Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  አሜሪካ ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ ለመጣል ያቀደችው ማዕቀብ ይዘትና አንድምታዎቹ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በፈረሙት ፕሬዚዳንት ትዕዛዝ፣ የትግራይ ክልል ግጭት በተኩስ አቁም ስምምነት መፍትሔ እንዳያገኝ ያደረጉና በግጭቱ በንፁኃን ላይ ለተፈጸሙ አሰቃቂ ሰብዓዊ ጥሰቶች ተጠያቂ ባሏቸው ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አዘዋል፡፡

  የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት እንዲቻል ያዘዙት የማዕቀብ ማዕቀፍ እንጂ፣ ማዕቀብ ተጥሏል ማለት እንዳልሆነና የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊዎች ሰሞኑን ተናግረዋል፡፡

  ፕሬዚዳንቱ በዘዙት የማዕቀብ ሕግ ማዕቀፍ መሠረት የአገሪቱ የገንዘብ ግምጃ ቤት ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር ተግባራዊ የሚያደርገው እንዲሆን የሚገልጹት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ተጠሪ፣ ማዕቀፍ ተጣለ የሚባለውም በማዕቀፉ መሠረት የአገሪቱ የገንዘብ ግምጃ ቤት ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር ማዕቀቡ የሚመለከታቸውን አካላት በመለየት የማዕቀብ ውሳኔውን ሲያሳልፍ ነው፡፡

  እስካሁን ባለው ሁኔታ ማዕቀቡ እንዳልተጣለ የገለጹት ኃላፊው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአማራ ክልል፣ የሕወሓት አመራሮች፣ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ባለው ቀሪ ጊዜ በትግራይ ክልል ያለውን ግጭት ለማስቆም ትርጉም ያለው ዕርምጃ የሚወስዱ ከሆነ፣ የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀቡን ከመጣል የትብብር መንገድን ሊከተል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ትርጉም ያለው ዕርምጃ ተብለው ከተጠቀሱት መካከልም፣ የአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚናን መቀጠልና ተደራዳሪ ቡድን መሰየም ይገኙበታል፡፡

  የአፍሪካ ኅብረት በትግራይ ክልል ያለውን ግጭት ለመፍታት በማሰብ፣ በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምን በተመለከተ የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ልዩ መልዕክተኛ አድርጎ ሰይሟል፡፡

  የሕወሓት ቡድን የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትን እንደማይቀበል በይፋ የገለጸ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም በተመለከተ በተደጋጋሚ የተጠየቁት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ሥዩም ግልጽ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

  የቀድሞው ናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴንጉን ኦባሳንጆ በተጠናቀቀው ሳምንት አዲስ አበባ ገብተው ከተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የተነጋገሩ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ምን እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

  የአሜሪካ መንግሥት ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ እንዲጣል ያዘዘው ማዕቀብ የሕግ ማዕቀፍ፣ በትግራይ ክልል ግጭት ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙትን ሁሉንም አካላት ወደ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲመጡ ለመጫን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል፡፡

  የማዕቀቡ አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፍ ይዘትና አንድምታው

  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባይደን የፈረሙት የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ እንዲጣል ለታሰበው ማዕቀብ ገዝ ማዕቀፉን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ይህንን ጥቅል ማዕቀፍ መሠረት በማድረግ ማዕቀቡ እንዲጣልባቸው የሚፈለጉ አካላትን የመለየት ሥራ ለአገሪቱ የገንዘብ ግምጃ ቤትና ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጋራ የተሰጠ ተግባር ነው፡፡

  ማዕቀቡን ለመጣል የተቀመጠው ጥቅል የሆነው የሕግ ማዕቀፍ በአንቀጽ ሁለት ላይ እንዳስቀመጠው ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት፣ እንዲሁም መረጋጋት ጠንቅ የሆነ ማንኛውም ድርጊት ወይም ፖሊሲ ወይም በትግራይ ክልል ያለው ግጭት እንዳይቆም ወይም እንዲራዘም ማንኛውም ድርጊት የፈጸሙ፣ አልያም መሰል ውጤትን የሚያስከትል ዓላማና ድርጊት ባላቸው ላይ ማዕቀቡ እንዲጣል ያዛል፡፡

  በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ካለው ግጭት ጋር በተገናኘ ሰብዓዊ ጥሰትና ሙስና የፈጸሙ፣ በትግራይ ክልል ውስጥ እንዲሁም ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊነት ዕርዳታ እንዳይደርስ ያስተጓጎሉ፣ ወይም መንገድ የከለከሉና በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሠራተኞች ላይ ጥቃት በፈጸሙ ሰዎች ወይም አካላት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያዛል፡፡

  የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሒደት ወይም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንቅስቃሴ እንዲዳከም የሚያደርግ ድርጊት በፈጸሙ፣ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል ወይም በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የተሰማሩ የፀጥታ አካላት ወይም የጦር አካላት ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ማዕቀቡ ያዛል፡፡

  የመንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ተቋም ሆኖ በትግራይ ክልል ግጭት ውስጥ ድርሻ ያለው እንደሆነ፣ ወይም በክልሉ ያለው ግጭት ተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስበት ያስተጓጎለ ተቋምና በተቋሙ አማካይነት ተሳትፎ ያደረገ ባልደረባ ማዕቀቡ እንደሚመለከተው ይገልጻል፡፡

  የኢትዮጵያ መንግሥት ወይም የኤርትራ መንግሥት ንዑስ የፖለቲካ ክፍል የሆነ፣ ወይም የአማራ ክልል መንግሥት ወይም የክልሉ መደበኛ ያልሆኑ የጦር አባላት፣ የኤርትራ መንግሥት ገዥ ፓርቲና ሕወሓት ማዕቀቡ እንደሚመለከታቸው ይገልጻል፡፡

  ማንኛውም ተቋም ወይም የተቋሙ ባልደረባ ለትግራይ ክልል ቀውስ አስተዋጽኦ ያደረገ፣ ማንኛውም በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኝ የመንግሥት ተቋም ከትግራይ ክልል ቀውስ ጋር በተገናኘ ድርሻ ያበረከተና በዚሁ ጊዜ ውስጥ የተቋሙ አመራር የነበረ ማዕቀቡ እንደሚመለከተው ያመለክታል፡፡

  ከላይ በተቀመጠው ማዕቀፍ መሠረት ተጠያቂ የሚሆኑት አካላት በአሜሪካ የሚገኝ ሀብት እንዳይንቀሳቀስ እንዲታገድና ምንም ዓይነት የገንዘብም ሆነ የንግድ ልውውጥ እንዳይደረግ ያዛል፡፡

  በተጨማሪም በተጠቀሰው ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቁ ግለሰቦች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የጉዞ ዕዳ የሚጣልባቸው እንደሚሆን ያመለክታል፡፡ ይህ ቢሆንም ማዕቀቡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ እንዲፈጸም አጽንኦት ይሰጣል፡፡

  የሚጣለውን ማዕቀብ ይዘትና ስፋት የሚያስቀምጠው ገዥ ማዕቀፍ ማዕቀቡ የማይመለከታቸውን ለይቶ ያስቀመጡ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የግብርና ምርቶች፣ መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ማዕቀቡ እንደማይመለከታቸው አስታውቋል፡፡

  tender

  የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለሥልጣናትና ተቋማት ላይ በትግራይ ክልል ቀውስ ተሳትፏቸው አንፃር እንዲጣል የያዙት ማዕቀብ አንድምታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከማነጋገር አልፎ፣ ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገሮች ውጪ ያሉ እንደ ቻይናና ሩሲያን የመሰሉ አገሮች በግልጽ ተቃውመውታል፡፡

  የቻይና መንግሥት ሰሞኑን በጣው መግለጫ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እንዲጣል የወሰነችው የተናጠል ማዕቀብን እንደሚቃወም በይፋ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከውጭ መንግሥታት ከሚመጣ ማዕቀብ ወይም ሌላ ጫና ይልቅ ኢትዮጵያውያን የገጠማቸውን ችግር በራሳቸው መንገድ የመፍታት ዕውቀቱም አቅሙም እንዳላቸው የሚያምን መሆኑን አመልክቷል፡፡

  ቻይናና ሩሲያን ጨምሮ 11 አገሮች ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጻፉት ደብዳቤ፣ በሰብዓዊነት ስም በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንዲቆም በተጠናቀቀው ሳምንት ጠይቀዋል፡፡

  የአሜሪካ መንግሥት እንዲጣል ያዘዘው ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ማዕቀቡ ከመጣሉ አስቀድሞ የድርድር ጅማሮ ሊኖር እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

  አወዛጋቢ ሊሆን የሚችለው ድርድር የሚደረገው በእነ ማን መካከል ይሆናል የሚለው አከራካሪ ጉዳይ እንደሚሆን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

  በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ሕወሓት አካላት ጋር የመደራደር ፍላጎት እንደማይታይ የሚጠቅሱት ባለሙያዎቹ፣ ከሕወሓት ውጪ ለመደራደር የኢትዮጵያ መንግሥት ቢፈቅድ በተቃራኒ ወገን የሚሰጠው ምላሽ የማዕቀቡን አጠቃላይ ሁኔታ ሊቀይረው እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

  በተቀረፀው አጠቃላይ የማዕቀቡ ማዕቀፍ መሠረት ሁሉም ወገኖች በእኩል ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚናገሩት ባለሙያዎቹ፣ በአፋር ክልል በንፁኃን ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ፣ በአማራ ክልል በማይካድራ በደረሰው ተመሳሳይ ጥቃት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት ብሎም መረጋጋት በሚለው የማዕቀፉ አካልም ከኦነግ ሸኔ ጋር በደረሰው ስምምነት ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

  በኢትዮጵያ መንግሥት ላይም በተመሳሳይ በትግራይ ክልል በተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶችና በአክሱም ከተማ ደርሷል በተባለው ጭፍጨፋ፣ እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት ከቀዬአቸው በተፈናቀሉ ነዋሪዎችና ከአገር በተሰደዱ በርካቶች ሳቢያ ማዕቀብ ሊመጣ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

  ይህም የተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮችን የሚያካትት በመሆኑ ጉዳቱ ሰፋ ሊል፣ ይሁን እንጂ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቡ የላላ በመሆኑ አጠቃላይ ጉዳቱ አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -