- ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ጥሰት መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ እንዲሰማራ ተጠይቋል
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል በመጪው ዓርብ እንዲካሌድ የጠራውን ልዩ ስብሰባ እንደማይቀበልና በዚህ ስብሰባ የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ በኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።
ከትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ጋር በተያያዘ በመጪው ዓርብ እንዲካሄድ የተጠራው ልዩ ስብሰባ የሚካሄድበትን ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ የምክር ቤቱ ቢሮ ረቡዕ ታኅሳስ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በተወያየበት ወቅት በተመድ የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ አምባሳደር ማሕሌት ኃይሉ ተገኝተው የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም በግልጽ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተጠራው ልዩ ስብሰባ የምክር ቤቱን የአሠራር ደንብ ያልተከተለና የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ ለፖለቲካዊ ፍላጎቶች መጠቀሚያ የሚያደርግ እንዲሁም፣ ምክር ቤቱ አባል አገሮች ላይ መድሎ እንዲፈጽምና በተመሳሳይ ጉዳይ የተለያዩ አሠራሮችን እንዲከተል በማድረግ ተቋማዊ ኃላፊነቱን የሚያረክስ እንደሆነ ተናግረዋል።
አባል አገሮቹ ይህንን ያልተገባ አሠራርና አንዳንድ አገሮች ሰብዓዊ መብትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በምክር ቤቱ በኩል ለማስፈጸም የሚያደርጉትን ጥረት በማውገዝ የምክር ቤቱ ተቋማዊ መርህዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
“በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያን አስመልክቶ የተጠራውን አስቸኳይ ልዩ ስብሰባና የዚህ ስብሰባ ውጤቶችን አይቀበልም፤” ብለዋል።
“በመሆኑም የተጠራው ልዩ ስብሰባና ምክር ቤቱ በዚህ ስብሰባ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተብሎ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ጋር በቀጥታ የሚጣርስ በመሆኑ ስብሰባውም ሆነ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ እንዲሰረዙ እንጠይቃለን፤” ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶችን የሚመረምር ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ እንዲሰማራ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በአውሮፓ ኅብረት አማካይነት ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጋር በጥምረት ያደረጉት ምርመራ ውጤትን መነሻ በማድረግ ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲሰማራ የሚጠይቅ ነው።
ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድኑ የአንድ ዓመት ቆይታ እንዲኖረው የሚጠይቀው ይኸው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ፣ የሚላከው ቡድን ከሚያደርገው ምርመራ በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ የሚደረግበትን፣ ዕርቅና ተጠያቂነት የሚሰፍንበትን እንዲሁም፣ ሰብዓዊ ጥስት የደረሰባቸው ማገገም እንዲችሉ ምክረ ሐሳብና የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት እንዲኖረውም ይጠይቃል።