Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበትግራይ ክልል 73 የረድኤት ድርጅቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ገለጸ

  በትግራይ ክልል 73 የረድኤት ድርጅቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ገለጸ

  ቀን:

  በምግብና በምግብ ነክ ባልሆኑ አቅርቦቶች ላይ የተሰማሩ 73 የረድኤት  ድርጅቶች፣ በትግራይ ክልል ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ በድርጅቶቹ አማካይነትም ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ 1.2 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ክልል መላኩን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

   

  በክልሉ ውስጥ ያሉት 73 ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የውጭና የአገር ውስጥ መሆናቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ፣ ከሐምሌ 14 ቀን 2013 እስከ ታኅሳስ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ከ54 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ አቅርቦቶችን ማድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡

  በተጨማሪም ከሐምሌ ወር ጀምሮ ወደ ክልሉ በተደረጉ በረራዎች ከ337 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች፣ እንዲሁም አልሚ ምግብ ለትግራይ ክልል ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ዳይሬክተሩ የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በተደረጉት በረራዎች መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ማስገባቱን ገልጸው፣ ያስገባቸው መድኃኒትና ቁሳቁሶች የራሱና የጤና ሚኒስቴር መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

  የፌደራል መንግሥት በሰኔ 2013 ዓ.ም. ከትግራይ ክልል እስከወጣበት ጊዜ ድረስ 70 በመቶ የሚደርሰውን አቅርቦት እየሸፈነ መሆኑን ሲገልጽ የቆየ ሲሆን ከሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ግን አጋር አካላት ሙሉ ለሙሉ የሰብዓዊ ዕርዳታውን እንዲያቀርቡ ወስኗል፡፡ በዚህም ከተናጠል ተኩስ አቁሙ በፊት በክልሉ የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላትን ጨምሮ፣ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍና አገርና በቀል ድርጅቶችም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

  ከሐምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ አጋር አካላቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሥራውን ሙሉ ለሙሉ እያከናወኑ እንደሆነ፣ ኮሚሽኑ ቅዳሜ መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

  ይሁንና ሕወሓት ከታኅሳስ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአፋር ክልል በኪልበቲ ረሱ ዞን በአምስት ወረዳዎች ላይ ወረራ በማካሄዱ፣ ወደ ትግራይ ክልል ዕርዳታ ይገባበት የነበረው የአብአላ መስመር በመዘጋቱ የዕርዳታ አቅርቦቱ መስተጓጎሉን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ አስረድተዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን የጫኑ 43 ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ አብአላ እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ፣ 40 ኪሎ ሜትር ተጉዘው እንደተመለሱ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ 20 ምግብ የጫኑና ሦስት ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎችም በተመሳሳይ ወደ ሰመራ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

  በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም ማክሰኞና ሐሙስ በሳምንት ሁለት ጊዜ የነበረው በረራ በአጋር አካላት አቅም እስከፈቀደ ድረስ በየቀኑ ማስኬድ እንዲቻል መወሰኑን ያስታወቁት ኮሚሽነሩ፣ ከጥር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት (UNHAS) 34 በረራዎች፣ እንዲሁም 32 ሌሎች በረራዎች በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ መካሄዳቸውን አብራርተዋል፡፡ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሌሎች 56 በረራዎች እንደተካሄዱና ድርጅቶቹ በበራረዎቹ ሠራተኞቻቸውን፣ ለዕርዳታ አቅርቦት የሚውል ገንዘብ፣ እንዲሁም እንደ አውሮፓ ኅብረት ያሉት መድኃኒትና አልሚ ምግብ እንዲያጓጉዙ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

  ከአዲስ አበባ መቀሌ በተደረጉት የአየር በረራዎች በስምንት ወራት ውስጥ አጋር አካላቱ 1.2 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ክልል መውሰዳቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ምትኩ፣ ገንዘቡ ድርጅቶቹ በክልሉ ለሚቀጥሯቸው ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች ደመወዝ፣ ለሥራ ማስኬጃ፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ማስጫኛና ማውረጃ፣ ለመጋዘን ኪራይና ለሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ተግባራት እንደሚውሉ አስረድተዋል፡፡

  ድርጅቶቹ በአንድ በረራ ሲያጓጉዙት የነበረው የከፍተኛ ገንዘብ መጠን ሁለት ሚሊዮን ብር አሁን ወደ ሦስት ሚሊዮን ብር ማደጉን የገለጹት ኮሚሽሩ፣ የገንዘብ መጠኑ አጋር አካላቱን የሥራ መጠን፣ የሚያንቀሳቅሱትን የሀብት መጠን፣ እንዲሁም ያላቸውን የሰው ኃይል ብዛት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  መንግሥት የአየር በረራ በየቀኑ እንዲደረግ ቢፈቅድም ከጭነት አቅም አኳያ ከፍተኛ መጠን ያለው ዕርዳታ የሚጓጓዘው በየብስ በመሆኑ፣ የአብአላ መስመር መዘጋቱ የዕርዳታ አቅርቦቱን ቀንሶታል፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ያወጣው መረጃ እንደሚያሳያው፣ በትግራይ ክልል ውስጥ እየተደረገ ያለው የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት በከፍተኛ መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡ ከመጋቢት 1 እስከ መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ባሉት ስድስት ቀናት ውስጥ፣ ዕርዳታ ያገኙ ሰዎች ብዛት 68 ሺሕ ገደማ ብቻ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

  እስካሁን ድረስ 221.8 ሜትሪክ ቶን የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን ያስታወቀው ጽሕፈት ቤቱ፣ ይኼ አቅርቦት የክልሉን የሕክምና ፍላጎት አራት በመቶ ብቻ የሚሸፍን መሆኑን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ከመጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ወዲህ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ወደ ትግራይ እንዲጓጓዝ እንዳልተፈቀደ ጽሕፈት ቤቱ መረጃ አክሏል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...