Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናኢዜማ ሕዝብን ለሁከት ያነሳሱ ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀ

  ኢዜማ ሕዝብን ለሁከት ያነሳሱ ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀ

  ቀን:

  ለጥቅምት 22 ሕዝባዊ ስብሰባ ጠርቷል

  ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 13 እና 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ለደረሰው ጥፋት መነሻ ከሆነው ‹‹ተከብቤያለሁ›› በማለት ለመንግሥት አካል ማሳወቅ ሲገባው ወደ ሕዝቡ መረጃ ካሠራጨው ግለሰብ ጀምሮ፣ በየደረጃው በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ያደረሱ ሰዎች በሙሉ ለፍርድ ሊቀርቡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ጠየቀ፡፡

  ፓርቲው ይህን ጥያቄ ያቀረበው ማክሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለቀረበለት አገርን የማዳን ጥሪ በኅብረት መልስ መስጠት የሚገባው ወቅት ዛሬ ነው፤›› በሚል ርዕስ፣ በዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡

  በሁሉም ዜጎች መስዋዕትነት የተገኙ ድሎችን ወደ ራስ የመጠቅለልና የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል በሌሎች ወገኖች ላይ የመጫን ጉዳይ፣ ዛሬም ዓይኑን አፍጥጦ እየመጣ ነው በማለት ኢዜማ ሥጋቱንም ገልጿል፡፡

  ‹‹ዜጎች በእኩልነትና በወንድማማችነት መንፈስ መቆማቸውን የተመለከቱ የዘውግ ፖለቲካ ነጋዴዎች ጣዕረ ሞት ላይ መሆናቸውን በሚያሳይ ሁኔታ ተንፈራግጠዋል፡፡ የዚህም የመጨረሻ ማሳያዎች ለችግሩ የዘርና የእምነት ይዘት ለመስጠት መታተራቸው ነው፤›› በማለት፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታም ገልጾታል፡፡

  የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር፣ የመሠረት ልማትና የሥራ ዕድል ጥያቄዎች፣ መመለስ ያልቻሉ የመንግሥት ሹመኞች ጭምር፣ ይህን የዘር በሽታ እያራጋቡ መሆናቸውን መታዘቡንም ፓርቲው ገልጿል፡፡

  በመሆኑም እንዲህ ባለ እንቅስቃሴ የተሳተፉ ግለሰቦች ለፍርድ ይቅረቡ በማለት ፓርቲው ጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ለዜጎች ሞት ደንታ የሌላቸውና በግጭት የሚነግዱ የማኅበራዊ ድረ ገጽና የተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ሕዝባችንን ለሌላ ተከታታይ ግጭቶች ከመዳረጋቸው በፊት፣ ሥልጣን በተሰጠው አካል የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ፤›› በማለት ጠይቋል፡፡

  በችግሩ ምክንያት በየአካባቢው በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉ፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙና በአስቸኳይ መልሰው እንዲቋቋሙ፣ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ፈጽሞ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳና የፀጥታ ኃይሉን ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያረጋገጠ እንዲሆንና ጥንቃቄ እንዲደረግ በማለትም አሳስቧል፡፡

  እንደ ማኅበረሰብ አቀፍ ዓይነት አደረጃጀቶች በአስቸኳይ ተዘርግተው፣ ሕዝቡ ራሱን መጠበቅ የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ኢዜማ አሳስቧል፡፡

  እስካሁን ለተፈጸሙት ሕገወጥ ድርጊቶች መንግሥት አስተማሪ ዕርምጃ ባለመውሰዱ፣ ሕዝብ መንግሥትን ተጠያቂ እያደረገ እንደሆነ የገለጸው ፓርቲው፣ ‹‹የመንግሥት ኃላፊነቱን አለመወጣት ደግሞ ሕዝቡ ተደራጅቶ ራስን ወደ መከላከል ደመነፍሳዊ ሁኔታ ይገፋዋል፡፡ ይህም ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት የእርስ በርስ ዕልቂት ይከተናል፤›› በማለት፣ መንግሥት ኃላፊነቱን ካልተወጣ ከፍተኛ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል ሥጋቱን አስታውቋል፡፡

  ከዚህ ጋር በተያያዘም ፓርቲው ቀደም ሲል በያዘው ዕቅድ መሠረት ጥቅምት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ከአዲስ  አበባ ሕዝብ ጋር ለመወያየት ሕዝባዊ ስብሰባ ማዘጋጀቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህን ዕቅዱንም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ማስታወቁን ገልጿል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...