Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊደረጃዎች ኤጀንሲ አዲሱ የአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ሥጋት እንዳሳደረበት አስታወቀ

  ደረጃዎች ኤጀንሲ አዲሱ የአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ሥጋት እንዳሳደረበት አስታወቀ

  ቀን:

  መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀው ‹‹የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ተግባርና ሥልጣን መወሰኛ አዋጅ›› የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲን ሥራ ለመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት መስጠቱ የተቋሙን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ እንደከተተው ኤጀንሲው አስታወቀ፡፡

  ኤጀንሲው በኅዳር ወር ላይ ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ አዲሱ አዋጅ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተቆጣጣሪ አካላት ደረጃ የማውጣትና የመቆጣጠር ሥልጣን መስጠቱን ጠቅሶ የብሔራዊ የደረጃ ዝግጅትን ልዩ ይዘትና ባህሪ ‹‹ከግምት ውስጥ ያላስገባ›› መሆኑን አስረድቷል፡፡ ተቋማቱ ደረጃዎችን እንዲያዘጋጁ ተግባርና ኃላፊነት መሰጠቱ ከዓለም አቀፍ አሠራርና ብሔራዊ የደረጃ አወጣጥ ሥርዓት (National Standardization System) ‹‹ባፈነገጠ›› ሁኔታ ደረጃን የማዘጋጀት ሥራ ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ገልጿል፡፡

  ኤጀንሲው ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር ደብዳቤውን መላኩን ለሪፖርተር ያረጋገጡት የኤጀንሲው የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግሥቱ በአዋጁ መሠረት ለተቋማት የተሰጠው ሥልጣን ‹‹የጥቅም ግጭት›› የሚያመጣና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው አሠራር መሰረትም ‹‹መልካም የደረጃ አወጣጥ ትግበራን›› (Good standardization Practice) ለማምጣት የሚያስችል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

  ከዚህ በፊት ባለው አሠራር የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የምርትና አገልግሎት ብሔራዊ ደረጃን የሚያወጣ ሲሆን፣ በየዘርፉ ያሉ ተቋማት በብሔራዊ ደረጃ የወጣውን ደረጃ መሠረት አድርገው የቁጥጥር ሥራ ይሠራሉ፡፡ አዲሱ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ተግባርና ሥልጣን መወሰኛ አዋጅ ክፍል ሦስት ‹‹የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ስያሜ›› በሚለው ሥር አንቀፅ 11/1 ‹‹ባለሥልጣን›› ለሚለው ስያሜን ሲያስቀምጥ ‹‹የቁጥጥር ደረጃ የማውጣትና በወጣው ደረጃ መሠረት መተግበሩን የሚያረጋግጥ›› በማለት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡

  አቶ ይልማ ተቆጣጣሪ አካላት ቁጥጥር ማድረግ ያለባቸው እንደ አገር በወጣ መሥፈርት መሆኑን ተናግረው ‹‹ተቆጣጣሪ አካል ደረጃ አውጥቶ ራሱ ማስተግበር ማለት ፖሊስ ራሱ ሕግ አውጥቶና ዳኛ ሆኖ እንደማየት ነው›› ብለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙ አገሮች ‹‹ብሔራዊ የደረጃ አውጪ አካል›› እንዳለ ያስረዱት ዳይሬክተሩ ‹‹እኛም እነሱም የመንግሥት አካል ሆነን ተመሳሳይ ሥራ የምንሠራ ከሆነ ብሔራዊ የደረጃ አውጪ አካል መኖር የለበትም ማለት ነው›› በማለት የኤጀንሲው አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

  ኤጀንሲው ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‹‹አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ በርካታ ተቋማት ደረጃዎችን ለማዘጋጀት የመፈለግ አዝማሚያና ፍላጎት እያሳደሩ ይገኛሉ›› በማለት ይሄም የደረጃዎችን ሳይንሳዊ ትርጉም፣ ዓላማና ቴክኒካዊ ይዘት ሳያሟሉ የሚዘጋጁ ደረጃዎች በአገሪቱ እንዲኖሩ ያደርጋል የሚል ሥጋት እንዳለው አስታውቋል፡፡

  የኤጀንሲው የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግሥቱ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ከኤጀንሲው ጋር ‹‹ጥሩ›› ግንኙነት የነበራቸው እንደ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣንና የኮንስትራክሽን ግብዓት ቁጥጥር ባለሥልጣን ያሉ ተቋማት ‹‹አዋጁ ፈቅዶልናል›› በማለት የደረጃ አውጪ ሥራ ክፍል እንዲሁም ቤተ ሙከራ የማቋቋም ሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአዋጁ ደረጃ የማውጣት ሥልጣን በተሰጣቸው ተቆጣጣሪ አካላት በኩል ‹‹በተሰጠን ሥልጣን ካልሠራን ተጠያቂ እንሆናለን›› የሚል ሐሳብ እንደተነሳም አክለዋል፡፡

  ‹‹በየቦታው ቤተ ሙከራ እያቋቋምን መልካም የደረጃ አወጣጥ ትግበራን ባልተከተለ መልኩ የምንሠራው ሥራ ዋጋ ያስከፍለናል›› ያሉት ዳይሬክተሩ አገሪቱ ከዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባም አስታውቀዋል፡፡

  ኤጀንሲው ለሚኒስቴሩ በላከው ደብዳቤ ላይ በአዋጁ ላይ የተቀመጠው የተቋማት ስያሜ ትርጓሜ የብሔራዊ የደረጃ ተቋም የሆነውን ‹‹የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ›› ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ እንዲቃኝና ‹‹ብሔራዊ (የኢትዮጵያ ደረጃዎችን) የማዘጋጀት ሥልጣንና ኃላፊነት አሻሚ ባለሆነ መንገድ ቢገለጽ ወይም ሌላ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ቢፈለግ›› በሚል ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

  ዳይሬክተሩ አቶ ይልማ እንደገለጹት ከደብዳቤው መላክ በኋላ ሚኒስቴሩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ‹‹የተወሰኑ›› አካላትን በማካተት ከኤጀንሲው ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ ፍጻሜ ላይ ተቋማቱ የተቋቋሙበትን አዋጅ የሚያስፈጽም መመርያ ሲያወጡ ‹‹የብሔራዊ ደረጃን ያስተገብራሉ›› የሚል አገላለጽ እንዲጠቀሙና ችግሩ በመመርያው ላይ እንዲስተካከል ንግግር ተደርጓል፡፡ ተቋማቱም ከኤጀንሲው ጋር ‹‹ተስማምተን እንሰራለን›› ማለታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

  ይሁንና ይሄ ውሳኔ አዋጁ ብሔራዊ ደረጃን የማዘጋጀት ሥልጣንና ኃላፊነት አሻሚ ባለሆነ መንገድ በመግለጽ እንዲስተካከል ለጠየቀው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አርኪ አይደለም፡፡ አቶ ይልማ እንደሚያስረዱት የበላይነት ባለው አዋጅ የተሰጠን ኃላፊነት ዝቅ ያለ ሥልጣን ባለው መመርያ ለማስተካከል መሞከር ‹‹የላላ›› ውሳኔ ነው፡፡ አሁን የተወሰነው ውሳኔ ተቋማቱና ኤጀንሲው በመግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) ላይ ተስማምተው እንደመሥራት መሆኑን ተናግረው ‹‹ይሄ ደግሞ ሲፈልጉ አብረው ይሠራሉ ሳይፈልጉ ሲቀር በራሳቸው ይሠራሉ የሚል አንድምታ አለው›› ብለዋል፡፡ መመርያው ላይ ካሰፈሩት በኋላ በአዋጁ ተመሥርተው በራሳቸው ደረጃ ማውጣትና ቁጥጥር ቢጀምሩ ኤጀንሲው የማስቆም ሥልጣን እንደማይኖረውም አክለዋል፡፡

  ‹‹አዋጁ ላይ ጥርት ብሎ ቢቀመጥ ሁሉንም ግርታ ይፈታል›› የሚሉት አቶ ይልማ ኤጀንሲው ደግሞ ብሔራዊ ደረጃውን ሲያወጣ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማረጋገጥ ኃላፊነቱ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ለተፈጠረው የሥልጣን መጣረስ ‹‹የተሻለ›› እና ‹‹ዘላቂ›› መፍትሔ የሚሆነው አዋጁን ማስተካከል እንደሆነ የኤጀንሲው የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግሥቱ አስረድተዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...