Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትበአዲስ አበባ የተቀጣጠለው የኦሊምፒክ ችቦ

  በአዲስ አበባ የተቀጣጠለው የኦሊምፒክ ችቦ

  ቀን:

  አትሌቶች በሕይወት ዘመናቸው ሊሳተፉባቸው ከሚገቡ ስፖርታዊ ክንውኖች ኦሊምፒክ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ይህን ትልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ለሁለተኛ ጊዜ ለማሰናዳት ዕድሉን ያገኘችው ጃፓን ዝግጅት ማጠናቀቋ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በማራቶን ከሻምበል አበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ የባዶ እግር ድል ተከትሎ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰችው ኢትዮጵያ መላውን የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ንቅናቄ መፍጠር ይቻላት ዘንድ በመስቀል አደባባይ የለኮሰችው የኦሊምፒክ ችቦ ወደ ክልሎች የሚያደርገውን ጉዞ እሑድ የካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሯል፡፡

  በአዲስ አበባ የኦሊምፒክ ችቦው በተለኮሰበት መስቀል አደባባይ ፕሬዚዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እንዲሁም የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ዮናስ አረጋይ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡

  በርዕሰ ብሔሯ የተለኮሰው የኦሊምፒክ ችቦ ከመስቀል አደባባይ በወጣለት ዕጣ መሠረት ጉዞውን ወደ ድሬዳዋ ከተማ አምርቷል፡፡ በርካታ የአዲስ አበባና አካባቢዋ የማኅበረሰብ ክፍሎች በታደሙበት የችቦ መለኮስ ሥነ ሥርዓት ላይ በአየር ኃይል ሔሊኮፕተር በመታገዝ የኦሊምፒክ ባህልና እሴቶችን የሚገልፁ መልዕክቶች ተበትነዋል፡፡

  በመጪው ሐምሌ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ለትውልድ የሚተላለፍ ዘመናዊ የኦሊምፒክ አካዴሚ የመገንባት ዕቅድ ይዛ በምትንቀሳቀስበት ወቅት መሆኑ እንደተጠበቀ፣ እንደ አገርም ውጤት ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ መንግሥት ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጎን በመሆን የሚቻለውን ሁሉ የሚያደርግ ስለመሆኑ ጭምር ርዕሰ ብሔሯ ተናግረዋል፡፡

  ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የተቋቋመውን ብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴ የመንግሥት ሙሉ ድጋፍ እንደማይለየው የገለጹት ርዕሰ ብሔሯ፣ አቅማቸው በፈቀደ መጠን በግላቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጭምር ገልጸዋል፡፡

  ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የምትወከልባቸውን የስፖርት ዓይነቶች ማሳደግ እንደሚጠበቅባት ያስረዱት ፕሬዚዳንቷ፣ በዚህ ረገድ በተለይም እንደየስፖርት ዓይነቱ ከታች ጀምሮ በመሥራት ሁሉም የሚጠበቅበትን ማድረግ ከቻለ የተፎካካሪነት አቅም በማሳደግ ማጎልበት የማይቻልበት ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

  ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በተለይ ለጥቁር ሕዝቦች የተለየ ሥፍራ እንዳለው ያስረዱት ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ፣ የሻምበል አበበ ቢቂላ ታሪክ ለዚህ ትልቅ ማሳያና ምሳሌ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

  በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ውጤት ለምታስመዘግብባቸው የውድድር ዓይነቶች ዕጩ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ በዝርዝሩ መሠረት ለመካከለኛ ርቀት በዋና አሠልጣኝነት አቶ ብርሃኑ መኮንን ሲመደቡ፣ በረዳትነት ደግሞ አቶ ሀብታሙ ግርማና አቶ ኢሳ ሽቦ ተመድበዋል፡፡ ተጠባባቂዎች አቶ አብርሃም ኃይለ ማርያምና አቶ ስንታየሁ ካሳሁን መሆናቸው ታውቋል፡፡

  ለ3000 ሜትር መሰናክል አቶ ተሾመ ከበደ በዋና አሠልጣኝነት፣ ዶ/ር ብዙአየሁ ታረቀኝና አቶ ከፍያለው ዓለሙ ሆነዋል፡፡ ለ5000 ሜትር ኮማንደር ሁሴን ሽቦ ዋና እንዲሁም አቶ ቶሌራ ዲንቃ፣ ንጋቷ ወርቁና አቶ ኃይሌ ኢያሱ በረዳትነት ሲመደቡ በተጠባባቂነት ደግሞ አቶ ተፈሪ መኮንንና አቶ በሪሁን ተስፋዬ ሆነዋል፡፡ ለማራቶን አቶ ሐጅ አዴሎና አቶ ገመዶ ደደፎ ሲሆኑ፣ በተጠባባቂነት አቶ ጌታነህ ተሰማና አቶ ይረፉ ብርሃኑ መሆናቸው ፌዴሬሽኑ በድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የመጻሕፍት ቡፌ

   ሕፃናትና ወጣቶች የትምህርት ዕረፍታቸውን ከትምህርት አጋዥ በተጨማሪ ልብ ወለድ፣...

  የእናት ጡት ወተት የመጀመርያው የሕይወት ክትባት

  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን አስከትሏል፡፡ ከዚህ...

  ቻይናና ታይዋን የተወዛገቡበት የናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት

  የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን ለመጎብኘት...

  የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 13 የቴክኖሎጂ ዘርፎችን አካቶ ሊካሄድ ነው

  አሥራ ሦስት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎችን ያካተተ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ...