[ክቡር ሚኒስትሩ ለቅሶ ቤት ከአንድ ለቀስተኛ ጋር እያወሩ ነው]
- በጣም ያሳዝናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው የሚያሳዝነው?
- የሰሞኑ ትራጄዲ ነዋ፡፡
- ምን ታደርገዋለህ?
- ያማል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እ. . .
- ስንት ለአገር የደከሙ የቁርጥ ቀን ልጆች በአንዴ ሲያልቁ ያሳዝናል፡፡
- በጣም አሳዛኝ ነው፡፡
- መቼ ነው ግን የሚያበቃው ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ?
- የሴራ ፖለቲካው፡፡
- እ. . .
- ምነው ደነገጡ?
- የምን ሴራ አመጣህብኝ ብዬ ነዋ?
- የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴራ ፖለቲካ አይደል እንዴ?
- ብለህ ነው?
- ምን ጥያቄ አለው?
- እ. . .
- ቤተ መንግሥት የሚገባው በሴራ ነው፡፡
- እኛ እንኳን የገባነው በምርጫ ነው፡፡
- ለቅሶ ቤት ነን እንዳያስቁኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን ትስቃለህ?
- በምርጫ ነው የመጣነው ሲሉኝ ነዋ፡፡
- ትጠራጠራለህ?
- ክቡር ሚኒስትር 100 ፐርሰንት አሸነፍን ብላችሁ አገሪቱ 100 ፐርሰንት እየታመሰች ነው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ይኸው ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እየታመሰች አይደል እንዴ?
- ለውጥ በአንዴ አይመጣማ?
- የምን ለቅሶ መልሶ መላልሶ አሉ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ለውጥ ምናምን የምትሉትን ነጠላ ዜማ ረስታችሁ አገሪቱን በሚገባ ምሯት እንጂ፡፡
- እ. . .
- ጥያቄዬ ምን እንደሆነ ያውቃሉ?
- ምንድነው?
- መቼ ነው የእኛ አገር ፖለቲካ የሚያልፍለት?
- ምን አልከኝ?
- ለነገሩ መልሱን ራሴ አውቀዋለሁ፡፡
- ምንድነው?
- መቼም ነዋ፡፡
- እንደዚህ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፖለቲከኞቻችን እኮ በሐሳብና በውይይት አያምኑም፡፡
- ምን?
- ለምን እንደማያምኑ ያውቃሉ?
- ለምንድነው?
- የሠለጠኑና የተማሩ ስላልሆኑ ነዋ፡፡
- እንዲህማ ማለት አትችልም፡፡
- ለምን አልችልም?
- አብዛኛው ባለሥልጣን እኮ ዶክተር ነው፡፡
- እኔ የምልዎት ዋናውን እንጂ የተገዛውን ዶክትሬት አይደለማ፡፡
- ምን?
- ፖለቲከኞቻችን በእርግጥ የተማሩ ቢሆኑ የሰሞኑ ዓይነት ድራማ ባልተመለከትን ነበር፡፡
- እ. . .
- ጉጉቴ ፖለቲካችን በተማሩና በሠለጠኑ ሰዎች ሲመራ ማየት ነው፡፡
- እዚህ ላይ ታቆማለህ፡፡
- ምኑን ነው የማቆመው ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ እኔ ክቡር ሚኒስትር ብቻ አይደለሁም፡፡
- ሌላ ደግሞ ምን አልዎት?
- ዶክተር ኢንጂነር ክቡር ሚኒስትር!
[ክቡር ሚኒስትር እዚያው ለቅሶ ቤት ከአንድ ምሁር ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ፊትዎ ጠቋቁሯል ክቡር ሚኒስትር?
- ሠርግ ቤት አይደለም እኮ ያለሁት፡፡
- ሁልጊዜ የደስ ደስ አለዎት ብዬ ነው፡፡
- ለቅሶ ቤት እንዳለን ረሳኸው?
- ፊትዎ ተጎሳቁሏል ብዬ ነው፡፡
- ሜካፕ ተቀብቼ መምጣት ነበረብኝ?
- ሌላ ጊዜ ይቀባሉ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን?
- ማዲያትዎ ራሱ ወጥቷል እኮ፡፡
- እየተሳደብክ ነው?
- ስድብ ሲያንሳችሁ ነው እናንተ፡፡
- ምን አልክ?
- ምን እያሰባችሁ ነው ለመሆኑ?
- ማለት?
- አገሪቱ ምን እስክትሆን ነው የምትጠብቁት?
- ምን ሆነች?
- ከዚህ በላይ ምን ትሁን?
- እ. . .
- የአገር ጀግኖችን ልንሸልም ሳይሆን ልንቀብር እኮ ነው የተገናኘነው፡፡
- ፖለቲካ መቼም ታውቃለህ፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- ፖለቲካና ቁማር አንድ ነው እኮ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በሰው ሕይወት እየቆመሩ ግን መቀጠል አይቻልም፡፡
- ምኑ ነው የማይቀጥለው?
- ሥልጣኑ፡፡
- እ. . .
- ለውጥ አለ ብላችሁ አልነበር እንዴ?
- እሱማ ለውጥ ላይ ነን፡፡
- አይቀልዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለቅሶ ቤት የምን ቀልድ አለ?
- ለማንኛውም እኔም ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡
- በምኑ ነው ተስፋ የቆረጥከው?
- በፖለቲካችን ነዋ፡፡
- ዋጋ ያስከፍለናል እንጂ መለወጡ አይቀርም፡፡
- እንዲህ እያላችሁ እኮ ሕዝቡን አስፈጃችሁት፡፡
- ምን አድርገን?
- ለውጥ አለ፣ ዴሞክራሲ መጥቷል ብላችሁ ሸወዳችሁን፡፡
- ከዚህ በላይ ምን እናድርግ?
- ክቡር ሚኒስትር አሁንም ፖለቲካችን ከሴራ ፖለቲካ አልተላቀቀም፡፡
- ምን እናድርግ ታዲያ?
- ሕዝቡ እኮ ልቡ ተሰብሯል፡፡
- አውቃለሁ፡፡
- እናንተ ስትመጡ አገራችን አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ትገባለች ተብሎ ተስፋ ተጥሎ ነበር፡፡
- ግድ የለም አዲስ ምዕራፍ ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡
- እኔ የምፈራው ሌላ ነው፡፡
- ምንድነው የምትፈራው?
- አስፈሪ ምዕራፍ ውስጥ እንዳንገባ፡፡
- አታስብ ይኼን የብሔር ፖለቲካ ካጠፋነው ሰላም መውረዱ አይቀርም፡፡
- እንዴት ነው የብሔር ፖለቲካ የሚጠፋው?
- እ. . .
- ለማንኛውም ለአገሪቱ የደኅንነት ሥጋት የብሔር ፖለቲካ ነው ብላችሁ ነበር፡፡
- ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
- ከእሱ በላይ ለአገሪቱ ደኅንነት ሥጋት የሆነ ነገር አለ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- የሴራ ፖለቲካ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ባለሀብት ጋር እዚያው ለቅሶ ቤት እያወሩ ነው]
- የእኛ ነገር እንዲህ ሆነ በቃ ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት?
- በቃ ከድጡ ወደ ማጡ ነዋ፡፡
- ተወኝ እስኪ?
- ክቡር ሚኒስትር ትናንት ምንም እንቅልፍ አልወሰደኝም፡፡
- እኛ መተኛት ካቆምን ስንት ጊዜያችን?
- ነገሩ ሁሉ እኮ በእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነብን፡፡
- ምን ይደረግ?
- ክቡር ሚኒስትር ፖለቲካው ሊሻሻል ነው ስንል በአፍጢሙ እኮ ነው የተደፋው፡፡
- እ. . .
- ከዚህ በኋላ ኢኮኖሚው እንዴት ሊሆን ነው?
- ምን ይሆናል ብለህ ነው?
- ለነገሩ አሁንስ የት አለና?
- ምን እያልክ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እናንተ እኮ ፖለቲካው ላይ ብቻ ተወጥራችሁ ኢኮኖሚውን ረስታችሁት መቀመቅ እየወረደ ነው፡፡
- እስኪ ደግ ደጉን አስብ፡፡
- አሁን ደግሞ ፖለቲካው ጭራሽኑ ስለባሰበት ኢኮኖሚው ያልቅለታል፡፡
- ለውጥ ላይ መሆናችንን አትርሳ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ እኮ ለውጡን የተቀበለው ጥሩ ነገር ጠብቆ ነው፡፡
- እኛም ለውጡን ያመጣነው ጥሩ ነገር ለማምጣት ነው፡፡
- እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው፡፡
- እንዴት?
- ይኸው የአገሪቱ ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ነው የመጣው፡፡
- እሱማ እኛም ግራ ገብቶናል፡፡
- እኔማ አገሪቱን ለቅቄ ልሄድ እያሰብኩ ነው፡፡
- ለምን ብለህ?
- ክቡር ሚኒስትር በሁሉም ነገር ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡
- ግድ የለም ሁሉም ነገር መሻሻሉ አይቀርም፡፡
- እውነቱን ለመናገር እዚህ አገር ንግዱ ራሱ አስጠልቶኛል፡፡
- ለምን አስጠላህ?
- ክቡር ሚኒስትር እንጀራ ውስጥ ጀሶ እየገባ፣ በርበሬ ውስጥ ሸክላ እየተደባለቀ ሲሸጥ እያየን እንዴት አያስጠላን?
- በቃ ሰው ሁሉ ክፉ ሆኗል ምን ታደርገዋለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ንግዱ ውስጥ ራሱ ሴራ ተንሰራፍቷል፡፡
- እ. . .
- ንግዱ ውስጥም ሴራው ለምን እንደተንሰራፋም ገብቶኛል፡፡
- ለምንድነው?
- አሁን ንግድ ውስጥ ያሉት በአብዛኛው ፖለቲከኞች ናቸዋ፡፡
- እ. . .
- ስለዚህ ፖለቲካ ውስጥ የተማሩትን ሴራ ንግዱ ላይም ተክነውበታል፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- ግን ክቡር ሚኒስትር ሴራ ለማንም ቢሆን አያዋጣውም፡፡
- እሱማ ግልጽ ነው፡፡
- የእኛ አገር ፖለቲከኞች ግን እንደ ፋሽን የያዙት ነገር ሴራ ነው፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- ቁም ነገሩ ግን ዛሬ ያሴረ ነገ ይሴርበታል፡፡
- እ. . .
- ሰው እኮ የዘራውን ነው የሚያጭደው፡፡
- ምን አልከኝ?
- እንዲያውም ንፋስ ዘርቶ አውሎ ንፋስ ነው የሚያጭደው፡፡
- አለቅን በለኛ?
- ብቻ የሰሞኑን ነገር ሳጤን ፖለቲካችን ምን እንደሆነ ያውቃሉ?
- ምንድነው?
- ጭቃ ፖለቲካ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ተቃዋሚ ጋር ለቅሶ ቤት እያወሩ ነው]
- ምን ተሻለን ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት?
- በቃ ቢወቅጡን እምቦጭ ሆነን ቀረን፡፡
- አልገባኝም?
- እኔ እኮ ትንሽ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡
- ምኑን ነው ተስፋ ያደረግከው?
- ለውጡን ነዋ፡፡
- ለውጡማ የሁላችንም ተስፋ ነው፡፡
- አሁንማ ተስፋ ቆረጥኩኝ፡፡
- ለምን ትቆርጣለህ?
- አሁንም መላቀቅ አልቻልንማ፡፡
- ከምን?
- ከሴራ ፖለቲካ፡፡
- እ. . .
- መቼ ይሆን ግን የገዳይ፣ አስገዳይና ተገዳይ ድራማ የሚያበቃው?
- ምን አመጣህብኝ?
- ፖለቲካችን እኮ ይኸው ነው፡፡
- እንዴት?
- አንዱ አሲሮ አንዱን ይገድላል፡፡
- እ. . .
- ገዳይ ደግሞ በሌላው ወዲያው ይገደላል፡፡
- እ. . .
- የገዳይ አስገዳይ ቀጥሎ ይሞታል፡፡
- የምን ድርሰት ነው እባክህ?
- የሰሞኑ ፖለቲካችንን የሚያንፀባርቅ ድርሰት አይመስልዎትም?
- ምንድነው የምታወራው?
- ክቡር ሚኒስትር አሁንም ፖለቲካችን የሴራ መሆኑ ቀጥሏል፡፡
- ግድ የለም ቀስ እያለ ይለወጣል፡፡
- እንዴት ነው የሚለወጠው?
- ለውጥ ላይ ነና፡፡
- የምን ለውጥ ክቡር ሚኒስትር?
- የአመለካከት ለውጥ ነዋ፡፡
- አሁን ያለው የአመለካከት ለውጥ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድነው ያለው?
- የሴራ ለውጥ!