Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ እየፈተነ ያለው የትግራይ ክልል ሁኔታ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  በመንግሥት በኩል ሕግ የማስከበር ዘመቻ የሚል ስያሜ የተሰጠው በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከጀመረ መንፈቅ አለፈው፡፡ በጦርነቱ የመጀመርያ ሳምንታት በአጭር ጊዜ ‹‹ሕግ የማስከበር›› ዘመቻው እንደሚጠናቀቅና በአፋጣኝ ትግራይን መልሶ ወደ መገንባት ሥራ እንደሚገባ ተገልጾ ነበር፡፡

  ሆኖም ከወራት በኋላ የትግራይ ክልልን መልሶ መገንባት ሳይሆን፣ በክልሉ የሚኖሩ ዜጎች አስቸኳይ የምግብና ሌሎች መሠረታዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያትቱ በርካታ ሪፖርቶችን መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡

  በተለይ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የተለያዩ አካላትን ጨምሮ በክልሉ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ አስደንጋጭ መሆኑን በመጥቀስ፣ አፋጣኝ ዕርምጃ በጊዜው ካልተወሰደ የበርካቶችን ሕይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡

  በዚህም የተነሳ የተቋረጠና ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚደርስበት መንገድ እንዲመቻች የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወትወት ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈም ጉዳዩ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚፈትን እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡

  ከዚህ አንፃር በቅርቡ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አንጋፋው ዲፕሎማት ጄፍሪ ፊልትማን በአካባቢው አገሮች ማለትም በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ በኤርትራ፣ እንዲሁም በግብፅ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ አሜሪካ በአካባቢው አገሮች የምትይዘውን አቋምና ቀጣይ አቅጣጫ የሚያመላክት ሊሆን እንደሚችል የገመቱት በርካቶች ናቸው፡፡

  ግምቱ የሰመረ ሲሆን አሜሪካ በትግራይ ጦርነት ሳቢያ በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ፣ እንዲሁም በአማራ ክልልና በሕወሓት አመራሮች ላይ ያነጣጠረ የጉዞ ማዕቀብ ጥላለች፡፡

  ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የጂኦ ፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኞች የአሜሪካ የማዕቀብ ማዕቀፍ በጉዞ ዕገዳ ብቻ የማያበቃ እንደሆነ፣ ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ወደ የሚያስተጓጉሉ ዕርምጃዎችም ሊሸጋገር እንደሚችል በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

  በተለይም የጉዞ ማዕቀብ የጣለችው አሜሪካ ሌሎች አገሮችም ይህን መሰል አቅጣጫ እንዲከተሉ መወትወቷ፣ በቀጣይም ከሌሎች አገሮች ወይም ተቋማት ተመሳሳይ ወይም ከፍ ያለ ማዕቀብ ሊከተል እንደሚችል በመግለጽ፣ ጉዳዩ የሰከነና የተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚጠይቅ እንደሆነ በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡

  በተለይም ጉዳዩ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት የጉዞ ዕገዳ በላይ እንደሆነ በመጥቀስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በባህሪው ዘርፈ ብዙ ክንውኖችን የሚመለከት በመሆኑ፣ በሁሉም መስክ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ከግምት ያስገባ እንቅስቃሴ እንዲኖርም ይመክራሉ፡፡

  አሜሪካ የባለሥልጣናት የጉዞ ማዕቀብን ለመጣል ዋነኛው ምክንያት በትግራይ ክልል ያለው ጦርነት ቢሆንም፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍል የሚስተዋሉ ግጭቶችም እንደሚያሳስባት በመግለጽ ጭምር ነው፡፡

  ከዚህ አንፃር በትግራይ ክልል የሚገኙት የኤርትራና የአማራ ክልል ኃይሎች በአስቸኳይ ክልሉን ለቀው እንዲወጡ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ የሚያስችል ያልተገደበና ያልተቆራረጠ መንገድ እንዲኖር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሚጠይቅ አቋሟን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ነው ማዕቀቡን የጣለችው፡፡

  ማዕቀቡን ተከትሎ በአገር ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ተቃውሞዎችን እያሰሙ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መንግሥትም ከያዘው አቋም ምንም የተለየ ነገር አልተስተዋለም፡፡

  እሑድ ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ይህንን ማዕቀብ የሚያወግዝ ‹‹ድምፃችን ለነፃነታችን›› የሚል የተቃውሞ ሠልፍ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ተካሂዷል፡፡ በሠልፉ ላይም ‹‹ኢትዮጵያ ሞግዚት አያስፈልጋትም››፣ ‹‹ግድቡ ይሞላል››፣ ‹‹በሉዓላዊነታችን ላይ ለሚሰነዘሩ ድፍረት አዘል ጫናዎች አንንበረከክም››፣ ወዘተ የሚሉ መፈክሮችም ተደምጠዋል፡፡

  ምንም እንኳን የአሜሪካው የልዩ መልዕክተኛ ወደ ቀጣናው አገሮች ያደረጉትን ጉዞ ተከትሎ አሜሪካ ማዕቀብ መጣሏን ተቃውሞ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ቢደመጡም፣ አሜሪካ ግን አሁንም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት መስጠቷን በሚያሳይ ሁኔታ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በድጋሚ የትግራይ ክልል ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው የሚገልጽ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

  ረቡዕ ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሹን ከነጩ ቤተ መንግሥት የወጣው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መግለጫ፣ የአገሪቱን አንድነት ለመጠበቅና አገሪቱን ወደ መረጋጋት ለመመለስ ሁሉን አቀፍ አሳታፊ የፖለቲካ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል፡፡

  በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው ጦርነት ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ እንደሆነ ከመግለጽ ባለፈ፣ ሁሉም ተፈላሚ ወገኖች በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ አሳስበዋል፡፡ ይህ የፕሬዚዳንቱ መግለጫ ከማዕቀቡ በኋላ የመጣ ከመሆኑ አንፃር፣ አሜሪካ ሌሎች ቀጣይ ማዕቀቦች ልትጥል እንደምትችል አመላካች መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡

  ለዚህም አንዱ ማሳያ ፕሬዚዳንቱ ለቀጣናው ልዩ መልዕክተኛ አድርገው የሾሟቸው ጄፍሪ ፊልትማን፣ በዚህ ሳምንት ዳግም ወደ አካባቢው እንደሚያመሩ መጠቆማቸው ነው፡፡

  አሜሪካ ማዕቀቡን ከጣለች በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) አማካይነት ጥቅል ምላሽ የተሰጠ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተከናወነው የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቅን ተከትሎ የኢትዮጵያ ምላሽ ይታወቃል በሚል በርካቶች የስብሰባውን መጠናቀቅ በጉጉት ጠብቀውት ነበር፡፡ ሆኖም የሰብሰባው መጠናቀቅን ተከትሎ የወጣው መግለጫ በመደበኛው ወቅት ከሚወጡ መግለጫዎች ምንም ያልተለየ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን አቋም በግልጽ ያስቀመጠ እንዳልሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡

  ‹‹ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው መቆም አለባቸው›› የሚለው የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ፣ ‹‹አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ ከባቢ ዛሬም እንደ ትናንት የዓለም ዓይን ማረፊያ ሆኖ ይገኛል፤›› በማለት፣ አገሪቱ ያለችበት ቀጣናዊ ከባቢ የበርካታ ኃያል አገሮች ዓይን ማረፊያ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

  ከዚህ ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅም አንፃር አካባቢውን ለመቆጣጠር የሚደረገው ፉክክርና እሽቅድምድም ለማሳካት የኢትዮጵያን መዳከም እንደሚፈልጉም፣ ‹‹እንደ መጥፎ ዕድል ሆኖ አንዳንድ አካላት ቀይ ባህር ላይ ያላቸው ፍላጎት የሚሳካ የሚመስላቸው አገራችን ስትዳከም ነው፡፡ ይኼ ደግሞ እንደ ሉዓላዊ አገር በፍፁም ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት በስም የማይጠቅሳቸውን፣ ነገር ግን ‹‹አንዳንድ አካላት›› በማለት በጥቅሉ የሚገልጻቸው ኃይሎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው ይገልጻል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ምንም እንኳን አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል ያስቀመጠቻቸውን ምክንያቶች አስመልክቶ ቀጥታ የተሰጠ ምላሽ ባይሆንም፣ ግንቦት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የወጣው የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ የተጀመሩ፣ ‹‹የሕግ የበላይነትና ሰላምን የማስከበር›› ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከመግለጽ ባለፈም፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በፍጥነት ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እንደሚሠራም ያትታል፡፡

  ከአሜሪካ በኩል የማዕቀብ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች ውስጣዊ በመሆናቸው፣ ስለዚህም መፍትሔው የተፈጠሩትን በርካታ ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሆነ የሚያሳስቡ በርካቶች ናቸው፡፡

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -