Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትለቶኪዮ ኦሊምፒክ 143 ሚሊዮን በጀት ተመደበ

  ለቶኪዮ ኦሊምፒክ 143 ሚሊዮን በጀት ተመደበ

  ቀን:

  አትሌቶች በተመጣጣኝ ክፍያ ዝግጅት ይጀምራሉ ተብሏል

  በማራቶን ሁለት ተከታታይ ኦሊምፒክ ቀዳሚዎቹን የወርቅ ሜዳሊያዎች ለአገሩና ለራሱ ከማስመዝገቡም በላይ ለአፍሪካውያውን የድል ተምሳሌት ተደርጎ በታሪክ የሚዘከረው አበበ ቢቂላ በጃፓን ቶኪዮ ከተማ ላይ የዛሬ ሃምሳ ስድስት ዓመት የሠራው ገድል የትውልድ ኩራት መሆኑ አያከራክርም፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ቶኪዮ ለሁለተኛ ጊዜ ለምታስተናግደው የኦሊምፒክ ጨዋታ የታላቁን አትሌት ገድል የሚመጥን ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ ይገኛል፡፡

  እየተደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ብሔራዊ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለፈው ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በጋራ እንደገለጹት፣ በኦሊምፒክ መድረክ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በማስጠራት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው አትሌቲክስ ለሦስት የዝግጅት ምዕራፍ በጀትና አስፈላጊው ቁሳቁስ ተሟልቶ ዝግጅት ተጀምሯል፡፡

  ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በበላይነት የሚመራው ሁለት የዝግጅት ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙም ተነግሯል፡፡ የመጀመሪያው በቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራ የሀብት ማሰባሰብና የገጽታ ግንባታ ብሔራዊ ኮሚቴ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የስፖርት ምክትል ኮሚሽነር በሆኑት አቶ ዱቤ ጅሎ የሚመራው የአትሌቶች ዝግጅትና ምልመላ ብሔራዊ ኮሚቴ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

  በመግለጫው ኢትዮጵያ ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ ቶኪዮ ላይ በሴቶች ብስክሌትና የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ሁሉን አቀፍ ተደራሽነትን ማስፋፋት በሚል በዋና በአንድ ወንድና በአንድ ሴት ተሳትፎ እንደሚኖራት ሲጠበቅ፣ በቦክስና ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርቶች ደግሞ በመጨረሻው ማጣሪያ ላይ መሆኗ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፣ በሞሮኮ የወርልድ ቴኳንዶ አትሌቶች (የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም.) ማጣሪያቸውን በማጠናቀቅ ላይ ናቸው፡፡ ቦክስ ከየካቲት 20 እስከ 29 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከናወን ይሆናል፡፡

  ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መሳተፍ ከጀመረችበት ሜልቦርን ኦሊምፒክ (እ.ኤ.አ 1956) ጀምሮ በሦስት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አልተሳተፈችም፡፡ አንደኛውና የመጀመሪያው በሞንትሪያል ኦሊምፒክ ከደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ጋር በተገናኘ ሲሆን፣ ሁለተኛው በሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ፣ ዓለም በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ሁለት ጎራ በተከፈለችበት ወቅት ኢትዮጵያ የሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም ተከታይ በመሆኗ ሲሆን ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ሲኦል ኦሊምፒክ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በመወገን እንደሆነም መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

  ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ በተሳተፈችባቸው ኦሊምፒኮች ባስመዘገበቻቸው ሜዳሊያዎች ከዓለም አገሮች በአጠቃላይ 36ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በመግለጫው ተነግሯል፡፡ በጥቂት አትሌቶች የግል ጥረት ከሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውጭ ሆና የማታውቀው ኢትዮጵያ፣ ከወራት በኋላ በጃፓኗ ቶኪዮ በሚጀመረው ኦሊምፒክ ቢቻል የተሻለ፣ ካልተቻለ ደግሞ ለቀጣዮቹ ኦሊምፒኮች መሠረት የሚሆኑ ሥራዎችን ሠርቶ ማለፍ እንደሚያስፈልግ በተነገረበት መግለጫ ለቶኪዮ የሚያስፈልገው በጀት በዝርዝር ቀርቧል፡፡

  በዚሁ መሠረት ኦሊምፒክን በሚመለከት ኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ ለፕሮግራሙ ማስኬጃ 3.725 ሚሊዮን፣ ለቅድመ ዝግጅት ሥልጠና ድጎማ ሦስት ሚሊዮን፣ ለትጥቅና ተዛማጅ ቁሳቁሶች ሦስት ሚሊዮን፣ ለመስተንግዶና ግብዓት አቅርቦት 30 ሚሊዮን፣ ለማጣሪያና ለአቋም መለኪያ ውድድሮች 7.2 ሚሊዮን፣  ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ተሳትፎ 80 ሚሊዮን፣ ለሀብት ማሰባሰብ ሥራ ማስኬጅያ 2.14 ሚሊዮን፣ ለማበረታቻ ሽልማት 30.5 ሚሊዮን፣ ለብሔራዊ አትሌቶች የአራት ወር ወርኃዊ ክፍያ ስምንት ሚሊዮንና ለአሠልጣኞችና ሌሎች ሙያተኞች 2.4 ሚሊዮን  በድምሩ 143.965 ሚሊዮን ብር በጀት ስለመያዙ ጭምር ተነግሯል፡፡

  የኢትዮጵያ አትሌቲስ ፌዴሬሽን ባለፈው ሳምንት በማኅበራዊ ድረ ገጹ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ መካከለኛ ርቀትን ጨምሮ 3,000 ሜትር መሰናክል፣ ለ5,000 ሜትርና ለማራቶን ውድድሮች ዋናና ምክትል አሠልጣኞች ዝርዝር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሦስት የዝግጅት ምዕራፍ ከ90 በላይ አትሌቶችና ሌሎች ተያያዥ ሙያተኞችን መርጦ ይፋ እንደሚያደርግም የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ተናግረዋል፡፡

  በመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት እንደተፈታ፣ ከእንግዲህም ሁለቱ ተቋማት ለአንዲት ኢትዮጵያ በጋራ እንደሚሠሩ ከስምምነት የደረሱ ስለመሆኑ ጭምር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ በሁለቱ ተቋማት ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ያን ያህል የጎላ እንዳልነበረ ተናግረው አሁንም እንደ አንድ ተቋም ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...