ከወርዋሪዎቹ ውስጥ አንዱ በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሏል
ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ 22 ሰዎች ተለቀዋል
በአዲስ ዓመት መስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት እስከ 2፡00 ሰዓት በሚገመት ጊዜ ውስጥ፣ በቡራዩ ከተማ የኦሮሚያ ልዩ የፖሊስ ኃይል ማረፊያ ቤት (ካምፕ) ውስጥ ቦምብ የወረወሩት የኦነግ ታጣቂ ቡድን (ሸኔ) መሆኑ ተገለጸ፡፡
በተወረወረው የቦምብ ጥቃት በስምንት የፖሊስ አባላትና በአንዲት ምግብ አዘጋጅ ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አንድ ተጎጂ ጉዳቱ በደረሰበት አካባቢ ባለ መለስተኛ ክሊኒክ ዕርዳታ ተደርጎለት ወደ ካምፕ የተመለሰ ሲሆን፣ ስምንቱ ተጎጂዎች ፖሊስ ሆስፒታል ተወስደው እየታከሙ መሆኑንም አክለዋል፡፡ የደረሰባቸው ጉዳት ቀላል የአካል ጉዳት በመሆኑ ለክፉ እንደማይሰጥም ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቦምቡ እንደተወረወረ በአካባቢው የሚገኙ 22 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር፡፡ ጉዳዩ በምርመራ ሲጣራ ተጠርጣሪዎቹ ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለቸው በመታወቁ፣ ከእስር መፈታታቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱን የፈጸሙት የኦነግ ታጣቂ ቡድን (ሸኔ) መሆኑ እንደተደረሰበትና አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡ ሌላኛው ታጣቂ በማምለጡ የፀጥታ ኃይሎች ክትትል እያደረጉበት መሆኑን አክለዋል፡፡