Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየኢትዮጵያ ልማት ባንክን ካፒታል ለማሳደግ የቀረበው ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ አዋጅ ተቃውሞ...

  የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ካፒታል ለማሳደግ የቀረበው ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ አዋጅ ተቃውሞ ቀረበበት

  ቀን:

  የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ካፒታል ለማሳደግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ፣ በምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ቀረበበት።

  መንግሥት የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የበጀት እጥረት ስላለበት ካፒታሉን ለማሳደግ የወሰደው አማራጭ፣ ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ አዋጅ በምክር ቤቱ እንዲፀድቅ ማድረግ ነው።

  ይኸው ልዩ የመንግሥት የዕዳ ሰነድ ዓርብ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ለተካሄደው የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ቀርቧል። የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሟቸውን ያሰሙት የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ መንግሥት የተከተለውን ልዩ የዕዳ ሰነድ አዋጅ የማፀደቅ አማራጭን በተመለከተ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለምዝበራ የተጋለጠ የሀብት አስተዳደር ላይ ነው።

   የምክር ቤቱ አባል  አቶ መሐመድ አብዱሽ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ40 በመቶ በላይ የብድር ብልሽት ያለበትና የአገሪቱን ክፍለ ኢኮኖሚ ያሽመደመደ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ ባንኩ የካፒታል ማሻሻያ ሊደረግለት አይገባም ብለዋል። አክለውም ባንኩ በኢንቨስተር ስም በተደራጁ ቡድኖች በብድር መልክ የተዘረፈና ለአገሪቱ ዜጎች ጥቅም ያላስገኘ፣ እንዲሁም የአገሪቱን አንጡራ ሀብት ያወደመ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ የአገርና የሕዝብ ባንክ ያላግባብ ባክኖ መቅረት እንደሌለበትና በሕግ የሚጠየቅ አካል መኖር አለበት ብለዋል፡፡

  በመሆኑም ረቂቅ የዕዳ ሰነዱ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በትኩረት እንዲመለከተው ጠይቀዋል። ተመሳሳይ ትችት ያነሱት ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ወርዶፋ በቀለ ናቸው፡፡ እሳቸውም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በርካታ ብልሹ አሠራሮች ያሉበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ካነሷቸው ችግሮች መካከል ባንኩ የፖሊሲ ባንክ እንደ መሆኑ መጠን መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማበደር ሲገባው፣ ግለሰቦች ከዚህ ባንክ ተበድረው የሌላ ባንክ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ሲያገለግል የቆየ ተቋም ነው ብለዋል።

   ከልማት ባንክ ብድር ወስደው በእርሻና በአበባ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ሥራ ሳይገቡና ብድር ሳይመልሱ ዓመታት ያስቆጠሩ በመሆናቸው፣ በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ያሳሰቡት የምክር ቤቱ አባል፣ ባንኩ ተጨማሪ ካፒታል ሳይሆን ሪፎርም እንደሚገባው ተከራክረዋል። በርካታ ተመሳሳይ ክርክሮች ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም በመጨረሻ ላይ የቀረበለትን ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ መርቷል፡፡

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ፣ ልማት ባንክ የተቋቋመበት ደንብ እንዲሻሻል የወሰነ ሲሆን፣ ይኼንንም መሠረት በማድረግ አሁን ባለው የተከፈለ 7.5 ቢሊዮን ብር የባንኩ መመሥረቻ ካፒታል ላይ ተጨማሪ 21 ቢሊዮን ብር ታክሎበት፣ በድምሩ 28.5 ቢሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል።

  ከሁለት ሳምንት በፊት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ፣ የታሰበው ማሻሻያ ባንኩን ትልቅ የመንግሥት ፖለሲ ባንክ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። ባንኩ እያስተዳደረ ካለው ሀብት አንፃር ሊኖረው የሚገባውን አቅም እንዲይዝ ካፒታሉ እንዲያድግ ተወስኗል ብለዋል፡፡

  የባንኩን ካፒታል ማሳደግ አስፈላጊ ካደረጉት መሠረታዊ ምክንያቶች ዋነኛው ባንኩ በብድርና በተለያዩ ድጋፎች የሚያገኛቸውን ከፍተኛ ሀብት ለማስተዳደር፣ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መሠረት የሚፈለገውን ዝቅተኛ የካፒታል መጠን ባንኩ የሚያሟላ ባለመሆኑ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል። ‹‹ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር በምንሠራበት ወቅት ይህ ጥያቄ ይቀርብ ነበር፤›› ሲሉ ያስታወሱት አቶ ኃይለየሱስ፣ የባንኩን የተከፈለ ካፒታል ለማሳደግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ሲደረግ፣ ባንኩ የካፒታል መሥፈርቱን እንዲያሟላ እንደሚያደርገውና ለገጽታ ግንባታም እንደሚያሰናዳው አስረድተዋል።

  ተጨማሪ ካፒታሉ እንዲያድግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በሚያዚያ ወር የተወሰነ ሲሆን፣ አሁን ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ተጨማሪ ካፒታሉን በልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ለመክፈል የሚያስችል ነው።

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...