Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትፋሲል ከተማ በአኅጉራዊ መድረክ ሁለተኛው ተወካይ ክለብ ሆኗል

  ፋሲል ከተማ በአኅጉራዊ መድረክ ሁለተኛው ተወካይ ክለብ ሆኗል

  ቀን:

  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለአሸናፊነት ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል ፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ ቀዳሚ ነበር፡፡ ይሁንና እኩል ግምት የነበረው መቐለ 70 እንደርታ ዋንጫውን አንስቶ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ መሆን የቻለበትን ዕድል አግኝቷል፡፡

  ፋሲል ከተማ በበኩሉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሁለተኛ ደረጃ ባስቀመጠው ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የሚሆንበትን ዕድል ፈጥሯል፣ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡

  የኢትዮጵያ ዋንጫ እንደ ስያሜው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን የሚያሳትፍ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በይበልጥም ዘንድሮ የፕሪሚየር ሊግ ብዙዎቹን ክለቦች ሳያሳትፍ መርሐ ግብሩን በፎርፌ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ባለፈው እሑድ ሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ግማሽ ፍጻሜውን በፎርፌ አልፈው ለፍጻሜው ፋሲል ከተማንና ሐዋሳ ከተማን አገናኝቷል፡፡

  በፍጻሜው ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ ላይ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛው የጨዋታ ጊዜ አንድ እኩል በሆነ ውጤት አጠናቀው አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው መለያ ምት ፋሲል ከተማ 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸናፊ ሆኗል፡፡ በዚሁ ውጤት መሠረትም ፋሲል በሚቀጥለው የውድድር ዓመት ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመጀመርያ ጊዜ ይሳተፋል፡፡

  በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ በመሳተፍ የተሻለ ክብረ ወሰን ያለው ዘንድሮ ወደ ታችኛው (ከፍተኛው) ሊግ መውረዱን ያረጋገጠው የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ነው፡፡ በውጤት ደረጃ አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀዳሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በመድረኩ እስከ ምድብ ድልድሉ መድረሱ ይታወቃል፡፡

  ካፍ እ.ኤ.አ ከ2004 ጀምሮ እያከናወነው የሚገኘው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በመድረኩ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን 1.25 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር፣ ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው 625,000 ዶላር እንዲሁም ግማሽ ፍጻሜና ሩብ ፍጻሜ የሚገቡ ቡድኖች 450,000 እና 350,000 ዶላር ተሸላሚ ሲሆኑ፣ እስከ ምድብ ድልድሉ የሚደርሱ ቡድኖች ደግሞ 275,000 ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ፡፡ በዚህ መሠረት ከኢትዮጵያ ክለቦች እስከ ምድብ ድልድሉ የዘለቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካልሆነ የተቀሩት ክለቦች ተሸላሚ የሆኑበት አጋጣሚ አለመኖሩ የካፍ ድረ ገጽ መረጃ ያመለክታል፡፡

  ብዙዎቹ ክለቦች በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ብዙም ዕውቅና የላቸውም፡፡ ለዚህም ይመስላል፣ ‹‹ክለቦች ለዚህ መድረክ በሚያበቃው የኢትዮጵያ ዋንጫ ብዙም ትኩረት መስጠት አይፈልጉም፤›› የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ‹‹በመድረኩ የሚሳተፉት ክለቦቻችን ተፎካካሪነታቸው የማጣሪያ ማጣሪያውን ካልሆነ ለትልቅ ሽልማት የሚያበቃ ውጤት ስለሌላቸው ትርፉ ድካምና ወጪ ብቻ ነው፤›› ወደሚል ድምዳሜ እንደሚደርሱ ያስረዳሉ፡፡

  ከዚህ በመነሳት ፋሲል ከተማ በኮንፌዴሬሽኑ ዋንጫ በተፎካካሪነትም ሆነ በፋይናንስ ዝግጅት ከወዲሁ ጠንካራ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል ተብሎ በክለቡ ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ ነፃ አገልግሎት ሲሰጡ እንደቆዩ የሚነገርላቸውና ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የቡድኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ፍሥሐ አገኘሁ (ዶ/ር) እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ፋሲል ከተማ ለዚህ ውጤት መብቃቱ እንዳስደሰታቸው በክለቡ ይፋዊ ድረ ገጽ ገልጸዋል፡፡

  ይሁንና ክለቡን ለዚህ ድል ያበቃው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ምንም እንኳን ክለቡም ሆነ አሠልጣኝ ውበቱ በጉዳዩ ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም፣ አሠልጣኝ ውበቱ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ወደ አንዳቸው ሊያመሩ እንደሚችሉ እየተነገረ መሆኑ፣ በኮንፌዴሬሽኑ ዋንጫ ሩቅ ላለመው ፋሲል ከተማ አስቸጋሪ እንደሚሆን የሚናገሩ አልጠፉም፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...