Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ለኮሮና የተባበረ ክንድ ይኑረን!

  አገር ድርብርብ ችግሮች በደጇ ተኮልኩለውባታል፡፡ ሰርስረው በመግባት  የሚፈታተኑ ችግሮችን እየታዩ ነው፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የሚፈጥሯቸው ችግሮችን በማሰብ የተፈጠሩ ሥጋቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተሰማ ጀምሮ ቀላል የማይባል ፈተና እየመጣ ለመሆኑ ሁሉም በቀላሉ የሚገነዘበው ነው፡፡

  በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የታወቁ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱ፣ በሽታው በዚህ አካሄዱ ከቀጠለ ኑሯችንና መላ እኛነታችንን ማወሳሰቡ አይቀርም፡፡ ችግሩ የዓለም ነው፡፡ በአገራችን ደቃቃ የኢኮኖሚ አቅም፣ የመጣውን ወጀብ እንዴት መቋቋም ይቻለን ይሆን? የሚለው በእጅጉ ያሳስባል፡፡ የአኗኗር ዘያችን፣ ማኅበራዊ ኑሯችንና አመለካከታችን ሲታከልበት፣ ቫይረሱ በቀላሉ የሚስፋፋበት ምቹ አገርና ሕዝብ ማግኘቱ እንደማይቀር በማሰብ የሥጋታችን ሙቀት ከወዲሁ እየጨመረ በፍርኃት ቢያርደን ይገባናል፡፡ ከመራድ ግን ተግቶ ለመመከት መዘጋጀት፣ ምክር መስማትና ለእኔ ብሎ መከተት ብልህነት ነው፡፡  

  ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስና ሊያስከፍለን የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በመቀልበስ፣ አካሄዳችንን አስተካክሎ መገኘት አርቆ አሳቢነትን ይጠይቃል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን የኮሮና ጦስ የብዙ ጊዜ ጥረታችንን ወደ ኋላ ጎትቶ የሚያስቀር ጉዳት ሊያመጣ ይችላል፡፡

  በአሁኑ ወቅት የገባንበትና ወደፊት ሊገጥመን የሚችለው ችግር ብዙ የታሰበበትን ፖለቲካዊ መንገድም እየነካካ ነው፡፡ ከሰሞኑ እንደተሰማውም የኮሮና ቫይረስ አገሪቱ ለማካሄድ ያቀደችውን ምርጫ ለማራዘም ሰበብ ሆኗል፡፡ ኮሮና ጤናችንን ቢያጣ እንኳ በእጅ አዙር ሁሉ ነገሮቻችንን እየነካና፣ በርካታ ዕቅዶቻችንን እያሰናከለ እንደሚጓዝ ከወዲሁ እያሳየን ነው፡፡ ከጅምሩ እንዲህ ባለ መንገድ እየመጣ ያለውን የኮሮና ተፅዕኖ መንግሥትና ዜጎችም የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በተለየ አኳኋን መረባረብና መተባበር እንዳለባቸው ያመለክተናል፡፡

  - Advertisement -

  የፖለቲካ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የሕክምና ተቋማትና ባለሙያዎች፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተንታኞች፣ የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳቸውና አንገብጋቢ ብሔራዊ አጀንዳቸው ከህዳሴው ግድብ እኩል፣ ይህ በሽታ አስከፊ ጉዳት ሳያደርስብን እንዴት መወጣት ይኖርብናል በሚለው ላይ መሆን እንዳለበት ነጋሪ አያሻውም፡፡ አገር ከገጠማት የችግር ማጥ ወጥታ እንዴት ወደፊት እንራመዳለን የሚለውን በአግባቡ ሊፈታ የሚችል መፍትሔና የዚህ አካል መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡

  አገራዊ ምርጫውን ማካሄድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ከተደረሰ፣ ግርግርና ጭቅጭቅ ውስጥ ሳንገባ የፖለቲካ ድርጅቶችም አገር በማዳን ተግባር ላይ ቅድሚያ በመስጠት ለሕዝብ ውለታ በመዋል፣ መንግሥትም ይህንን ጊዜ በማሰብ እከሌ ከእከሌ ሳይል አገር አቀፍ ጥሪ በማድረግና በመረባረብ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ጥረቱን ያጠናክር፡፡  

  ከሰሞኑ እንደሰማነው ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ አካላት ይበጃል ያሉትን ውሳኔ እያሳለፉ ነው፡፡ ባለሀብቶችና ሌሎችም ግለሰቦች ለአገር ጥሪ እጃቸውን እየዘረጉ ነው፡፡ በመልካም የሚወደስ ተግባር ቢሆንም፣ አገራዊ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው ርብርብ ግን በአንድ የዕዝ ሰንሰለት ሥር የሚመራና የተደራጀ አካሄድ ሊኖረው እንደሚገባ ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው፡፡ በተናጠል ድጋፍ ማሰባሰብ፣ በተናጠል ውሳኔ እያስተላለፉ መጓዝ ያልታሰበ አደጋ ሊኖረው ይችላል፡፡ የሚሰበሰበው ሀብት ከወዲሁ ወዲህና ወዲያ መሸንሸን የለበትም፡፡ በየትኛውም ማዕዘን ከዚህ ጉዳይ ጋር ለሚፈጠር ችግር በየትም ቦታ የተገኘው ሀብትና ድጋፍ ቢቻል በእኩል ደረጃ መዳረስ አለበት፡፡ ወይም ችግሩ አሳሳቢ ለሚባሉ አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት በቶሎ ችግሩን ለመቋቋም መንቀሳቀስ ተገቢ ነው፡፡

  ክልሎች ድንበር ዘግተናል፣ ትራንስፖርት አቁመናል የማለታቸው ነገር መታየት እንዳለበትን ምክር እየቀረበበት ነው፡፡ አደጋውን የምንቀንሰው ድንበር በመዝጋት ብቻ አይደለም፡፡ ድንበር ከተዘጋ በኋላ ከአንዱ ወደ ሌላው ክልል የሚሄዱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እንዴት ማስኬድ ይቻላል የሚለውንም ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ መተግበር እንደሚያስፈልግ ሐሳቦች እየቀረቡ ነው፡፡

  ክልከላው የታዩና ያልታዩ ጎኖችን መርምሮና አረጋግጦ ወሳኝ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዳይቋረጡ ማድረግ መቻል አለበት፡፡ አንዱ ከሌላው ክልል ጋር በመመካከር የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ እንዴት እናድርግ፣ ቁጥጥር እየተደረገና በተገደበው እንቅስቃሴ ውስጥም ግብይት እንዴት ይፈጸም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ኮሮናን ሰበብ አድርጎ በር ዘግቶ ወጪና ገቢ የንግድ እንቅስቃሴን ማስታጎል ሳይሆን፣ ብልሃት የታከለበት፣ ጥንቃቄ ያልተለየው ሥርዓት መከተል ያስፈልጋል፡፡

  በፌዴራል ደረጃ ጠንካራ ግብረ ኃይል ወይም ኮማንድ ፖስት ሊኖር ይገባል፡፡  ተናቦ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ሥርጭቱን ከመግታት አኳያ ሰዎች እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብ ከተደረገ፣ መሠረታዊ የሚባሉ አቅርቦቶች በቀላሉ ማግኘት የሚችሉባቸው መንገድ መታሰብ አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ የተናጠል ሳይሆን የጋራ ጥረትና ርብርብ በማድረግ ጠንካራ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ለአገር የታሰበው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአጭር ጊዜ ያውም ለአደጋ ጊዜ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአፋጣኝ ተዘጋጅቶ ጉዳቱን አስልቶና ገምቶ አስቸጋሪውን ጊዜ ለማለፍ የመንግሥት ኃላፊነት የበረታ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ጊዜ ማባከንና መዘግየት ችግሩን ከቁጥጥር ውጭ ሊያደርገው ይችላል፡፡  

  ይሁን እንጂ ችግሩን ለማቃለል በሚወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል የሚፈጸሙ አጉራ ዘለል ተግባራት አንገት እያስደፉ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ዜጋ ደኅንነት ተብሎ የተላለፈ ውሳኔን፣ ያውም ለጋራ ደኅንነት ሕፃን አዋቂው እኩል የሚያውቀው ብሔራዊ አደጋ ተደቅኖ ተግሳጽና ማሳሰቢያን መጣስ ከማሳዘን አልፎ መንግሥት አስገዳጅ ትዕዛዝ እንዲያስተላልፍ መገፋፋት ይሆናል፡፡

  ከውጭ የሚመጡ መንገደኞች በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለ14 ቀን መቆየት አለባቸው የሚለውን መመርያ በተለያየ መንገድ ለመጣስ ሲሞከርና ሲጣስ መስማት ያሳምማል፡፡ አገር በጭንቅ ውስጥ በምትገኝበት ወሳኝ ወቅት እጅ ማበሻ አልኮልና ማፅጃ ፈሳሾችን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ፣ በርዞና ከልሶ ለገበያ ማቅረብ፣ ምን ያህል አስከፊ ህሊና የተጠናወታቸው ስግብግቦች እንዳፈራን ያሳያል፡፡ ዋጋ ተጨመረብን ብቻ ሳይሆን፣ ቫይረሱን ለማጥፋት የገዛነው ‹‹ማፅጃ›› በሽታ የሚያመጣብ ከሆነ፣ የክፋታችን ልክ የለሽነት በሽታውን በግድ እንደመጥራት ይሆናል፡፡ ያልተገባ ግብይት ሲፈጽሙ የነበሩ ከ15 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ሕጋዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው የሚገለጽ ዜና ስንሰማ፣  እንዲህ ባለወቅት እንኳ ሰው እንዴት በሐጢዓት ለመክበር ይጥራል? ያስብላል፡፡ የምንፅናናው ግን ችግሩን ለመቅረፍ ቤታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ሌላም ንብረትና ሀብታቸውን እንካቹ ለወገን ይትረፍ የሚሉ እጆች ሲዘረጉ በማየታችን ነው፡፡ ከእኩያን መካከል ስንቱ ልበ ብርሃን እንዳሉ የኮሮና ቫይረስ እያሳየን ነው፡፡ ይህም ያልፍና ደግነትና ክፋታችንን የምናወጋበት ጊዜ ይመጣል፡፡

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት