Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  በኮሮና ‹‹ሥራህ ያውጣህ›› አይሠራም

  የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ከተገለጸ ከአንድ ወር በላይ ሆኗል፡፡ እስከ ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ (ወደ ኅትመት እስከተገባበት ምሽት) በጠቅላላው 92 ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች እንደተመዘገቡ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ማገገማቸው መልካም ዜና ነው፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ የወረርሽኙ ስፋትና ልክ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ግን ብዙ ሥራ ይቀራል፡፡

  የመመርመር አቅም እየጨመረ ሲሄድ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥርም ከፍ እያለ ሊመጣ እንደሚችል ይታመናል፡፡ የመዛመት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡ ዜጎች ቫይረሱን ለመከላከል እንደሚያግዙ የታመነባቸውን መመርያዎች በአግባቡ ሲተገብሩ አለመታየታቸውና መንግሥትም ማሳሰቢያዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን ከማስተጋባት የዘለለ የጥቃቄ ዕርምጃዎች ላይ ቁርጠኛ ዕርምጃ አለመውሰዱ የባሰውና የሚያስከፋው አደጋ እንዳይመጣ ሥጋት አለን፡፡ በሚፈለገውና በሚመከረው ልክ ጥንቃቄ እየተደረገ ባለመሆኑ አደጋው አገራችንና ሕዝቦቿን ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ከባድ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

  ስለዚህ ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ከማድመጥና ከመስማት ባሻገር የሚጠበቁ የውዴታ ግዴታዎችን ማክበር የህልውናችን ጉዳይ ነው፡፡ የቫይረሱ መገኘት በተገለጸ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በኢኮኖሚው ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ሲታይ፣ እያንዳንዱ  ዜጋ ራሱን ገዝቶና ተቆጥቦ ጉዳቱን ለመቀነስ አስተዋጽኦ ማድረጉ አንዱና ዋናው ቁም ነገር ነው፡፡ በመንግሥት፣ በጤና ባለሙያዎች እንዲሁም በሃይማኖት አባቶች ጭምር የሚደረጉትን የልመና መልዕክቶች መተግበር አዋቂነት ነው፡፡ በዓለም ላይ እየሆነ ያለውን፣ የሠለጠውና ሁሉ የተረፈው ዓለም የሚያየው ስቃይ እያዩ ከዚያ ለመዳን መረባረብም ‹‹ብልህ ከሰው፣ ሞኝ ከራሱ ይማራል›› የተሰኘውን ብሂል በተግባር መተርጎም ነው፡፡

  ይሁን እንጂ ምንም እንዳልተፈጠረ በየአካባቢው የሚታየው የሕዝብ መግተልተልና ትርምስ፣ ገንድሶ ሊገባ ከደጃፍ የሚያንዣብበውን ሁሉ አቀፍ ቀውስ ከማንወጣበት ማጥ ሊያሰምጠን እንደሚችል እያየን ነው፡፡ በሽታው ቀስ በቀስ እጅግ እግሩን እያስገባ፣ በሌሎች አገሮች የምናየውን በእኛም ላይ ለማድስ እያደባ ነው፡፡  አማራጫችን የጤናና የንፅህና አጠባበቅ መመሪያዎችን ያለ አስገዳጅ ማክበርና መተግበር ብልህነት ነው፡፡

  - Advertisement -

  ይህ ካልሆነ ግን ተያይዞ ከማለቅ በፊት መንግሥት በኃይል እያስገደደ ጭምር ሕግ ለማስከበር የሚያስችለውን አዋጅ አውጥቷል፡፡ ስለዚህ በደካማ ኢኮኖሚያችን ላይ ያፈጠጠው ዱብ ዕዳ የከፋ እንዳይሆን፣ ሕዝብ በውዴታ የሚባለውን በመስማት መጠንቀቅ አለበት፡፡ አሁንም ከጫናና ከግዳጅ በፊት በብርቱ መመርያዎችን ሁሉም ለሁሉም ሲል የመተገበር ማኅበራዊ፣ ሰብዓዊና ሕጋዊ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

  ምርጫ የለንም፡፡ ጊዜም የለንም፡፡ ያለን አማራጭ አብሮ ተሳስቦ፣ በቤት ተሰብሶ መኖር አልያም በጅምላ ማለቅ ነው፡፡ ሲሆን የምናየው ይህ ብቻ ነው፡፡ መዘናጋታችን ሊያስፈራን ይገባል፡፡ ከተጠቀቅን ወደ ተስፋ መሻገር የምንችልበት ዕድል አለን፡፡ በሽታው ያመጣብን ቀውስ የሚታለፍ እንደሆነ ማሰብ አለብን፡፡ እገሌ ከእገሌ የማይለው ይህ ወረርሽኝ የመከላከልና ኃላፊነትን የመወጣቱ ድርሻ የሁሉም ዜጋ ነው፡፡

  በቤት እንዲቆይ የተነገረው እንደምንም ራሱን ገዝቶ በቤቱ ይቀመጥ፡፡ መከራ የሚታለፈው በመሸሸግ ጭምር ነው፡፡ የጦርነት ቋያ ቢፈጠር ኖሮ ሁሉም መሸሸጊያ ዋሻ ፍለጋ እንደሚያደባው ሁሉ፣ ይህ በሽታም ሥውር ጦር በመሆኑ፣ የሰበቀው ጅምላ ጨራሽ ሳይርከፈከፍብን ጥንቃቄ በማብዛት ራሳችንን፣ ልጆቻችንን፣ ቤተሰባችንን፣ የምንወዳቸውን፣ ጎረቤቶችንን፣ ቀዬአችንን ሁሉ ማትረፍ እንችላለን፡፡ መዘናጋታችን ግን አገር ያጎብጣል፡፡ የሰቆቃ ጣርና የሞት ዋይታ ለማናችንም አይበጅም፡፡ ጅምላ መቃብር ከመውረድ የምንድንበት መንገድ ጥንቃቄ ነው፡፡ 

  በመሆኑም ሕዝብ አልታዘዝ አልገዛ ሲል ይህንን እምቢ ባይነት እንዲያስተካከል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትክክል እንዲተገበር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በየአውቶቡስ ፌርማታ ደንብ የለበሱ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አስቁሞ በሥርዓት ማሰለፍ በቂ አይደለም፡፡ አንዳንድ ቦታ እንደምናየው ሰዓታቸው ሲደርስ ጥለው የሚነጉዱ ሕግ አስከባሪዎች ‹‹ሥራህ ያውጣህ›› የሚሉበት ጊዜም አይደለም፡፡ የአንዱ ቸልታ ለሌላው ሞት ደቅኗል፡፡ ‹‹ያንተ መኖር ለእኔ ህልውና ነው›› ብቸኛ መርኅ ነው፡፡ ስለዚህ ፈረቃቸው ሲያልቅ በምትካቸው ተረኛው ዘብ ወይም ወታደር ሥርዓት እንዲያስከብር ሰንሰለቱ የተጠበቀ አሠራር መከተል እንጂ እንደ ከርሞው በተበላሸ አካሄዳችን አንዘልቅም፡፡ ይህን ለወታደር መምከር ቂልነት ቢመስልም በከተማው የሚታየው መዝረክረክ ግን የወታደሩም ጭምር በመሆኑ፣ ጎበዝ አብሮ ማለቅ አያዋጣም ለማለት ነው፡፡  

  የወጣው አዋጅ ዝርዝር ጉዳዮችን የተመለከተ የማስፈጸሚያ ደንቡም ከ26 በላይ ክልከላዎችን ያካተተ ድንጋጌዎች ይዞ ቢወጣም፣ ተግባር ላይ እንዲውሉ መንግሥት ቁርጠኛ መሆን መቻል አለበት፡፡ ለምሳሌ ወረርሽኙን ለመከላከል በዝርዝር ከተቀመጡት ክልከላዎች አንዱ ሰዎች ሲንቀሳቀሱ የፊት መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ ያስገድዳል፡፡ መሃረብ፣ የአንገት ልብስ ወይም ስካርቭና የመሳሰሉትን በመጠቀም አፍና አፍንጫን መሸፈን ይቻላል ተብሏል፡፡ ይሁንና የአፍ መሸፈኛ ጭምብል ከገበያ ማግኘትም ቢሆን አሁን ብዙም ፈተና አይደለም፡፡ እርግጥ በርከታ ሠራተኞች ያሏቸው መሥሪያ ቤቶች  የፊት መሸፈኛ ጭንብል ለማግኘት ሲቸገሩ እያየን ነው፡፡ መሥሪያ ቤቶች ለሠራተኞቻቸው ለማቅረብ ፈልገው እንኳ በቀላሉ ማግኘት እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው፡፡

  ደንበኛው ጭምብል በድብቅ ይሸጣል እንጂ በበቂ ሁኔታ የለም፡፡ እርግጥ ነው በገፍ ይገኛል ተብሎ ባይታሰብም ባለው አቅም በርካታ ሠራተኞች ላሏቸው ተቋማት በተለየ አቅርቦት እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ባለማድረግ የሚፈጠረው ችግር ቀላል ስለማይሆን የበለጠ የሚያስፈልገው የቱ ነው? በማለት ጭምርና በመለየት አገልግሎቱ ቢሰጥ የተሻለ ይሆናል፡፡

  የዓብይ ፆም ፍቺን ምክንያት በማደረግ የተዘጉ ሥጋ ቤቶች ተከፍተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ያልበሰለ ጥሬ ሥጋ መመገብ ለበሽታው መተላለፊያ አመቺ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ነው፡፡ ይህን ክልከላ በሥነ ምግባር ታግዞ፣ ህሊውናው በመሆኑ ጭምር እንዲህ ካለው አመጋገብ ሥርዓት የሚከለከል ራሱን ብቻም ሳይሆን ሕዝብን ከአደጋ ይታደጋልና የአገር ጥሪ አለበት፡፡ ቢቻል ግን ሥጋ ቤቶች ተዘግተው መቆየት ቢችሉ ተመራጭ ነበር፡፡

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት