Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቅን በተመለከተ የራሷን ሰነድ ለድርድር ልታቀርብ ነው

  ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቅን በተመለከተ የራሷን ሰነድ ለድርድር ልታቀርብ ነው

  ቀን:

  የኢትዮጵያ መንግሥት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን የተመለከተ ሰነድ አዘጋጅቶ ለድርድር እንደሚያቀርብ ተሰማ። አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጭ እንደገለጹት፣ በአሜሪካና በዓለም ባንክ አመቻችነት የግድቡን የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ሲደረግ የቆየው ድርድር ውጤት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን የአገሪቱን ሉዓላዊነትና ጥቅም የሚያስከብር የድርድር ሰነድ እንዲያዘጋጅ በመንግሥት ታዞ ሰነዱን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

  ከተደራዳሪ ቡድኑ በተጨማሪ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የዓለም አቀፍ ሕግ ስምምነት ባለሙያዎች፣ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ሰነዱን በማዘጋጀት ሒደት ላይ ሌት ተቀን እየሠሩ እንደሚገኙ ማረጋገጥ ተችሏል።

  ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ጠንካራ ትስስር ያላት አገር በመሆኗ በድርድሩ መሳተፍ ትክክል ቢሆንም፣ አሜሪካ ያዘጋጀችው የመጨረሻው ሰነድ ውስጥ ያልተፈቱ ጉዳዮች መኖራቸውን ምንጩ ጠቁመዋል፡፡ ታዛቢዎቹ በድርድሮች ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ግፊት እያደረጉ እንደነበር ተሰምቷል። ይህ የአገሪቱን ጥቅም የሚፃረር ስለሆነ በቀጣዩ ድርድር ላይ ላለመሳተፍ የተሰጠው ውሳኔ ትክክለኛ መሆኑን አክለዋል።

  የታዛቢነት ሚና የተሰጣቸው አሜሪካና ዓለም ባንክ ድርድሩን ወደ ሽምግልና መቀየራቸውና በመጨረሻም ራሳቸው አዘጋጅተው ለስምምነት ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ፣ ኢትዮጵያ እንደማትደራደርባቸው የገለጸቻቸውን በርካታ ነጥቦች ያላካተተና ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮችም ጥቅም በእጅጉ ያደላ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንደማይኖረው አቋም መያዙን እኚሁ ምንጭ አስታውቀዋል።

  የቀረበው ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ ከህዳሴ ግድብ አልፎ የዓባይ ውኃ ክፍፍልን የሚመለከቱ አንቀጾች የተካተቱበት በመሆኑ፣ ከድርድር አጀንዳው ያፈነገጠ እንደሆነ ተለይቷል ሲሉ ምንጩ ገልጸዋል።

  ኢትዮጵያ የግድቡ ባለቤትና በግዛቷ ውስጥ የሚገኝ እንደ መሆኑ መጠን፣ እንዴት መሞላት አለበት የሚለውን ጉዳይ በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም መርሆን መሠረት በማድረግ ለታችኞቹ አገሮች ማሳወቅ፣ አገሮቹ ሊያነሱ የሚችሉት ሥጋትም በዓለም አቀፍ መርሆች ውስጥ የሚወድቅ ከሆነ ለማካተት ድርድር እንደሚደረግበት ያሳወቁት እኚሁ ምንጭ፣ በዚህ አግባብ ሰነዱን የማዘጋጀት ሥራ በመፋጠን ላይ መሆኑን አስረድተዋል። የሰነዱ ዝግጅት ሲጠናቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለግብፅና ለሱዳን እንደሚላክ ገልጸዋል።

  በአሜሪካና ዓለም ባንክ አመቻችነት በሦስቱ አገሮች መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር ባለፈው ሳምንት ይፈረማል ተብሎ ዕቅድ ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ለስምምነት ዝግጁ እንዳልሆነና ልዑካኑንም ወደ አሜሪካ እንደማይልክ በይፋ አስታውቋል።

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሳምንት በፊት ለግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በላኩት መልዕክት፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድሩን አስመልክቶ የተረቀቀውን ሰነድ ለማጤን ኢትዮጵያ በቂ ጊዜ እንደምትፈልግ ማስታወቃቸው ይታወሳል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን መልዕክት ለግብፅ ፕሬዚዳንት ያደረሰው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመራ ልዑክ መሆኑም እንዲሁ።

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በላኩት በዚህ መልዕክት ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ ጊዜ ወስዳ ማጤን እንደምትፈልግ፣ የምትደርሰበትን አቋም እንደምታሳውቅ የሚያስረዳ እንደሆነ መዘገባችን አይዘነጋም። መንግሥት ይህንን አቋሙን ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ይፋ ካደረገ በኋላ፣ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የተወሰደውን አቋም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲደግፉ ተስተውለዋል።

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...