Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትየአገራችን የፖለቲካ ጭጋግና ቀውሰኛ የትግል ሥልት

  የአገራችን የፖለቲካ ጭጋግና ቀውሰኛ የትግል ሥልት

  ቀን:

  በታደሰ ሻንቆ

  የዓብይ መንግሥት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከመምጣቱ/እንደመጣ የወሰዳቸው አፈናን፣ በአስተሳሰብ መወንጀልንና መታሰርን፣ መሰደድንና ብረት አንስቶ ጫካ መግባትን፣ እንዲሁም ጎራ ፈጥሮ መኮራረፍን ያቀለሉ ዕርምጃዎች፣ በጥቅሉ የአፈና ሥርዓት መገፈፍንና የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጮራ መፈንጠቅን ያበሰሩ ነበሩ፡፡

  ከጥያቄዎችና ከትግሎች ጋር ይከሰቱ የነበሩ የጥፋት ተግባራትን (ግጭቶችን፣ አውዳሚነትንና የጅምላ ጥቃቶችን) በሠራዊት ቅጥቀጣና በገፍ እስር መቅጣት፣ መልሶ የተስፋ ጮራን የሚያጠፋና በሕዝብ ቅዋሜ ተመትቶ በቅልበሳ እንቅስቃሴ ለመወራረድም የሚያጋልጥ ነበርና መንግሥት ለኃይል ዕርምጃ አለመቸኮሉ ትክክል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከመብት ጥያቄ ጋር ተያይዞም ሆነ በሌላ መነሾ የሚራባ ቁርቁስና አውዳሚነት የሕዝብን ኑሮ ሲያምስ፣ የሰዎችን ሕይወት ሲበላና በገፍ መፈናቀልን ሲወልድ ‹‹ትዕግሥት›› መርዘሙ ወይም ችግሩ መፍትሔ አልባ ሆኖ መቀጠሉ ምንም ዓይነት የተገቢነት መከራከሪያ ሊቀርብለት የሚችል አልነበረም፣ አይደለምም፡፡ የዚህ ዓይነቱን ቀውስ አቅጣጫ የሚያስለውጥና መንግሥታዊ የፀጥታ ኃይል  ሊያጎናፅፍ ያልቻለውን የሕዝብ ሰላምና የተረጋጋ ኑሮ የሚያስቀጥል ሕዝበ ገብ የለውጥ እንቅስቃሴ ክፍተቱን መሙላት ነበረበት፡፡ በዚህ ረገድ ለውጡ የነበረበት ድህነት ከኋላ የጀመረ ነበር፡፡ እነዚህን ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡

  ለውጡ የዴሞክራሲ ግንባታን የተለመና የተደራጀ የፖለቲካ መሪነት ጀርባ አልነበረውም፡፡ በብዙ ነገር የግብታዊ ትግል ውጤት ነበር፡፡ ጥያቄዎችና ቅዋሜዎች ተበታትነው በተናጠል የሚመጡ ነበሩ፡፡ በሒደትም የተሳሰረ የጋራ የትግል አመራር አልፈጠሩም፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረው የውስጥ ትግልም ሜዳ ላይ ከነበረው የሕዝብ ትግል ጋር የተቆጣጠረ (የተሳሰረ) አልነበረም፣ እስከምናውቀው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ተነጣጥለው ብቅ ጥልቅ ሲሉ የነበሩት ጥቄዎችና ቅዋሜዎች፣ በአያሌው በመንግሥታዊው አናዳጅ አፈናዎችና ጥፋቶች የሚቆሰቆሱና በአፀፋዊ ምልልስ እየከረሩና እየሰፉ የመጡ ነበሩ፡፡ የማዶ ለማዶ ትግግዝ ስሜት በስተኋላ የመጣውም ከዚሁ ሒደት ነበር፡፡ በኢንተርኔት በስልክ ትግሉን የማስተባበርና እንዳይበርድ የማድረግ ሥራ የመሥራቱም ሆነ፣ የኢሳትና የኦኤምኤን አራጋቢነት የትግሉን የጋራ ትልም የለሽነትና የጋራ መሪ የለሽነትን ያልቀየረ ነበር፡፡ ከአካባቢያዊ/ብሔርተኛ ጉዳዮች ታልፎ ‹‹ኢሕአዴግ ይወረድ!›› የሚል ነገር የመጣውም በስተኋላ ቁጣዊ ትግሉ እየተባዛ መሄዱ በፈጠረው መደፋፈር ነበር፡፡ አፋኙን አገዛዝ መገላገል የሁሉም ፍላጎት ቢሆንም፣ ከዚያ ያለፈ መግባቢያ ግን ትግሉ አላበጀም ነበር፡፡ በስተኋላ ሲነገር እንደሰማነው ትግልን አስተባብሮ ለማካሄድ ኅቡዕ ድርጅታዊ ሰንሰለት ነበረው የሚባለው የኦሮሞ ወጣቶች ትግል እንኳ፣ ከዓላማ አኳያ የሚጣረሱ ፍላጎቶች ሁሉ አንድ ላይ የተለሰኑበት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ አንድ ጋር ሲታይ በአገር ውስጥ ያሉ የተደራጁ ሕጋዊ የተቃውሞ ቡድኖች፣ በአብዛኛው ከተመልካችነት ያለፈ ሚና በኅቡዕ እንኳ አልነበራቸውም ለማለት የሚያስደፍር ነው፡፡ 

  የሕዝቡ/የወጣቱ ትግል ‹‹ዴሞክራሲንና ተሃድሶን ማጥለቅ›› በሚል የኢሕአዴግ ቅብጥርጥር የማይሸነገልበት ቁጣና ምሬት ውስጥ ገባ፡፡ ከዚያ ወዲያ የካቢኔ ለውጥም ሆነ የኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄን የተጎዳኘ የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ተሞካክሮ፣ የተከተለው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሰየም ጉዳይ በትግሉም ሆነ በኢሕአዴግም ዕጣ ላይ ወሳኝ ምዕራፍ ነበር፡፡ በሕወሓት/ኢሕአዴግ የ27 ዓመት ታሪክ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያልደረሰው ኦሮሞ ባይሾም ኖሮ፣ በኦሮሞ በኩል የለየለት ነውጥ ለማንሳት በእልህ የተሞላ መቁነጥነጥ ነበር፡፡ የዓብይ አህመድ መመረጥ ይህንን ውጤቱ አስቀድሞ ሊገመት የማይችል ማዕበል አስቀርቷል፡፡ ከዓብይ አህመድ የመጀመርያ የፓርላማ ንግግር አንስቶ ተከታትለው የተወሰዱ ፈጣን ዕርምጃዎች ያጎኑት (ከፍ ያደረጉት) ድጋፍ ደግሞ ለቅልበሳም ፋታ ያልሰጠ፣ ቢሞከርም የሚቦጫጭቅ ነበር፡፡ እንደ አጀማማሩ ፍጥነት የዓብይ መንግሥት ዕርምጃዎች ድጋፍ አባዥነት እየተምዘገዘገ ሊቀጥል ግን አልቻለም፡፡

  የለውጥ ሥራዎቹ ውሳኔ ከመስጠት፣ ተቃዋሚዎችን ከመጥራት፣ የህሊና እስረኞችን ከመፍታትና ጎራ የሠሩ ኩርርፎችን ከመፈርከስ የበለጠ ጥናትና የእርጋታ ሥራ የሚሹ መሆናቸው አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፀጥታ ኃይሎችን የሚመለከቱ ማሻሻያዎች ጥንቃቄ የሚሹ መሆናቸው ሌላው ነው፡፡ ፖሊሲዎችን ማረቅ፣ አፋኝ ሕጎችን ማሻሻል፣ መቀየርና አዳዲስ ማመንጨትም ሆነ ተቋማትን በአዲስ መንፈስ ማደራጀት በየፈርጁ የበሰሉ ባለሙያዎችን ከማሰባሰብ ጀምሮ ብዙ ሥራን የሚጠይቅ ነው፡፡

  ሌላው ትልቁ ሰበዝ ለውጡ ያልተጠበቀ (ሳይታጠቁ ድንገት የደረሰ) መሆኑ ያስከተለው ጉድለት ነበር፡፡ ለውጡ መርሐ ግብርና የማንቂያ/የመቀስቀሻ ስንቅ ያላሰናዳ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ጉድለት በማጤን የለውጥ ፖለቲካኞች/ቡድኖች ፈጥነው በአዲሱ መንግሥት ዙሪያም ሆነ እርስ በርስ ተሰባስበው ለለውጡ ፍንትው ያለ ብርሃን መስጠት፣ በዚህም ምልዓተ ሕዝብን እየነቀነቀና አዕምሮን እያበራ እስከ ታች ድረስ ወዶ ገባ ታጋዮችንና አታጋዮችን ያትረፈረፈ ተከታታይ የፖለቲካ ንዝረት መፍጠር አልቻለም፡፡ ቢታይ ቢታይ በድፍኑ ‹‹እንደመር›› ከሚል ነገርና ‹‹ቲም ለማ››ን ከሚያወድሱ ዘፈኖችና የፎቶ ወረርሽኞች ያለፈ የኅብረተሰብ ህሊናን ያነቃ፣ መፈራራትና ዝምታን ነዳድሎ ከተለያየ ማዕዘናት ነገሮችን የሚያብሰለስል የዴሞክራሲያዊ ውይይት ሰደድ ብቅ አላለም ማለት ይቻላል፡፡

  ይህንን መሰሉ አዲስ ነገር መጉደሉ፣ በተለመደው የኑሮ ሥርዓትና የአዕምሮ ሙሽት ውስጥ ሆኖ የታፈኑ አሮጌ ጥያቄዎችንና ብሶቶችን መዘርገፍ (ዞን/ክልል ልሁን ማለት፣ በወሰን ጉዳይ መራኮት፣ የአካባቢዬን መሬት/ሲሳይ ተቀራመተኝ በሚሉት ላይ ጥቃት መሰንዘር፣ ወዘተ) የለውጡ  ይዘት መሰሉ፡፡

  ሌላው የለውጡ የድህነት ገጽታ ከእሳት፣ ከዝርፊያና ከሰብዓዊ ጥቃት ጋር የተዛመደ የትግል ዘይቤን እንኳ የማስለወጥ አቅም ማጣቱ ነበር፡፡ በግልፍታ ሰክሮ ውድመትና ጥቃት የፈጸመ ህሊና፣ ግልፍታው ካለፈ በኋላ አነሰም በዛ ኃፍረትና ፀፀት ይጎበኘዋል፡፡ በቅድመ ለውጡ ጊዜ አታጋይ ነን ያሉ ሚዲያዎች/ግለሰቦች አገዛዙን  የማዳቀቅ ብልኃት አድርገው የመረቁት አውዳሚነትና አጥቂነት ኃፍረትንና ፀፀትን ተሻግሮ በጀብዱ ኩራት ለመሞላት በቃ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ አኩሪ ገድልነቱ አልተሸማቀቀም፡፡ የለውጡ አንድ የቅርብ አዋላጅ መሆኑ ሲታይ የባለ ገድሎቹ ኩራት ጣሪያ ነካ፡፡ የማውደም ድርጊትም መንግሥትን አዝረጥርጦ ፈጣን ውጤት በማምጣት ፍቱን የትግል ሥልት ተደርጎ የመቆጠር ሹመት ተቀዳጀ፡፡ ከዚያ ወዲያ አርበድብጄ ፈጣን ምላሽ ላግኝ ያለ ባለ ጥያቄም፣ ጥላቻና በቀል የገነፈለበትም፣ በግጭቶች እያነካካና እያዋከበ ለውጡን ለመገዝገዝ የፈለገም፣ ነባር ዝርፊያ ለመሸፋፈንም ሆነ ትኩስ ዘረፋ ያማረው ሁሉ የሚያነሳሳው ሥልት ሆነ፡፡ ሐረርን በቆሻሻ አወጋገድና በመጠጥ ውኃ አጣብቂኝ ውስጥ ይዞ አፈሳ ገንዘብ የማስተፋት ድርጊት መፈጸሙ ፖለቲካን ተገን ያደረገ ምርጥ የዘረፋ ምሳሌ ነው፡፡

  የአገሪቱ ፖለቲካዊ እውነታ በድንግዝግዝ የተዋጠበት (የፖለቲካዊ መስመር ዕርዳታና ኃይል የማሰባሰብ ነገር ገና ጥሬ የነበረበት) ደረጃ ሁነኛ የለውጥ ድክመት መሆኑን ለማስተዋል መክበዱም፣ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የቆሙ የደጅ ቡድኖችን አስቀድሞ ስቦና በውስጥ ካሉት ጋር አጎዳኝቶ በተባበረ መርሐ ግብር ለውጡን የማንደርደርና በለውጡ ፈር የያዘ ግስጋሴ ውስጥ የመነጠል ትግል ውስጥ ተሰማርተው የቆዩ ቡድኖችን ወደ አገራዊ አንድነት የመሳብ፣ ይህ ባይሆን ከእነ አቋማቸው ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ የማድረግ ቅደም ተከተላዊ ታክቲክ ለመጠቀም አላስቻለምና በጋጋታ ውስጥ ለሚካሄድ ሥውር ሥራ አጋልጧል፡፡ በዚህ ረገድ የዳውድ ኢብሳ ኦነግ ሰላምን ተጠልሎ ከፍቶት የነበረው ትጥቅ ትግልን የማራባት ተግባር ተጠቃሽ ነው፡፡

  ለዚህ ሁሉ የተመቸ የፖለቲካ ፍዝነትም አለ፡፡ በስተኋላ በመቶ ቤት ተቆጠሩ የሚባልላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ብዙዎቹ ኅብረተሰባዊ ሥር የለሾች ነበሩ፡፡ ፓርቲ ነን ባዮች በየፖለቲካ ፕሮግራማቸው ዙሪያ ሕዝብን ሲያደራጁና ሲያንቀሳቅሱ አልታዩም፡፡ ንቅናቄ ነን ባዮችም የሕዝብ ንቅናቄ ሲፈጥሩ አልታዩም፡፡ አንዳንዶቹ ዘመን ያለፈበት ጥያቄና አተያይ ላይ ተገትረው የቀሩ ናቸው፡፡ ሕወሓትን ሲኮንኑ ከነበሩት ውስጥም ሕወሓት ከበላይ ዘወር ካለ ወዲያ የሚሉት የጠባቸውና የዓብይ አህመድ መንግሥት ተስፈኛ በመሆን ላይ የወደቁም ታይተዋል፡፡

  ከእነዚህ በተነፃፃሪ የተሻለ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ አቅም ያላቸው በሚመስሉት፣ (እንዲያውም ‹‹ይህ ዕድል ካመለጠና ዴሞክራሲን የመገንባቱ ነገር እንደ በፊት ጊዜያት ከከሸፈብን አገሪቷ ልትበታተንም ትችላለች›› እስከ ማለት ‹‹በሚሠጉት››) ዘንድ አስገራሚ ተመልካችነት ሠልጥኗል፡፡ ለዴሞክራሲ በመረባረብ የመበታተን ሥጋታቸውን ለማስቀረት ሲተጉ አልታዩም፡፡ አንዳዶቹ የዴሞክራሲ ለውጡ እንዳይከሽፍ የማድረጉን ተግባር የዓብይ መንግሥት ዕዳ፣ ተቺነቱን ደግሞ ለራሳቸው የሰጡ ናቸው፡፡ ከዚህ አለፍ የሚሉት ደግሞ ጥምር ወይም ብሔራዊ መንግሥት በማቋቋም እስካልተሳተፉ ድረስ፣ ለለውጡ መሳካት መንጦልጦል የዓብይ መንግሥት አጫፋሪ መሆን መስሎ የሚታያቸው (ለለውጡ መዋደቅን መንግሥት ከመሆን ጋር ብቻ አዛምደው የሚያዩ) ይመስላሉ፡፡

  ፍዝነት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ዳፈንም አለ፡፡ በዴሞክራሲ ፈላጊነት አፉን ያላወዛ ቡድን የለም ማለት ይቻላል፡፡ እስካሁን ያለውን የብሔርተኞች አገዛዝ በዴሞክራሲ አጋጊጦ ለማስቀጠል የሚሹትም፣ የአሁኑን መንግሥት በቀውስ አስምጠው ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› አምባገነንነትን ለመመለስ የሚቃዡትም፣ ኢትዮጵያ ተበታትና ከክልልነት ወደ አገርነት የማለፍ ዓላማን በሙዳይ የደበቁትም ሆኑ፣ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንሻለን ባዮች የሚሳተፉበት ትችትና ሽርደዳ በሽበሽ ነው፡፡

  ‹‹የዓብይ መንግሥት ፍቅር ከመስበክ አልፎ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥራውን እየሠራ አይደለም…. የሚኒስትር ሹመቱን ከችሎታ ይልቅ እንዳለ መሸናገያ አድርጎታል፣ … የተረጋጋ ካቢኔ ሊፈጥር አልቻለም …›› ከማለት ገራም ትችት አንስቶ፣ ‹‹እንደ መንግሥት አገር ማስተዳደር አቅቶት ጨንግፏል …  በትጥቅ ትግል መልክ የተካሄደው መታመስ፣ የባንኮች ዘረፋና የሕዝቦች መፈናቀል ሁሉ የመንግሥት እጅ ከጀርባ ያለበት ነው…›› እስከ ማለት ድረስ እጅ እግሩ የጠፋ ነቀፋ በአገሪቱ ሚዲያዎች አማካይነት ሳይቀር ተመላልሷል፡፡ እንዲህ ያለውን መረን (በመዝገበ ቃላት ትርጉሙ ልቅ፣ ባለጌ፣ ስድ) ነቀፋቸውን መልሶ የሚያሽሟጥጥባቸው ደግሞ፣ ለመንቀፍ የደፈሩት አሁን ያለውን ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ተማምነው መሆኑ ነው፡፡ እጅግ አስደንጋጩ ገጠመኝ ደግሞ (ቴሌቪዥን የማያሳየው የለም) ስለመንግሥት መጨንገፍም ሆነ ቀውስ ስለማባዛቱ ሲያወሩ፣ ስለት የደረሰላቸው ይመስል የደስ ደስ ስሜት ፊታቸው ላይ ሲራጭ ማየታችን ነው!! መንግሥት ስለመጨንገፉና አገሪቱ ወደ መፋጀት እያመራች ስለመሆኗ አምነው የሚያወሩ ከሆነ አደጋው አስጨንቋቸው አገርና ሕዝብ ለማትረፍ ሲደክሙ አለማየታችን ነው!!!

  ለአገርና ለሕዝብ ኧረ መላ እንበል የሚል ጥረት የሌለበት ‹‹መንግሥት ጨንግፏል›› ባይነት የዓብይ መንግሥት ነገረ ሥራ እንደ አባ ጨጓሬ ከሚኮሰኩሳቸው ሰዎች በኩል (የሕወሓት ግትሮችን ጨምሮ) ሲወረወር እንደምንሰማ ሁሉ፣ በሕወሓት የትግራይ ገዥነት ላይ ጦር እንዲዘምት ከሚመኙም በኩል የፌዴራል መንግሥቱ ጦር አለማዝመቱን የመጨንገፍ ማረጋጋጫ በማድረግ ወሬ ይሰለቃል፡፡ ይህ ሁሉ የፖለቲካችን ጭጋግ ነው፡፡

  የዓብይን መንግሥት አስጠልቶ ለማስመጥ ዓላማ ያላቸው ባይጠቀሙም ለምኞታቸው እየሠሩ ነው፡፡ የሚገርመው የመንግሥት መጨንገፍ መመዘኛ ምልክቶችን ይዞ፣ ኢትዮጵያን በሜካናኒካዊነት እየለኩ የመጨንገፍ ‹‹ግምገማ›› የሚያስተጋቡ ጥራዝ ነጠቆች በየት አገር የጨነገፈ መንግሥት ሳይርድ ለዴሞክራሲ መሠረት የመጣል ሥራ ላይ ሲጠመድ ታየ? ጭንጋፍነት ውስጥ ከወደቀስ ወዲያ በቀቢፀ ተስፋ አንኳሳሾቹን የማያሳድደውና የመናገር ነፃነትን የማያጥመለምለው ስለምን ብሎ ነው? በጠብመንጃና በስደት ትግል ውስጥ የነበሩ የመነጠል ፍላጎት የነበራቸውስ በጨነገፈ ሁኔታ ከማፈንገጥ ፈንታ፣ በሰላማዊ ትግልና በዴሞክራሲ ምርጫ ውስጥ ለመሰማራት ሲተጉ እንደ ምንስ ለመታየት ፈቀዱ? ብሎ የሚጠይቅ ትንሽም ማስተዋል ማጣታቸው የፖለቲካ ኃፍረታችን ነው፡፡

  በኢሕአዴግ ግንባር ውስጥ የአመለካከትና የድርጅቶች መጣጣም አለመኖሩ፣ በስመ ኢሕአዴግ ያለው የመንግሥት መሪነት ላይ የሚያስነክስ ተፅዕኖ ማሳረፉ እውነት ነው፡፡ ከመከለከያ እስከ ፖሊስ ድረስ ያለውን ኃይል ከፖለቲካ ታማኝነት የማላቀቁ ሥራ የቅርብ ጊዜ እንደ መሆኑ፣ የደፈረሰ ፀጥታን ወደ ነበረበት ለመመለስ ኃይል በመጠቀም ግለሰቦች ሊማግጡ፣ ከሕዝብ አባላት በኩልም በቀድሞው ዓይን መኮነን ሊያጋጥም የሚችል መሆኑ እውነት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ዕንከኖች እየተመላለሱ የመንግሥትን ሕዝባዊ ድጋፍ እንዳያራግፉ መጠንቀቅም ተገቢ ነው፡፡ ይህ ጥንቃቄ ግን ሰዎችን በጅምላ እያጠቁ ግዳይ የሚጥሉና የሚያፈናቅሉ ግጭቶችንና ትርምሶችን መታገስ በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡

  ወደ አምባገንነት ላለማምራት ሲባል ሥርዓት አልባነትን የሚያራቡ ቀውሶችን ማስታመም፣ ላለማሰርና ላለመግደል እጠነቀቃለሁ ሲሉ የሰዎችን ሕይወትና ኑሮ በጭፍን የሚበሉ ጨካኝ ጥቃቶችን መታገስ አይጣጣሙም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ገዳዮችንና አፈናቃዮችን ተኩሶ ከመግደልና አፍሶ ከማሰር በመሸሽ ትዕግሥቱ፣ ሕዝብ ላይ የሚደርስ ግድያንና መፈናቀልን አላስቀረም፡፡ ዋናው ጉዳይም ቀውስ እዚያም እዚያም የሚፈነዳበትን ሁኔታ ታቅፎ ቀውስ ሲከሰት ከመተኮስና ከማፈስ መራቅ ሳይሆን፣ እንደ ምንም ለውጡን በሕዝብ ውስጥ ማስረፅና ለሰላምና ለፀጥታው ሕዝብን ማነቃነቅና የቀውስን ዕድል እያመከኑ ሕግና ሥርዓት ማስከበሪያ አውታራትን አድሶ መደበኛ ሥራቸውን በንቃት እንዲሠሩ የማብቃት ሒደትን ማፋጠን ነው፡፡

  ይኼንን ማካሄድ የዓብይ መንግሥት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደምን ተሳነው? የሚል ፍርድ አይሞከረንም፡፡ የሽግግር ጊዜ ምን ያህል ፈተና እንዳለበት እናውቃለን፡፡ ዛሬ የዓብይ መንግሥት ኢትዮጵያን በውስጥ ስደት አንደኛ አድርጎ የውርደት ውርደት ውስጥ ከተታት ሲሉ የሰማናቸው የሕወሓት መሪዎችም፣ እንዲያ ለመመፃደቅ የሚያበቃ ሞራል እንደሌላቸው እነሱም ያውቁታል፡፡ የደርግ መንግሥትን ሠራዊት እየኮነኑ ያለ ጉርስ በመበተናቸው ምክንያት በአገሪቱ ዙሪያ ገባ ጫካዎችንና ዓውራ ጎዳናዎችን እየተጠቀሙ በመሣሪያ አስገድደው የሚዘርፉ ቡድኖች ያራቡበት ታሪክ፣ ምን ያህል ጊዜያት ሕዝብ አንገላቶ እንደከሰመ ያንን ዘመን ያየ ያስታውሳል፡፡ እስካሁን ድረስ በሚያምሱን ጣጣዎች ውስጥም የእነሱ የጥርነፋ አገዛዝ መሐንዲስነት ዋናው ባለድርሻ እንደሆነ ለማሳመን ሐተታ መደርደርም አይኖርብኝም፡፡

  በቅርቡ አንድ የካሜራ ሰው ኮንሶ ሄዶ የመጣበትን ዓላማ ለአስተደደሩ በማሳወቅ ድጋፍ ተደርጎለት ቀረፃ ከጀመረ በኋላ፣ ‹‹ኮንሶ መከራ ሲያይ ብቅ ያላለ ጋዜጠኛ ዛሬ ከየት መጣ? ኮንሶን ልትሰልል ነው እንጂ›› ከሚል ጥርጣሬ የወጣቶች ቁጣ ያገነግንበታል፡፡ አደጋ እንዳያደርስበትም ፖሊሶች ወደ ፖሊስ ተቋም ያሸሹታል፡፡ እነሱ ዘወር ሲሉ ግን፣ ሌሎች ፖሊሶችና የአስተደደር ሰው ጋዜጠኛውን ከነበረበት አውጥተው ድብደባ ይፈጽሙበታል፡፡ ይህንን የነገረን ራሱ ተጎጂው (በኢሳት ቲቪ፣ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም.) በሰጠው ምስክርነት ነው፡፡ ገጠመኙን ያለምክንያት አልጠቀስኩትም፡፡ ጣጣዎቻችን ከዓብይ አህመድ በፊት ከነበረው የመንግሥት ደቋሽነት ጋር የተያያዘ አመጣጥ እንዳላቸው፣ ጅብደኛ አታጋዮች በትግል ሥልትነት ቡራኬ የሰጡት የደቦ ዕርምጃ ከመንገድ ወጣት እስከ ሕግ አስከባሪ ድረስ እንደ ሰፋ፣ ለውጡ ሕዝባዊና አስተዳዳራዊ ሥር ታች ድረስ አለማበጀቱም ለግርግር ፈጣሪዎች ቀዳዳዎች እንዳበዛላቸው ለመገንዘብ የሚያስችል ቀላል ምሳሌ ስለሆነ ነው፡፡

  ለውጡ በነፃነትና በእኩልነት ስሜት መሸካከርና መፈራራትን እየዘነጣጠለ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ወጣቱን ከወጣት እያያያዘ፣ የውድመትና የብቀላ ዕድሎችንና ውጥኖችን ሊሰለቃቅጣቸው አልቻለምና በደቦ ጥቃትና ውድመት ሕዝብ አካላዊ ደኅንነቱና ሠርቶ የማደር መስተጋብሩ መጎዳቱ፣ ይህም የሥራ ከፈታ ዕድል ከሩቅ እያበረረ ሥራ አጥነትን መጥቀሙ፣ ብሶትና ማንን ፈርቼ ባይነት በሕግ አስከባሪነት መፍዘዝ ታግዞ በሰበብ አስባብ ለጥፋት እንቅስቃሴ መደፋፈሩ፣ ተጠቃሁ ባይነትና መንግሥታዊ የደኅንነት ዋስትና ማጣት የተሰማውም ራሱንና ብጤዎቹን ሕግ አድርጎ መበቀልን ሙጥኝ ወደ ማለት ማለፉ እርስ በርስ ተመጋጋቢ ለመሆን በቅተዋል፡፡     

  ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በዋልታ ቲቪ ‹‹ነፃ ሐሳብ›› ዝግጅት ላይ ካየነው በብሔርተኛ አታጋይነት ልቡ ከተሞላ አንድ ወጣት የሰማናቸው ቃላት ያስገነዘቡን ነገር ቢኖር፣ የ‹ሕግ በጄ› የትግል ሥልት ምን ያህል ሚዲያ ላይ ወጥቶ እስከ መኮፈስ ድረስ በወጣቶች አካባቢ እየተንጎማለለ እንደሆነ፣ ለውጡም ምን ያህል የብዙኃን እንቅስቃሴ ድህነት እንዳለበት ነው፡፡ ወጣቱ በዕለቱ ከሰጠው ቃለ መጠይቅ እንደተረዳሁት፣ የእኔ ያለው ሕዝብ መካች ያጣ ተጠቂ ሆኗል የሚል የግንዛቤ ማዕዘን አበጅቷል፡፡ “የእኛን ሰላም መነሳት እነሱም ይቅመሱት›› የሚልም ተበቃይነት ቋጥሯል፡፡ ሥርዓት  አልባነትን እንደ ትግል ሥልት መጠቀምን መምረጣቸው ስለምን ብለው እንደሆነ ሲጠየቅም፣ አምባገነኖች የሚያጠቁትና ሰላም የሚነሱት በሕግ አማካይነት ስለሆነ ነው፣ በሕግ ስትታፈንና ስትጠቃ ሕግና ሥርዓቱን በመረበሽ መታገል አግባብ ነው› ሲል ተከራክሯል፡፡ ለትግላቸውም ማዘማመጃ የብሮዳክስት ኔትወርክ እያቋቋሙ ስለመሆናቸም ነገሮናል፡፡

  የወጣቱ አስተሳሰብ የብዙ ወጣቶችን አስተሳሰብ እንደሚወክል ሳንዘነጋ ያሉበትን ጉልህ ውልቃቶች እንጠቃቅስ፡፡ ሥርዓት አልባነት እንደ ትግል ሥልት አምባገነን ሥርዓትን ለመጣል እንኳ ሲውል፣ ወደ ፋሽስታዊነትና ወደ አሸባሪነት የሚያንከባልሉ ድጦች እንዳሉበት ወጣቱ አልተገነዘበም፡፡ ‹‹የእኛን ሰላም መነሳት እነሱም ይቅመሱት›› በሚል አስተሳብ ውስጥ መጨፋጨፍን የሚያበቅሉ ዘሮች አሉ፡፡ አሁን የምንገኝበት ወቅት በአምባገነንነት መዳፍ ውስጥ ሆነን ለዴሞክራሲ የምንታገልበት ሳይሆን፣ በዴሞክራሲ ጮራ ውስጥ ሆነን የአምባገንነትን ቀሪ ቅልጥሞችንና አንጓዎችን ለመሰባበርና ለመጠራረግ የምንታገልበት ምዕራፍ መሆኑንና ምዕራፉ የተለየ የትግል ሥልት የሚሻ መሆኑን ወጣቱ ብሔርተኛ ስቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ትልልቅ ጉድለቶችን በያዘ መራራ የተጠቂነት ስሜት ውስጥ የወጣቱ መቆየት፣ ማንቃትና መቀስቀስ ለቸገረው ለውጥ ቅሌቱ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ለውጡ አሁንም በቶሎ ዴሞክራቶችን አሰባስቦ/አስተባብሮ ኅብረ ብሔራዊ የብዙኃን እንቅሰቃሴ በመሆን ረገድ ያለበትን ድህነት ወደ ማራገፍ ካልዞረ፣ የ‹አታጋይነት› እና የ‹ነፃ አውጪነት› ተልዕኮ ይዘው ያሉ ነባርና አዲስ የሥርጭት ሚዲያዎች ባህርያቸውን ካልቀየሩ፣ የሚዲያ ‹አታጋይነት› እየተባዛ አገሪቱ የተተካታኪዎች አውድማ ሆና ለውጡና አገሪቷ አይሆኑ ለመሆን እንደሚጋለጡ አያጠራጥርም፡፡

  የአገራችን ዕጣ ከዴሞክራሲው መራመድ ጋር፣ የዴሞክራሲውም ዕርምጃ ወጣቶችንና መንግሥትዊ አውታራትን ታች ድረስ እያደሱ ከመሄድና አለመሄድ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ በዕዳ የተወጠረውንና በአገጠጠ ዱቤ የሚውተረተረውን የቋፍ ኢኮኖሚያችንን ከመደንቆር ለማትረፍ መቻልና አለመቻልም የዕጣ ገመዳችንን የሚወስን ሆኗልና የለውጡ ትግል ድርብ ነው፡፡ የዴሞክራሲ አመለካከትን በማስፋፋትና የአገራችንን የኢኮኖሚ ፈተና በማስገንዘብ፣ ግርግርና መፈናቀልን ማዳከም፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንም አሁን እንደተያዘው በቶሎ ከመኸር እርሻ በፊት ወደ ቀዬቸው በመመለስና ሠርቶ ለመብላት እንዲበቁ በማቋቋም ረገድ ርብርቡን ማጣደፍ፣ በተባበረና በተነሳሳ ተቆርቋሪነት ከግብርና፣ ከማዕድንና ከኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሻለ ውጤት እንዲገኝ መትጋት፣ በለውጥና አገርን ከውድቀት በማዳን ስሜት ብክነትን፣ ቡጥቦጣን፣ የቀረጥና የግብር ሸፍጥንና ኮንትሮባንድን ማዳከም፣ ኑሮ የከበደ ቢሆንም የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄን ዛሬ ካለንበት ጭንቅ ጊዜ ጋር ማገናዘብ፣ በጥቅሉ የውጭ ምንዛሪ መራገፍ፣ የመሠረታዊ ኑሮ ፍጆታ መራቆትና የዋጋዎች መመንጠቅ አንድ ላይ ተገናኝተው እንዳያንቁንና እንዳያባሉን ቀበቶ ያጠበቀ ብልህ ትግል ማድረግ የአጣዳፊ ርብርባችን ገጾች ናችው፡፡ ‹‹የአሁኑን የለውጥ ዕድል እንዳለፉ ጊዜያት ካባከንን ሌላ ዕድል ላናገኝ እንችላለን›› የምንል ልሂቃን የምንለውን የምር እምናምንበት ከሆነም ከታዛቢነት ወጥቶ አጣዳፊውን ርብርብ ማስላት ግዳችን ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...