ከአንድ ዓመት በፊት ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል ጅግጅጋና ሌሎች ከተሞች ላይ በተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ማጉደሎች፣ የአብያተ ክርስቲያናትና የንግድ ተቋማት ቃጠሎ፣ ማፈናቀሎችና የተለያዩ ወንጀሎች ክስ የተመሠረተባቸው የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣ ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ ባቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ እንደሚያቀርቡ ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡
ተከሳሹ አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር በተሻሻለባቸው ክስ ላይ መቃወሚያቸውን ማቅረብ የነበረባቸው ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ ጠበቆቻቸው ባለመቅረባቸው ሳያቀርቡ ቀርተዋል፡፡ አቶ አብዲ ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን በአግባቡ የማይሰማቸው ከሆነ ጠበቃ እንደማያስፈልጋቸው ቀደም ብሎ በነበረ ችሎት ላይ ተናግረው ስለነበር፣ ጠበቆቹን ባሉት መሠረት አሰናብተዋቸው ይሁን በሌላ ምክንያት መሆኑ ባይታወቅም በዕለቱ አልቀረቡም፡፡
ተከሳሹ ከጠበቆቻቸው ጋር በተሻሻለው ክስ ላይ ስለሚያቀርቡት መቃወሚያ ሲነጋገሩ እንደነበር ጠቁመው፣ በዕለቱ ለምን ሳይቀርቡ እንደቀሩ እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡ በድጋሚ ተነጋግረው መቃወሚያቸውን እንደሚያቀርቡም አስታውቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን ምላሽ ከሰማ በኋላ መቃወሚያቸውን እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ እንዲያቀርቡ፣ ዓቃቤ ሕግም ለመቃወሚያው ምላሽ ካለው እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመንገር መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሌላው የሰጠው ትዕዛዝ በተመሳሳይ መዝገብ ክስ ተመሥርቶባቸው እጃቸው ያልተያዙ ሰባት ሰዎች ክርክሩ በሌሉበት እንዲታይ፣ ለአምስት ሰዎች ደግሞ የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡