Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በግንባታ ዘርፍ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን የሚፈታ ቦርድ ሊቋቋም ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በግንባታ ዘርፍ ውስጥ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን የሚፈታ ቦርድ ሊቋቋም መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።

  ይህ የተገለጸው ማክሰኞ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን፣ በግንባታ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ያስጠናው ጥናት ሲቀርብ ነው፡፡

  ባለሥልጣኑ በግንባታው ዘርፍ በተቋራጮችናግንባታ አሠሪዎች መካከል እየተፈጠሩ ያሉትን አለመግባባቶች ለመፍታት ያስችላል ያለውን ቦርድ ለማቋቋም የወሰነው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባስጠናው ጥናት መነሻነት መሆኑ ተገልጿል።

  ጥናቱ በተለይ በሕንፃ ተቋራጮችና በባለቤቶች መካከል በግንባታ መጓተት፣ በጥራት፣ በዲዛይን ለውጥናሌሎችም ምክንያቶች በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ግንባታዎች ለዓመታት እንደሚቋረጡ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ኢንጂነር) ገልጸዋል።

  ጥናቱ የተደረገው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲና ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተውጣጡ ምሁራን አማካይነት መሆኑን፣ በጥናቱ መሠረትም በግንባታ ዘርፍ ውስጥ የሚፈጠሩትን አለመግባባቶች ለመፍታት በፍርድ ቤት የሚደረጉ የክስ ሒደቶች የተጓተቱና ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርጉ በመሆናቸው፣ ፍርድ ቤት ከመድረሳቸው በፊት በቦርድ መፍታት የተሻለ አማራጭ መሆኑ በጥናቱ ግኝት ተመላክቷል ብለዋል።

  የጥናት ቡድኑ መሪ ውብሸት ዠቅአለ (ዶ/ር) ጥናቱ በመንገድ፣ በሕንፃ፣ በውኃና በሌሎችም ዘርፎች የሚገኙ 248 ፕሮጀክቶች ላይ የተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ለ20 ዓመታት ያህል የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

  በግንባታ ተቋራጮችና በአሠሪዎች መከካል የሚፈጠረው አለመግባባት፣ በአብዛኛው የቅድመ ሥራ ኮንትራትና የዲዛይን ዝግጅት በበቂ ሁኔታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ባለመገባቱ እንደሆነ አውስተዋል። ይህም በተለይ የግንባታው ባለቤቶች በዋጋ ንረትና በዲዛይን ለውጦች ምክንያት ጥያቄ በማንሳት አለመግባባት ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

  አለመግባባቶቹን ለመፍታት የሚቋቋመው ቦርድ ወደ ፍርድ ቤት ከሚሄዱት ውስጥ፣ ቢያንስ 75 በመቶ የሚሆኑትን ውዝግቦች መፍታት እንዲችል መታሰቡን ውብሸት (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

  በጥናቱ በርካታ አገሮች በግንባታ ሒደት የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን የሚፈቱበት መንገድ እንደ ልምድ የተወሰደ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ኬኒያ፣ ናይጄሪያና አንጎላ ይገኙበታል።

  ቦርዱን ለማቋቋም ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤትና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አቶ መስፍን ተናግረዋል።

  የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፣ እየተስፋፋ ከመጣው ከተሜነትና የግንባታ ዘርፍ አንፃር አሁን ያሉ ችግሮች በአፋጣኝ የሚፈቱበት አማራጭ መፈለግ ተገቢ ነው ብለዋል።

  ከአገሪቱ በጀት እስከ 60 በመቶ ያህሉን የግንባታው ዘርፍ እንደሚይዝ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በዚህ ዘርፍ የሚያጋጥመው መጓተትና ከፍተኛ ብክነት የሚያስከትል ነው ሲሉ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ከ2,335 በላይ ከተሞች እንደሚገኙ ጠቁመው፣ የግንባታው ዘርፍ እያደገ ሲመጣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከ18,000 በላይ ከተሞች እንደሚፈጠሩና ለዚህም የግንባታው ዘርፍ ማደግ ወሳኝ መሆኑን አክለዋል።

  ባለሥልጣኑ በአጠቃላይ 11 ጥናቶችን እያስጠና መሆኑን የገለጹት መስፍን (ኢንጂነር)፣ ቀሪዎቹ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ይፋ እንደሚደረጉና ትኩረታቸውም የግንባታ ዘርፍ ደኅንነትን፣ የዘርፉን አሠራር ማቅለል፣ ሙስናና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ይሆናል ብለዋል።

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች