አሁን ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት እምንሸጋገርበት ነው፡፡ አንዳንድ ባለሥልጣኖች ግን አሁንም ድረስ ኃላፊነታቸውን የሚወጡት የግል ጥቅማቸውን ለማካበት ነው ይባላል፡፡ ይህን ዝንባሌ በምሳሌ ለመጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን እኔ በምኖርበት ሠፈር በግል ከተገነቡ መኖሪያ ቤቶችና ሽንት ቤቶች ሰገራ በመሰብሰብ ባዮ ጋዝ ለማምረት የተቀናጀ እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡ በድርጊቱ እኛ እንደምንጎዳ እያወቁ ከእኛ ከነዋሪዎች ጋር ምንም ውይይት ሳያደርጉ፣ ስምምነታችንንም ሳያገኙ በግል ሀብታችን የሠራነውን ግንባታ ያፈርሱብናል፡፡ የሥራው ዋና ዓላማ በእርግጥ ባዮ ጋዝ ማምረት ከሆነ፣

  1. በከተማው አንዳንድ ዳርቻ የተከማቸውን ሰገራ ለምን በቅድሚያ አይጠቀሙበትም?

  2. እኛ ከ10 እስከ 18 ዓመት በፊት የገነባነውን ግንባታ ከማፍረደስና ለጉዳት ከሚያጋልጡን ለምን ከየሽንት ቤቱ እያስመጠጡ አይጠቀሙም?

  3. ባዮ ጋዝ ማምረቱ ዘላቂነት እንዲኖረው በአሮጌ ሳይሆን በአዲስ ሠፈር ቢሆን አይጠቅምምን? በአሮጌ ቤቶች የተዘረጉት ቱቦዎች በቀላሉ ስለሚሰበሩ ጉዳት አያመጡብንምን?

  4. የፈረሰውን የኮብል ስቶን መንገድ ሽንት ቤትና ግቢ መልሶ ለማስተካከል ወይም ለመገንባት ወጪውን የሚሸፍነውስ ማነው?

  5. ተመሳሳይ ሥራ ቀደም ብሎ በተፈጸመበት አንዳንድ አካባቢ በሰገራ የተሞሉ ቦታዎች እየፈነዱ አካባቢውን በመጥፎ ሽታ ይበክላሉ ይባላል፡፡ ወረርሽኝ በሽታም ሊያስከትል ይችል ይሆናል፡፡ ችግሩ እየታወቀ በነባር ቤቶች ዙሪያ ሥራው ለምን ይቀጥላል? ድርጊቱ ‹‹በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት›› አይሆንምን? ዴሞክራሲ እየተጠነሰሰባት ነው በተባለች አገራችን ችግሩ በመከሰቱ ያሳዝናል፣ ተስፋም ያስቆርጣል፡፡

  (ፍቅሩ አማረ፣ ከአዲስ አበባ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...