Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  አነጋጋሪው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ለመሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና መንግሥት ከዚህ አንፃር የሚከተለውን ግልጽነት የጎደለውን አሠራር በመተቸት፣ በርካታ የዘርፉ ተቋማት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሚያወጧቸው ሪፖርቶች የተነሳ እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ መታዘብ የተለመደ ክስተት ነበር፡፡

  በተለይ ከዚህ ቀደም እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሒውማን ራይትስዎች የተሰኙ ተቋማት የሚያወጧቸው ሪፖርቶች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተቀባይነት ማጣት ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹የኒዮሊበራል ኃይሎች የአገሪቱን ሁለንተናዊ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ጉዞ ለመቀልበስ የሚያደርጉት የተደራጀ ጥቃት ነው፤›› በማለት በሪፖርቶቹ ይፋ የሚደረጉ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት ማጣጣል፣ እንዲሁም ደግሞ ጆሮ ዳባ ሲል ይታወቅ ነበር፡፡

  በዚህም የተነሳ በእነዚህ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መከበር አለበት በማለት በሚወተውቱ ተቋማትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የነበረው ግንኙነት የሻከረና በመወነጃጀል ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡

  ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ከዚህ ቀደም ይወጡ የነበሩ ሪፖርቶች በአብዛኛው በተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ወትዋቾች ዘንድ፣ እንደ ዋነኛ የመንግሥትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማሳያ ተደርገው ይወሰዱ ነበሩ፡፡ በዚህም በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በሚገናኙበት አጋጣሚ ሁሉ፣ በእነዚህ ተቋማት የቀረቡ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመምዘዝ ጥያቄዎች ያቀርቡና ይከራከሩ እንደነበረም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

  ለበርካታ ዓመታት በአገሪቱ ተገኝተው ሪፖርት ለማጠናቀር የሚያደርጉት ጥረት በመንግሥት እንቢተኝነት ተስተጓጉሎብናል በማለት ሲከሱ የኖሩት እነዚህ ተቋማት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የሚሰነዝሯቸው አስተያየቶችና የሚያወጧቸው ሪፖርቶችም እንደ ከዚህ ቀደሙ በመወነጃጀል ላይ ያተኮሩ ሳይሆኑ፣ በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ሰብዓዊ መብቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆንና እነዚህንም እንዲያጠናክር የሚያሳስቡ ነበሩ፡፡

  አብዛኛዎቹ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና መረጋገጥ ላይ የሚሠሩ ተቋማት፣ እንዲሁም ከመናገርና ከመጻፍ ነፃነቶች ጋር በተገናኘ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ‹‹በኢትዮጵያ የለውጥ ንፋስ መንፈስ ጀምሯል››፣ ወዘተ የሚሉ ጥንቅሮችን በማቅረብ መንግሥት ከዚህ አንፃር የተጠናከረ ሥራ እንዲያከናውን የሚመክሩ ነበሩ፡፡

  እንዲህ መሰሉ የጫጉላ ሽርሽር ጊዜ ግን ያበቃለት ይመስላል፡፡ በተለይ ባለፈው ሳምንት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥትን በመብት ጥሰት እንደገና የከሰሰ ሲሆን፣ መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሪፖርቱን ሀቀኝነት በማጠየቅና በማጣጣል ጋብ ብሎ የነበረው ሙግት ዳግም ተቀስቅሷል፡፡

  የሪፖርቱ መውጣትን ተከትሎ መደበኛውም ሆነ የማኅበራዊ ትስስር አውታሮች የተለያዩ ዘገባዎችን በማስተናገድ ላይ ሲሆኑ፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚቀርቡ ዘገባዎች በአብዛኛው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሪፖርቱን ማጣጣልና ሪፖርት አጠናቃሪውን ተቋም በመወረፍ ላይ ያተኮሩ ሆነው ሰንብተዋል፡፡ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ደግሞ ሪፖርቱን በመደገፍና በመቃወም ላይ ያተኮሩ በርካታ ዘገባዎችና ሙግቶች እየተሰሙ ነው፡፡

  በዚሁ ልክ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የቀረበውን ሪፖርት አስመልክቶ የተለያየ አቋም እያንፀባረቁ ናቸው፡፡

  ከዚህ አንፃር ሦስት ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) ‹‹የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ልዩ ትኩረት ያሻዋል›› በማለት፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በአገሪቱ ሰላምና የሕግ የበላይነት ማስከበር አለመቻሉን የሚያሳይ እንደሆነ በመጥቀስ፣ በሪፖርቱ የቀረቡትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦችና ተቋማት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የማጣራት ሒደቱም ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳውቅ መንግሥትን ጠይቋል፡፡

  ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አምነስቲ ኢንተርናሽናል አጠናቅሮ ያቀረበው ሪፖርት የሚጠበቅበትን ሙያዊ ገለልተኝነት ያልተከተለ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሪፖርቱ ሊያካትታቸው እየተገባ ሆን ብሎ ያለፋቸው በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተከስቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሪፖርት ያልተደረገው ደግሞ ‹‹በተቋሙ ውስጥ በሴራ የተሰማሩ ግለሰቦች በሕዝብ ትግል ለተሸነፉ ኃይሎች ቀድመው ያደሩና ባደረባቸው የፖለቲካ አሠላለፍ ወገንተኝነት ተፅዕኖ ምክንያት መሆኑን አብን በውል ይገነዘባል፤›› በማለት፣ በሪፖርቱ ጥንቅር ላይ ያለውን ተቃውሞ አሰምቷል፡፡

  ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሎቹ ልዩ ኃይል፣ እንዲሁም በሚሊሻ ታጣቂዎች አማካይነት ተከሰቱ ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በማቅረብ፣ ይህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር በመጀመርያዎቹ ወራት ሲያከናውናቸው የነበሩ የሰብዓዊ መብቶች ማስከበር እንቅስቃሴን ወደኋላ የሚመልስ እንደሆነ አብራርቷል፡፡

  በሪፖርቱ ውስጥ በሁለቱ ክልሎች የተከሰቱ ሕገወጥ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስር፣ በኃይል ከመኖርያ ቀዬ መፈናቀል፣ በማኅበረሰቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ውጥረቶችን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎች ቀርበዋል፡፡

  በሪፖርቱ ውስጥ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በእስር ላይ የነበሩ፣ እንዲሁም ሌሎች የዓይን እማኞችን እንደ መረጃ ምንጭነት መጠቀሙን የሚገልጸው ሪፖርቱ እነዚህ እማኞቹ የነገሩትን በዝርዝር አስፍሯል፡፡

  በሪፖርቱ መሠረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እ.ኤ.አ. በ2019 በምሥራቅ ጉጂ ዞን በዱግዳ ዳዋ ወረዳ ሃራቀሎ ከተማ ኦጋ ኡዴሳ የተባለ ወጣት መግደላቸውን፣ የግድያው ምክንያት ደግሞ በወቅቱ ተከልክሎ የነበረውን የሞተር ብስክሌት መጠቀምን ተላልፏል የሚል መሆኑን ገልጿል፡፡

  በተመሳሳይ እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2019 አዳዴ ቀበሌ ነዋሪ የሆነውን የ32 ዓመት ነጋዴና የሦስት ልጆች አባት የሆነውን አራቲ ሹኑንዴን መግደላቸውን ሪፖርቱ አካቷል፡፡ ለዚህ ግድያ ምክንያት የሆነው ደግሞ የሟች ስልክ መጥራት እንደሆነ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም የቀበሌ ሚሊሻዎች፣ የኦሮሚያ ፖሊስ፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት አባላት በምሥራቅና በምዕራብ ጉጂ የዘፈቀደ እስር ማካሄዳቸውን አትቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሪፖርቱ በምዕራብና ምሥራቅ ጉጂ፣ እንዲሁም በስንቅሌ በታሳሪዎች ላይ ግርፋት (ቶርቸር) እና ያልተገባ አያያዝ መፈጸሙን ዘርዝር አቅርቧል፡፡

  በአማራ ክልል ደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በተመለከተ ደግሞ በቅማንት ተወላጆች ላይ ደረሰ ያለውን የጉዳት መጠን በማስረዳት፣ በወቅቱ የመከላከያ ሠራዊት ኃይል ከጥቃቱ አካባቢ በቅርብ ርቀት ቢኖርም የደረሰውን ጥፋት ለመከላከል ግን ምንም እንዳላደረገ ከእማኞች ያገኘነውን መረጃ መሠረት አድርጎ አቅርቧል፡፡

  ሪፖርቱ ይፋ ከሆነ በኋላ በርካታ አካላት አቋማቸውን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ የአማራና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት ሪፖርቱን እንደማይቀበሉት በይፋ ከመግለጽ ባለፈ የሪፖርቱን ግኝቶች አጣጥለዋል፡፡

  የሪፖርቱን ግኝት ከማጣጣል ባለፈም ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ተከስተው የነበሩ ግጭቶችና የዜጎች ሞት አልተካተተም በማለት ተቃውመዋል፡፡ በተለይ የኦሮማያ ክልላዊ መንግሥት ሪፖርቱን ‹‹የተሳሳተና ሚዛናዊነት ያደለው ነው›› በማለት አጣጥሎታል፡፡

  ‹‹ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በነበሩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ዝምታን የመረጠ ነበር፤›› በማለት ሪፖርቱን ያጣጣሉት የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ ‹‹ሪፖርቱ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበና ሊታረም የሚገባው ነው፤›› ብለዋል፡፡

  የእሳቸውን የተቃውሞ መግለጫ ተከትሎ ግን በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ምን እንደሆነ ለመግለጽና ከዚህ ቀደም ደረሱ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓለም አቀፍ ተቋማት ወይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ሲወጡ ነው ወይ የሚነሱት በማለት፣ የክልሉ መንግሥት አካሄድ ራሱ ከመስመር የወጣ ነው ሲሉ የሚተቹ ድምፆች በርክተዋል፡፡

  በሪፖርቱ ያልተካተቱ ነገር ግን ደርሰዋል የሚባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ‹‹እኛ ብቻ አይደለንም›› ለሚል መከራከሪያና ራስን ለመከላከል ጥቅም ላይ ማዋል ከመንግሥት የሚጠበቅ አይደለም በማለት ትችት የሚሰነዝሩ ወገኖች ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም ደረሱ የሚባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የአምነስቲ ሪፖርት ባይወጣ ተዳፍነው ሊቀሩ ነበር ወይ በማለት መልሰው ሪፖርቱን የሚቃወሙትን አካላት ይጠይቃሉ፡፡

  ከክልላዊ መንግሥታት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎች መግለጫ በተለየ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ‹‹ሰብዓዊ መብት የምናከብረውና የምናሰከበረው ለማንም ብለን ሳይሆን፣ ለሕዝባችን መከበርና ለፍትሕ ስንል ነው፤›› በማለት በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡

  አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን መግለጫ እንደተመለከቱት የገለጹት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጓ፣ ‹‹የማጣራት ሥራችንን አጠናቀን ምላሽ ለመስጠት በሒደት እያለን መግለጫው በተለያዩ ማዲያዎች ተሠራጭቷል፤›› ብለው፣ ለሪፖርቱ ምላሽ ለመስጠት መንግሥት እየሠራ እንደነበር አውስተዋል፡፡

  አክለውም፣ ‹‹በማጣራት ሥራችን በሚገኘው ውጤት ሪፖርቱ እውነት በሆነበት መወሰድ ያለባቸውን ዕርምጃዎች እንወስዳለን፡፡ ሐሰት በሆነበት ወይም በተጋነነበት ደግሞ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋር በመወያየት ሪፖርቱ እንዲስተካከል እንጥራለን፡፡ ይህ ባይቻል እንኳን ሕዝባችንና ዓለም እውነቱን እንዲያውቀው በመረጃ አስደግፈን እናሳያለን፤›› ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

  ዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፖርት ባወጡ ቁጥር በመንግሥትና በተቋማቱ መካከል የሚኖረውን ውዝግብ የማይርቀው መንግሥት፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የገባውን ቃል ማክበር ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ምክር የለገሱም በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ቃሉን ጠብቆ ተቋማቱን ዝም ያሰኛል? ወይስ ሌላ ውዝግብ ውስጥ ይገባል? የሚለው በሒደት የሚታይ ቢሆንም፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አሁንም ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -