በተመስገን ተጋፋው
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሥር ሺሕ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ አረጋውያንን ለመርዳት ዝግጅት መጨረሱን አስታወቀ፡፡
‹‹የዕድሜ ባለፀጎችን በመደገፍ እንመረቅ›› በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 18 እስከ መስከረም 20 አረጋውያንን ለመርዳት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን እንደሚዘጋጁ መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዝመን ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል፡፡
ፕሮግራሙም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ እንደ ሚከናወን ታውቋል፡፡ በዕለቱ የክብር ተምሳሌት እንዲሆን የአረጋውያን እግር ይታጠባል ተብሏል፡፡ የሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በዝግጅቱ ላይ አረጋውያን ምርቃት እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ አክለውም በኢትዮጵያውያን የዕድሜ ባለፀጎች የተሠሩ ሥራዎችን የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚብሽን እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡
ከመስከረም 18 እስከ 20 ባሉት ቀናት ውስጥ ለአረጋውያን ብቻ ነፃ የትራንስፖርትና የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡ ጤናን ከመጠበቅ አኳያ አቅመ ደካማ ለሆኑ አረጋውያን ትኩረት ሰቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ እንድትደርስ ትልቁን ሚና የተጫወቱ የአገር ባለውለታ አረጋውያን እንደሆኑ፣ በአሁኑ ሰዓት ግን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ወድቀው የሚገኙ ብዙ እንደሆኑ፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ትልቅ ሥራ እንደሚሠራ ሚኒቴር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡
በፊት የነበረውን የመከባበር እሴት ወደ ነበረበት ለመመለስ ይህ ንቅናቄ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎችና አርቲስቶች በጋራ በመሆን አረጋውያንን ለመርዳት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንና ወደፊትም ዘላቂ ሥራዎችን እንደሚሠሩም ታውቋል፡፡
ቁሳቁሶችንና አልባሳትን መደገፍ ለሚፈልጉ ሰዎችም በአምስት ቦታዎች ላይ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ጣቢያዎችን መቋቋማቸውን ተናግረዋል፡፡ ጣቢያዎች በመገናኛ፣ በሜክሲኮ፣ በፒያሳ በመስቀል አደባባይና በካሳንችስ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡም አረጋውያንን በመደገፍም አጋርነቱን ማሳየት አለበት በማለት ሚኒስቴር ዴታዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሥራው የሚከናወነው በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልል ከተሞች ላይ እንደሆነ የማኅበራዊ ደኅንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀንበር ተናግረዋል፡፡ በአሁን ሰዓት ግን በዋናነት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋውያንን ለመርዳት በግልም ሆነ በመንግሥት እየተንቀሳቀሱ የሚሠሩ ድርጅቶችን በመጎብኘት የተለያዩ ክትትሎች በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አቶ ፈለቀ ተናግረዋል፡፡ ይኼ ሥራም ለወደፊት ቀጣይነት እንዳለውና መንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋውያንን መሠረታዊ ፍላጎቶችን በማሟላትና በመርዳት የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አረጋውያን የአገር ባለውለታ በመሆናቸው ትኩረት ፍቅር፣ እንክብካቤንና አክብሮት እንዲያገኙ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አረጋውያን ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ ተናግረዋል፡፡ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍም በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ዘርፍ ከሚያከናውናቸው ዓብይ ተግባራት አንዱ የመደጋገፍና የመረዳዳትን መልካም እሴት የሚያጠናክሩ ተግባራትን ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡