Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  አዲስ ቅርፅ የያዘው የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ‹‹በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል አሁን ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተወሰነ መልኩ አጠራጣሪ ነው፡፡ በተለይ ሱዳን በኢትዮጵያ በኩል ያለውን የጋራ ድንበር በኃይል ከያዘች በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው መተማመን ተሸርሽሯል፡፡››

  ከላይ የተቀመጠውን አስተያየት ከአንድ ሳምንት በፊት የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ሥዩም ናቸው፡፡

  ቃል አቀባይዋ ይህንን የተናገሩት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል እየተካሄደ ያለውን ወታደራዊ ግጭት በፖለቲካዊ ድርድር ለመፍታት ጥረት መጀመራቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም እንዲያብራሩ በጋዜጠኞች ተጠይቀው ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡

  ‹‹መተማመን ለማንኛውም ድርድር መሠረት ነው፡፡ ሱዳንን በአደራዳሪነት ለመቀበልም በሱዳን በኩል ያለው የተዓማኒነት ችግር በመጀመርያ መልስ ማግኘት አለበት፤›› ሲሉ ቢልለኔ በሱዳን መንግሥት የተያዘውን የማደራደር ፍላጎት ጥያቄ ውስጥ ከትተውታል፡፡

  በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት በተለይም የሱዳን አብዮትን ተከትሎ የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ፣ ማለትም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ ሻክሯል፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምክንያት ያለው አለመግባባት አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ በትግራይ ክልል በሚገኘው የሕወሓት ኃይል ላይ የሕግ ማስከበር በጀመረ በማግሥቱ የሱዳን ጦር ኢትዮጵያና ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱበትን የጋራ ድንበር በኃይል መያዙ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ወደ መካረር እያስገባው ነው፡፡

  ሁለቱ አገሮች በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ሙሉ በሙሉ አልተቋረጠም፡፡ በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ የሚመራው የሱዳን የሲቪል አስተዳደር መንግሥት ከሌሎቹ የተረጋጋ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በመቅደም፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ በፖለቲካዊ ድርድር ለመፍታት ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል፡፡

  ከሱዳን የአደራዳሪነት ተልዕኮ ጀርባ ምን አለ?

  በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የሱዳን የሽግግር መንግሥት በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ በድርድር ለመፍታት እንቅስቃሴ ከመጀመሩ አስቀድሞ በነበሩ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን፣ የሁለቱም አገሮች መንግሥታት ቃል አቀባዮች ባወጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡

  የሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት በስልክ ያደረጉት ውይይት ማጠንጠኛ የነበረው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንደነበር ያመለከተው የሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት፣ በውይይታቸውም በትግራይ ክልል በውጊያ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉና በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ መፍታታ እንደሚገባ ትኩረት ሰጥተው ተነጋግረዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በነበሩት ቀናት ውስጥ፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታታ የልማት ድርጅት (ኢጋድ) አባል ከሆኑት የአፍሪካ ቀንድና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መሪዎች ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ የተናጠል የስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ዲፕሎማት እንደሚሉት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ በድርድር እንዲፈታ ጥረት ማድረግ የጀመሩት፣ ሱዳን የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር መሆኗን መሠረት አድርገው ነው፡፡

  ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ለኢጋድ አባል አገሮች መሪዎች ስልክ በመደወል የተናጠል የስልክ ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ ለኢትዮጵያ አቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አለመደወላቸውን ዲፕሎማቱ ጠቁመዋል፡፡

  ይህ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለሱዳኑ አቻቸው ስልክ በመደወል የጀመሩት ጥረትን በተመለከተ ያነጋገሯቸው መሆኑን፣ ከላይ የተገለጸውንም የመንግሥታቸውን አቋም  በግልጽ እንዳሳወቋቸው ዲፕሎማቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  የትግራይ ክልል ቀውስ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ በቀጥታ ኤርትራ ስለሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የድርድር መፍትሔ ፍለጋ የምታውቀው ጉዳይ ባለመኖሩ፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ኤርትራ የኢጋድ አባል አገር ባለመሆኗ ልዑካኗን ወደ ሱዳን በመላክ አቋሟን እንድታሳውቅ አስገድዷታል፡፡

  በኤርትራ ፕሬዚዳንት የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ የማነ ገብረ አብና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን ሳላህ የተመራው የኤርትራ ልዑክ፣ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅን መልዕክት ለሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረሰ ሲሆን፣ መልዕክቱን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ በኢጋድ በኩል የትግራይ ክልል ቀውስን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ያለመና በትግራይ ክልል ያለውን  ቀውስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ እንዲሁም ወደ ክልሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚደርስበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲባል እንደሆነ ገልጸውላቸዋል፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዲፕሎማት እንደሚሉት ከሆነ የሱዳን መንግሥት ፍላጎት ሰላማዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ ለትግራይ ክልል በሱዳን በኩል የሰብዓዊ ዕርዳታ ኮሪደር እንዲከፈት ለማድረግ ያለመና የአሜሪካ መንግሥት ብሎም የአውሮፓ አገሮች በአፍሪካ ቀንድ ለመትከል የፈለጉትን አዲስ መዋቅር አቀናጅቶ ለማሳለጥ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

  እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻ፣ የእነዚህ የአውሮፓ መንግሥታትና የአሜሪካ ፍላጎት ግብፅንና ሱዳንን በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ውስጥ ማንገሥ ነው፡፡

  ሱዳን ከፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነት

  በአፍሪካ ቀንድ አገሮች በተለይም በኢትዮጵያና በሱዳን ፖለቲካ ላይ ለረዥም ዓመታት ምርምር ያደረጉት የፖለቲካ ተንታኙ ጆን ያንግ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አልፎ አልፎ በወዳጅነት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሚከተሉት የፖለቲካ ርዕዮት ውጥረት ውስጥ ለዘመናት ሲዋዥቅ እንደቆየና አሁንም በዚሁ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡

  በሁለቱ አገሮች መካከል የድንበር ውዝግብ፣ ሰፊ የኢኮኖሚ አቅም ልዩነት መኖር፣ እንዲሁም ደካማ መንግሥታት በሁለቱም አገሮች ውስጥ መከሰት ሁለቱን አገሮች የግጭት ዑደቶች ውስጥ ሲከቱ እንደቆዩ የሚገልጹት ተመራማሪው፣ አንደኛው መንግሥት የአንዱን አገር የፖለቲካ አማፂ ሲያስጠልልና ሲደግፍ ከ40 ዓመታት በላይ መዝለቃቸውን ያስረዳሉ፡፡

  ለአብነትም የሁለቱም አገሮች መንግሥታታ ተቃራኒ የፖለቲካ አማፂዎችን በማስጠለልና በመደገፍ ታሪካቸውም ከኢትዮጵያ የኤርትራን መገንጠል ሲያስከትል፣ ከሱዳን ደግሞ የደቡብ ሱዳንን መገንጠል እንደፈጠረ ያስታውሳሉ፡፡

  በዓባይ ውኃ ላይ ያሉ የተጠቃሚነት ውዝግቦች፣ በአዲስ አበባ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ ላይ በሱዳን ሰርጎ ገቦች የግድያ ሙከራ መደረግና ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ የጦር ኃይል ወደ ሱዳን ድንበር በመዝለቅ ጥቃት መክፈቱ፣ ይህም ሳይፈታ በቆየው የሁለቱ አገሮች የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ላይ ሌላ እሳት እንደጫረ ያስረዳሉ፡፡

  ይህ ቢሆንም የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር የሱዳን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አፍላቂ የነበሩትን ቁልፍ ባለሥልጣን ሀሰን አል ቱራቢ ገለል ካደረጉ በኋላ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥታት መካከል ሰላማዊና የተረጋጋ ግንኙነት እ.ኤ.አ. በ2018 ፕሬዚዳንት አልበ ሽር በሱዳን አብዮት ከሥልጣን እስኪወገዱ ድረስ ሰፍኖ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ ይህ ግንኙነትም ሱዳንን በኢትዮጵያ ተፅዕኖ ሥር ያደረገ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሱዳን ኢትዮጵያ መገንባት የጀመረችውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግፋ እስከ መቆም ያደረሳት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

  ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ቀድሞ በኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ የነበረውን የሕወሓት ኃይል በውስጣዊ ትግል አስወግደው መንበሩን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት መሻከር ውስጥ መግባቱን ይገልጻሉ፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በነበረው የመጀመርያው ዓመት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት መልካም የሚባል የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ በተከተሉት ዓመታት ግን ግልጽ ወደሆነ ግጭት ውስጥ እየገቡ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡

  ለዚህ መነሻ የነበረው ምክንያት በሱዳን መንግሥት ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ከተወገደው የሕወሓት ኃይል ጋር በድብቅ መገናኘታቸውን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት እንደተረዳና በግለጽ ይህ እንዲቆም በማስጠንቀቁ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

  በሁለቱ አገሮች መካከል ዲፕሎማሲያዊ መሻከር በተፈረጠ ቁጥር የሚከሰተው የድንበር ውዝግብም፣ ይህንኑ ተከትሎ ማቆጥቆጡና ወደ መካረር መሸጋገሩን ያወሳሉ፡፡

  በሌላ በኩል የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ኃይሎች በቀይ ባህር ቀጣና የተፈጠረውን የኤደን ባህረ ሰላጤ የዓረብ አገሮችና ቱርክና ኳታርን፣ እንዲሁም የኢራን ወደዚህ አካባቢ መሳብ የሚፈጥረውን ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ቀድሞ ለመመለስ ትኩረታቸውን የሱዳን የሽግግር መንግሥት ላይ ማድረጋቸው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ፖለቲካዊ ፉክክር እንዲነግሥ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

  ሱዳን በቀይ ባህር ቀጣና ጎልት እንድትወጣ የተባበሩት አሜሪካና የአውሮፓ ኃያላን በሱዳን ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ ከማንሳታቸው ባለፈ፣ በማዕቀቡ ምክንያት ሱዳን ተሸክማው የነበረውን 56 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከአንድ ወር በፊት ሰርዘዋል፡፡

  ከሳምንታት በፊት ደግሞ የዓለም የገንዘብ ድርጅት 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሱዳን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ማበደሩን አስታውቋል፡፡

  ይህንን ተከትሎም ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና የእነዚሁ ተቀናቃኝ የሆነችው ቱርክ ከሱዳን መንግሥት ልሂቃን ጋር ወዳጅነትን ለመመሥረት በሚያደርጉት ፉክክር፣ የሱዳን ተፅዕኖ ፈጣሪነትና የፖለቲካ ጉልበት በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ቀጣና ጎልቶ መውጣት ጀምሯል፡፡

  የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ሰሞኑን ለአገሪቱ ሽግግር ምክር ቤት ባቀረቡት የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት በምሥራቅ ሱዳን (ከኢትዮጵያ በምትዋሰንበት አካባቢ) ያለውን ቀውስ መፍታትና በቀይ ባህር የግዛት ክልሏ አካባቢ ሰላምና መረጋጋትን፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትንና ጠንካራ አስተዳደርን መፍጠር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ውስጥ በተለይም በወታደራዊውና በሲቪል አስተዳደሩ መካከል ያለው የሥልጣን ሽኩቻ አገሪቱን መልሶ ወደ ቀውስ ሊከታት እንደሚችል፣ ይህም ከኢትዮጵያ መድከም ጋር ተያይዞ  የቀይ ባህር ቀጣና ቀጣዩ የዓለም ፖለቲካዊ ፈተና ሆኖ ይፈጠራል የሚለውን ሥጋት በርካታ ተንታኞች እያነሱ ይገኛሉ፡፡

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -