Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበአዋጆች ስለፆታ ሲገለጽ ‹‹በወንድ የተገለጸው ሴትንም ያካትታል›› መባሉ ጥያቄ አስነሳ

  በአዋጆች ስለፆታ ሲገለጽ ‹‹በወንድ የተገለጸው ሴትንም ያካትታል›› መባሉ ጥያቄ አስነሳ

  ቀን:

  የዳኞች የጡረታ ዕድሜ 70 ዓመት እንዲሆን በረቂቁ ተካቷል

  የፌዴራል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 ለመተካት በቀረበው ‹‹የፌዴራል የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ›› ረቂቅ ላይ ስለፆታ በተጠቀሰው በረቂቅ አዋጅ አንቀጽ ሦስት፣ ‹‹በዚህ አዋጅ በወንድ ፆታ የተገለጸው የሴትንም ያካትታል›› የሚለው አገላለጽ ጥያቄ አስነሳ፡፡

  ጥያቄው የተነሳው ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፌዴራል የዳኝነት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አከላት ጋር የመጨረሻ ግብዓት ለመሰብሰብ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል ለአንድ ቀን አዘጋጅቶት በነበረው ውይይት ላይ ነው፡፡

  የፆታን አገላለጽ በሚመለከት ጥያቄ ያነሱት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ሲሆኑ፣ ‹‹የፆታ ጉዳይ የተገለጸው አሁንም በወንዶች ነው፡፡ ይኼ ያላለቀ ትግል ነው፡፡ ወደኋላ ሊመልሱን የሚሞክሩ በርካታ ደካሞች አሉ፡፡ መጠንቀቅ አለብን፤›› በማለት ሁለቱንም ፆታዎች እኩል ያላደረገ አገላለጽ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

  የፕሬዚዳንቷን አስተያየት ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ መልካሙ ኦጎ እንደገለጹት፣ ሕዝቡ የሚጠይቀው ሴቶች ፆታን መሠረት ያደረገ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና ማግኘት የሚገባቸውን የመብት ጥያቄ እንዲያገኙ ነው፡፡ ጥቃቅን ነገር በማንሳት በዋናው የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ መካተት ያለበት ትኩረት እንዳያጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አገርን በሴት መጥራትና ዛፍን ወይም ሌላ ነገርን በወንድ ስያሜ መጥራት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያደገ እሴት በመሆኑና እሱንም መናድ ተገቢ ባለመሆኑ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ በአዋጁ ውስጥ ‹‹እሷ፣ እሷ…›› እያሉ መጥቀስ ያልተለመደ ከመሆኑም በላይ፣ ከሕጉ ይልቅ ፖለቲካዊ አስተሳሰቡ ስለሚጎላ ዓላማውን እንዳይስትም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ሌላው አስተያየት የሰጡት የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ሲሆኑ፣ በወንድ የተገለጸው ፆታ በሴት ቢገለጽ ችግር እንደሌለው ተናግረው፣ የፀረ ሽብር ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ ላይ ሲሠሩ ‹‹በሴት ፆታ የተገለጸው ለወንድም ይሠራል›› ካሉ በኋላ፣ አዋጁ የሽብር መሆኑን ሲያስተውሉ እንደቀየሩት በመግለጽ ተሰብሳቢን ፈገግ አሰኝተውታል፡፡

  የመጨረሻ ግብዓት ለመሰብሰብ ለውይይት የቀረበው የፌዴራል የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ፣ በሰባት ምዕራፎች ተካፋፍሎ 44 አንቀጾች ያሉት ነው፡፡ አዋጁ ሦስት ዓላማዎች ያሉት ሲሆን፣ የመጀመርያው ዓላማ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሾሙ ዳኞች ግልጽ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ በሆነ አሠራር የሚሾሙበት ሥርዓት በመዘርጋት የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት፣ ገለልተኛነትና ተጠያቂነት የሚያከናውኑበት አሠራር ማረጋገጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የዳኝነት ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠና የሕዝብ አመኔታን ያገኘ እንዲሆን ሲሆን፣ ሦስተኛው የዳኝነት ሥርዓቱን ከማናቸውም ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ እንዲሠራ ማስቻል መሆኑ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ አራት ላይ ተቀምጧል፡፡

  በተቀመጠው ዓላማ ላይ የውይይቱ ተካፋዮች ጥያቄም ሆነ አስተያየት ባይኖራቸውም የዳኞች ሹመት፣ ሥልጠና፣ የሥራ ዘመንና ከኃላፊነት ስለሚነሱበት ሁኔታ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ የፌዴራል ዳኛ የጡረታ መውጫ ዕድሜ 70 ዓመት እንዲሆን በመደረጉ ገሚሱ በዛ ሲሉ፣ ገሚሱ ጥሩ መሆኑን በመግለጽ አስተያየት የሰጡ ቢሆንም፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሾም ዳኛ ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገለ እንዲሆን መደረጉ ዳኞች ተስፋ ቆርጠው ወደ ሌላ ሥራ እንዲሄዱ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

  ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ታምራት ኪዳነ ማርያም በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ዳኞች የሥነ ምግባር ጥፋት ፈጽመው ሲገኙና በጉባዔው ሲረጋገጥ ከሥራ ይሰናበታሉ›› የሚለው ጥቅል ሐሳብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አንድ ዳኛ ሕገ መንግሥቱን አልተቀበለም ተብሎ ከዳኝነት ዓለም መሰናበቱን አስታውሰው፣ የሥነ ምግባር ጥፋት የሚለው በዝርዝር መቀመጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናን በሚመለከት ‹‹የመሳተፍ ግዴታ አለበት›› የሚለውም ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው መደረግ እንደሌለበት ጠቁመው፣ ቀደም ባሉት ዓመታት የዳኞች ማሠልጠኛ ተቋም ውስጥ ምን ዓይነት ሥልጠና ይሰጥ እንደነበር የሚታወቅ መሆኑን ሲጠቅሱ፣ አሠልጣኝ የነበሩ የሕግ ባለሙያዎች በስብሰባው ታድመው የነበረ በመሆኑ፣ በርካታ ዓይኖች ወደ እነሱ አተኩረው ታይተዋል ብለዋል፡፡ በዳኞች የሥነ ምግባር ችግር ላይ ጠበቃዎችም ጥቆማ እንዲያቀርቡ በግልጽ በአዋጁ እንዲካተት ጠይቀዋል፡፡

  የውሳኔን ግልጽነት በሚመለከት እስካሁን በሚሠራበት በፎረም ብቻ ‹‹አያስቀርብም›› ማለት ሳይሆን፣ በግልጽ ምክንያቱ ተገልጾ እንዲቀርብ በአዋጁ መካተት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ‹‹በመዝገብ ቤት ስሙ›› የሚለውን አሠራርም እንደሚያስቀር አክለዋል፡፡

  የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ሚኒስቴር ውጪ በሆነ አደረጃጀት መደረጋቸውን በሚመለከትም፣ በደል ቢደርስባቸው ይግባኝ የሚሉበት አሠራር በግልጽ እንዲቀመጥም ጠይቀዋል፡፡ ዳኞች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደሌለባቸው በረቂቁ መቅረቡ ጥሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

  የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔም በአዋጁ እንደሚቋቋምና ጠበቆችንና ሁለት ስመ ጥር ግለሰቦችን ጨምሮ 16 አባላት ያሉት እንደሚሆንም ተገልጾ በረቂቁ ቀርቧል፡፡ ስብጥሩን በማድነቅ የተወሰኑት አስተያየት ሰጪዎች መብዛቱን ሲገልጹ፣ የተወሰኑት ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  በረቂቁ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በዕለቱ የተገኘው ግብዓትና የማስተካከያ አስተያየቶች ተካተውበት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡             

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...