Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትሀብት ክፍፍል ላይ ያተኮረው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ

  ሀብት ክፍፍል ላይ ያተኮረው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ

  ቀን:

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኅዳር 28 እና 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በግራንድ ኤሊያና ሆቴል ባካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ተቋሙ ለክልልና ለከተማ አስተዳደር ፌዴሬሽኖች በሚደጉመው የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ላይ ካልሆነ፣ የአትሌቲክሱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሚወስኑ ስትራቴጂዎችና አሠራሮች ጊዜ ወስዶ ሲከራከር፣ ወቅቱን የሚመጥን ሐሳብ በማፍለቁ ረገድም ቢሆን ጉባዔው ግልጽ የአቅም ውስንነት የታየበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡

  ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለጉባዔው የሁለት ቀን ውሎ ከያዛቸው አጀንዳዎች፣ የፌዴሬሽኑ የ2011 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ይጠቀሳል፡፡ መደበኛ ዓመታዊ ጠቅላላ በዋናነት እንደነዚህ የመሰሉ ሪፖርቶች የስፖርቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ እንደመሆናቸው መጠን እንደየ ውድድሩ ባህሪና ዓይነት ከውጤት መገለጫው ጭምር በጥልቀት ሊታይ የሚገባው መሆኑ ይታመናል፡፡ ይሁንና በዚህ ረገድ ጉባዔውን “ጉባዔ” ሊያስብል በሚችል መልኩ ሐሳቦችንና አስተያየቶችን ሲያንሸራሸሩ የተስተዋሉት በጣት የሚቆጠሩ የክልል ፌዴሬሽን ተወካዮች ነበሩ፡፡

  ያለፈው የውድድር ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ለጉባዔው ከቀረበ በኋላ፣ የነበረበትን ጠንካራና ደካማ ጎን እንዲሁም በሪፖርቱ ሊካተት ይገባው ነበር ተብሎ ከተነገረው በጥቂቱ፣ ሪፖርቱ የአስተዳደራዊ ሥራ የሚበዛበት መሆኑ፣ በስፖርቱ የሚገኘውም ሆነ የሚመዘገበው ውጤት የሚታይና የሚዳሰስ በመሆኑ በየውድድር ዓይነቱ በዝርዝር ሊቀመጥ እንደሚገባው፣ ሪፖርቱ በዚህ ረገድ ሲታይ በጥቅል መቅረቡ ትክክል አለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

  ስፖርቱን ሊያሳድግ በሚገባው መልኩ ማለትም አትሌቲክስ ሲባል በውስጡ ብዙ ዓይነት ውድድሮች መሆናቸው ግምት ውስጥ ገብቶ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የተሻለ ውጤት ሲባል በማራቶን፣ በረዥም ርቀት አልያም ደግሞ በመካከለኛ የሚለውን ሪፖርቱ እንደማያሳይ፣ አትሌቲክሱ በአሁኑ ጊዜ እንደ ላለፉት ዓመታት የትርፍ ጊዜ ሥራ እንዳልሆነና ሙሉ ጊዜ ተሰጥቶት መሠራት እንደሚገባው የሚያሳይ በዝርዝር ያስቀመጠው ምንም ዓይነት ነገር የሌለው ስለመሆኑ አያመላክትም ብለውታል፡፡

  አትሌቲክሱን በሚመለከት የመንግሥት ሚናና እገዛ ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲመጣ በአትሌቲክሱ የሚመዘገበውን ውጤት ብቻ መነሻ እያደረገ ሽልማት ከማዘጋጀት ባለፈ፣ ስፖርቱ ወቅቱን የጠበቀ አደረጃጀት ይኖረው ዘንድ ማድረግና ማገዝ ስለሚገባውም ሪፖርቱ አያመላክትም ሲሉ ተችተውታል፡፡ ምክንያቱም ስፖርቱ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሁሉም አገሮች ዘርፉ ጊዜውን በሚመጥን መልኩ እንዲዋቀርና እንዲደራጅ በማድረግ የተፎካካሪነት አቅማቸውን እያሳደጉ መሆኑ፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከሚያደርገው የዕለት ዕለት እንቅስቃሴ ውጭ እንደ ባለድርሻ ከመንግሥትም ሆነ፣ ከሚመለከታቸው የክልል ፌዴሬሽኖች ይህ ነው የሚባል ድጋፍና ክትትል እንደማይደረግለት፣ ለዚህ ደግሞ ፌዴሬሽኑ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ወሳኝነት እንደሚኖራቸው ጭምር ተነግሯል፡፡

  ከዓምናው የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባልተናነሰ፣ ፌዴሬሽኑ በ2012 የውድድር ዓመት የሚከውነውን ዕቅድ አቅርቧል፡፡ ዕቅዱ ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ሊካተቱ የሚገባቸው ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት የጉባዔውን ግብዓት ቢፈልግም፣ ለዕቅዱ የሚመጥን ነገር ሲቀርብ አለመደመጡ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡ ይሁንና ተቋሙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚሰጣቸውን የዓይነትና የገንዘብ ድጋፎችን በሚመለከት ግን ከሁሉም አቅጣጫ የተቋሙ ሀብት ከየትና እንዴት ይገኛል የሚለውን ጉባዔው በውል የተረዳው ባይመስልም የሀብት ክፍፍሉ ላይ ትዝብትን ያጫሩ ሐሳቦች ሲንፀባረቁ ተስተውሏል፡፡

  ከሁለቱ አጀንዳዎች ጎን ለጎን የጉባዔውን ትኩረት ከሳቡት ሌሎች አጀንዳዎች መካከል፣ አትሌቲክሱ የሀብት ምንጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙዎቹ አትሌቶች በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገርን ከመወከል ይልቅ በግል ለሚደረጉ ውድድሮች ፍላጎት እያሳዩ የመጡበት ሁኔታ ይጠቀሳል፡፡ ጉባዔው ለዚህ አጀንዳ እንደ ምክንያት የጠቀሰው፣ የተቋሙ የማስፈጸም አቅም ውስንነት ነው፡፡

  በእነዚህና በሌሎችም አጀንዳዎች ላይ የጉባዔውን የመረዳት አቅም አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዘርፉ ሙያተኞች፣ “ታዳሚዎቹ የጉባዔውን ስያሜ የሚመጥን አቅም፣ ቅርጽና ቁመና የሚረዱ አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ በኮታዊ አሠራር የመጡ በመሆናቸው፣ ጉባዔው የስፖርቱ ትልቅ የሥልጣን አካል ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚመራበት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በዚህ አካል ጭምር የሚቀርብና የሚዘጋጅ ስለመሆኑ በውል የሚረዱ አይደሉም፡፡ እዚህ ላይ በትልቁ ሊታሰብ የሚገባው፣ ውክልናው አቅምንና ችሎታን ያማከለ እንዲሆን ክልሎች የሚያቀርቧቸው ዕጩዎች አቅምና ችሎታው ያላቸው እንዲሆኑ ማድረጉ ላይ ነው፣” በማለት ትዝብታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

  የታዩ ጠንካራ ጎኖች

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ በአትሌትነት፣ በአመራርነትና በአሠልጣኝነት የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ፣ በመወጣት ላይ የሚገኙ ሰዎች ለመኖራቸው አያጠያይቅም፡፡ ይሁንና እነዚህ ሰዎች ያላቸውን አቅም ሳይሰስቱ ለስፖርቱ እንዲያበረክቱ፣ ሌሎችም የእነሱን አርአያ በመከተል የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ መነሳሻ የሚሆን ማበረታቻ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ ከሌሎች አካላት ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡

  በዚህ በዘንድሮ ጉባዔ ከታዩ ጠንካራ ጎኖች አንዱና በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለአትሌቲክሱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አትሌቶች፣ አመራሮችና ሙያተኞች ዕውቅናና ማበረታቻ የገንዘብና የዓይነት ሽልማት አበርክቷል፡፡ በዚሁ መሠረት በሕይወት በነበሩበት ወቅት ውጤታማ አትሌቶች በማበረታትና ዕውቅና በመስጠት የሚታወቁት አቶ አቤሰሎም ይህደጎና በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበርና በሌሎችም ታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት የምንጊዜም ምርጥ የአትሌቲክስ አሠልጣኝ በመሆን ተደጋጋሚ ሽልማቶችንና ዕውቅናዎች ያገኙት ወልደ መስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) እንዲሁም በቅርቡ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ምስጉን ባለሙያ በሚል ዕውቅና ያገኙት የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ ልዩ ተሸላሚ ሆነው እያንዳንዳቸው 20 ግራም ወርቅ እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡

  ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ የደቡብ ፖሊስ አትሌት የሆነው ሰለሞን ባረጋ 20 ግራም ወርቅ፣ የበቆጂ አካባቢ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል 65 ኢንች ቴሌቪዥን፣ አሠልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ 20 ግራም ወርቅ፣ ከማናጀሮች የግሎባል ስፖርት ባለቤት ሆላንዳዊ ጆንስ ሔርመንስ በተመሳሳይ ሲሸለሙ፣ ፌዴሬሽኑን ከ1993 እስከ 2005 ዓ.ም. በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ወ/ሮ ብስራት ጋሻውጠና 100,000 ብር፣ ሻምበል ባሻ ዋሚ ቢራቱ 50,000 ብር ተሸልመዋል፡፡

  የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ የመከላከያው አትሌት ሙክታር እድሪስ፣ የትራንስ ኢትዮጵያ ለተሰንበት ግደይ፣ የኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻና የኦሮሚያ ደንና ዱር እንሰሳት ክለብ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ለእያንዳንዳቸው 20 ግራም ወርቅ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

  የደቡብ ፖሊስ ክለብ፣ የመከላከያ ክለብ፣ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንሰሳት ክለብ፣ የትራንስ ኢትዮጵያ ክለብና የኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ክለብ ለእያንዳንዳቸው 65 ኢንች ቴሌቪዥን ተበርክቶላቸዋል፡፡ እንዲሁም ከአሠልጣኞች የትራንስ ኢትዮጵያው ኃይሌ አንድነትና የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳቱ ብርሃኑ መኮንን 20 ግራም ወርቅ ተሸልመዋል፡፡

  ከክልሎች የኦሮሚያ ክልል 240,000፣ የአማራ ክልል 180,000፣ የደቡብ ክልል 140,000፣ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 100,000፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 80,000፣ የትግራይ ክልል 60,000፣ የአፋር ክልል 40,000 እና የሐረሪ ክልል 20,000 ብር ሽልማት የተበረከተላቸው ናቸው፡፡

  ከክለቦች የመከላከያ አትሌቲክስ ክለብ 300,000፣ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች 240,000፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 180,000፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 140,000፣ ሲዳማ ቡና 100,000፣ የጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል 80,000፣ የኦሮሚያ ፖሊስ 60,000 እና የፌደራል ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ 40,000 የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለክልሎች 860,000 እና ለክለቦች 1,140,000 ብር ያበረከተ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...