Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናአቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ የአራት ግለሰቦች ክርክር በሌሉበት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ተሰጠ

  አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ የአራት ግለሰቦች ክርክር በሌሉበት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ተሰጠ

  ቀን:

  በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ወንጀሎች ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ፣ የአራት ግለሰቦች ክርክር በሌሉበት እንዲቀጥል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

  የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አቶ አሰፋ በላይ፣ አቶ ሽሻይ ልዑልና አቶ አጽበሃ ግደይ የሚገኙት በትግራይ ክልል መሆኑ ከመገለጹ በስተቀር፣ ትክክለኛ አድራሻቸው ሊታወቅ ባለመቻሉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

  በመሆኑም ለአራቱም ተከሳሾች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ቢደረግላቸውም ሊቀርቡ ባለመቻላቸው፣ ፍርድ ቤቱ ማክሰኞ ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በችሎት አስተናባሪ ሦስት ጊዜ እንዲጠሩ አድርጎ አለመቅረባቸውን ካረጋገጠ በኋላ፣ በአቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ የቀረበው የክስ ክርክር አራቱ ተከሳሾች በሌሉበት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

  ፍርድ ቤቱ ሌላው የሰጠው ትዕዛዝ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ የቆጠራቸው 29 ምስክሮች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ያቀረበውን ማመልከቻ፣ በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/03 አንቀጽ 6(2) ድንጋጌ መሠረት አሻሽሎ እንዲቀርብ ሰጥቶት በነበረው ትዕዛዝ ላይ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ለምስክሮቹ ጥበቃ እንዲደረግለት የጠየቀውን ማመልከቻ እንዳላሻሻለ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፍርድ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 699/03 አንቀጽ 6(2) መሠረት እንዲያሻሽል ትዕዛዝ ቢሰጠውም፣ በተጠቀሰው አንቀጽ የሚቀርቡ ምስክሮች ማመልከቻ የሚፀድቀው በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እንደሆነ በአዋጁ ተደንግጎ ስለሚገኝ በመቸገሩ መሆኑን አስረድቷል፡፡

  በአዋጁ አንቀጽ (23) ድንጋጌ መሠረት ፍርድ ቤቱ የመወሰን ሥልጣን ቢኖረውም፣ ደኅንነት ሲባል የምስክሮች ስም እስከ ውሳኔ ድረስ እንዳይገለጽና በመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ የሚለውን ድንጋጌ ማረጋገጥ እንጂ፣ የእያንዳንዱ ምስክር ስም ዝርዝር ሊደርሰው እንደማይገባ መሆኑን በመግለጽ ተከራክሯል፡፡ በመሆኑም ግልጽ በመሆኑና ለሕዝብ ክፍት ስለሆነ፣ የምስክሮች ደኅንነት ሥጋት ውስጥ ስለሚገባ ማቅረብ እንዳልቻለ አስረድቷል፡፡

  ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ትዕዛዝ የሰጠው ዓቃቤ ሕግ የሚያሻሽለው ማመልከቻ የሚቀርበው ለችሎቱ ሳይሆን ለዳኞቹ መሆኑን አስረድቷል፡፡ እስከ ዕለቱ ድረስ ምንም የቀረበ የምስክሮች ጥበቃ እንደሌለ አስታውቆ፣ ወደፊት ክርክር ተደርጎ የሚወሰን ከሆነ እንደሚታይ አስታውቆ አልፎታል፡፡

  ተከሳሾችና የተከሳሾች ጠበቆችም አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ማመልከቻ ዓቃቤ ሕግ ከ160 በላይ ምስክሮችን የቆጠረ ቢሆንም፣ ማን በየትኛው የሰነድ ማስረጃና ክስ ላይ እንደሚመሰክር ለይቶ ስላልሰጣቸው ለመከራከር አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው አመልክተዋል፡፡ በትዕዛዝ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

  ተከሳሾች በበኩላቸው ይሠሩበት በነበረው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ ይቆጥቡት የነበረ ገንዘብ ሊሰጣቸው ስላልቻለ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ምስክርነት ከሚሰጡበት ሐምሌ 18፣ 19፣ 23፣ 25 እና ነሐሴ 7 እና 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በፊት ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን የክስና የሰነድ ማስረጃ ለይቶ እንዲያቀርብ (እንዲሰጣቸው) ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች ያቀረቡት ጥያቄ በፍትሐ ብሔር የሚታይ በመሆኑ ለጠበቆቻቸው በጽሑፍ በማቅረብ በዚያ በኩል እንዲታይላቸው እንዲያደርጉ አስታውቋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ችሎቱ የሚያየው የወንጀል ድርጊትንና ተያያዥ ጉዳዮችን በመሆኑ እንደሆነ አክሏል፡፡ ምስክሮችን ለመስማት በተያዘው ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...