ተቋርጦ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር፣ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ዓርብ ሰኔ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ዳግም ተጀመረ፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአካል መገናኘት ስላልተቻለ የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴዎች ድርድሩን እያካሄዱ የሚገኙት፣ በበይነ መረብ አማካይነት በሚደረግ የቀጥታ ቪዲዮ ውይይት (ቪዲዮ ኮንፈረንስ) አማካይነት ነው፡፡
በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የሚካሄደውን ድርድር የአፍሪካ ኅብረትን በመወከል የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የሆነችው ደቡብ አፍሪካ እየመራች ነው፡፡
ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባለሙያዎች በታዛቢነት ድርድሩን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ የድርድሩ ትኩረት የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ፣ የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴዎች ከዚህ ቀደም ሲያደርጓቸው በነበሩ ድርድሮች መግባባት ባልደረሰሱባቸው ጉዳዮች ላይ ነው፡፡
ከእነዚህም ጉዳዮች መካከል የውኃ ሙሌትና የግድቡ አስተዳደርን በተመለከተ ሦስቱ አገሮች ተደራድረው የሚደርሱባቸው ስምምነቶች አፈጻጸም ላይ አለመግባባት ቢከሰት፣ እንዲሁም በውኃ ሙሌት ወቅት ድርቅ ቢከሰት እንዴት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ይቻላል? እንዴትስ ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል? የሚሉትን ጉዳዮች የተመለከቱት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የስምምነቶቹ አፈጻጸም ላይ አለመግባባት ቢከሰት በድርድርና በአሸማጋይ ሊፈታ ይችላል የሚል አቋም ስታንፀባርቅ፣ ግብፅና ሱዳን በበኩላቸው አሁን የሚደረሰው ስምምነት የማያዳግምና አስገዳጅ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የድርቅ ጉዳትን የመቀነስ ኃላፊነት የሦስቱም አገሮች መሆን እንዳለበት ስትከራከር፣ በተለይ ግብፅ ይህ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ብቻ ኃላፊነት እንዲሆን ትሻለች፡፡
የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴዎች ዳግም የጀመሩት ውይይትን የተመለከተ ሪፖርት፣ ለአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡