የብሔርና የዘር ማንነት መረጃን መመዝገብና ማቀናበርን ይከለክላል
በኢትዮጵያ የግል መረጃ የሚጠበቅበትን የሕግ ማዕቀፍ የሚያበጅና በሕግ ማዕቀፉ መሠረት፣ የግል መረጃ መጠበቁን የሚያረጋግጥና የሚከታተል የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን የሚያቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተሰናድቶ ወደ ማፅደቅ ሒደት ሊገባ መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አመለከተ።
ሪፖርተር ያገኘው ረቂቅ የሕግ ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ የሕግ ማዕቀፉ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለግል መረጃ ጥበቃ እንዲደረግ የሚያጎናፅፈውን የግል መብት መሠረት አድርጎ፣ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውንም መብት ግለሰቦች ማግኘት እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
በዚህም መሠረት ማንኛውን የግል መረጃ የመያዝ ኃላፊነት ያለበት አካል የሚሰበስበውን የግል መረጃ፣ በሕግ ላልተፈቀደ አካል እንዳይደርስ ጠንካራ የጥበቃ ሥርዓት መዘርጋትና ደኅንነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
በተጨማሪም የግል መረጃ የመያዝ ወይም የመመዝገብና የማቀናበር ሥራ ፈቃድ በሚሰጠው አካል ብቻ የሚከናወን እንደሚሆን፣ ይህንንም ለማረጋገጥና ለመቆጣጠር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሚሆንና በዚሁ ምክር ቤት የሚቋቋም የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን እንደሚቋቋም በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ ድንጋጌዎች ይገልጻሉ።
ረቂቅ አዋጁ ጥንቃቄ የሚደረግላቸው መረጃዎችን የሰየመ ሲሆን፣ እነዚህን መረጃዎች በአገር ደኅንነትና በሌሎች ውስን ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም አካል መመዝገብና ማቀናበር እንደማይችል ይደነግጋል።
ጥንቃቄ የሚደረግላቸው ወይም መመዝገብና ማቀናበር የማይደረግባቸው የግል መረጃ ተብለው በረቂቅ ሕጉ የተሰየሙትም፣ የብሔርና የዘር ማንነትን የተመለከቱ መረጃዎች፣ የሃይማኖትና መሰል እሞነቶችን የተመለከቱ መረጃዎች፣ የዘረመል መረጃ፣ የአዕምሮ ጤንነት ሁኔታን የተመለከተ መረጃ፣ የግብረ ሥጋ ሕይወት ምርጫን የተመለከተ መረጃ፣ የፖለቲካ አቋምን፣ የሠራተኛ ማኅበር አባልነትን የተመለከተ መረጃ ዋነኞቹ ናቸው።
እነዚህ ጥንቃቄ ይደረግላቸዋል ተብለው የተሰየሙ የመረጃ ዓይነቶችን ማንኛውም መረጃ መዝግቦ የመያዝና የማቀናበር ፈቃድ የተሰጠው ሕጋዊ አካል፣ መመዝገብና ማቀናብር እንደማይችል ክልከላ ረቂቅ አዋጁ ይጥላል።
ነገር ግን ጥንቃቄ የሚደረግላቸውን መረጃዎች መመዝገብና ማቀናበር የሚፈቀድበት ውስን ልዩ ሁኔታዎች ረቂቅ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በንግድ ዓላማ ያልተቋቋመ የመንግሥት ተቋም ሕጋዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት መረጃው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ የሌሎች ግለሰቦችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል የግል መረጃው ለሕክምና ተቋም የሕክምና ዓላማ አስፈላጊ ከሆነ፣ መረጃው የሌላን ግለሰብ መብት የሚመለከትና ፍትሕ ለማግኘት መብት አስፈላጊ ከሆነ፣ የመረጃው ባለቤት መረጃውን ለማስመዝገብ በጽሑፍ ፈቃዱን የገለጸና ይህንን ማድረጉም አስፈላጊ ከሆነ ጥንቃቄ የሚደረግለት መረጃን መመዝገብና ማቀናበር ሊፈቀድ ይችላል።
ከላይ በተገለጹት ልዩ ሁኔታዎች ምክንያት ጥንቃቄ የሚደረግለት መረጃን መመዝገብና ማቀናበር ረቂቅ አዋጁ የሚፈቀድ ቢሆንም፣ ጥንቃቄ የሚደረግላቸው ተብለው ከተሰየሙት ውስጥ የብሔርና የዘር ማንነትን የተመለከቱ መረጃዎች ግን በምንም ዓይነት ሁኔታ መመዝገብና ማቀናበር እንደማይቻል ረቂቅ አዋጁ ይገልጻል።
ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል መረጃን ከአገር ውጭ ለማስተላለፍ በቅድሚያ የኮሚሽኑን ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል።
ለየትኛውም ዓላማ የተቀናበረ የግለሰብ መረጃ አስፈላጊ ከሆነበት ጊዜ በላይ መቀመጥ እንደሌለበትና መረጃውን ለመመዝገብ የተፈቀደለት አካል፣ መረጃውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ ለመስጠት የሚችልበትን ሥነ ሥርዓትም አስቀምጧል።
በአገሪቱ የተጀመረው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጋር ተያይዞ በርካታ የግል መረጃ የመሰብሰብ ተግባር በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋማት በዲጂታል መተግበሪያዎች፣ ማለትም በዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች፣ በፋይናንስና የቴሌኮም ተቋማት እንቅስቃሴ ምክንያት የግለሰቦች የግል መብት እንዳይገሰስ ለማድረግና አጠቃላይ የመረጃ ጥበቃ ሥርዓትን ለማበጅትም ያለመ ነው።
ረቂቅ አዋጁ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመጀመሪያ ውይይት እየደረገበት ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ማፅደቅ ሒደት ውስጥ እንደሚገባ ለማወቅ ተችሏል።