Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የመንግሥትን ዕርምጃ የሚማፀኑ ድምፆች

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 13 እና 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና በአዲስ አበባ በተፈጠረ ግጭት የ67 ዜጎች ሕይወት ሲያልፍ፣ በበርካታ ግለሰቦች ንብረት ላይ ውድመት ደርሷል፡፡ በርካቶችም የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ሰለባ ሆነዋል፡፡

  ይህን ክስተት ተከትሎ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስርን ጨምሮ በርካቶች የአገሪቱ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደገባ በማውሳት፣ መንግሥት ዝምታውን ሰብሮ አፋጣኝና አስተማሪ ዕርምጃ እንዲወስድ በመወትወት ላይ ናቸው፡፡

  ከዓመት ከስድስት ወራት በፊት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በፓርቲያቸው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የተመረጡት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በሥራ ዘመናቸው የመጀመርያ ወራት በሚያደርጓቸው ንግግሮች የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችለው የነበረ ሲሆን፣ ከንግግራቸውም በመነሳት በርካቶች ጊዜ ተሰጥቷቸው ያሰቡትን ይተገብራሉ የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡

  አሁን ግን ብዙዎች የሰነቁት ተስፋ ሲገመገም የበርካቶች ተስፋ ወደ ሥጋት መቀየሩን የሚያሳዩ አስተያየቶችን መታዘብ ይቻላል፡፡ ለዚህ አንድ ማሳያነት የሚጠቀሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ‹‹በሆደ ሰፊነት›› አጥፊዎች ላይ ዕርምጃ አለመውሰዱን በማውሳት ነው፡፡

  በበርካቶች ዘንድ መንግሥት አጥፊዎችን እስከ መቼ ነው ዝም የሚለው? ጥፋተኞችን ለመቆጣጠርስ መንግሥት እጁን የሚያስገባው የጥፋት መጠኑ ምን ያህል ሲሆን ነው? መንግሥት ኃላፊነት ያለባቸውን ግለሰቦች ወደ ፍትሕ አደባባይ ለማምጣት የምን ያህል ሰዎች ሕይወት ማለፍ አለበት? ምን ያህል ንብረትስ መውደም አለበት? የሚሉ ጥያቄዎች የሚሰነዝሩ በርካቶች ናቸው፡፡

  ከዚህ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጧቸው መግለጫዎችና ማብራሪያዎች በማሰርና በመግደል የሚሰፍን ዴሞክራሲ እንደማይኖር በመግለጽ፣ ስለዚህ ከዚህ ቀደም ከነበረው አካሄድ በመውጣት አገሪቱን ወደ የሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በትዕግሥትና በሰከነ መንፈስ ሥራዎች ሊከናወኑ እንደሚገቡ በመግለጽ ተሰፋው እንዳይጠፋ ጥረት ሲያደርጉ ይታያል፡፡

  በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን ባለፈው ሳምንት የተፈጠረው ክስተት ነገሩን ወደ ሌላ ደረጃ አሻግሮ በርካቶች ስለአገር ህልውና የመቀጠል ጉዳይ ላይ ተጠምደው አስተያየት እንዲሰጡ አስገድዷል፡፡ ከዚህ ባለፈም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መድረኮች አገሪቱ የማትወጣው አረንቋ ውስጥ እየገባች በመሆኑ፣ መንግሥት በአስቸኳይ ኃላፊነቱን እንዲወጣና በአገሪቱ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ በአስቸኳይ ዕልባት እንዲሰጠው የሚጠይቁ ድምፆች ተበራክተዋል፡፡

  በማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መድረኮች ያለውን ውትወታ በተመሳሳይ መንገድ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች በመጋራት፣ መንግሥት አስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁና የሚወተውቱ ድምፆችም እንዲሁ ተበራክተዋል፡፡

  በተለይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች የሚሰጡት አስተያየቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት ለመረዳት ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ካለፈው ሳምንት ክስተት በኋላ አስተያየታቸውን የሚሰጡት የፖለቲካ አመራሮች ያሉዋቸውን ፖለቲካዊ ልዩነቶች ለጊዜው ወደ ጎን በማድረግ፣ የአገሪቱን ሰላምና ደኅነንት ለማስጠበቅና የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመመከት በጋራ መሥራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ ቅድሚያ ለአገር አንድነት፣ ሰላምና ደኅንነነት መስፈን በጋራ መሥራት እንደሚገባ ውትወታ ውስጥ ገብተዋል፡፡

  በዚህ ሁሉ ውትወታ ውስጥ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች በሚያሰኝ ሁኔታ የመንግሥት ጠንካራ ዕርምጃ አስፈለጊነትን በአጽንኦት የሚገልጹ ሲሆን፣ ለዚህም በተለያዩ መንገዶች መልኩ ለመተባበር ዝግጁነታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡

  በዚህ ጉዳይ ላይ ማክሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለቀረበለት አገርን የማዳን ጥሪ በኅብረት መልስ መስጠት የሚገባው ወቅት ዛሬ ነው፤›› በሚል ርዕሰ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ በአገሪቱ  ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና  ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ጉዞ የተቃና እንዲሆን፣ ከመንግሥት ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡

  በመግለጫው ወቅት የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይኑን ከዋናው ጉዳይ ላይ እንዲያነሳ፣ ማለትም ለመጀመርያ ጊዜ በታሪኩ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠርና ራሱ በመረጠው ሕዝብ መተዳደር የመፈለጉን ሒደት ረስቶ በደመነፍስ ራስን ለመከላከል ብቻ ያንን ቁም ነገር እንዲተወው ለማድረግ የታሰበ ነገር ሊሆን ይችላል፤›› በማለት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩት አለመረጋጋቶች ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገውን ጥረት የማደናቀፍ ሙከራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ይህ ሆን ተብሎ ዴሞክራሲ መሬት እንዳይረግጥና ሕዝቡ በነፃነት የሚፈልገውን እንዳይመርጥ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው፤›› ሲሉም የክስተቱን አጠቃላይ ፖለቲካዊ ዓውድና አንድምታ አስረድተዋል፡፡

  ክስተቱን የአገር አንድነትን ለመበጠስ ከተሰነዘረ ጥቃት አንፃር የተመለከቱት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ ሲሆኑ፣ ‹‹በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ትስስሩ ጠንካራ ስለሆነ የአንድነታችን ገመድ አልበጠስም ብሎ ነው እንጂ፣ ክስተቱ አንድነታችንን ለመበጠስ የተሠራ ነው፤›› በማለት፣ ክስተቱ ከፖለቲካዊ አንድምታው ይልቅ አገራዊ ህልውናን የሚፈታተን፣ እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት አደጋ ውስጥ ለመክተት የተፈጸመ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

  በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ (ኢሀን) ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፣ ‹‹ላለፉት በርካታ ዓመታታ እንደተሠራበትና ኃላፊነታችንን እንዳለመወጣታችን መጠን፣ ሕዝቡ በሥርዓት መኖሩ አሁንም አለመርፈዱን ያሳያል፡፡ ሌላ አገር ቢሆን ይኼኔ ግልብጥብጥ የሚልበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡ መከራን ተሸክሞ ነገን በተስፋ ማየት ባህላችን ነው፤›› ብለው፣ የተከሰቱት ነገሮች የሕዝቡ በሥርዓት መኖር ባይታከልበት ኖሮ ለአገሪቱ ህልውና አደጋ ሊሆን የሚችሉ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

  ይህን የሕዝቡን ባህል ማክበር በአገሪቱ ህልውና ላይ የተጋረጡ ፈተናዎችን ለማለፍ ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን ከመግለጽ ባለፈ ግን፣ ባለፈው ሳምንት የሆነው ነገር ለዓመታት በይደር ቆይተው ሲንከባለሉ የመጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ማሳያ እንደሆኑ በመግለጽ፣ ‹‹የጋራ አገራዊ ራዕይ አለመኖር ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ምንጭ ነው፤›› በማለት፣ የአንድነት መንፈስ መላላቱ ከነበሩት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ ጥያቄዎች ጋር ተዳብለው የፈጠሩት ችግር ነው በማለት ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡

  ከዚህ ባለፈም፣ ‹‹ከዚህ ቀደም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ይሰጡ ከነበሩ አስተያየቶች ተነስተን ከገመገምነው፣ ያለፈውን ሳምንት ክስተት ባልተጠበቀ ሁኔታ የተፈጠረ አናስመስለው፡፡ የሆነውም ነገር ታቅዶ የተሠራ እንደሆነ ነው የማስበው፤›› ሲሉም፣ ከዚህ ቀደም በነበሩ ንግግሮችና ግብሮች ላይ ምንም ዕርምጃ አለመወሰዱ እዚህ እንዳደረሰው  ገልጸዋል፡፡

  የተለያዩ ፖለቲከኞችና ልሂቃን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ሥልጣን ከያዘበት ዕለት አንስቶ የፍኖተ ካርታን አስፈላጊነት በማውሳት መንግሥት በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ምን ሊሠራ እንዳቀደ ሊያሳውቀን ይገባል የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

  ከዚህ አንፃር በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችንና አለመረጋጋቶችን እንዳይከሰቱ ለማድረግ አቅም ሊኖረው ይችላል የተባለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ አለመኖር አሁንም ጥያቄ መሆኑን ቀጥሏል፡፡

  ባለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ ወገኖች የሚነሳው ሌላው ጥያቄ ደግሞ፣ መንግሥት ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ የውይይትና የድርድር መድረክ እንዲፈጥር የሚጠይቅ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት መድረክ እንዲፈጠር የሚጠይቁ ወገኖች ዋነኛ መከራከሪያቸው፣ በውይይትና በድርድር ነጥረው የሚወጡ ጥያቄዎችን በየፈርጁ በመሰደር ለአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ያስችላል የሚል ነው፡፡

  አሁን በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ለማርገብም ቢሆን አንዱ መፍትሔ ሊሆን የሚገባው የጋራ የሆነ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ይልቃል ሲሆኑ፣ ‹‹የጋራ መግባባት የተደረሰበት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀት አለበት፡፡ ይህም የወደፊቱን ሁኔታ እንዴት እንደምንሄድበት የሚያመላክት መሆን ይኖርበታል፤›› ይላሉ፡፡ አሁንም በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመጀመርና ለመሥራት አለመርፈዱን በማውሳት፣ መንግሥት ለዚህ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  መፍትሔው ምንድነው?

  የባለፈው ሳምንት ክስተትን ጨምሮ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አመረጋጋቶች ሲከሰቱ፣ የዜጎች ሰላምና ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ በገባበት ጊዜ የበርካቶች ጥያቄ መንግሥት ወዴት አለህ የሚል ነበር፡፡

  አሁንም ቢሆን የመንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ ከተጋረጠው የህልውና አደጋ አንፃር ወሳኝ መሆኑን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር አቶ ሙሉጌታ፣ ‹‹ከዚህ ዓይነት የችግር አዙሪት ለመውጣት በመጀመርያ መንግሥት መንግሥትን መሆን መቻል አለበት፡፡ በዚህም መሠረት ከንግግር ባለፈ ሕግን መሠረት አድርጎ የዜጎችን ሕይወት መጠበቅና አጥፊዎችንም በሕጋዊ መንገድ ተጠያቂ ማድረግ አለበት፤›› ብለው ዋነኛው የመፍትሔው አካል መንግሥት መሆኑን በመጥቀስ፣ መንግሥትም ይህን ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  እንደ እሳቸው አተያይ ሁለተኛው የመፍትሔ አቅጣጫ ደግሞ መንግሥት ወይም እከሌ ይሥራው ማለትን በመተው፣ ሁሉም ወገኖች አገራዊ ዕርቅ የሚሰፍንበት ነገር ላይ መሥራት እንደሚገባቸው ያሳስባሉ፡፡ ይህ ጉዳይ ፖለቲካዊ ሳይሆን አገራዊ እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹ከዚህ እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ ትርፍ አገኛለሁ የሚል አካል ካለ ርካሽ ነው፡፡ አገር እየፈረሰ ፖለቲካዊ ትርፍ አገኛለሁ ማለት ሞኝነት ነው፤›› በማለት፣ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በመጠየቅ መንግሥትም እንዲህ ዓይነት አካሄዶችን የሚፈቅድ አገር አቀፍ ጥሪ ማቅረብ እንደሚኖርበት በማሳሰብ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

  በተመሳሳይ ሁለት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ሲሆኑ፣ የመጀመርያው መፍትሔ ‹‹ኅብረተሰቡ ራሱን ሊከላከል የሚችልበትና አካባቢውን የሚጠብቅበት የማኅበረሰብ ፖሊስ፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት እንደነበረው በሰላምና በመረጋጋት ዓይነት  ተደራጅቶ ራሱን እንዲጠብቅና እንዲከላከል ማድረግ፤›› የሚል ነው፡፡

  ሁለተኛው የመፍትሔ አቅጣጫ ደግሞ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ከምንም ነገር በላይ መጠበቅ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹መንግሥት ኃላፊነቱን መወጫ ጊዜው አሁን ነው፡፡ እኛ እንደ ድርጅት ከኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በላይ ምንም የሚመለከተን ነገር የለም፡፡ ይህ ነገር የሥልጣን ወይም ማን የበላይነት ይያዝ የሚል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ አገርን የማዳንና በሰላም ወደሚቀጥለው ምዕራፍ አገርን ማሸጋገር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ጋር በምንም መልኩ እንተባበራለን፤›› በማለት፣ መንግሥት የተጠናከረ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባውና ፓርቲያቸውም ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

  በተለያዩ መድረኮች ፖለቲከኞችና ልሂቃን አገሪቱ ከገጠማት ችግር ትወጣ ዘንድ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ እንዲሁም አስቸኳይ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ነው፡፡ መንግሥት እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች የሚሰጠውን ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችልም የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡ መንግሥት ሆይ ወዴት አለህ ሲሉም ይጣራሉ፡፡   

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -