ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ሥጋት ባለባቸው ቀጣናዎች በሦስተኛ ወገን የሚፈጸም ይሆናል
መንግሥት ትግራይን ጨምሮ በጦርነትና ግጭቶች የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ነዋሪዎችን ለማቋቋም፣ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረገው የገንዘብ ሚኒስቴር ሲሆን፣ ዓርብ መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከውጭ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያደረገበት መሆኑን፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይፋ የተደረገው የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው፡፡ በሰሜኑ ቀጣና ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች በመጀመሪያው ምዕራፍ ቅድሚያ የተሰጣቸው አካባቢዎች መሆናቸው ታውቋል።
በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙትና በተደጋጋሚ ግጭቶች የተጎዱት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎችም፣ በዚሁ የመጀመሪያ ዙር የመልሶ ግንባታ ማቋቋም ፕሮጀክት እንዲካተቱ ቅድሚያ የተሰጣቸው መሆኑን የሚኒስቴሩ ሰነድ ያመለክታል።
የመጀመሪያውን ምዕራፍ ፕሮጀክት ለመፈጸም አምስት ዓመት ይወስዳል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ በዚህም ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የመልሶ ግንባታ፣ የመልሶ ማቋቋምና የማገገሚያ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ታቅዷል።
ለዚህ ፕሮጀክት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጪ ውስጥ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ከዓለም ባንክ የሚገኝ እንደሆነ፣ ቀሪው ድርሻ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ለማወቅ ተችሏል።
በፕሮጀክቱ የታቀዱት ተግባራት በግጭት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን አፋጣኝ ፍላጎቶችን መፍታት፣ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች እንዲያገግሙ የሚያግዙ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ማዕከላትን ማቋቋም፣ በግጭት የተጎዱ ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎችንና መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በዘላቂነት መደገፍ የሚችሉ ተቋማትን ማጠናከር ዋነኞቹ ናቸው።
ፕሮጀክቱ በግጭት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን መሠረታዊ ፍላጎቶቾ ለማሟላትና መልሶ ለመገንባት በተለይም በጤና፣ በትምህርት፣ በንፅህናና በሎች አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተነደፈ መሆኑን ሰነዱ ያመለክታል።
በተጨማሪም ጊዜያዊ የድጋፍ አገልግሎቶችን በተለይ ለፆታዊ ጥቃት ተጎጂዎች የሳይኮሶሻል እንክብካቤ፣ እንዲሁም በእነዚህ ተጎጂዎች ሥር ለሚገኙ ታዳጊዎች ድጋፍ ማግኘት የሚችሉባቸው ፕሮጀክቶችንም ያካተተ ነው።
ፕሮጀክቱ አገራዊ ወሰን እንዲኖረው ተደርጎ የተቀረፀ ቢሆንም፣ በቅርቡ የተከሰቱ ግጭቶች ያደረሱትን መጠነ ሰፊ ጉዳትና ያለውን ውስን የፋይናንስ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ለአማራ፣ ለአፋር፣ ለቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ለኦሮሚያና ለትግራይ ክልሎች ድጋፍ ቅድሚያ እንደሚሰጥ መረጃው ያመለክታል።
እነዚህ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠሩ ግጭቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከዓለም ባንክና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የመልሶ ማቋቋምና የመልሶ ግንባታ ፍላጎት ልየታና ምዘና በማካሄድ ላይ ነው።
ፕሮጀክቱን ለማስፈጸምና ለመከታተል የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ያካተተ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን በዋናነትም የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴርና የሰላም ሚኒስቴር ተካተውበታል።
ፕሮጀክቱን የመፈጸም ኃላፊነት በዋናነት የተሰጠው ለገንዘብ ሚኒስቴር ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ በተመረጡት አካባቢዎች ፕሮጀክቶቹን ለማስፈጸም የሥራ ግንኙነት የሚያደርገው፣ ከወረዳዎች ወይም ከቀበሌዎችና ከአካባቢዎቹ ማኅበረሰቦች ጋር እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።
የፕሮጀክት ትግበራ ሒደቱ በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ቀጣይነት ያለው ግጭትና ከፍተኛ ሥጋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች፣ ከመንግሥት ድጋፍ ውጪ መግባትና መሥራት በሚችሉ ሦስተኛ ወገን አካላት ጋር በመዋዋል ፕሮጀክቱ እንደሚተገበር ሰነዱ ይገልጻል።
በዚህም መሠረት ውል የሚገቡት የሦስተኛ ወገን አካላት ፕሮጀክቶቹን ግልጽና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ተፈጻሚ የማድረግ ኃላፊነት እንደሚኖርባቸው፣ የአካባቢ አስተዳደሩን ሚና በመተካት የፕሮጀክት ሒደቱን የማመቻቸትና ውጤታማ የማድረግ ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስዱም መረጃው ያመለክታል።
ግጭት በማይስተዋልባቸው ሥጋት አልባ ወረዳዎች ደግሞ የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥታት፣ የተመረጡ ወረዳዎች፣ የወረዳዎቹ ማኅበረሰቦችና የሦስተኛ ወገን አስፈጻሚ አካላት በጋራ በመሆን ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሏል።
ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) በመስከረም 2014 ዓ.ም. ይፋ ያደረገውን መረጃ የሚጠቅሰው ይኸው ሰነድ፣ በኢትዮጵያ ከ4.2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውንና ይህም በዓለም ደረጃ ካሉት ተፈናቃዮች መካከል ትልቁ እንደሆነ ያመለክታል።
ከተጠቀሰው የተፈናቃዮች መጠን ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ፣ ቢያንስ 720,000 ሕፃናትም መፈናቀላቸውን ያስረዳል።
በተጨማሪም 85 በመቶ የሚሆኑት በግጭት ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ እንደሆነና 50 በመቶ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ማለትም ወደ 2.08 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ባለፉት ስድስትና ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ የተፈናቀሉ መሆናቸውንም መረጃው ይገልጻል።
ከተፈናቃዮቹ ውስጥ ወደ 90 በመቶ (ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች) የሚጠጉት በትግራይ ክልል እንደሆነ፣ አዲስ በዚህ መረጃ ያልተካተቱ ተፈናቃዮች በአፋርና በአማራ ክልሎች እንደሚገኙና አጠቃላይ የተጎጂዎች ልየታና ምዘና በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁሟል።