Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ማባሪያ ያጣው የዜጎች ዕልቂት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኢትዮጵያ ስም የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ቀልብ በተለየ ሁኔታ ገዝቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክተው፣ ‹‹ግብፅ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች›› በማለት የሰጡት አስተያየት፣ ከመገናኛ ብዙኃኑ ትኩረት በላቀ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የውይይት አጀንዳ ነበር፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እየተባባሰና ሥር እየሰደደ የመጣው የዜጎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተለያዩ ጥቃቶች መዳረግ እንዲሁ፣ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ቀልብ ስቧል፡፡ እነዚሁ የብዙኃን መገናኛዎችም በዚህ ክልል በደረሰ ጥቃት ይህንን ያህል ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን አጡ፣ ይህን ያህሉ ጉዳት ሲደርስባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለዘመናት ከሚኖሩበት ቀዬና ቤት ንብረት ተፈናቀሉ የሚሉ ዘገባዎች ለታዳሚዎቻቸው በማቅረብ ተጠምደዋል፡፡

  ምንም እንኳን የዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ መፈናቀልና ያፈሩት ሀብት መና ሆኖ መቅረት፣ ግድያ እንዲሁም የአካል ጉዳትን የተመለከቱ ዜናዎች የኢትዮጵያ መገለጫዎች ከሆኑ የሰነባበቱ ቢሆንም፣ ሰሞኑን ግን የጉዳቱ መጠንም ሆነ ሽፋን በእጅጉ የበዛና የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ከምንጊዜውም በላይ አንገብጋቢ የሆነበት ወቅት ላይ መደረሱን ብዙዎችን ያስማማል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር ከጨበጡ አንስቶ ከሰላምና ደኅንነት ጋር የተለያዩ መንገራገጮች እዚህም እዚያም ይታዩ የነበረ ቢሆንም፣ የዚያን ያህል ደግሞ የአገሪቱ ዜጎች በተስፋ የተሞሉም ነበሩ፡፡ የመጀመርያዎቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ወራት ተስፋ የሰነቁ ዜጎች የድጋፍ ጊዜ እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚከሰቱ ግጭቶችና በአንዳንድ ወገኖች አጠራር ደግሞ ‹‹የዘር ማጥፋት›› ክስተቶች ግን የብዙዎችን ተስፋ እንደ ጉም እያተነኑ ነው፡፡ እየተደጋገመ በመጣው የዜጎች ሕይወት እንደ ዋዛ መቀጠፍ አብዛኛው ዜጋ ከፖለቲካዊ ድጋፍና ተቃውሞ ወጥቶ፣ በቀጣይ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ዙሪያ እንዲብሰከሰክ ምክንያት ሆኗል፡፡

  2013 ዓ.ም. ከባተ ጀምሮ ደግሞ የዜጎች ሞት፣ እንግልት፣ ሥቃይ፣ መፈናቀልና የአካል ጉዳት ከምንጊዜውም በላይ ገዝፎ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያነት በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ እንዲሁም በሶማሌና በአፋር ክልል መካከል የተፈጠሩት ግጭቶች ለብዙዎች የሰቀቀንና የመብሰክሰክ ምንጭ ሆነው ሰንብተዋል፡፡

  በቤንሻንጉል ክልል የዜጎች ሞትና መፈናቀል ዜና ቀለሙ ገና ሳይደርቅ የጉራፈርዳው ተከተለ፡፡ በዚህ አጀብ አጀብ ሲባል በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ  ላይ የተከሰተው ተሰምቶ፣ ‹‹መንግሥት ምን እየሠራ ነው?›› የሚለው ጥያቄ ቀርቦ  ሳያበቃ፣ ሌላ አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት ከወደ ኦሮሚያ ተሰማ፡፡

  ይህ አሳዛኝ ዜና ደግሞ እንዲሁ የዜጎችን መሞትና መፈናቀል የሚያረዳ ነው፡፡ እሑድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዋጋ ቃንቃ ቀበሌ በንፁኃን ዜጎች ላይ ጥቃት መድረሱን የሚያትቱ የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ዜናውን ሲያዘዋውሩት የነበሩ ሲሆን፣ ሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ከረፋዱ ጀምሮ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ጉዳዩን በማውገዝ የተለያዩ መግለጫዎችን መስጠት ጀመሩ፡፡ አሁንም ሌላ የመግለጫ ጋጋታ ተባለ፡፡

  ወደ መንግሥት የተቀሰሩት ጣቶች

  ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት አዲስ አመራር ያስተናገደችው ኢትዮጵያ አዲሱን አመራር ተከትሎ ተፈጠሩ በተባሉት ስንጥቆች ሳቢያ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች ግጭቶች ሲከሰቱ ዜጎች ሲሞቱና ሲፈናቀሉ ማስተዋል እየተለመደ ሲመጣና የዜጎች ሞት ቁጥር ወደ መሆን ሲቀየር፣ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ ወስዶ የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ያስከብር የሚሉ ድምፆች መስማት ጀምረው ነበር፡፡

  ነግር ግን በወቅቱ የመንግሥት ምላሽ የነበረው ከነበርንበት ኢዴሞክራሲያዊ ባህል አንፃር እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ በትዕግሥት ማለፉ አስፈላጊ ነው የሚል ነበር፡፡

  የዜጎች በደቦ ፍርድ መሞት፣ ለአካል ጉዳት መዳረግና መፈናቀል ከዕለት ወደ ዕለት ከመቀነስና በቁጥጥር ሥር ከመዋል ይልቅ መልክና ባህሪውን እያቀያየረ መከሰት፣ የበርካታ ዜጎችና ፖለቲከኞች ‹‹መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ በመውሰድ ሰላምና ደኅንነትን ያረጋግጥ›› ለሚሉ በርካታ ጥያቄዎችና መግለጫዎች ምክንያት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ነገሮችን በትዕግሥት መመልከቱ ይሻላል የሚለው አተያይና ማብራሪያ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ፣ የጉዳቱ መጠን እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል በማለት የሚከሱትና የሚተቹት በርካቶች ናቸው፡፡

  ከዚህ አንፃር በምዕራብ ወለጋ ከተከሰተው ማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት በኋላ መግለጫዎች ያወጡና ሐሳባቸውን የሚሰነዝሩ ተቋማትና ግለሰቦች፣ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ለመድረሱ ዋነኛ ተጠያቂ መንግሥት እንደሆነ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግሥትም አሰቃቂ ዕልቂቱን የሚኮንን መግለጫ ከማውጣትና ከማውገዝ የዘለለ ያለውን የብቸኛ ኃይል ባለቤትነት ተጠቅሞ አገሪቱን ከማረጋጋት፣ ሰላምና ደኅንነት ከማስፈን አንፃር ያከናወነው ተግባር ‹‹እዚህ ግባ›› የሚባል አይደለም በማለትም ይተቻሉ፡፡

  ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የምዕራብ ወለጋውን ጥቃት ተከትሎ ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ ‹‹መንግሥት የሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫው፣ መንግሥት አሁን ችግሮችን ለመፍታት እየሄደበት ያለውን መንገድ ‹‹ሕጋዊ፣ ትክክለኛና ተገቢ›› ነው ብሎ እንደማያምን አስታውቋል፡፡

  ‹‹በመሆኑም፣ ጉዳቱን በማድረስና በመደገፍ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ ናቸው በማለት የሚወነጅላቸውን አካላት በመግለጫዎች ከማውገዝ ባለፈ፣ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብና ለተጎጂዎች ፍትሕ ይሰጥ፤›› በማለት፣ መንግሥት የዜጎችን ዕልቂትና እንግልት በመግለጫ ከማውገዝና ከመኮነን ባለፈ ሕጋዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡

  ከዚህም ባሻገር፣ ‹‹መንግሥት ተጨባጭ የደኅንነት ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት፣ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን በማዘጋጀት ወደ ፈጣን ዕርምጃ ይግባ፤›› የሚል ጥሪም አስተላልፏል፡፡

  በተመሳሳይ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ ‹‹በአገሪቱ ዕለት ዕለት እየተመለከትናቸው ያሉ ዕልቂቶች የሚከሰቱት ወይ ሆን ተብለው ነው አልያም ደግሞ መንግሥት ዕልቂቶቹን የመቆጣጠር አቅም ስለሌለው ነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

  ‹‹ከዚህ ቀደም ባንኮች ሲዘረፉ፣ ሰው ተዘቅዝቆ ሲሰቀልና ዜጎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲፈናቀሉ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ በመቆየቱ ሳቢያ አሁን እዚህ ላይ ደርሰናል፤›› በማለት ጉዳዩ ሳይቃጠል በቅጠል መሆን እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡  

  ሰሞነኛውን አሳዛኝ ዕልቂት ተከትሎ በመንግሥት ወገን እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎች እንዲህ ያለ የዜጎችን ዕልቂት እያደረሱ ያሉት ‹‹ኦነግ ሸኔና ሕወሓት›› ናቸው የሚል ክስ ይሰማል፡፡ ከዚህ አንፃር አቶ ጌታቸው፣ ‹‹እንዲህ ያለውን ዕልቂት እያደረሱ ያሉት እነሱ ከሆኑ ዕርምጃ የማይወሰድባቸው ለምንድነው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

  መንግሥት በአግባቡ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ አገሪቱ እንዲህ ያለ የቀውስ አረንቋ ውስጥ መዘፈቋን ከሚስማሙት ፖለቲከኞች አንዱ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር አቶ አዳነ ታደሰ፣ ባለፉት 27 ዓመታት በአገዛዙ ባህሪ የተነሳ በርካታ ችግሮች ሲከሰቱ መክረማቸውን በመግለጽ አሁን ግን ዕልቂቱ በተለየ ሁኔታ እየደረሰ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  ‹‹እርግጥ ነው ባለፉት 27 ዓመታት አገሪቱ በርካታና ዘርፈ ብዙ ችግሮች አስተናግዳለች፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን በተለየ ሁኔታ አንድ ዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች አሁን ያቆማሉ፣ መንግሥትም ዕርምጃ ወስዶ አገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት ይመልሳታል ብለን ብንጠብቅም፣ መፍትሔ ጠፍቶ በአሳዛኝ ሁኔታ በዜጎች ዕልቂት አንገታችንን ደፍተናል፤›› በማለት፣ ‹‹መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን እየተወጣ ባለመሆኑ ምክንያት ነው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ይፈጠር የምንለው፤›› ሲሉ አቋማቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

  ሁሉን አቀፍ የሆነ አገር አቀፍ የምክክርና የውይይት መድረክ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት አቶ አዳነ፣ ‹‹አሁን በአገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ ውጥረቶች አንድ ፓርቲ ለብቻው የሚፈታቸው አይደሉም፤›› ብለው፣ ዳግም መንግሥት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  በዚህ የሁሉን አቀፍ ድርድርና ውይይት የሚስማሙት አቶ ጌታነህም፣ ፓርቲያቸው ባልደራስ ከዚህ ቀደም ያቀረበውን፣ ‹‹አገሪቱን ለተወሰነ ጊዜ ቴክኖክራት ይምራት›› የሚለውን ሐሳብ በማስታወስ፣ ‹‹አሁንም ቢሆን ችግሩን ለመፍታት በዋናነት ልንከተለው የሚገባው መንገድ ውይይት ብቻ ነው፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ነገር ግን ሥርዓቱ የሚሰማ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

  በምዕራብ ወለጋ የተከሰተውን ዕልቂት ተከትሎ በርካታ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ሐዘናቸውንና ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ወዘተ. የሚጠቀሱ ሲሆን፣ እነዚህ ተቋማትም ያሳሰቡት በአገሪቱ የረበበውን ውጥረት ለማርገብ ዋነኛው የመፍትሔ መንገድ ሁሉን አቀፍ ውይይት መሆኑን ነው፡፡

  ጥቃቱን ያወገዙት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በዜጎች ላይ ጥቃት የሰነዘሩ አካላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ተጠያቂ እንዲሆኑ ከመጠየቅ ባለፈ፣ በአገሪቱ ፖለቲከኞች የሚነሳው የውይይት ጥያቄ አስፈላጊ መሆኑን በማስረገጥ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ተዋናዮች አካታችና ሁሉን አቀፍ ውይይት በማድረግ፣ በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባት እንዲፈጠር አሳስበዋል፡፡

  በተመሳሳይ የአውሮፓ ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ውጥረቶች በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው በመጥቀስ፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ ውይይት ለማከናወን ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ከምንጊዜውም በላይ የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

  የመንግሥት ምላሽ

  የምዕራብ ወለጋውን ጥቃት ተከትሎ ፕሬዚዳንቷ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዘናቸውን ከመግለጽ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የፀጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሰማርተው ዕርምጃ እየወሰዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጥቃቱን በማውገዝ መግለጫዎች አውጥተዋል፡፡ ከነዚህም ተቋማት መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንዱ ሲሆን፣ ‹‹ይህን መሰል ወንጀል በተደጋጋሚ እየተፈጸመ የዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈ ይገኛል፤›› በማለት፣ እንዲህ ያለ የተደጋገመ ጥቃትን ለማስቆም መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡

  ሐሳባቸውን የሰነዘሩት ባለሥልጣናትም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት የማይክዱት አንዱና ዋነኛው ሀቅ፣ እንዲህ ያሉ መሰል ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ሲሆን፣ ለዚህም መንግሥት የማያዳግም መፍትሔ እንዲሰጥ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

  የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞችም ሆኑ ፖለቲከኞች፣ የአገሪቱ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የአብዛኞቹ ምክርም ሆነ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያተኩረው የውይይትና የድርድር አስፈላጊነት ላይ ነው፡፡

  ከዚህ አንፃር አሁንም ቢሆን ቀጣይ አሳዛኝ ዕልቂት ከመከሰቱ በፊት በአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ የሚሳተፉበት ሁሉን አቀፍ የንግግር መድረክ መዘጋጀት የሚወተወት አጀንዳ ሆኗል፡፡ በመሆኑም መንግሥትን ጨምሮ ያገባናል ባዮች ሁሉ የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ካልተጀመረ፣ የአገሪቷ ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ስለሚገባ በድርድር መፍትሔ ማምጣት የዜጎች አንገብጋቢና ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ሆኗል፡፡

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -