ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች የሚተገብሩት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሒሳብ አሠራር ሥርዓት ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት በዓለም ላይ ከ140 በላይ የሚሆኑ አገሮች እንደሚተገብሩት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሆኑና ለኅብረተሰቡ ግልፅ የሒሳብ ሪፖርት ያላቸው ተቋማትና ድርጅቶችን ለመፍጠር ታስቦ በኢትዮጵያም ተግባራዊ ለማድረግ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ይህንን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ብሎም ግንዛቤ በመፍጠር ትግበራውን እንዲያስፋፋ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 847/2006 ተቋቁሞ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡
ቦርዱ በተለይ በአምስት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝን ተግባራዊ ለማድረግ በማቀድ እስከ 2012 ዓ.ም. የቆየ የትግበራ ፕሮግራም አውጥቶ ሲሠራ ቢቆይም እንደታሰበው ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉን የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ምክትል ዋና ዳይሬክተ አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ይገልጻሉ፡፡
የአገሪቱ የሒሳብ አያያዝ፣ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ብሎም ኦዲት አሠራር የሚፈለገለው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ በሚፈለገው ደረጃ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓቱን ለማስተግበር እስከ 2016 ድረስ የሚቆይ ሌላ የትግበራ መርሐ ግብር አዘጋጅቶ እንዲንቀሳቀስ ግድ ብሎታል፡፡
የትግበራው እንደታሰበው ያለመሳካት ምክንያት ከሒሳብ አያያዝ ቦርዱ መቋቋም ጋር እኩል ሲቋቋም መጀመሩና በወቅቱ የነበሩትን ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ እንደነበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ስንታየሁ ደምሴ ይገልጻሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ ቦርድ ጋር በቅርበት የሚሠሩት አቶ ስንታየሁ ቦርዱን የማዋቀር ሥራና የሒሳብ አያያዝ ትግበራ ሥራው በተመሳሳይ ጊዜ መጀመሩ በትክክል ያልታሰበበት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝን እንተግብር ወደሚል ሐሳብ ሲገባ በመጀመሪያ ግምት ውስጥ መግባት የነበረበት በሙያው የሠለጠነ የሰው ኃይል ሲሆን፣ በእኛ አገር በቂ የሰው ኃይል በሌለበት ወደ ትግበራ ለመግባት መሞከሩ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ ሌሎች የትምህርት ተቋማት አይኤፍአርኤስን ሳይሆን ጋፕ (Generally Accepted Accounting Principles) የትባለውን ሥርዓት እንደነበር ተናግረው ወደ አዲስ ሥርዓት ሲገባ የትምህርት ተቋማቱንም ዝግጁ አለመደረግ ሌላው እንቅፋት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
የባለሙያዎች በአገር ውስጥ አለመገኘት፣ የሚገኙትም በቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ መሆን ሥርዓቱን ለመተግበር ውድ ክፍያ እንዲያስፈልገው አድርጎታል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የግል ድርጅቶችም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት የሒሳብ አያያዝ ሥርዓቱ ምን ዓይነት ጥቅም እንዳለው ግንዛቤ ሳይኖራቸው ቀጥታ ተግብሩ መባላቸው ከወጪው ጋር ሲያነጻጽሩት ኪሳራ ብቻ መስሎ እንዲታያቸው ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ድርጅቶቹ ለግብር ተቆጣጣሪው አካል ከሚያሳውቁት ሒሳብ ውጪ ለሌላ አካል ግልጽ የማድረግ ልምድ ባለመኖሩ አስቸጋሪ መሆኑንና አሁንም ድረስ ይህ ፈተና መቀጠሉን አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል፡፡
የአይኤፍአርኤስ ትግበራ ከግለሰብ እስከ አገር ጠቃሚ ነው የሚሉት አቶ ስንታየሁ ድርጅቶች ትርፋቸውን፣ ኪሳራቸውን፣ ሀብታቸውንም ይሁን ብድራቸውን ለኅብረተሰቡ ግልጽ ሲያደርጉ አብረው የሚሠሩ ገዢዎችና ተጠቃሚዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት፣ አምራቾች እንዲሁም በአጠቃላይ የአገር ሀብት በግልጽ እንዲታወቅና ሁሉም አካል ለሚወስደው ውሳኔ መነሻ የሚያደርገው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህም በተለይ በቅርቡ እንገባበታለን ተብሎ ለሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ዝርዝር ውስጥ ለመካተት ለሚፈልጉ ድርጅቶች ትልቁ መነሻ ነውም ብለዋል፡፡
በድርጅቶች ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሳው የክፍያ ውድነት በባለሙያዎች እጥረት የተፈጠረ በመሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን አሠልጥነው ቢሠሩ ችግሩን መቅረፍ እንደሚችሉ ይመክራሉ፡፡ በተጨማሪም አይኤፍአርኤስ ለትልልቅ ድርጅቶች የሚተገበርና ለአነስተኛ ድርጅቶች ተስማሚ የሆነ በሚል በሁለት ዓይነት መንገድ ተግባራዊ የሚደረግ በመሆኑ ለአነስተኛ ድርጅቶች በተዘጋጀው ሥርዓት መሥራት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት አይኤፍአርኤስን ተግባራዊ ያደረጉት ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ የሚሠሩበትን የፋይናንስ ተቋማት ጨምሮ 1,167 መሆናቸውን የቦርዱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሒሳብ ሪፖርታቸውን ለቦርዱ አቅርበው በምልከታ ላይ የሚገኙ 12 ድርጅቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተቋማት ከዚህ በበለጠ ፍጥነትና ጥራት እንዲተገብሩ ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ለሚሠሩ ባለሙያዎችና የኦዲት ድርጅቶች ቦርዱ ከመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለባለሙያዎቹ ፈቃድ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ እስካሁንም በቦርዱ ዕውቅና የተሰጣቸው የሒሳብ ባለሙያዎች 915 ሲሆኑ፣ የተመሰከረላቸው የኦዲት ድርጅቶች ደግሞ 152 መሆናቸው ገልጸው ይህም ዘርፉ ከሚፈልገው የባለሙያ ቁጥር አንፃር እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በአጠቃላይ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚቻልበትን መንገድና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድን አሠራር ለማሻሻል እ.ኤ.አ. በጥር ወር 2021 መሠረቱን እንግሊዝ ካደረገውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ120 ዓመታት በላይ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት በዘርፉ ሲሠራ ከቆየው ኤሲሲኤ (ACCA) ከተሰኘ የሙያ ማኅበር ጋር ለአንድ ዓመት የሚቆይ የፕሮጀክት ትግበራ ስምምነት አድርጎ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በዋነኝነት ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ራሱን የቻለ ኢንስቲትዩት ለማቋቋም እንዲቻል ስትራቴጂ በማዘጋጀት ለቦርዱ ማቅረቡን የኤሲሲኤ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዮዲት ካሳ ይናገራሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማኅበሩ ከ170 በላይ አገሮች የሚሠራ በተለይ የተሻሉ ልምዶችን እንደ ኬኒያና ሩዋንዳ ካሉ አገሮች በመውሰድ የሙያ ማኅበሩ የሚቋቋምበት ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ በአይኤፍአርኤስ ትግበራ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካለው የሙያ ማኅበር ዕውቅና ማግኘት እንደሚጠይቅ የሚጠቁሙት ዮዲት ለዚህም ውጪ አገር ከሚገኙ የሙያ ማኅበራት ባለሙያ ከማስመጣት እዚሁ ማኅበሩን ማቋቋም ተመራጭ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የኦዲት ባለሙያዎች የሚሠሩበትን መንገድ ሕጋዊና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ድርጅቶቹን ሲከታተልና የማስተካከያ ምክረ ሐሳብ ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸው ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸውን ተቋማትና አሠራሮች ለቦርዱ አቅርቧል ብለዋል፡፡ የድርጅቶችን የሪፖርት ግልፀኝነት በተመለከተ ደግሞ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ባንክና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ድርጅቶች ተደራራቢ ሪፖርት እንዳይጠየቁና ተቋማቱ ተናበው እዲሠሩ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ተቋማት አይኤፍአርኤስን መሠረት አድርገው የትምህርት ዝግጅታቸውን እንዲያደርጉ ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት እንዲወስድ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከኤሲሲኤ በቀረበው ምክረ ሐሳብ መሠረት የአካውንቲንግ የሙያ ማኅበር ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፣ የቦርዱ ኃላፊነት መቆጣጠርና ፈቃድ መስጠት በመሆኑና ይህም እርስ በእርሱ የሚጋጭ አሠራር በመሆኑ ራሱን የቻለ ተቋም ያስፈልገዋል በማለት ለዚህም የሙያ ማኅበሩ ሥልጠናዎችንና ምዘናዎችን በማድረግ ለባለሙያዎቹ ዕውቅና የሚሰጥ ተቋም ይሆናል ብለዋል፡፡
ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ቦርዱ ያስቀመጠው መስፈርት ውስጥ የሚካተቱ ድርጅቶች ሪፖርታቸውን ለኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ማቅረብ ግዴታ እንደሚሆንና በማያቀርቡት ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ፍቃዱ ጠቁመዋል፡፡ ባለሙያዎችም የቦርዱ ፈቃድ ከሌላቸው ምንም ዓይነት የሒሳብ ሥራ መሥራት እንደማይችሉ አክለዋል፡፡