Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ከዓመታት በፊት ከኢንተርኔት የዓለም ወሬዎችን ስቃርም ድንገት ዓይኔ አንድ አስገራሚ ዜና ላይ አረፈ፡፡ ዜናውን ይዞት የወጣው ‹‹ዘ ጄሩሳሌም ፖስት›› የተባለ የእስራኤል ጋዜጣ ሲሆን፣ ምንጭ ያደረገው ናይሮቢ ውስጥ የሚታተመውን ‹‹ናይሮቢያን›› የተባለ ጋዜጣ ነበር፡፡ ይህ አስገራሚ ዜና፣ ‹‹ኬንያዊው ጠበቃ በኢየሱስ ክርስቶስ ግድያ የእስራኤል መንግሥትንና አይሁዳውያንን ዘ ሔግ ችሎት ከሰሱ›› ይላል፡፡ ይህ ርዕስ ሲታይ ለጊዜው ግራ መጋባት ቢፈጥርም፣ ጠበቃው ሚስተር ዶላ ኢንዲዲስ መቀመጫውን በሔግ ያደረገው ዓለም አቀፍ የፍትሕ ችሎት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሕገወጥ ፍርድ በማስተላለፍ ስቅላት የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሊዳኙ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

  ጠበቃው እንደሚሉት የእስራኤል መንግሥት የበለጠውን የኃላፊነት ድርሻ ሲወስድ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ42 እስከ ከክርስቶስ ልደት በኋላ 37 ድረስ የነበረው የሮማ ንጉሥ ታይቤሪየስ፣ ጲላጦስ፣ የተወሰኑ የአይሁድ ሽማግሌዎች፣ ንጉሥ ሔሮድስ፣ የጣሊያን መንግሥትና የእስራኤል መንግሥት ተጠያቂ ናቸው፡፡

  እንደ ዘገባው ከሆነ፣ ጠበቃው እነዚህ የተጠቀሱት ተከሳሾች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በፈጸሙት ሕገወጥ ፍርድና ስቅላት በቂ ማስረጃ ይጠቀስባቸዋል፡፡ ‹‹ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ማስረጃ አለ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ማስረጃ ደግሞ ማንም ሊያጣጥለው አይችልም፤›› በማለት ጠበቃው ለጋዜጣው ተናግረዋል፡፡ ጠበቃው ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ለተፈጸመው ድርጊት ተጠያቂ የነበሩ ሰዎች በሕይወት ባይኖሩም፣ እነሱ ይወክሉዋቸው የነበሩ መንግሥታት ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡

  ጠበቃው የኢየሱስ ክርስቶስ ክስ፣ ችሎት፣ ክርክርና ውሳኔ ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ የተፈጸመበት ድብደባ፣ ማሰቃየትና ስቅላት ወንጀል ነው ብለው ነበር፡፡ እሳቸውም ይህንን ጉዳይ ከመረመሩ በኋላ የተጠቀሱት ወገኖችን የሚከሱት በዚያን ዘመን ስላልተፈጠሩ መሆኑን ገልጸው፣ ዛሬ ግን እንደ አንድ የኢየሱስ ወዳጅ ክስ መመሥረታቸውን ተናግረዋል፡፡ ክሳቸው በናይሮቢ ፍርድ ቤት ውድቅ ቢደረግባቸውም እሳቸው ግን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለመሄድ መገደዳቸውን ተናግረው ነበር፡፡ በወቅቱ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱም ይህንን ጉዳይ የማየት ሥልጣን እንደሌለው መግለጹን ከዘገባው ተረድቻለሁ፡፡

  ብዙዎች በጠበቃው ድርጊት ተገርመዋል፣ ግራ ተጋብተዋል፣ አሹፈዋል፡፡ ዘመናችን በርካታ የሚያስገርሙና የሚያስደነግጡ ጉዳዮች የሚከሰቱበት ቢሆንም፣ በበኩሌ የጠበቃውን ምልከታ አከብራለሁ፡፡ አንድ ሰው የመሰለውን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ሲያቀርብ የመቀበልና ያለመቀበል መብቱ የእኛ ሲሆን፣ ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ሐሳባቸውን በማቅረባቸው ምክንያት ሊወገዙ አይገባም፡፡ የሆኖ ሆኖ የጠበቃው ሐሳብ ያስኬዳል ወይም አያስኬድም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሕገወጥነትን በሕጋዊ መንገድ አደብ ለማስገዛት የሚነሱ ሰዎች ሲኖሩ አስደሳች ነው እላለሁ፡፡

  እስኪ ዙሪያችንን እንመልከት፡፡ ኃይለኞችና ጉልበተኞች ሕግ ባለበት አገር ውስጥ እንዳሻቸው እየፈነጩ የማፊያ ተግባር ሲፈጽሙ ‹‹ጎመን በጤና›› እየተባለ ይታለፍ የለም ወይ? በሀብቱ የሚመካ ሕገወጥ በሙስና ከተለወሱ ባለሥልጣናት ጋር ሰምና ወርቅ ሆኖ ድሆችን ሲያስለቅስ፣ መሬታቸውን ወይም ንብረታቸውን ሲነጥቅ፣ በአጃቢዎቹ አማካይነት የሰው ሚስት ሲቀማ፣ ኬላ እየጣሰ ኮንትሮባንድ ሲነግድ ማን ደፍሮ ይናገራል? ደፈር ብለው የሚጠይቁ ሲነሱ ‹‹ታፔላ›› ተለጥፎላቸው እንዲመክኑ ይደረጋሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ አክቲቪስት ነን ባዮች በንፁኃን ደም እንጀራቸውን ሲጋግሩ ዝም ይባላል፡፡ ደፋሮች ካልተገኙ እኮ ጉልበተኞች አገር መጫወቻ ያደርጋሉ፡፡ ልብ እንበል፡፡

  የኬንያውን ጠበቃ አስገራሚ ዜና የነገርኩት ጓደኛዬ የሚገርም ነገር ነው የነገረኝ፡፡ እሱ እንደሚለው የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ አንድ የሚያውቀው ሰው የንግድ ድርጅቱን የሚመራበትን የመንግሥት ቤት ‹‹ለቀህ ውጣ›› ይባላል፡፡ ምክንያቱን ሲጠይቅ ‹‹ልቀቅ ተብለሃል እንጂ ምክንያት ጠይቅ አልተባልክም፤›› የሚል ምላሽ ያገኛል፡፡ ማስጠንቀቂያው በተሰጠው በአሥረኛው ቀን ቤቱ ይታሸጋል፡፡ ከ30 ዓመታት በላይ በሕጋዊ መንገድ ተሰጥቶት የሚሠራበት ቤት ተቀምቶ፣ ዕቃው የትም ተጥሎ፣ በመጨረሻ ለሌላ ግለሰብ ይሰጥበታል፡፡ የደረሰበትን ኢፍትሐዊ ድርጊት በፍርድ ቤት ለመከራከር ይወስናል፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ ተከራክሮ በሐሰተኛ ምስክሮች ጭምር በተሠራበት ደባ ይረታል፡፡ ይግባኝ ቢልም አይቀናውም፡፡ በመጨረሻ ጭንቅላቱን ነካ ያደርገዋል፡፡ ብቻውን ማውራት ሲጀምርም ‹‹አበደ›› ይባላል፡፡ አንድ ቀን የተወረሰበት የንግድ ቤት ግድግዳ ላይ፣ ‹‹ዛሬ በኃጢያት የተቀማሁትን ቤቴንና ንብረቴን የሚያስመልስ ጀግናና ደፋር ዜጋ እስኪመጣ እጄን ሰጥቻለሁ፤›› ብሎ ጻፈ አለኝ፡፡ ለፍትሕና ለርትዕ የሚቆሙ ነፍሶች የተባረኩ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው በሰው እንባና ደም የሚቀልዱ ደግሞ እኩያን ናቸው፡፡ ለማንኛውም ፍትሕን እየረገጡ ወንጀል ከሚፈጽሙ ይልቅ ፍትሕን ከወንጀል የሚታደጉ ብፁዓን ናቸው፡፡

  (አሸብር ተፈሪ፣ ከመሳለሚያ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...