Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የህዳሴ ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት...

  የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የህዳሴ ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

  ቀን:

  የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቲቨን ምኑችን ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር፣ የህዳሴ ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ሰሞኑን በስልክ መወያየታቸው ተገለጸ።

  የሱዳን መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ምኑቺን ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በስልክ መወያየታቸውን አስታውቋል።

  ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ለገንዘብ ተቋሙ ኃላፊ ስልክ በመደወል የኮሮና ቫይረስ በአሜሪካ ላይ እያደረሰ ባለው ከፍተኛ ጉዳት የተሰማቸውን ሐዘን እንደገለጹላቸው በመግለጫው ተጠቁሞ፣ ስቲቨን ምኑችን በበኩላቸው ስለተቋረጠው የህዳሴ ግድብ ድርድር ማንሳታቸው ተገልጿል።

  ይህንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያና ግብፅ በመሄድ የተቋረጠው ድርድር እንዲጀመርና ስምምነት ባልተደረሰባቸው የህዳሴ ግድቡ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ጉዳዮች ላይ ድርድር በማድረግ፣ ችግሩ እንዲቋጭ ለማድረግ ማቀዳቸውን እንዳስረዱ በመግለጫው ተመልክቷል።

  ሁለቱ ወገኖች ባደረጉት የስልክ ውይይትም የህዳሴ ግድቡን ድርድር በፍጥነት ማጠናቀቅ አስፈላጊነት ላይ መግባባታቸውን፣ የኮሮና ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደረሰ ያለውን ጉዳት መንግሥታት ተቆጣጥረው ቀልባቸውን ከሰበሰቡ በኋላ ድርድሩን ከተቋረጠበት ማስቀጠል ተገቢ እንደሆነ መስማማታቸውን መግለጫው ያስረዳል። የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያና ግብፅ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ ግብፅ የዓረብ አገሮችን በግድቡ ጉዳይ በማስተባበር በዓረብ ሊግ በኩል እንዲወጣ ያደረገችውን የአቋም መግለጫም ሱዳን እንደማትቀበለው አስታውቆ ነበር።

  ሱዳን በግድቡ ላይ ሲደረግ የነበረው ድርድር ከተቆመበት እንዲቀጥል ፍላጎት ብታሳይም፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ወደ ድርድር ለመመለስ ችግር እንደሌለባት ነገር ግን የአሜሪካ መንግሥት የታዛቢነትም ሆነ የአደራዳሪነት ሚና ገለልተኛ ነው ብላ እንደማታምን አስታውቃለች።

  በዚህም ምክንያት የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ከታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ጋር ለመነጋገር የሚያስችላትን አዲስ የውይይት ሰነድ እንዳዘጋጀች፣ ሰነዱም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ መዘገባችን ይታወሳል።

  በአዲስ ገጽታና ይዘት የተዘጋጀው የድርድር ሰነድ በኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን፣ በብሔራዊ የባለሙያዎች መማክርት፣ እንዲሁም ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ የሕግና የውኃ ምህንድስና ባለሙያዎች፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሙያዎች በጋራ መረቀቁን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

  በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የድርድር ሰነድ ለግብፅና ለሱዳን ብቻ እንደሚቀርብ፣ ነገር ግን በሦስቱ አገሮች ስምምነት መሠረት ሌሎች አጋሮች በድርድሩ ሚና እንዲኖራቸውም ክፍት መደረጉን ከመረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የተዘጋጀው አዲስ ሰነድ የህዳሴ ግድቡ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ ድርድር የማታደርግባቸውን ጉዳዮች ለይቶ ማስቀመጡንና የማያወላዳ አቋሟን አስረግጦ ያስቀመጠ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።

  ኢትዮጵያ በግድቡም ሆነ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን ጥቅም የሚያስከብርና አሳልፎ የማይሰጥ እንደሆነ፣ የታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮችን ተጠቃሚነትም በዓለም አቀፍ መርሆች መሠረት የሚያረጋግጥ፣ እንዲሁም በሦስቱ አገሮች መካከል ትብብርና መልካም ግንኙነትን የሚያሰፍን እንደሆነ ከምንጮች ገለጻ ታውቋል።

  በዚህ ሰነድ መነሻነት የሚደረገው ድርድር የሚመነጨው የመፍትሔ ሐሳብ ምን መምሰል እንደሚገባውና አመላካቾችንም ያስቀመጠ እንደሆነም ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ሰነዱን መነሻ በማድረግ የሚደረገውን ድርድር ለሦስቱም አገሮች ቅርብ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት እንዲመራ በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን የገለጹት ምንጮች፣ መንግሥት ይህንኑ ዕውን ለማድረግ እየጣረ መሆኑን ጠቁመዋል።

  የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ እንዲያደራድሩ ኢትዮጵያ የጠቀች ሲሆን፣ ከሁለት ወራት በፊት በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይህንኑ የመንግሥታቸውን ፍላጎት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...