Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናልማት ባንክ በዋስትና የያዘውን ቦታ የቤኒሻንጉል ጉምዝ አስተዳደር ለሌላ ድርጅት መስጠቱን ተቃወመ

  ልማት ባንክ በዋስትና የያዘውን ቦታ የቤኒሻንጉል ጉምዝ አስተዳደር ለሌላ ድርጅት መስጠቱን ተቃወመ

  ቀን:

  ብድር የወሰደው ጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል ሕገወጥ ድርጊት ተፈጽሞብኛል ብሏል

  የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባህር ዳር ዲስትሪክት ለጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በብድር ለሰጠው 7.3 ሚሊዮን ብር በመያዣነት የያዘውን 114.9 ሔክታር ቦታ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ 20 ሔክታር በመቀነስ ለሌላ ድርጅት መስጠቱን ተቃወመ፡፡

  ባንኩ ላበደረው 7,375,001 ብር ዋስትና የያዘው የማዕድን ቦታ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን፣ በቡላን ወረዳ ልዩ ስሙ ቱሉ ሞዬ በሚባል አካባቢ ስፋቱ 19.9 ሔክታርና በተመሳሳይ ወረዳና ልዩ ስሙ አከን በሚባል አካባቢ ስፋቱ 95 ሔክታር የሆነ የማዕድን ቦታ መሆኑን፣ ባንኩ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምስተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ያስረዳል፡፡

  ክርክሩ የተጀመረው የተጠቀሱትን የማዕድን ቦታዎች በሊዝ ወስዶ ብዙ የልማት ሥራዎች ማከናወኑን የሚናገረው ጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መካከል እንደነበር፣ ለፍርድ ቤት ያቀረቧቸው የአቤቱታ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

  ጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል በክልሉ የእምነበረድ ማዕድን ፈልጎ ወደ ልማት ለመግባት በ1994 ዓ.ም. ፈቃድ ሲጠይቅ፣ የክልሉ አስተዳደር እንደ ፈቀደለትና በ200 ሔክታር ቦታ ላይ ምርምር ማድረጉን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ድርጅቱ ባደረገው የምርምር ፍለጋ በ59 ሔክታር ቦታ ላይ ማዕድኑን በማግኘቱ፣ በ1996 ዓ.ም. የማልማት ፈቃድ ጠይቆ እንደተሰጠውም ይጠቁማል፡፡ በመሆኑም ልማቱን ሲጀምር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባህር ዳር ዲስትሪክት ጋር ጥቅምት 30 ቀን 1997 ዓ.ም. የመጀመርያውን የብድር ስምምነት ማድረጉንና ጥር 13 ቀን 2002 ዓ.ም. ደግሞ ሁለተኛ ውል በመፈጸም፣ በአጠቃላይ 7,375,001 ብር መቀበሉን ድርጅቱ ለፍርድ ቤት ያቀረበው ሰነድ ያሳያል፡፡ ባንኩ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ሲያበድር ድርጅቱ ደግሞ አከን (የተራራ ስም ነው) አንድና ሁለት በሚባለው ቦታ ላይ የወሰዳቸውን፣ እንዲሁም ቱሉ ሞዬ ላይ የወሰደውን ቦታ በድምሩ 114.9 ሔክታር መሬት በመያዣነት መያዙን ክሱ ያብራራል፡፡

  ልማት ባንክ ወደ ፍርድ ቤት እንዲያመራና ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር ያደረገው፣ የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል አልምቶ የእምነ በረድ ምርት የሚያመርትበት ቦታ ላይ 20 ሔክታር በተደራቢነት ለቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. በመስጠቱ መሆኑን ባንኩ ያቀረበው መከራከሪያ ሰነድ ያሳያል፡፡ ጢስ ዓባይ የኤጀንሲውን ድርጊት በመቃወም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የመሠረተ ቢሆንም፣ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ‹‹ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሱን የማየት ሥልጣን የለውም›› ብሎ በመከራከሩ፣ ፍርድ ቤቱ በክርክሩ ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ እያለ ልማት ባንክ ጣልቃ ገብቷል፡፡

  ልማት ባንክ ቦታውን በመያዣነት እንደያዘውና ተበዳሪው ድርጅት ከፍሎ ሳይጨርስ ቦታውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት እንደማይችል፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 423/2010 እና የክልሉን ደንብ ቁጥር 117/2010 በሥራ ላይ ከመዋላቸው በፊት በመያዣነት የያዘው በመሆኑ፣ ተበዳሪ ድርጅት ከፍሎ እስኪያጠናቅቅ ድረስ ቦታው ተከብሮ እንዲቆይለት የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ማረጋገጫ እንደ ሰጠውም አስታውሷል፡፡ የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ በሰጠው የዋስትና ደብዳቤ ተማምኖ ብድሩን እንደለቀቀም አክሏል፡፡

  የልማት ባንክ የመያዣ መብት የተቋቋመው የተጠቀሱት ደንቦች ከመውጣታቸው በፊት በመሆኑ፣ አዲስ የወጡ ደንቦች ወደኋላ ሄደው ተግባራዊ ሊደረጉ እንደማይችሉ በማስታወስ፣ በመያዣነት ከያዘው ቦታ ላይ 20 ሔክታር ቀንሶ መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ መብቱ ሊከበርለትና ሊታይለት የሚገባው ደግሞ በወቅቱ በሥራ ላይ የነበረው የፌዴራል ደንብ ቁጥር 182/96 እና በክልሉ ደንብ ቁጥር 86/2007 መሠረት መሆኑን በማውሳትም ተከራክሯል፡፡ በመሆኑም ተበዳሪ ተቋሙ የባንኩን ብር ከፍሎ መጨረሱ ሳይረጋገጥ በዋስትና ከተያዘው ቦታ ላይ መቀነስ እንደማይቻልም አስረድቷል፡፡

  የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ያለ ባንኩ ፈቃድና ስምምነት ከቦታው ቀንሶ ለሌላ ተቋም ለመስጠት መወሰኑ፣ በመብቱ ላይ መተኪያ የሌለው ጉዳት እንደሚያደርስበትም ጠቁሟል፡፡ የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ውሳኔ ተገቢነት የሌለውና የሕዝብ ሀብት በሆነው ልማት ባንክ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑንም አስምሮበታል፡፡

  ጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል ከተበደረው ገንዘብ ውስጥ 3,916,104 ብር ዕዳ እንዳለበት፣ የብድር መክፈያ ጊዜውን እስከ ግንቦት 31 ቀን 2021 ዓ.ም. ያራዘመ በመሆኑ፣ ኤጀንሲው የብድር ዘመኑ እንዳለበፈበት በመጥቀስ ሊከራከር መነሳቱ ተገቢነት የሌለው መሆኑንም አስረድቷል፡፡ 

  ተበዳሪው ድርጀት፣ ኤጀንሲውና የእምነበረድ ማዕድን ቦታ በተደራቢነት የተሰጠው ቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ድርጅት መካከል ያለው ክርክር ብይን ሳያገኝ፣ ኤጀንሲው ለጢስ ዓባይ የዕግድ ደብዳቤ በመጻፉና ሥራውን በማስተጓጎሉ፣ ፍርድ ቤቱ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቶ  ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ያወቁት ዳይሬክተሩ፣ ከሳሾች አቤቱታቸውን እንዲያነሱ በመጠየቅ እሳቸውም የተጻፈው ዕግድ ቀሪ እንዲሆን በማድረጋቸውን፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንደቀሩና ትዕዛዙም መታለፉ ታውቋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያቀረበውን ጣልቃ ገብቶ የመከራከር መብት ፈቅዶ፣ በጉዳዩ ላይ ክርክር ከመደረጉ በፊት፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ሥልጣን አለው? ወይስ የለውም?›› በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡    

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...