Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የጅግጅጋ ልዩ ገበያዎች

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ከአዲስ አበባ 637 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ሃባ አብዱላሂ ሰማያዊ ቀሚስ፣ ብርቱካናማ ሂጃብ ጠቆር ያለ ሸበጧን ለብሳ ቅዳሜ በጠዋት ገበያ ላይ ተገኝታለች።

  በቀኝ እጇ አነስ ያለች የገንዘብ ቦርሳ፣ በግራ እጇ ደግሞ አነስ ያለ ሰማያዊ ዘምቢል ይዛለች። ለጎብኚዎች አስገራሚ ለነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ክስተቶች በሚታዩበት የሰልባጅ ገበያ ሮጥ ሮጥ እያለች ዕቃዎችን ለመሰብሰብ ትጥራለች። “አንድም ቅዳሜ ቀርቼ አላውቅም፤” የምትለው ሃባ በቤትዋ ያላትን ገንዘብ ሰብሰባ ከሌላትም ከባልዋ ለቤቷ ከጎርቤት ተበድራ በጠዋት ወደ ገበያ ታመራለች።

  እስከ እኩለ ቀን በገበያው ስትሸምት የምትውለው የ34 ዓመቷ ሃባ፣ ደህና ብር ካለት ወደድ ያለ ቆንጆ ድርያ፣ ቀሚስ፣ ሽቶ፣ ዕጣንና አወዳይ ጫት ገዝታ ትገባለች። ገንዘብ ከሌላት ደግሞ አንድ አራት ደህና ሰልባጅ ልብሶቿን ትገዛና ረከስ ያለ ጫት ጨምራበት ወደ ቤቷ ታመራለች።

  “ብዙዎቻችን የጅግጅጋ ነዋሪዎች ከዚህ ብዙም የተለየ ቅዳሜ አናሳልፍም፤” የምትለው ሃባ፣ “ገንዘብ ብናገኝም ባናገኝም በገበያ ቀን አይቀርም፤” ስትል ገበያው ለእሷ ያለውን ትርጉም ታስረዳለች። “ብዙ ብር ኖረህ አልኖረህ፣ 100 ብርም ያዝክ ሁለት ሺሕ ብር፣ ገበያ ከወጣህ ባዶ እጅህን አትመለስም፣ የያዝካትን ብር ግን ሳትጨርስ መምጣት የማይታሰብ ነው” ትላለች ስለ ሶማሌ ክልል መዲና ጅግጅጋ ከተማ አውርታ የማትጠግበው ሃባ።

   በጅግጅጋ ሰልባጅ ገበያ የሌለ ዕቃ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከአምስት ብር እስከ 50 ሺሕ የሚያውጡ ዕቃዎች በግልጽ ይሸጣሉ። “100 ብር ይዘህ ወጥተህ ሁለት ፌስታል ልብስ ገዝተህ፣ የግመል ወተትህን ከሻይ ጋር በብስኩት እያዋዛህ ጠጥተህ ወደ ቤት ልትገባ ትችላለህ፤” የሚለው የ22 ዓመቱ በጅግጅጋ ተወልዶ ያደገው ዳዊት ዮናስ፣ “ሰልባጅ ገበያ ተገብቶ የሚታጣ ነገር እንደሌለ፤” ያነሳል።

  ዋጋቸው ለመገመት በሚያስቸግር ሁኔታ ርካሽ የሆኑ ዕቃዎችን በጅግጅጋ ገበያዎች ማግኘት ለከተማው ነዋሪዎች ላያስገርም ይችላል። ይሁን እንጂ ለጎብዒዎች አሊያም ከሌላ የኢትዮጵያ ከተሞች ለመጡ ዜጎች በሚያስገርም መልኩ “አምስት አምስት ብር” አሊያም “ሸንሸሪያ” የሚሉ በጋሪ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የተለበሱ ልብሶችን የሚሸጡ ነጋዴዎች በጅግጅጋ ሞልተዋል። ተለብሰው ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ የሙሉ ልብስ ኮቶችን በጅግጅጋ ገበያ ለመግዛት ሸማቾች ይዘው መምጣት የሚጠበቅባቸው 10 ብር ብቻ ነው።

  በግምት ከ500 በላይ ፈቃድ ወስደው የሚነግዱ ነጋዴዎች አሉበት ተብሎ በሚታመነው በጅግጅጋ ሰልባጅ ገበያና ሌሎች አዋሳኝ ገበያዎች ቁጥራቸው ከዚህ የላቀ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ጋሪያቸው ላይ አስቀምጠው አሊያም ምንጣፋቸውን ዘርግተው ልብሶችን፣ ጫማዎችን፣ ጌጣጌጦችን፣ ጫት፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ምርቶችን ይሸጣሉ። ልክ መርካቶ በውስጧ የተለያዩ ገበያዎችን እንዳቀፈችው በጅግጅጋ ገበያ ውስጥም ታይዋን፣ ኩድራ፣ እንጨት፣ ዕጣን፣ ጫት፣ ሱድያና ወተት ተራዎችን በውስጡ ይዟል።

  ገበያው ሳምንቱን ሙሉ ክፍት ቢሆንም፣ በጣም ሞቅ የሚለው ቅዳሜና እሑድ ነው። ይሁን እንጂ ወደ ገበያው በማንኛውም ብቅ ላለ ጎብኚ ምናልባትም ሁሌም ሞቅ ያለ ሊመስለው ይችላል። በየቀኑ የሚመጣ ሰው አይጠፋም። ሁሌም ሥራ አለ፣ ሁሌም ገዢ አለ”፡፡

  በገበያው እየተዘዋወረ የተለያዩ የቀን ሥራዎችን የሚሠራው ከድር መሃመድ “ተማሪ ብሆንም እንኳን በትርፍ ጊዜ ወደ ገበያው መጥቼ እስከ ከሰዓት ደረስ ዕቃዎች ባሻሽጥ ወይም ዕቃ ባወርድ 200 ብር አላጣም፤” ሲል ስለ ገበያው ያለውን ምልከታ ለሪፖርተር አጋርቷል።

  ብዙውን ጊዜ ወደ ሰልባጅ ገበያ ለመሸመት ብቅ የሚሉት የመንግሥት ሠራተኞች፣ የቀን ሠራተኞችና ሌሎች አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቢሆኑም፣ የቡቲክ ባለቤት የሆኑ ነጋዴዎች ሳይቀር ወደ ገበያ ብቅ እንደሚሉ ሻጮች ያነሳሉ። “የምንሸጠው ልብስ የተለበሰ ቢሆንም፣ ጥራት ያላቸውን እየመረጡ የሚወስዱ ነጋዴ ደንበኞች አሉኝ፤›› የሚለው ከአራት ዓመታት በላይ በነጋዴነት ያሳለፈው ዳልመር መሃመድ፣ “አንዳንዶች ሳይቀር አዲስ አበባን ጨምሮ ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የሚመጡ ናቸው፤” ሲል ይናገራል።

  የጅግጅጋ ልዩ ገበያዎች

   

  ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ወደ ጅግጅጋ በቋሚነት የሚመጡ ነጋዴዎች ቁጥራቸው ቀላል እንደማይሆንም የከተማው ነዋሪዎች ያነሳሉ። ብዙዎቹም ወደ ከተማው የሚመጡት ጫማና ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ለመግዛት ነው።

  ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በጅግጅጋ የሚሸጡ ምርቶች ርካሽ መሆናቸው ሲሆን፣ ምርቶቹም በአዲስ አበባና በደቡብና ሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች ጥሩ ዋጋ ስለሚያወጡ እንደሆነ ይነሳል። ለምሳሌ በጅግጅጋ አንድ ናይክ ወይም አዲዳስ ኦርጂናል ጫማ ተወደደ ቢባል በ500 ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ ሌላ ቦታ ተመሳሳይ ሞዴል ያለው ተመሳሳይ ስያሜ ያለው ምርት እስከ 2,500 ብር ይሸጣል። የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ልዩነትም ከፍ ያለ ነው። በአዲስ አበባ 10 ሺሕ ብር የሚሸጥ ስልክ በጅግጅጋ እስከ 7,500 ብር ይሸጣል፡፡ ለተከራከረ ከዚህም በታች ሊሸጥ ይችላል።

  ሌላው ጅግጅጋን ልዩ የሚያደርጋት የወርቅ ገበያዋ ነው። ምናልባትም ከተማዋ ብቸኛ ወርቅ መንገድ ላይ የሚሸጥባት ልትባል ትችላለች። በዚህ ገበያ አንድ ግራም 21 ካራት ወርቅ እስከ 3,500 ብር ይሸጣል። ብዙውን ጊዜ በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሴት ነጋዴዎች ሲሆኑ፣ በመንገድ ላይ የሚሸጧቸው አንዳንድ የወርቅ ጌጣጌጦች እስከ ስምንት ግራም ድረስ ይደርሳሉ፡፡ ይህም ማለት 28 ሺሕ ብር የሚያወጡ ጌጣጌጦችን መንገድ  ላይ በግላጭ ይሸጣሉ እንደማለት ነው።

  የጅግጅጋ ገበያዎች ገጽታ አንዱ በእነዚህ ገበያዎች ተገኝቶ መከራከር አለመኖሩ ነው፡፡ የተጠየቀውን ከፍሎ መሄድ! “ከተከራከርክ” ይላል ከድር፣ “እውነትም ለከተማው እንግዳ ነህ።

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች